መጋቢት 23 ቀን 2ዐ15 ዓመተ ምሕረት
እግዚአብሔር የሠራት ቀን ይህች ናት፤ሐሤትን እናድርግ፤በእርስዋም ደስ ይበለን፡፡መዝ፥117፤23-24፡፡
ባለፈው 1ዐዐ ዓመት ውስጥ ወደዚህች ምድር መጥተው ታላላቅ ሥራዎችን አበርክተውልን ካለፉ ድንቅ ሰዎች አንዱ የሆኑት ክብር አባታችን አለቃ አያሌው ታምሩ ፤ የተወለዱት መጋቢት 23 ቀን 1915 ዓመተ ምሕረት ሲሆን ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ደግሞ ነሐሴ 14 ቀን 1999 ዓ.ም ነው፡፡
የአለቃ አያሌው ታምሩን ግለ ታሪክ በተመለከተ በሥማቸው በተከፈተው ድረገጽና እንዲሁም ልጃቸው የሆኑት ወ/ሮ ሥምረት አያሌው "አባቴ እና እምነቱ"በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ ላይ መረጃ ማግኘት ይቻላል፡፡
ለ100ኛ ዓመት ልደታቸው መታሰቢያ ይሆኑ ዘንድ ምናልባት እንደገና ቢታወሱ ይጠቅሙ የሆናል ብለን የምንገምታቸውን ጥቂት ጽሑፎች በተከታታይ ለወገኖቻችን ስናካፍል ደስታ ይሰማናል፡፡
የክቡር አባታችን የአለቃ አያሌው ታምሩ ሙሉ ሕይወት ከኢትዮጵያ እምነትና ታሪክ ጋር በጥብቅ ተቆራኝቶ የኖረ እንደመሆኑ መጠን እሳቸው ያወቁትን ለትውልድ ለማሳወቅ በወሰዱት የዕድሜ ልክ ተሰጥዖም በርካታ የትምሕርት ቅርሶችን ለትውልድ አስቀምጠዋል፡፡ ክቡር አባታችን ያስተማሯቸው ትምሕርቶች ከፊሎቹ ትላንትን፣ ከፊሎቹ ዛሬን የቀሩት ደግሞ ነገን የሚያመላክቱ በመሆናቸውና ለኢትዮጵያ፣ ለኢትዮጵያውያን አንዲሁም ለቅድስት ቤተክርስቲያናችን የሚበጁ በርካታ ምክሮችን የያዙ በመሆናቸው የሚመለከታቸው ሁሉ አንብበው ቢጠቀሙባቸው ከተጨማሪ ጥፋትና ከታሪክ ተወቃሽነት ለመዳን ምክንያት ይሆናሉ ብለን አናምናለን፡፡
“ምርጢቱ”፣ “የእግዚአብሔር የግል ርስቱ”፣ “የክርስቶስ ሥረ ወጥ ልብሱ”፣“የአፍሪካ ንግሥት”…እያሉ የሚያከብሯትን ኢትዮጵያን እና “ስንዱ እመቤት”፣ “እጥፍ ድርብ እናት” እያሉ የሚያወድሷትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ ካስተማሯቸው ትምሕርቶች መካከል በጥቅምት ወር 1985 ዓ.ም. ሙዳይ መጽሔት ፣"ኢትዮጵያን አናድናት" በሚል ርዕስ ያወጣውን ጽሑፍ በመቀጠል የምናካፍል ሲሆን ተከታታይነት ባለው ዝግጅት 100ኛ ዓመት ልደታቸውን እናስባለን፡፡
ጸሎታቸው ረድዔትና በረከታቸው ከሁላችን ጋር ይሁን!
Blogger Comment
Facebook Comment