ከገዳማውያኑ አባቶቻችን ለተዋሕዶ ልጆች የተላከ መልእክት፤



1. አትፍሩ፣ ጥቂት የመከራ ጊዜ ይቀራል። በእመቤታችን ሱባዔ ያነባችሁት እንባ የንስሐ መንገዳችሁ የተወደደ ነውና ቀጥሉበት። እንደ ጥንቱ እንደ አባቶቻችን የጳጉሜን ሳምንት ለሚመጣው የሰማዕትነት ጊዜ ያበረታን ዘንድ ሁላችንም በያለንበት በፆምና በሱባዔ እናሳልፈው።
2. በሱባዔያችን አጋማሽ እሑድ ጳጉሜ ሦስት ከቅዳሴ መልስ በያለንበት ሀገር የሚከተለውን መልእክት ይዘን በዝማሬ "ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየኝ ማን ነው? ተዋሕዶ ንፅኅት እምነቴ" እያልን እየዘመርን የተዋሕዶን ክብር እንድናሳይ ይሁን። በዚህች ቀን የሚነቅፋችሁም የሚቃወማችሁም ማንም አይኖርምና አንድም ነፍስ ከቤቱ እንዳይቀር። ሁሉም ከየአጥቢያው ቅዳሴ እንዳበቃ በቀጥታ "ኃይል የእግዚአብሔር ነው" እያለ እያዜመ በየከተማው አደባባይ ተገኝቶ እናታችን እምዬ ተዋሕዶ ሃይማኖታችን መቅደሷ ሲቃጠል ካህናቷ ሲታረዱ የተሰማንን ሀዘን ይግልፅ። የተዋሕዶ ጠላቶችም በዚህች ቀን እጃቸውን በእፋቸው ይጭናሉ። እፍረትንም ይለብሳሉ። የተዋሕዶ ልጆችም ሊገድሉ ሳይሆን ክርስቲያን አራጅ አይድልምና ከተዋሕዶ እናታቸው በፊት ሰማዕት ሊሆኑ መዘጋጀታቸውን ይገልፃሉ። የተዋሕዶ ልጆች መልእክትም፦ ከእንግዲህስ እኛ በሕይወት እያለን ከተዋሕዶ እናታችን ደጅ አንድ ሣር አይቃጠልም፤ አንድ ካህን አይታረድም፤ በተዋሕዶ አማኝነቱም አንድ ምእመን ከመኖርያ ቀዬው አይሰደድም፤ ከሥራው አይባረርም። ተዋሕዶ ሃይማኖታችን መቼም በዘር አትከፋፈልም። በመላው ኢትዮጵያና በዓለማት ሁሉ ጳጉሜ ሦስት ተዋሕዶ ልጆች እንዳሉዋት ዓለም ያያል። በዚህ ቀን የተዋሕዶ ልጅ ሁሉ ለእናት ቤተክርስቲያኑ እጋርነቱን ያሳይል። ሁሉም ተዋሕዶ እናቴ እያለ ይተማል። ጠላትም አንገቱን ይደፋል። ሁሉም በሰላም ለተዋሕዶ ያለውን አጋርነት አሳይቶ ወደቤቱ በሰላም ይገባል።
3. ኢትዮጵያ ቀና ትላለች። የሰማዕትነት ጊዜ መጥቷል ዘመኑ አጭር ነውና በርቱ። በቅድስት ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ስላለው ነገር የቤተ ክርስቲያን ውድመት አምላክ ፍርዱን ይሰጣል። አሁን እንፀልይ እንደጀመርነውም ጥቂት ንስሐ እንግባ ጥቂትም ሰማዕታት ይመጣሉ፣ ከዚያ በኋላ ግን የቤተክርስቲያን ጠላቶች "ይህች ተራራ ትውደቅብን" ይላሉ። መሸሸጊያም አይኖራቸውም።
4. በመስቀል ዐለት በመስቀል አደባባይ እግዚኦታ አድርሱ። "መስቀል ኃይላችን ነው" በሉ። ዕለቱን የተዋሕዶ መድምቂያ እንጂ የፖለቲካ ሰዎች መታወቂያ አታድርጉት። እሳቱን የተዋሕዶ አባቶች ይለኩሱት። ዕለቱ በፖለቲካ ንግግር እንጂ ሃይማኖታዊ ለዛውን ለማሳጣት ጠላት አቅዷልና እናንተስ እግዚኦ በሉበት። ምስጋናም አይረሳ። የመስቀሉ ቃል ኃይላችሁ ነውና።
የእኛዋ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ለዘላለም ደምቃ ትኖር ዘንድ የሚመጣውም የመከራ ዘመን የበለጠ ያጥር ዘንድ ተግታችሁ ፀልዩ። መቀለድ እና እንደዋዛ መዘባበቱ ይበቃል ማመናችን በሥራ የሚገለጥበት ጊዜ ነው፡፡ 

አሜን::



Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment