ከማእከላዊ ዕድሜ ጀምሮ ወደ ኋላ ያለ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሚያስታውሰው እግዚአብሔር የለም የሚለው ትምህርት በይፋ በኢትዮጵያ የተነገረበት ዘመን የደርግ ዘመን ነው። ይህ የክሕደት ትምህርት የተነገረው በቤተ መንግሥትና በሕዝባውያን ቦታዎች ብቻ ሳይሆን በቤተ ክህነትም ነበር። ይህ ዘመን በቤተ ክህነቱ የስብከተ ወንጌል አዳራሽ ውስጥ «በስመ ማርክስ ኤንግልስ ወሌኒን ብንል ምናለበት?» ተብሎ እስከ መነገር የተደረሰበት ከፍተኛ ክሕደት የተፈጸመበት ጊዜ እንደ ነበረ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ሰዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን በይፋ ሄደው መሳለም የፈሩበት፥ ልጆቻቸውን ክርስትና ማስነሣት ያፈሩበት፥ የእግዚአብሔርን ስም በግልጥ መጥራት የተሰቀቁበት ጊዜ ነበር። በዚህ ጊዜ ነበረ በአንዱ የመስቀል ደመራ በዓል ዕለት አለቃ አያሌው ታምሩ በመስቀል ዐደባባይ ለተሰበሰበው ሕዝብ ትምህርት እንዲሰጡ የተጋበዙት።
የመስቀል ዐደባባይ ብዛት ባለው ሕዝብ ተሞልቷል። ሕዝቡም ሥነ ሥርዓቱን ይከታተላል። መዘምራን በዕለቱ የሚቀርበውን ያሬዳዊ ዜማ አሰሙ። አለቃ አያሌው ደግሞ ትምህርት ሊሰጡ ቀረቡ። ትምህርት በሚሰጡበት ጊዜ የሆነውን ነገር በጊዜውና በቦታው የነበሩት ፕሮፌሰር ነቢያት ተፈሪ እንደሚከተለው አቅርበውታል።
«በደርግ ዘመን መስቀል በዓል በሚከበርበት ጊዜ አብዮት ዐደባባይ ይባል ነበረ አሁን እንኳ ለስሙ መስቀል ዐደባባይ ተብሏል ለደመራ ወጥተው በሚያስተምሩበት ጊዜ ኻያና ሠላሳ ሺ ሰው ተሰብስቧል፤ ትዝ ይለኛል ብቻ ባልሳሳት አብዮተኛ ፓርቲዎች ወይንም ድርጅቶች አንድ የሆኑበት አምስት ድርጅቶች አንድ የሆኑበት ጊዜ ነበርና በዚያን ጊዜ ደርግ ሕዝቡን እየሰበሰበ በያደባባዩ መፈክር ያስተምር ነበር። ሁሉም ሰው አብዮታዊት እናት አገር ወይም ሞት! አያለ ግራ እጁን እየወረወረ ሁላችንም እንል ነበር።
እሳቸው ስለ መስቀል አስተማሩና ከጨረሱ በኋላ አሁን እንግዲህ ይህንን ከተረዳችሁ አሉና «መስቀል ኃይላችን ነው! መስቀል መድኃኒታችን ነው!» ብለው ቀኝ እጃቸውን አንሥተው ይጮሃሉ። ሕዝቡ ዝም አለ መሰለኝ። ኋላ ሁለተኛ ደገሙት። ሕዝቡ ምን እንደሚፈልጉ ገባው። ከዚያ ሕዝቡ «መስቀል ኃይላችን ነው! መስቀል መድኃኒታችን ነው!» አለና ቀኝ እጁን ወረወረና መፈክር አሰማ። ከዚያ «መስቀል መድኃኒታችን ነው! መስቀል ቤዛችን ነው!» ሲል በቃ አለቀ። ሕዝቡን ሙሉ በሙሉ ቀየሩት። ከዚያ በኋላ ሕዝቡ ተበረታቶ ወደ ቤተ ክርስቲያን ማምራት ጀመረ። እስከዚያ ድረስ ግን የሃይማኖት ጉዳይ ተዳፍኖ ነበር።»
የአቡነ ወልደ ጊዮርጊስ (አለቃ አያሌው ታምሩ) በረከታቸው ይደርብን። አሜን!!!
የመረጃ ምንጭ፦ የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ መጽሔት።
መጋቢት 23 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል
Blogger Comment
Facebook Comment