ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው በራእይ የተሰጣቸውን መልእክት‼️

ክቡር አባታችን አለቃ አያሌው ግን፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሮም ጥገኛ መሆን የለባትም፥ ፓትርያርኩ መሓላቸውን አፍርሰዋል፥ ጉዳዩንም ቅዱስ ሲኖዶስ ሊያየው ይገባል በሚለው አቋማቸው ጸኑ። በይበልጥ ደግሞ ሐምሌ ፭ ቀን ፲ ፱፻፹፭ ዓመተ ምሕረት ያዩት ራእይ ያነሡትን ጥያቄ በቆራጥነት እንዲገፉበት ምክንያት ሆነ። ይህንንም ራሳቸው በአንደበታቸው እንደሚከተለው ገልጸውታል። 

«ዛሬ ካለው የቤተ ክርስቲያን አመራር ጋራ ወደ ትግል ሰልፍ እንድገባ ያደረገኝ የኔ ፈቃድ፥ ዐቅምም አይደለም። በ፲ ፱፻፹፭ ዓመተ ምሕረት ሐምሌ ፭ ቀን ኦፕራሲዮን ሆኜ በሰመመን ውስጥ በነበርኩበት ጊዜ በሥርዓተ ሙታን ወደ አምላኬ ፊት ቀርቤ የተሰጠኝ ትእዛዝ ነው። በዚያች ሰዓት፤ ከቅዱስ ማርቆስ እስከ ሳድሳዊ ቄርሎስ የነበሩ የእስክንድርያ ፓትርያርኮችና ሊቃነ ጳጳሳት፥ ከአትናቴዎስ፥ ከሰላማ እስከ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ የነበሩ የኢትዮጵያ ሊቃነ ጳጳሳትና ፓትርያርኮች የእሳት ነበልባል በከበበው፥ የእሳት ልሳን ያለው መጋረጃ በተንጣለለበት በዚያ አዳራሽ፥ በዚያ የግርማ ዙፋን ግራና ቀኝ ተሰልፈው ቁመው ነበር። 

በኤፌሶን ጉባኤ ንስጥሮስን ያወገዘው የእስክንድርያ ሊቀ ጳጳሳት ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ቄርሎስ በመንበሩ ፊት ለፊት ቆሟል። ቀድሞ የተወገዘው ንስጥሮስ የማዕረግ ልብሱን ተገፎ በስተጀርባው ቆሟል። አባ ጳውሎስ በማዕረጋቸው እንዳሉ ተከስሰው ከንስጥሮስ ጎን ቁመዋል። በዐጸደ ነፍስ የሚገኙት የእስክንድርያና የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አበው፤ አባ ጳውሎስ ሺ ስድስት መቶ ዓመት የኖረ ውግዘት ጥሰው፥ በሥጋው በደሙ የማሉትን መሓላ አፍርሰው የኢትዮጵያን ቤተ ክርስቲያን የሮም ቅኝ ግዛት ስላደረጉ፤ ፍርድ ይሰጥልን ሲሉ ለኀያሉ አምላክ አቤቱታ አቀረቡ። ከዙፋኑ የመጣው መልስ ግን፤ እስከ ዕለተ ምጽአት ፍርድ የቤተ ክርስቲያን ነው፤ የሚል ነበረ። 

ይህ ሁሉ በሚከናወንበት ጊዜ የማላውቀው ኀይል ከዚህ ዓለም ነጥቆ ከቅዱስ ቄርሎስ ጎን አሰልፎኝ ከቆየ በኋላ ከዙፋኑ የመጣው ድምፅ፤ አንተ ያየኸውን፥ የሰማኸውን ለቤተ ክርስቲያን፥ ለምእመናን ንገር፤ ሲል አዝዞ ወደ ነበርኩበት መለሰኝ። ይህ ትእዛዝ ነው እዚህ ሰልፍ ውስጥ ያስገባኝ። ኢትዮጵያዊ፥ ኦርቶዶክሳዊ የሆነ ሁሉም ስለ ቤተ ክርስቲያኑ አጥብቆ መታገል አለበት።»
በራእይ የተሰጣቸውን መልእክትም መጀመሪያ ለፓትርያርኩ ቀጥሎም ለቅዱስ ሲኖዶስ ቢያቀርቡም ጉዳዩ በመታፈኑ ለእያንዳንዱ ጳጳስ በግል ደብዳቤ ለማሳወቅ ተገደዱ። ኅዳር ፳፫ ቀን ፲ ፱፻፹፯ ዓ፤ ም፤ ለቅዱስ ሲኖዶስ የላኩት ደብዳቤ ሙሉ ቃል የሚከተለው ነበር። 

«ጥቅምት ፲ ፯ ቀን ፲ ፱፻፹፯ ዓመተ ምሕረት ስለ ቤተ ክርስቲያናችን ያለውን ጠቅላላ ሁኔታ በመግለጥ ቅዱስ ሲኖዶስ እርምጃ ወስዶ ቤተ ክርስቲያንን ከውድቀት እንዲያድን፤ ይህን ሳያደርግ ግን ወደ ሌላ ሥራ እንዳይገባ ሲኖዶሱን በሾመና በሚመራ በመንፈስ ቅዱስ ዳኝነት ተማጽኜ የጻፍኩትን ማመልከቻ ለሲኖዶሱ ጽሕፈት ቤት አቅርቤ ነበረ። እስከ አሁን ለሲኖዶሱ አለመቅረቡንና ሲኖዶሱም ያልተወያየበት መሆኑን ስለ ተረዳሁ እንደገና ቅጂውን አንዳንድ የቀሩ ቃላትንም በማስተካከል በፖስታ ቤት በኩል ልኬዋለሁ። የሲኖዶሱ ብፁዓን አባሎች እንደምታውቁት እኔ አንድ ተራ ድኻና ደካማ ሰው ነኝ። ግን ያለሁበት የሥራ ወንበር በታሪክ ፊት ተጠያቂነት ያለው ነው። ለዚህ ነው መላልሼ ለማመልከት የተገደድኩት።

ብንወድም ባንወድም በአሁን ጊዜ ያለነውን የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ታሪክ ተጠያቂ አድርጎናል። በእግዚአብሔር ፊትም መጠየቅ ይጠብቀናል። ቤተ ክርስቲያንና ኢትዮጵያ በሕግ አንድ ሆነው ከመኖር ከተለያዩበት ከ፲ ፱፻፷፮ ዓ፤ ም፤ ጀምሮ እስከ ዛሬ ኢትዮጵያ ከውድቀት ወደ ውድቀት በመሄድ ላይ ስትሆን ድንበሯን፥ ሰንደቅ ዓላማዋን፥ ሃይማኖቷን፥ አገርነቷን፥ ሕዝቧን እያጣች ነው። ቤተ ክርስቲያንም ስሟን፥ ክብሯን፥ ታሪኳን፥ ሃይማኖቷን፥ ሀገረ ስብከቷን፥ ጽዮንንና መመኪያዋን የክርስቶስን መስቀል እያጣች ነው። ጠላቶቿና የአገሯ ጥንተ ጠላቶች እየተተከሉ አገሯና እሷ ግን ከህልውናቸው እየተነቀሉ ናቸው። እግዚአብሔር መንፈሳውያን ሰዎቹን፤ «ክላህ በኃይልከ ወአንሥእ ቃልከ ወኢትምሓክ።»

 «በኃይል ጩኽ፤ ድምፅህን አሰማ፤ ይሉኛል አትበል፤» እያለ ሲቀሰቅሳቸው መኖሩ ይታወቃል በዚህ ምክንያት ነቢያትና ሐዋርያት ተከታዮቻቸውም በሰው ፊት በዓለም እየተናቁና እየተጠሉ ፍቅሩንና ዐደራውን ሲመሰክሩ ኖረዋል። ዛሬም ያለነው የቤተ ክርስቲያን ሰዎች ይበልጡንም በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉ አባቶች ስለ ኢትዮጵያ፥ ስለ ትውልዷ፥ ስለ ቤተ ክርስቲያኗ፥ ስለ ሃይማኖቷ፥ ስለ ታሪኳ ተጠያቂዎች ናቸው። ተጠያቂዎች ነን። ሌላ ማድረግ ባይቻል እንኳ ድምፅን ማሰማት ከቤተ ክርስቲያን በኩል የሰውም የእግዚአብሔርም ግዴታ ነው።

ስለዚህ እላይ እንደ ጠቀስኩት በዚህ ደብዳቤ አማካይነት የፊተኛውን ቅጂ እንደገና አቅርቤአለሁ። ከዚህ በፊት ሲኖዶሱ ተወያይቶበት በቤቱ ውስጥ በሚሰጠው ውሳኔ ይፈጸማል በማለት ወደ ውጪ አላሰማሁም። አሁን ግን በዚህ በኩል ፍሬ ማግኘት ካልተቻለ ጉዳዩን ክርስቲያኑ ሕዝብ እንዲያውቀው ለማድረግ የወሰንኩ መሆኔን በፍጹም ትሕትና ስገልጽ አሁንም ሲኖዶሱ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ በቸልታ እንዳያልፈው ሞቷም የእናት ሞት ነውና ችላ እንዳይለው በድጋሚ ሲኖዶሱን በሾመና በሚመራ በመንፈስ ቅዱስ ዳኝነት ተማጽኜአለሁ።»

የመረጃ ምንጭ፦ የክቡር አለቃ አያሌው ታምሩ የመንፈቅ መታሰቢያ መጽሔት።

 መጋቢት 23 100ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment