ሰንደቅ አላማችን ለቤተ ክርስቲያን ምኗ ነው? ሰንደቅ አላማ መስቀልን ይተካል?

ለተዋሕዶ ልጆች በሙሉ የቀረበ ]

▹▸ ተዋሕዶ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ለኢትዮጵያ እስትንፋሷ ሆና ከጥንቷ ጀምሮ ኖራለች፤ ወደፊትም ትኖራለች። ቤ/ክኗ ከማንነት እስከ ሥልጣኔ፣ ከሰንደቅ እስከ ፊደልና ቀመር ለኢትዮጵያ የሰጠች ነች።

▹▸ ሆኖም አሁን ላይ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ቤ/ክ ከመንግሥት የወረሰችው፣ ባለቤትነት የሌላትና ምሥጢር አልባ አድርገው የሚያወሩ የቤታችን ሰዎች በርክተዋል። ጥላቻቸው ከሰንደቁ ባይሆንም ሰንደቁን በቃልኪዳን ምልክትነቱ የሚቀበሉትን ሰዎች ለመቃወም ሲባል ሰንደቁን የሚያቃልሉ ናቸው።

▹▸ በዚሁም ላይ 'መስቀልን የሚተካ አርማ' ተደርጎ እንደሚታሰብ አሉባልታ የሚነዙ ሆነዋል። ጠላት ፈጥሮ፣ ስም አሰጥቶ እውነቱን ከተጠዪው አካል ጋር ለማጥፋት የሚደረግ ስልት ነው። (ልክ እንደ ዘር አጥፊ ፕሮፕጋንዳ)

 የኢትዮጵያ ባንዲራ ምንጩ ከየት ነው?

▹▹ በመጽሐፍ ቅዱስ በዘፍ 9፥8-17 ላይ እንደተገለጸው እግዚአብሔር በኖኅ በኩል ለሰው ልጆች ሁሉ ዓለምን ዳግመኛ በጥፋት ውኃ ላያጠፋት የቃልኪዳን ምልክትና ምስክር ትሆን ዘንድ “ቀስቴን በደመና ላይ እዘረጋለሁ የምሕረት የቃል ኪዳን ምልክት ትሁን” ያለው ነው።

 ቃልኪዳኑም ዘላለማዊ ሲሆን እግዚአብሔር ዳግመኛ የሰውን ልጅ በንፍር ውኃ ላለማጥፋት የሰጠው ቃል ኪዳን ነው፡፡ ለሰው ብቻ ያይደለ ሥጋ ለለበሰ ፍጡር ሁሉ የተሰጠ ቃል ኪዳን ነው፡፡ በኋላም ለሰው ልጆች "በሥጋ ተወልጄ አድንኻለው" ብሎ የገባውን ኪዳን በእመቤታችን ፍጻሜን አግኝቷል።

"ከልቅሶ ደመና የጥፋት ውሃ ዳግመኛ በምድር ፊት ላይ እንዳይዘንብ የኖኅ የመሐላው ምልክት የሆንሽ የተመሰገንሽ #ማርያም ሰላምታ ላንቺ ይገባሻል” በማለት አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ እንዳመሰጠረ።

 ስለዚህም ቀስተ ደመና በኪዳናት መፈ°ጸሚያ እመቤታችን ጋር ተያይዞ የማርያም መቀነት ይባላል።

'መቀነትሽን አታጥብቂባት' ስንል እንኳ 'አትጨክኚባት፣ ስትለምንሽ ፊት አትንሻት' እንደመሆኑ የምሕረት ኪዳንን የታጠቀች እመቤታችን ናትና ይህን የምሕረት መቀነት (ቀስተደመናውን) ከወገቧ ላላ አድርጋ ሁሌ መዳናችንን የምትለምን ስለሆነች ይሆን #የማርያም_መቀነት የተባለው?

 ከጥፋት ውኃ በኋላ፥ ርስቱ የአፍሪቃ ምድር (ኢትዮጵያ) በሆነች በአባታችን ኖኅና በትውልዶቹ ዘንድ ተጠብቃ የኖረች ዓርማ ነች። ዓርማነቱ ርስት በሆነችው ምድር ሲኖር የእግዚአብሔርን ቃልኪዳን የሚያስብበት ነች። በኋላም እነዚህ ሦስት ቀለማት በንጉሥ ሰንደቅ አልማ ዘመን (ከጌታ ልደት 4500 ዓመታት በፊት) ከሃይማኖታዊ እስከ መንግሥታዊ አርማነት ሰፍቷልና (መንግሥቱም ከእግዚአብሔር ነውና) የቃልኪዳን ምልክቱም በንጉሡም ስም መነሻነት "ሰንደቅ አላማ" ተባለ።

ይህም ማለት ሰንደቁ ከመንፈሳዊ ወደ ሀገራዊ ዓርማነት የተወረሰ ነው እንጂ ቤ/ክኒቱ በኢትዮጵያ ምድር ስለተተከለች ከመንግሥት የወሰደችው አይደለም። በእርግጥ ከክርስቶስ ልደት በፊት ቤ/ክ አሁን ባላት ሕንጻና ሥርዐት ባትገኝም የቤ/ክ ታሪኳ ግን ከመላእክት መፈጠር ጀምሮ የኖረ ነው። [የቤ/ክ ታሪክ በዓለም መድረክ]

 ይህም በሕገ ልቦና ሲኖሩ የነበሩ አባቶቻችን መንፈሳዊ ሰንደቃቸው አድርገው በልባቸውና በዓላማቸው ያስቀመጡት ነው። መንግሥታቸው ከእግዚአብሔር፣ ኑሯቸው ከመንፈሳዊነት ጋር የተጣበቀ ነበርና ቀስተ ደመናውን በምድራዊ ርስታቸው ዓርማ አድርገውታል።
 ቀስተ ደመና 7 ቀለማት ሲኖረው ለምን ባንዲራው ሦስት ኖረው?

በቀስተ ደመና ውስጥ ያሉ ቀለማት ሰባት ናቸው። 3ቱ መሠረታዊ ቀለማት (ሰማያዊ፣ ቢጫ፣ ቀይ) ሲሆኑ ቀሪ 4ቱ በውሕደትና በውርርስ የሚፈጠሩ ናቸው።

▹ ሰማያዊ + ቢጫ = አረንጓዴ*
▹ ቀይ + ቢጫ = ብርቱካናማ*
▹ ሰማያዊ ዋና ሆኖ ወይን ጠጅ* እና ሐምራዊ* በቀለም ለዛ ተለያይተው አሉበት።

በቀስተደመና ላይ ግን ጉልህ እና ቋሚ ሆነው በብዛት የሚታዩት ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ብቻ ናቸው። ወደ ምድር የተቀነበበው የቀስተደመናው ክፍል ጀርባው ላይ ካለው የሰማይ ቀለም የተነሣ ሰማያዊዎቹ ደብዝዘው የሚታዩ ናቸው። ብርቱካናማውም ቢሆን ከቢጫው ተነጥሎ በቀዩ ተውጦ ይታያል። [ሠዓሊ አምሳሉ]
 
▹[አንድም]፦ ሦስቱ ቀለማት የምሥጢረ ሥላሴ ምሳሌ ናቸው። "የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ፥ አንድ ሰንደቅ አላማ ሦስት መልክ፦ አብ ፥ ወልድ ፥ መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ተብሎ ሲመሰገንበት ሲመለክበት የኖረው አንድ ሰንደቅ አላማ" እንዲሉ አለቃ አያሌው ታምሩ።

ይህን ምሥጢር ደሞ በአንዳንድ የቅዱስ ያሬድ ሥዕላት ላይ የሚታይ ነው። ዜማ የገለጡለት ሦስት ወፎች (መላእክት) ሲሣሉ አረንጓዴ ->ግዕዝ፣ ቢጫ ->ዕዝል ቀይ ->አራራይ ተመስለው ይታያሉ። ግዕዝ ዜማ የአብ፣ ዕዝል የወልድ፣ አራራይ ደሞ የመንፈስቅዱስ ምሳሌ እንደሆኑ ደሞ ከነዜማ ጸባያቸው የቤ/ክ ት/ት ያስረዳናል።

 ቀስተ ደመና ከቃል ኪዳን ምልክትነቱም በላይ የልዑል እግዚአብሔር የክብሩ መገለጫም ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ዮሐንስና ነቢዩ ሕዝቅኤል በየራእዮቻቸው ልዑል እግዚአብሔር በክብርና በሚያስፈራ ግርማ በዙፋኑ ላይ ሆኖ ዙሪያውን በሚያምርና ኅብር ባለው የቀስተ ዳመና ጸዳል ተከቦ ተመልክተውታል፡፡ [ራዕ 4፥2-3፣ ሕዝ 1፥26-28]

በተጨማሪም ዓፄ ምኒልክ በአድዋ ጦርነት ወቅት ታቦት ይዘው ሲዘምቱ፥ ቅዱስ ጊዮርጊስ ሊረዳቸው ሲመጣ በቀስተ ደመና መገለጡን ልብ ይሏል። ይህም የትድግና (የማዳን) ምልክት ሆኖ ታይቷል።

 በተለያዩ 'መምህራን' የሚሰጡ የማጣጣል ሃሳቦች

▸ ጊዜው ጎሣንና ቋንቋን ማዕከል ያደረገ 'ክርስትና'ን ፈላጊ፣ በሌላው በኩል ደሞ እውነቱን ከማስረዳት ይልቅ 'ሌላው እንዳይከፋው' እየተባለ ማለፍ የተለመደበት ነውና አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን መለኮታዊ አርማ ላልፈለገ ክልላዊ ጨርቆችን በማዘጋጀት ቤ/ክ ላይ መለጠፍን የሚደግፉ አሉ።

▸ 'ጎሣዬን የሚወክል ባንዲራ ይሄ ነውና ቤ/ክ ላይ ይሄ ይለጠፍ ባዩ ሲመጣ በሌላ ጎኑ ከቤ/ክ "ይሁና ምናለበት? አረንጓዴ ቢጫ ቀይ የመንግሥት እንጂ የቤ/ክ ቀለም አይደለም" የሚሉ አዘናጊዎች በቤታችን መብዛታቸው ምእመኑን ክብሩን እንዳይረዳ እያደረጉት ነው።

▸ "የቤ/ክ አርማ መስቀል እንጂ ባንዲራ አይደለም" ይላሉ። ማን መስቀልን ይተካል እንዳላቸው ግን አይታወቅም። መስቀል ቤዛችን የድኅነትና የኃይል አርማችን ነው። ሰንደቁ ደሞ በሌላው ወገን የእግዚአብሔር የምሕረት ቃልኪዳን የምናስብበት፣ እስከ መስቀል የተከፈለልን የምሕረት ቃልኪዳን የምናስብበት አርማችን ነው።

▸ ሌላ ደሞ "ቤ/ክ ዓለም አቀፋዊት ነች። ስለዚህ የአንድ ሀገር ሰንደቅ አይወክላትም" የሚሉ 'መምህሮች' ናቸው። ቤ/ክ ዓለም አቀፋዊነቷ እውነት ቢሆንም ያለቦታው መጠቀሱ ቤ/ክንን ከባለቤትነት ለማራቅ መሣሪያ አድርገውታል። አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ እንዲሉ። ሌሎቹ የቃልኪዳኑን ሰንደቅ አልተጠቀሙም ማለት የኢትዮጵያ ቤ/ክ ከመንግሥት ወሰደችው አያስብልም።

~ለምሳሌ፦ የዘመን አቆጣጠራችን ከቤ/ክ ቀመር የተወረሰ ነው። የሚያምነውም የማያምነውም ይጠቀምበታል። መንግሥትም ዕቅድ ለማውጣት፣ በጀት ለማጽደቅ፣ ለሥራው የሚጠቀምበት ነው። ከቀመሩ በተጨማሪ #ዓመተ_ምሕረት የምትለዋን የነገረ ድኅነት ማሳያ ቃልን ይጠቀሙበታል። ይሄን ባይጠቀሙ እንኳ እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ብለው ቀመሩን ግን ከቤ/ክ ወስደው ይገለገሉበታል።

ታዲያ የዘመን አቆጣጠሩ መንግሥትና ሕዝብ በስፋት ይጠቀምበታልና የሀገሪቱ እንጂ የቤ/ክ አይደለም ልንል ነው? ቤ/ክ ዓለም አቀፋዊት ነችና ሌሎቹ መንበሮች (እነ ሕንድ፣ ሶርያ...) ስላልተጠቀሙበት አይወክላትም ልንል ነው? የኢትዮጵያን ብርቅዬ ወር ጷጉሜንን ከስንክሳር ልንፍቃት ነው?

የኢትዮጵያ ቤ/ክ ከሌሎች ቤ/ክን የሚለዩዋት ሌሎች ሥርዐቶችና ምሥጢራዊ ነገሮች የሏትም? ታዲያ እነዚህ ሁሉ ጠቅሰን ዓለም አቀፋዊ አይደለምና የኢትዮጵያ ቤ/ክ ትተወው ልንል ነው?

ለአብነት ያህል፥ የመድኃኔዓለም ቅዱስ መስቀል ቅርጽ ከዓለመ መላእክት እስከ ምድር ድረስ (ቀጥ ብለው የተመሳቀሉ ሁለት መስመሮችና አራት ጫፎች) መሆኑ ይታወቃል። የኢትዮጵያ ቤ/ክ ደሞ መልከ ብዙ የሆኑ አራቱን ጫፍ የያዙ ነገር ግን የተመሳቀለ መስመር የማናይባቸው፣ ሐረግና ክበቦችን የተሞሉ የተለያዩ የመስቀል ቅርጾች አሏት።

ታዲያ ቅርጾቹ ዓለም አቀፍ አይደሉም ብለን ልንተዋቸው ነው? የኢትዮጵያ ቤ/ክ በመስቀሏ ልትነቀፍ ነው? የራሷን ምሥጢርን ቀምማ በመስቀሏ ላይ ብታደርግ ምን ነውር አለው? መባረክና መቀደስ ያንሳቸዋል?

ልክ እንዲሁም ቀስተደመናውን ከ7 ቀለማት ወደ 3 ቀለማት አድርጋ ሰንደቋ ጌጧ ብታደርገው ምሥጢራዊነት አስይዛ ነውና መንፈሳዊ ቀለሟ ብታደርገው አያስነቅፋትም። የሀገሪቱ ሰንደቅ መሆን የጀመረውም ከቤ/ክ ተወርሶ ነውና ሰንደቁን መጠቀም ከኵላዊነት አያወጣትም።

ሌሎች ሀገራት ፖለቲካዊ መሠረት ያለው ሰንደቅ ስላላቸው ኢትዮጵያም በፖለቲካ ያገኘችው ማስመሰል አይገባም። ሰንደቋ ቀድሞውኑም መለኮታዊ መልእክትና ክብር ያለው ነውና። መስቀልን ኃይሏ፣ ሰንደቋን የቃልኪዳን ምልክት አድርጋ ኖራለች ትኖራለች።

ምነው ቤ/ክ አሐዝና ፊደል፣ ሥነ ጽሑፍና ሥልጣኔ ለሀገሪቱ ለሕዝቡ ሰጠች ስንል ቆይተን አሁን ሰንደቋን መጤ አደረጋችሁት? ያላልነውን አሉ፣ "ከመስቀል ይልቅ ባንዲራ ያድናል" አሉ እያሉ በፕሮቴስታንታዊ ነገሮችን የማክፋፋት ጠባይ ተጠመዳችሁ? (መና-ፍ-ቃን ለመስቀል ስንሰግድ አመለኩት ሲሉን እንደነበረው ማለት ነው)

ምንነቱን አምኖ አረንጓዴ ቢጫ ቀዩን ዓለም ሁሉ ልጠቀም ቢል አይከለከልም። ልክ የመስቀል ቅርጾቿን ከነምሥጢሩ ልጠቀም ቢል እንደሚችል። እንደሰው ምኞት የሚቀነስ የሚጨመር ሥርዓት ቤ/ክ የላትም። የሰውን ፊት፣ የፖለቲካን ክረት አይታ የምትለዋወጥ ቤ/ክ የለችንም። መንፈሳዊ ሰንደቋን ይዛ ወደፊት ትቀጥላለች እንጂ።

የመጣው መንግሥት የራሱን ዓርማ በሰንደቋ ላይ ጥገኛ አድርጎ ሲለጥፍ ኖረ እንጂ ቤ/ክ ከመንግሥት የወሰደችው ሰንደቅ አላማ የላትም። መስቀልንም ይተካል ብላ አስባ አታውቅም። ያሰበ ምእመን ካለም መለኮታዊ የቃል ኪዳን አርማ እንደሆነ አስረድቶ መመለሱ ይገባል እንጂ የጠሉትን ግለሰብ/ማኅበረሰብ ለመቃወም ብሎ እውነቱን ማጣጣል ክርስቲያናዊ አይደለም።

~×× ይቆየን ××~

 ስብሐት ለእግዚአብሔር፥
 ወለወላዲቱ ድንግል፥
 ወለመስቀሉ ክቡር አሜን፨

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment