ኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ስጋት ከደቀነባቸው አገራት መካከል ናት


አንበጣ


Image copyrightGETTY IMAGES
በኢትዮጵያ ጨምሮ በበርካታ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት የተከሰተውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት-ፋኦ አስቸኳይ ድጋፍ ጠየቀ።
የአንበጣ መንጋው ክፉኛ ከሚያሰጋቸው አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን አካባቢ በአንበጣው የውድመት ክልል ውስጥ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በአፋጣኝ እርዳታው ተገኝቶ መከላከል ካልተቻለ ከባድ ቀውስን ሊያስከትል ይችላል ተብሏል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአፍሪካና በኢሲያ የተወሰኑ አካባቢዎች ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ተከስቶ በሰብል ላይ ከፍተኛ ውድመት ያደርሳል የተባለውን የአንበጣ መንጋ ለመዋጋት ነው የድጋፍ ጥሪውን ያቀረበው።
ፋኦ እንደሚለው ተጨማሪ ድጋፍ የማይገኝ ከሆነ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ የምግብ አቅርቦት ቀውስ ይከሰታል። ይህንንም ለማስቀረት ለጋሾች 62 ሚሊዮን ዶላር እንዲሰጡ ጠይቋል።
የፋኦ ዋና ይሬክተር የሆኑት ኩ ዶንግዩ ከሚገኘው ድጋፍና ከሚወሰደው እርምጃ አንጻር መጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ወሳኝ ጊዜያት ናቸው።
የአንበጣ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ከምሥራቅ ኢሲያ ሕንድ ጀምሮ እስከ ምዕራብ አፍሪካዋ ሞሪታኒያ ድረስ ባሉ 13 አገራት ውስጥ ጥረት እየተደረገ ነው።
ዋነኛው ስጋት የተደቀነው የባሕረ ሰላጤውን አገራት ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካና በየመን ውስጥ ነው ተብሏል።
በቅርቡም የአንበጣ መንጋው በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ የታየ ሲሆን መንጋው ኩዌት፣ ባህሬን፣ ኳታርና በኢራን የባሕር ዳርቻ አካባቢ እንደደረሰም ተገልጿል።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ለቢቢሲ እንደገለጸው በአንበጣ መንጋው ክፉኛ በተጠቁት በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ቢያንስ 100 ሺህ ሔክታር ስፋት ያለው መሬት የጸረ አንበጣ መድኃኒት መርጨት ያስፈልጋል።
ነገር ግን እስካሁን በተደረገው ጥረት ይህንን ማሳካት አልተቻለም፤ ከፍተኛ መጠን ያለው መሬትም በእነዚህ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ በመድኃኒት መረጨት አለበት ተብሏል።

በየአገራቱ በአንበጣ መንጋው የተጠቃው አካባቢ ስፋት

  • ኢትዮጵያ 22,550 ሔክታር
  • ኬንያ 20,000 ሔክታር
  • ሶማሊያ 15,000 ሔክታር

የሚያስፈልገው ገንዘብ

በጥር ወር ላይ የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት የ76 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ ጠይቆ የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን የሚያስፈልገው ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ደረጃ ጨምሮ 138 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ገልጿል።
ነገር ግን እስካሁን ከተጠየቀው ገንዘብ ውስጥ 33 ሚሊዮን ዶላር ብቻ የተገኘ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 10 ሚሊዮን ዶላሩን የሰጠው የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ነው።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጠየቀው እርዳታ ገንዘብ በአንበጣ መንጋው የተጠቁት አገራት በምድር ወይም በአየር የመድኃኒት መርጨት ሥራ እንዲያከናውኑና በድንበሮች አካባቢ ያለውን ቅንጅት እንዲያሻሽሉ ለማገዝ ይውላል።
በተጨማሪም በአንበጣ መንጋው ምርታቸው ወድሞ ለችግር ለተጋለጡ አርሶ አደሮች አስቸኳይና የረጅም ጊዜ ድጋፍ ለማቅረብም እንደሚውል ተገልጿል።
በየዕለቱ እያንዳንዱ አንበጣ የእራሱን ክብደት የሚያክል ምግብ የሚፈልግ ሲሆን የሚራባውም በፍጥነት ስለሆነ፤ እየተደረገ ያለው ጥረት ተሳክቶ መስፋፋቱ ካልተገታ አሁን ያለው የአንበጣ መንጋው መጠን በመጪው ሠኔ ወር ላይ በ400 እጥፍ ተራብቶ ከባድ ቀውስን ሊፈጥር ይችላል።

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment