አለቃ አያሌው ታምሩ እና መንግሥቱ ኃ/ማርያም‼️ሐውልቱና የታኅሣሥ ገብርኤል በዓል‼️


ጊዜው ፲ ፱፻፸፮ ዓመተ ምሕረት የታኅሣሥ ገብርኤል በዓል ነበረ። በዚያ ዓመት በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ የኮሎኔል መንግሥቱ ኀይለ ማርያም ምስል ያለበት ሐውልት ተሠርቶ ቆሞ ነበር። አለቃ አያሌው ታምሩ በብሥራተ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ተገኝተው እንዲያስተምሩ ተጋብዘው ነበርና በዚያ ተገኝተው ነበር። ቅዳሴና የታቦቱ ዑደት ከተፈጸመ በኋላ በቦታው ለተገኘው ብዙ ሕዝብ ትምህርት መስጠት ጀመሩ። ስለ በዓሉ ታላቅነትም አስተማሩ።

 የበዓሉ ባለ ታሪኮች ሠለስቱ ደቂቅ ንጉሡ ናቡከደነፆር ላሠራው ሐውልት አንሰግድም በማለታቸው የተቀበሉትን መከራና እግዚአብሔርም ቅዱስ ገብርኤልን ልኮ እንዴት ከተጣሉበት እሳት እንዳወጣቸው በማስታወስ ካስተማሩ በኋላ፤ ወደ ሕዝቡ ዕለታዊ ሕይወት በመግባት፤ በጊዜው የነበሩት የአገሪቱ መሪዎች የሐውልት መታሰቢያ ለማቆም የሚያበቃ አንድም የረባ ነገር ሳይሠሩ ምስላቸው ያለበት ሐውልት ማቆማቸው ከናቡከደነፆር ሥራ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን፤ ምእመናን ለዚህ ሐውልት ሳይሆን ለአምላካቸው ለእግዚአብሔር ብቻ ክብርን ሊሰጡ እንደሚገባ የሚገልጽ ቅኔ ለበስ ተግሣጽ ይናገራሉ።

 ትምህርቱን ጨርሰው ወደ ቤታቸው ሲያመሩ ከመንገድ ላይ የሕዝብ ደኅንነት ሰዎች አፍነው ወደ ደኅንነት ቢሮ ይወስዷቸዋል። ያፈኗቸው ሰዎች አለቃ ያደረጉትን ንግግር በመቅረጸ ድምፅ ቀርጸው ይዘው በማስረጃ ለአለቆቻቸው ከሰሷቸው።ጉዳዩ የቀረበላቸው ኃላፊ ግን፤ «እባክዎ አለቃ! መንግሥትን የሚተች ነገር አይናገሩ። በጣም ብዙ ጊዜ እስዎን እንድንከታተል፥ እንድናስወግድ ትእዛዝ ተሰጥቶናል። ግን የቤተ ሰብ ታሪክዎን ስናጠና የብዙ ልጆችና የቤተ ሰብ ኃላፊ ነዎት። ስለዚህ የሚጎዳዎትን ነገር ለማድረግ ተቸግረናል። አሁንም የምንጠይቅዎ እንዲህ ዐይነት ትምህርት ከማስተላለፍ እንዲቆጠቡ ነው፤» በማለት አሰናብተዋቸዋል።

የመረጃ ምንጭ፦ የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ መጽሔት።

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment