አለቃ አያሌው ታምሩ በአፄ ኃይለ ሥላሴ እና በሹማምንቱ ፊት ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር‼️


«ግርማዊነትዎ የሚመሯትን አገር ኢትዮጵያን አያት ቅድመ አያቶችዎ እግዚአሔርን ከመፍራት ጋር ነበር ሲመሯት የኖሩ። ለዚህም ምክንያታቸው አገሪቱ ሀገረ እግዚአብሔር፥ ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር መሆኑን በማወቃቸውና መረዳታቸው ነው።

 እስዎንም በአባቶችዎ ዙፋን ላይ ሲያስቀምጥዎ እሱ በሰጠዎት ጸጋ፥ በተፈጥሮ ብልህነትና በትምህርት ያዳበሩትን ዕውቀት በመጠቀም ጭምር አገርዎንና ሕዝብዎን በበለጠ እንዲያገለግሉ ፈቃዱ ሆኖ ነው። አገርዎ ኢትዮጵያና ቀብታ ያነገሠችዎ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ነውር ነቀፋ የሌለባቸው ናቸው። ግርማዊነትዎም ይህችን ሀገረ እግዚአብሔርና ቀብታ ያነገሠችዎትን ቤተ ክርስቲያን በነበረ ክብራቸውና ታሪካቸው አንጻር የመጠበቅና ከተለያዩ የጠላት አመጣጦች የሚሰነዘርባቸውን አደጋ ሁሉ የመመከት ኃላፊነት አለብዎ።

 ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ሠለጠነ ከሚባለው ዓለም የሚያስፈልጋቸው የእደ ጥበብና የተለያየ ሙያ ነክ ሥልጣኔ እንጂ የሃይማኖት ወረርሽኝ አይደለም። ነገር ግን በአሁኑ ሰዓት ሃይማኖት የግል ነው አገር የጋራ ነው የሚለውን የግርማዊነትዎን መርኅ መግቢያ በማድረግ ከብዙ አቅጣጫ የሚወረወሩት ፍላፃዎች በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና በህልውናዋ ላይ እያነጣጠሩ ይገኛሉ።
 
ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ርስቱ መሆኗን መዘንጋት አይኖርበትም። ይልቁንም ግርማዊነትዎ የዚህችን ታሪካዊና ገናና ቤተ ክርስቲያን ህልውና የመጠበቅ ኃላፊነት አለብዎ። ይህንንም የምልዎ የቤተ ክርስቲያን ዕድል ከእያንዳንዱ ኢትዮጵያን እመራለሁ ከሚል መሪ ዕድል ጋር የተጣመረ በመሆኑ ነው። ዛሬ ዙሪያዎን ከበው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን ማፍረሻ ምክንያት ከእስዎ ለማግኘት በሥልጣኔና በዴሞክራሲ ስም ያሰፈሰፉ ሁሉ ነገ እስዎ ከእግዚአብሔር ተጣልተው ብቻዎን ቢቀሩ አጠገብዎ አይገኙም። ሁሉም ወደ ላኳቸው የውጪ ኀይሎች ጉያ ነው የሚገቡ።

 በዓለም የተለያዩ ክፍሎች ልዩ ልዩ ሃይማኖቶች ቢኖሩም እያንዳንዱ አገር ታሪካዊና ነባር የሥነ መንግሥትና የሥነ ሕዝብ አገነባብ አመጣጥ አንጻር ሁሉም አገር የራሱ ኦሪሴላዊ ሃይማኖት አለው። ይህም የየአገሩ የህልውና ምስጢር አስኳልና አውታር ነው። ይህንን ለመገንዘብ ግርማዊነትዎ የእኔን አስታዋሽነት ባይሻም በአባትዎ በዳዊት ዙፋን ላይ ያስቀመጠዎትን እግዚአብሔርንና ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን የተሰጠችውን ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጠብቀው ይኑሩ። ይህን ባያደርጉ ራስዎንና አገሪቱን በአደጋ ላይ ይጥላሉ። ዙፋንዎም ለዘርዎ አይተርፍም፤» የሚል ነበር።

ይህን ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ብዙዎች መኳንንት፥ መሳፍንትና ሹማምንት፤ «ይህ ልጅ ጃንሆይ ፊት ቢሰጡት ጊዜ ድፍረት አበዛ። ብሎ ብሎ እንዴት እንዲህ ይዘልፋቸዋል፤» በማለት እያጉረመረሙ እያሉ በቤተ መንግሥቱ አስተናጋጆች አማካይነት ከሰው መሐል አለቃ አያሌው (ያኔ መሪጌታ) ተጠርተው በተለየ ክፍል እንዲቆዩ ይደረጋል።

 እነዚያ ተቺዎችም፤ «አላርፍ ብሎ በገዛ እጁ ዋጋውን አገኘ፤ ታሰረ፤» እያሉ ይወያዩ ነበር። ከተወሰነ ቆይታ በኋላ ወደ ልዩ ክፍል ወስዶ እዚህ ጠብቅ ተብለሃል ያላቸው አስተናጋጅ ፭፻ ብር ይዞ መጥቶ፤ «ይህን ሽልማት ጃንሆይ ልከዋል፤» ብሎ ሰጣቸው። ከዚያም ወደ ቤታቸው ሄዱ።

👉የመረጃ ምንጭ- የአለቃ አያሌው ቤተሰቦች ያዘጋጁት የመታሰቢያ መጽሔት ።


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment