ስለ ወያኔ መጨረሻና የኢትዮጵያ እጣ ፋንታ የተነገሩ ትንቢቶች



✍ ዲያቆን ረዳ ውቤ


“ኤርትራም ወደ እናት ሀገሯ ትመለሳለች”
ለአምላክ የቀረቡ ቅዱሳንና ንጹሃን ሰዎች ወደፊት ገና እነሱ ያልኖሩበት ዘመን ሁኔታ አስቀድመው የማወቅ ጸጋ ስለሚሰጣቸው ” እንዲህ ይሆናል: ይሄ ይመጣል ይሄ ይሄዳል ” እያሉ ይናገራሉ :: እነዚህ ቅዱሳን የሚናገሩት እውነት ትንቢት ሲባል እነሱ ተናጋሪዎቹ ደግሞ ነብያት ይባላሉ:: የሚመጣውም ትውልድ አንብቦ ወደፊት ለሚሆነው ነገር ይዘጋጅ ዘንድም የትንቢት መጽሐፍት ይጽፋሉ:: ለምሳሌ በመጽሓፍ ቅዱስ ከትንቢተ ኢሳይያስ ጀምሮ ያሉት የትንቢት መጻሕፍቶች በሙሉ በየግዜው የሚከሰተውን ነገር አስቀድመው የሚናገሩ መጻሕፍት ናቸው::
በሀገራችንም በርካታ ቅዱሳን በሀገርም ላይ ሆነ በግለሰቦች ላይ ስለሚከሰት ጉዳይ : በርካታ ትንቢቶችን ተናግረዋል:: በተለይ በሀገር ዙርያ ትንቢት የተናገሩ ብዙ አባቶችን መጥቀስ ይቻላል:: የወሊሶው አባ ወልደ ትንሳኤ( በኋላ አቡነ ዴዎስቆሮስ) የታወቁ አጥማቂ ነበሩ:: አጋንንቱን እየገዘቱ ያናዝዙት ነበር:: እሳቸውም የሚናገሩት ትንቢት መሬት ወድቆ አያውቅም ነበር::የመቄቱ አባ አዳነ ካሳውም ይሄ ጸጋ የተሰጣቸው ልዩ አባት መሆናቸውን የሚያውቃቸው ያየና እሳቸውን የሚሉትን የሰማ ብቻ ነው::

እኔ በእድሜዬ ባህታዊ ገብረመስቀልን አስታውሳለሁ:: በ1980ዎቹ መጀመርያ ” ትልቁ ዘንዶ አራት ኪሎ ላይ ወደቀ:: የሱን ደም የነኩትም በሙሉ እፍረት ገጠማቸው” እያሉ ይናገሩ ነበር:: ያኔ ልጅ ብሆንም በደንብ እሰማቸውም አስታውስም ነበር:: ሲፈቱትም ዘንዶው አስተዳደሩ ወይም መንግስቱ እንደሆነ ደሙን የነኩትም የኢሰፓ አባላት እንደሆኑ ሲያስተምሩ በጆሮዬ ሰምቻለሁ::ያሉት አልቀረም:: ጥቂት አመታት ቆይቶ የኮሎኔል መንግስቱ አስተዳደር ወደቀ:: ኢሰፓም ፈረሰ::ባህታዊ ገበረ መስቀል አሁን ያሉበት ሁኔታ ለብዙዎች ያልተዋጠ ቢሆንም በግዜው ግን ብዙ የተናገሯቸው ትንቢቶች ደርሰዋል::

አሁንም ስለዚህ መንግስትና ስለመጻኢ ያገሪቱ ሁኔታ በርካታ አባቶች በማሳሰቢያ ጭምር ትንቢት እየተናገሩ ነው:: ይህንንም ለመስማት ወደ ትላልቆቹ ያገራችን ገዳማት በንግስ ግዜ ብቅ ማለት በቂ ነው:–ግሸን : ላሊበላ : ዝቋላ : አክሱም እና ሌሎችም ገዳማት ያሉ መነኮሳትና ባህታውያን ሰንሰለት ታጥቀው ማይክራፎን ይዘው በየግዜው ይናገራሉ:: አጭበርባሪው በበዛበት በዚህ ክፉ ዘመን ባህታዊ ሁሉ ይታመናል ባይባልም : በተለያየ አጋጣሚ ከታመኑ አባቶች ሲነገር የሰማሁትንና ዘግቤ የያዝኩትን ላካፍላችሁ::
በመጀመርያ ስለ ሀገራችን ኢትዮጵያ::

በሀገራችን በኢትዮጵያ በቅርብ ግዜ ይሆናል ተብሎ ከሚነገረው ትንቢት አንዱ እንዲህ ይላል::

“በኢትዮጵያ አህዛብ ጦርነት ይጭራሉ:: በኢትዮጵያም ላይ እሳት ይነዳል::እሳቱም ጉዳት ያደርሳል :: የፈጣሪውን ስም የጠራ ግን ይድናል::ጸልዩ”
ማን እና ምን ማለት ይሆን?

እንደገባኝ ከሆነ ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት የሚያውጁ ሀገራት ይኖራሉ ብዬ ገምታለሁ:: እንዳለመታደል ሆኖ ጎረቤቶቻችን ባብዛኛው የሚፈልጉን ለጠብ ነው:: ሱማሌ ኢትዮጵያ ጦር ለመስበቅ የምትፈልገው አጋጣሚ ነው:: ከጥንት ጀምራ ኢትዮጵያ ላይ እሳት ያላነደደችበት ግዜ የለም:: በአጼ ሃይለሥላሴ ግዜ: በዘመነ መንግስቱ ሁለት ግዜ ጦርነት ከፍታብናለች:: ሱዳንም የምትታመን ሀገር አይደለችም:: ከኤርትራ ጋር ያለውም የድንበር ጉዳይ እልባት ያገኘ አይደለም:: ከዛ ጋር ተያይዞ አቶ ኢሳይያስም ወዳጅ እንዳልሆኑ ይታወቃል:: ግብጽም ያዙኝ ልቀቁኝ እያለች ነው::ሌሎችም በቅርብ ርቀት ያሉ አረቦች የጥላቻቸው መጠን ልክ የለውም:: የስንት ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ሬሳ እደላኩልን ሁላችን የምናውቀው ነው:: ምናልባት ከነሱ አንዱ ይሆን ጦርነት የሚያነሳብን ወይስ ሌላ.? ማንንም ሀገር የማጥላላት ዓላማ የለኝም:: ግን ከሁነኛ አባቶች የሚነገሩ ትንቢቶች ስህተት ናቸው ብዬ ስለማላስብ ሀገሬ ለከፉ ቀን ትዘጋጅ እላለሁ::

ትንቢት ስለ ወያኔ

በርካታ ባህታውያንና መነኮሳት ስለ ገዥው አካል የሚናገሩት ነገር አንድ ነው:: እሱም እንዲህ ይላል
“ይሄ መንግስትም( ወያኔ) እንደ አመድ ቡን ብሎ ይጠፋል:: ብዙዎቹም ሀብታቸውን እንኳን የትም ይዘው ለመሄድ እድሉን አያገኙም:: “ምነው” የሚሉበት ግዜም ይመጣል:: ኤርትራውያንም ኢትዮጵያ ውስጥ እህል ውሃ አላቸው::

እንደ አመድ ቡን ብሎ መጥፋት ምን ማለት እንደሆነ ለመረዳት ተቸግሬያለሁ:: አመድ ቦኖ ሲጠፋ የት እንደገባ እንኳን አይታወቅም:: ብን ብሎ ይጠፋል::ምናልባት እንደዛ ማለት ይሆንን? ፈጣሪ ይወቀው:: ግፍ የሰሩ ሰዎችም ፍርድ ፊት መቅረባቸው የማይቀር ይመስላል:: “ምነው” ብለው እስኪጸጸቱ ድረስ ፍርዳቸውን ይቀበላሉ::
አስከፊው ግን ከወያኔ በኋላ ስለሚኖረው ሁኔታ የሚነገረው ነው::

ትንቢት ከወያኔ ውድቀት በኋላ

“በዚያን ግዜ የአህዛብ ንጉስ ይነግሳል:: ለቤተ ክርስትያንና ለክርስትያኖችም መልካም ያልሆነ ግዜ ይሆናል:: ደም ይፈሳል:: ብዙ በዳር ሀገር ያሉ ክርስትያኖች መክራ ያገኛቸዋል:: ሰማዕትነት ይቀበላሉ:: ትልቅ ክብርም ያገኛሉ::ከሰማዕትነት ይቆጠርላቸዋል:: ብዙ ወጣቶችም ይሄን ክብር ይቋደሳሉ:: እንደ ቅዱስ ጊዮርጊስ እንደ ቅዱስ መርቆርዮስ ሰማዕትነት ይቆጠርላቸዋል:: የኑሮ ውድነቱም የከፋ ይሆናል:: የኤድስ በሽታም የሚመሰገንበት ግዜ ይመጣል:: በኢትዮጵያም የሚቆመው መንግስትለ ዓለም መንግስታትም ያስቸገረ ይሆናል:: ነገር ግን ስለ ቅዱሳን ጸሎትና ምልጃ እድሜው አጭር ይሆናል”

ይሄም ምን ማለት እንደሆነ ትክክለኛውን ትርጓሜ እንዲህ ነው ማለት ባልችልም ምናልናትም እምነቱ የተለየ ሰው በኢትዮጵያ ላይ ይሾማል:: ኤድስ ለንስሓ ግዜ የሚሰጥ በሽታ ነው:: ምናልባትም ለንስሓ ግዜ የማይሰጥ አጣድፎ የሚገድል በሽታ ሳይሆን አይቀርም::

ትንቢት ስለ ንጉሥ ቴዎድሮስ

” ኢትዮጵያን በዘንግ አርባ አመት የሚገዛ ንጉሥ( ቴዎድሮስ ይሉታል) ይነግሳል:: የሚነሳውም ከምስራቅ ነው:: በሱ ዘመን ስደት ወደ ኢትዮጵያ ይሆናል:: አንድ እንጀራ ለአስር ሰው ያጠግባል:: በሱ ዘመን እንኳን የሰው የንጨት ጠማማ አይኖርም:: ኤርትራም ወደ እናት ሀገሯ ትመለሳለች:: ፍቅርና አንድነት ይሆናል:; የተከፈለው ሲኖዶስም አንድ የሚሆነው በሱ ዘመን ነው::ኢትዮጵያ እጅግ ታላቅ ሀገር ትሆናለች::በሱ ዘመን የሚነሱትም ፓትርያርክ እጅግ የበቁና ገቢረ ተአምር የሚያደርጉ ይሆናሉ:: “

ትንቢቱን ከተናገሩት አባቶች ደጋግሜ ማብራርያ የጠየኩት ይሄንን ክፍል ነው:: ማብራርያውም ይሄን ይመስላል:: ዘንግ የተባለው ያለ ጦርነት በፍቅር በሰላም ማለት ነው::በዚህ ሰው ንግሥና ዘመን በኢትዮጵያ ፍጹም ሰላም ይሆናል:: በሀሪቱም በረከት ይዘንባል:: ከሌላው ሀገር ተለይታም የጥጋብና የበረከት ሀገር ትሆናለች:: የበርካታ ሀገር ስደትኞችንም የምታስተናግድ የስደተኞች መጠለያና ማረፍያ ትሆናለች:: ለዘመናት ደም ሲቃቡ የነበሩት ኤርትራና ኢትዮጵያም አንድ ይሆናሉ:: ሁለቱ ወንድማማች ህዝቦች ወንድማማችነታቸውን አድሰው በሰላም በፍቅር ይኖራሉ:: የተከፈለው ሲኖዶስም አንድ የሚሆነው በሱ ዘመን ነው:: በዛ ዘመን የሚሾሙትም ፓትርያርክ ሕዝብን ከአምላኩ የሚያስታርቁ : ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ : ተአምር የማድረግ ጸጋ የተሰጣቸው ትልቅ አባት ናቸው::

ቴዎድሮስ ማነው? የሚነግሰውስ መቼ ነው?

ሌላው ብዙ የጠየኩትና የተመራመርኩት ነገር ቢኖር ስለ ቴዎድሮስ ማንነት ነው:: በዚህ ዙርያ ሁለት ነገሮችን ሰምቻለሁ:: አንዱ ቴዎድሮስ ማለት የተሰወረው ነአኩቶለአብ ነው እሱ ነው ተመልሶ መጥቶ ኢትዮጵያን የሚመራው የሚል ነው:: ይሄንን የሚሉት አንድ ሰው ብቻ ናቸው የገጠሙኝ:: ትልቅና የተከበሩ የሃይማኖት አባት ስለሆኑ የሳቸውንም ማብራርያ ጻፍኩት::

ብዙዎቹ ግን የሚሉት ቴዎድሮስ ሌላ ነው እሱም ተወልዷል :: አድጓል:: መሉ ሰው ነው:: መሰረቱም ከቀድሞዎቹ ነገስታት ወገን ነው:: የሚቀባው አባት ብቻ ነው የቀረው የሚል ነው:: ብዙዎቹ እንደሚሉት ከሆነም ቴዎድሮስ ባሁኑ ሰአት ወደተለያዩ ቅዱሳት ገዳማት በመጓዝ ከአባቶች በረከት እየተቀበለ እንደሆነ ተነግሮለታል:: በእምነቱ ጻድቅና ለማንም የማያዳላ: ለድሃና ለተበደለ የሚፈርድ እውነተኛ ዳኛ እንደሚሆንም ይነገራል::

ነገር ግን አሁን በየቦታ ” ቴዎድሮስ ማለት እኔ ነኝ ” እያሉ በየቦታው እንደሚለፈልፉት እንዳይደለና እንደዚህ የሚሉት ብዙዎቹ በሀሰት መናፍስት እየተመሩ የሚያብዱ መሆናቸውን ብዙ አባቶች ያስጠነቅቃሉ::

ሲጠቃለል

 ወያኔ መውደቁ አይቀርም:: አወዳደቁ ግን እጅግ የከፋ እንደሚሆንና እንደአመድ ብን ብሎ እንደሚጠፋ::
 በኢትዮጵያም ላይ የአህዛብ ጦርነት እንደሚነሳ:: ያም ብዙሰዎችን እንደሚለበልብ :: በዚያን ዘመንም እምነቱ ልዩ የሆነ ሰው መሪ እንደሚሆን: በሱም ዘመን ኑሮ ውድነቱ የከፋ እንደሆነ: በተለይ ለቤተ ክርስትያና ክርስትያኖች የመከራ ግዜ እንደሚሆን ነገር ግን ግዜው አጭር አንደሆነ::በመጨረሻ ግን ኢትዮጵያን በዘንግ የሚገዛ ጻድቅ መሪ እንደሚያስተዳድራት የ ኤርትራና የኢትዮጵያ ችግርም እንደሚፈታ ተነግሯል::ቤተክርስትያንም ከአስመሳዮች የምትላቀቅበት ወቅት እንደሚሆንና የሁለቱም ሲኖዶስ ፍጹም እርቅ የሚፈጸመው በዚያን ግዜ እንደሚሆን ተነግሯል::ቴዎድሮስ የማንንም እርዳታ የማይሻ : ራሱ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ለመታደግ በራሱ ሃይል: የሚልከው ስለሆነ “ቴዎድሮስ ይሄ ነው ያ ነው: በዚህ መጣ በዚህ ሄደ” በሚል አጓጉል ሀሰት ምእመናኑ እንዳይወናበድ ያስገነዝባሉ:: ክፉውም የሚርቀው መልካሙም የሚቀርበው በጸሎት ነውና የሁሉም ገዳማውያን ተመሳሳይ መልዕክት አንድ ነው ” የመከራ ዘመን ከፊታችን አለና ተግታችሁ ጸልዩ:: እግዚአብሔር ያርቀው ዘንድ”

በመጨረሻ

ይሄን ጽሁፍ የሚያነብ ሰው ከሁለት ጎራ ሊመድበኝ እንደሚችል ከወዲሁ ይታየኛል:: የመንግስት ደጋፊ የሆነ ሁሉ በመንግስታችን ላይ የሚያሟርት ቀልደኛ ፌዝ ብሎ ሊዘብትብኝ እንደሚችል እገምታለሁ:: የፈጠራ ድርሰትም የደረስኩ የሚመስለው ሊኖር ይችላል:: እኔ ግን የሰማሁትን ነው የነገርኳችሁ:: አለማመን መብታችሁ ነው:: ግን በልባችሁ አስቀምጡት:: ከሁሉም በላይ ስለሀገራችን ስለሕዝባችን አንዲት ደቂቃም ብትሆን በየቀኑ እንጸልይ:: አበቃሁ::

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment