✍ ሸንቁጥ አየለ
ከቀደሙ አባቶታችችን የምንማረዉ ጥበብ ምንድን ነዉ? የምንፈልገዉስ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቀዳማይ ጥበብ ምንድን ነዉ?
የኢትዮጵያን ትንሳኤ የሚያቀርቡ የተለያዩ ቡድኖችን : ዩቱዮበሮችን እና ሚዲያዮዎችን እከታተላለሁ::የኢትዮጵያ ትንሳኤም እንደሚመጣ አዉቃለሁ:: ካለን ጉጉት የተነሳ : በህዝባችን ላይ ከወደቀዉ ከመከራዉም ጽናት የተነሳ ምንም እንኳን ጊዜዉ የረዘመ ቢመስልም በመድሃኒዓለም የጊዜ ሰሌዳ መሰረት የኢትዮጵያ ትንሳዔ እዉን ይሆናል::
የኢትዮጵያ ትንሳዔን የሚናፍቁ እግዚአብሄርም ኢትዮጵያን እንደሚጎበኛት በአደባባይ የሚመሰክሩ ሰዎች መነሳታቸዉ እጅግ ደስ ይላል::ይሄ ቁፍ የሆነ ለዉጥ ነዉ::ኢትዮጵያን እግዚአብሄር ይታደጋታል የሚሉ ወገኖቼ ንግግር ላይ የምጨምረዉም የምቀንሰዉም ነገር የለም::
ማስተዋላችንን ግን አንድ ደረጃ ከፍ ማድረግ አለብን::እግዚአብሄር ኢትዮጵያን በሚታደጋት ቀን እኔስ ከበረከቱ ለመሳተፍ:ጠጠር ለመጣል : ስንጥር ለማቀበል: የመድሃኒዓለምን ስራ ለሌላዉ ወንድሜ ለማብሰር ዝግጁ ነን ወይ ብሎመጠዬቅ ግሩም የባህሪ ለዉጥ ነዉ::
ኢትዮጵያን መድሃኒዓለም ሊያድናት ሁሌም ይወዳል::ቁልፍ ጥያቄዉ ግን እኛ ፈቃደኞች ነን ወይ? የሚለዉ ነዉ::
ሊታረሙ የሚገባቸዉ አካሂያዶች
የኢትዮጵያን ትንሳኤ ለማምጣት የቀደመ የአባቶቻችንን ጥበብ መፈለግ አለብን የሚል ቅስቀሳ ላይ የተጠመዱ : በንግግራቸዉ እና በአቀራረባቸዉ እግዚአብሄርን የሚያዉቁ የሚመስሉ ግን ቀረብ ብለዉ ሲመረመሩ ፈጽሞ ከእግዚአብሄር ከመድሃኒዓለም አካሂያድ የተጣሉ ቡድኖችም አሉ::
የአንዱን የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ጥንታዊ ገዳም/ቤተክርስቲያን ይጠቅሱና በምን ጥበብ እና ሚስጢር እንደተሰራ ግን ሳያብራሩ ዝም ብለዉ የአባቶቻችንን ጥንታዊ ጥበብ መፈለግ አለብን የሚል ድምዳሜን ያቀርባሉ::
አንደኛ ምሳሌ ላንሳ:: በኢየሱስ ክርስቶስ ድንቅ አምላካዊ ታምር በባህር ላይ የተሰራዉን እና ከሽህ አመታት በላይ እድሜ ያለዉን የይምርሃነ ክርስቶስን ቤተክርስቲያን የሚያስጎበኘ ወይም በሚዲያ የሚያቀርብ ሰዉ በጥብቅ ደጋግሞ ማንሳት እና ማብራራት ያልበት ኢየሱስ ክርስቶስን ለሚያምኑት እና ለሚወዱት ለንጉስ ይምርሃነ ክርስቶስ ምን አይነት ጥበብን እንደ ሰጠዉ መግለጽ ይገባል:: ንጉስ ይምርሃነ ክርስቶስ ካህንም ስለነበረ ቀድሶም የሚያቆርብ የኢየሱስ ክርስቶስ ግሩም እና ታማኝ አገልጋይ ነበር::የይምርሃነ ጥበቡም ይህችዉ ነበረች::
ጥበብ እሱ ኢየሱስ ክርስቶስ ነዉ::በሱ የሚያምኑትም ጥበብ ይሰጣቸዋል::የአባቶቻን ጥንታዊ ጥበብም የምትባለዉም ኢየሱስ ክርስቶስን አምነዉ ጥበብን እንደ ጠቢቡ ሰለሞን ከእግዚአብሄር ማግኘታቸዉ ነዉ::
ሁለተኛም ምሳሌ ደግሞ የላሊበላ ዉቅር አቢያተ ክርስቲያናት ጉዳይ ነዉ:: የምዕራባዉያን ልሂቃን በእግዚአብሄር ካለማመናቸዉ የተነሳ ነገሩን በራሳቸዉ ሊገልጹት የሚባክኑበት አካሂያድ አለ::ለማያምን ሰዉ አንድን ነገረ እንዴትም መተንተን እና እንደተረዳዉ መተርጎምም ይፈቀድለታል::
ሆኖም የጥንታዉያን አባቶቻችን ጥበብ እፈልጋለሁ ብሎ ለተነሳ እና በእግዚአብሄር ለሚያምን ኢትዮጵያዊ ግን አንድ ቁልፍ ነጥብ ማስገንዘብ ይገባል::
ቅዱስ ላሊበላ እንደ ቅዱስ ይምርሃነ ክርስቶስ ሁሉ ልቡን ፈጽሞ በአምላኩ በኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ያሳረፈ እና ኢየሱስ ክርስቶስን የጥበብ ምንጩ በማድረጉ እግዚአብሄር በገለጸለት ጥበብ የላሊበላ ዉቅር አቢያተ ክርስቲያናትን መስራት ችሏል::
እንግዲህ የቀደሙ የአባቶቻችን የጥበብ ሚስጢር ለመመርመር የሚነሳ ማንም የሚያምን ሰዉ ደጋግሞ ሊረዳዉ የሚገባዉ የቀደሙ አባቶቻችን ጥበብ - የጥበብ ባለቤቷ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነዉ:: እነሱም ይሄን አዉቀዉ የጥበብ ምንጭ ኢየሱስ ክርስቶስን በመጠጋት ዘመናቸዉ የፍስሃ እንዲሁም ስራቸዉ በጥበብ የተከናወነ ሊሆንላቸዉ ችሏል::
ከቀደሙ አባቶታችችን የምንማረዉ ጥበብ ምንድን ነዉ? የምንፈልገዉስ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቀዳማይ ጥበብ ምንድን ነዉ?
የቀደሙ አባቶቻችን የጥበብ ባለቤት ኢየሱስ ክርስቶስን አምነው ጥበብን ሁሉ እርሱ እንዲግልጽላቸዉ የሚጠይቁ እና በክርስቶስን ጥበብ ነገርን ሁሉ የሚከዉኑ ነበሩ::የተፋዉን የኢትዮጵያን ስልጣኔ ፈልጎ ማግኘት ሲባልም ይሄዉ ነዉ::
ከቀደሙ አባቶታችችን የምንማረዉ ጥበብ ምንድን ነዉ? የምንፈልገዉስ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቀዳማይ ጥበብ ምንድን ነዉ? የሚሉትን ጥያቄዎች ሁል ጊዜም መድሃኒዓለም ኢየሱስ ክርስቶን አድርጋችሁ መመርመር የተቻለ እንደሆነ ጥበብ መድሃኒዓለም ይገኛል::ጥበብ መድሃኒዓለምየተገኘ እንደሆነ ጥንታዊ ስልታኔም የዛሬ ስልጣኔም የነገ ስልጣኔም ሁሉ በጥበብ ይከወናል::ይህቸዉም ጥበብ ምንጯ ከክርስቶስ የሆነ ጥበበ ክርስቶስ ነች::
ስለሆነም በሚቀርቡ የሚዲያ ፕሮግራሞች :በመሰባሰብ ወይም ደግሞ በማንናዉም የኢትዮጵያ ትንሳዔ እንቅስቃሴ በቀዳሚነት ኢየሱስ ክርስቶስን መድሃኒዓለምን ማእከል ማድረግ ወሳኝ ነዉ:: ከቀደሙ አባቶታችችን የምንማረዉ ጥበብ ሆነ የምንፈልገዉስ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ቀዳማይ ጥበብ አንድ ብቻ መሰረት አለዉ::እግዚአብሄርን ብቻ ማእከል ማድረግ::
Blogger Comment
Facebook Comment