"ኢትዮጵያን እናድናት" - አለቃ አያሌው ታምሩ

የክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ
100ኛ ዓመት ልደት መታሰቢያ
መጋቢት 15 ቀን 2ዐ15 ዓመተ ምሕረት

እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤
ሐሤትን እናድርግ፤
በእርስዋም ደስ ይበለን፡፡
መዝ፤117፥23-24፡፡

( ከቃለ መጠይቆቻቸው ስብስብ መካከል ለመታሰቢያ የቀረበ)

ሙዳይ መጽሔት ጥቅምት 1985
“ኢትዮጵያን እናድናት”

"ችግራችን የክልል፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የዘር ልዩነት አይደለም አንድነታችንን አጠናክሮ ከድህነት ማጥ ውስጥ በማውጣት ለተሻለ ሕይወት ሊያበቃን የሚችል ሕዝብ የመረጠውና የሾመው አስተዳዳሪ አለማግኘቱ ነው፡፡ በመሆኑም ይህች የሁላችንም መሰባሰቢያ የሆነችው ክብርት ኢትዮጵያ እንደ ዳቦ እየተቆረሰች እየጠፋች ነው፡፡ ፈጥነን ከዚህ መከራ እናድናት፡፡"
ይህን አስተያየት የሰጡት ታዋቂው ምሁር አለቃ አያሌው ታምሩ ናቸው፡፡ ከአራት ሰዓት በላይ በቆየንባቸው የጥያቄና መልስ ጊዜያቶች ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ ካሉበት የቤተ ክህነት ዓለም ውስጥ ወጥተው በወቅቱ የፖለቲካ አካሔድ ላይ የሰላ ሂስ በመሠንዘራቸው የሃይማኖት ሰዎችና ፖለቲካ አይገናኙም በሚል በአንዳንድ የዋሆች ዘንድ ያለውን እሳቤ መሠረት የለሽ አድርገውታል፡፡

አለቃ አያሌው ታምሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሆነው ለብዙ ዓመታት አገልግለዋል፤ አሁንም እያገለገሉ ነው፡፡ ከ1953 ዓ.ም. እስከአሁን ድረስ የሥነ ሃይማኖት፣ የባህል፣ የታሪክ የፍልስፍና እንዲሁም የተለያየ ዕውቀት ተጠቃሽ ምንጭ ሆነው በመገናኛ ብዙኃንና በየስብሰባው አዳራሽ ያሠራጩት ትምህርት በሕዝብ ዘንድ ፍቅርንና አክብሮትን አትርፎላቸዋል፡፡ ከዚህም ጋር ቤተ ክህነት ተሐድሶ ማድረግ እንዳለባት ከመንግሥት ተፅዕኖም ነጻ ሆና በራሷ አስተዳደር በነፃነት እንድትመራ ለማድረግ ከአፄ ኃይለ ሥላሴ ዙፋን ውድቀት ጀምሮ ከተተኪው እኩይ መንግሥት ጋር በግንባር የተጋፈጡ ሰው ናቸው፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ በግልጽ ይቃወማሉ፡፡ በገሐድ ይወቅሳሉ፡፡ አንደበተ ርቱዕ ናቸው የመጻሕፍት ገጽና ምዕራፍ ከጫፍ እስከጫፍ በአእምሮአቸው ውስጥ ቀርጸው በማስቀረት ዓይናማዎች የሚያጐድሉትን /የሚስቱትን/ ዕውቀት ፈጥሮ የማረም ችሎታቸው ከፍተኛ ነው፡፡

በወደቀው መንግሥት የሞት ቀለበት ውስጥ ወድቀው ሰማዕትነትን ይቀበሉ ዘንድ ከተፈረደባቸው ወገኖች መካከል አለቃ አያሌው ታምሩ አንደኛው መሆናቸው ይነገራል፡፡ የክቡር ደጃዝማች ከበደ ተሰማ እንዲሁም የኤርትራው ተወላጅ የክቡር ንቡረ ዕድ ድሜጥሮስ ጩኸትና ልመና ባይኖር ኖሮ እኒህ ታላቅ ምሁር በአሁኑ ወቅት የ16 ዓመት የመቃብር ዓለም ዕድሜያቸውን ያስቆጥሩ ነበር፡፡

ሕዝብ የሾመውን ፓትርያርክ ሕዝብ ያወርደዋል እንጂ መንግሥት ምን አገባው በማለት እነ ዶክተር ጌታቸው ኃይሌና እነ ዶክተር ሐዲስ የሻነህ ተቃውሞአቸውን በግልጽ አሰምተው እሥር ቤት ሲወረወሩ ድብደባ ሲፈጸምባቸው ለአለቃ አያሌው የተመረጠው የሞት ቅጣት ግን የብፁዕ አቡነ ቴዎፍሎስ ዕጣ ፋንታ ሆኖ የአንዱ ሕልፈት ለሌላው ሕላዌ ምክንያት ሆነና ተረፉ፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ የአለቃ አያሌው አንደበት የተሳለን ሰይፍ ፈረታ ዝምታን አልመረጠችም በቀብር ሥርዓት በበዓላት ቀንና በየትምህርት መስጫው አዳራሽ ላይ በመገኘት የሥርዓቱን ብልሹነትና የሃይማኖት የለሽ ኮሚኒስቶች የረከሰ ተግባር በሰም ለበስ አነጋገራቸው ሳይሸነቁጡ ያለፉበት ጊዜ የለም፡፡ የዓይን ብርሃናቸውን ስላጡ ብቻ የት ይደርሳል ይለፍልፍ በሚል ትምክህት መናቃቸው ግን ጠቀማቸው እንጂ አልጐዳቸውም፡፡ ስለሆነም በሕይወታቸው ተርፎ ዛሬን መኖር ቻሉ ለአለቃ አያሌው ግን ዘንድሮም ከአምና የተለየ ሆኖ አልተገኘም፡፡ አሁንም ከወቅቱ ጋር አልታረቁም፡፡ ....
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment