በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ከቃሉ አንዲቷም ፈፅሞ በማትታበል በአንድ አምላክ ስም
ኦርቶዶክስ ክርስትያንነት በዘመኑ ምእመን አያያዝ፣ ልክ ጨዋታውን አይተውለት የማያውቁት ግን ሲጠየቁ ብቻ ስሙን
አስታውሰው “የዚህ ቡድን ደጋፊ ነኝ” እንደሚሉት አይነት አያያዝ ሆኗል ሀይማኖቱን የያዛት።
ብዙውም መልካም ክርስትያን ሳይቀር በዚህ መልእክትና ይዘት፣ እንዲሁም ትንቢት ግር ሊለው ይችላል። የቤተክርስትያን
ሰወች ከሚባሉትም ሳይቀር ይህንን አፈታሪክ ብሎም ተሞኝቶም የሚያይ ብዙ የዋህ ይኖራል።
ነገርግን ይህ በሀገር ደረጃ ከደረስንበት፣ የመሪዎችና አባቶች ክፉኛ በጠላት ፅኑ ሴራ መዳፍ ተይዞ መውደቅና
የቤተክርስትያን ሰብሳቢና ባለቤት አልባነት ያስከተለው የምንጋራው ፍፁም ውድቀታችን ማሳያ ነው እንጂ ይህ ነገር ፈፅሞ የፀና
እውነትና የዘመኑ ምእመናን ልናውቃት ደንታ ኖሮን የማያውቀን የሀይማኖታችንም ደማቅ እውነትና የልዑል እግዚአብሄር የማያልፍ ቃል
ነው።
ደንዝዘን፣ በዋዜማው አጋንንት ልባችንን ሰውሮት ካልሆነ በስተቀረ ከነዚህ እንደው የትኛው ይሆን ልዩ ባእድ የሆነብን፧
የቅዱስ ራጉኤል ድርሳን፧ ይህን መፅሀፍ ነው የማናውቀው፧ ነው ወይስ ካድነው፧ የመልአኩን ቃል ካድነው፧ እምነት
ቀይረናልን፧ ወይስ ለኛ ሲባል ቤተክርስትያኑም ፈርሶ፣ ድርሳኑም ተቃጥሎ አዲስ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ይመስረትልን፧
ነው ወይስ የካድነው የቅዱስ ዑራኤልን ድርሳን ነው፧ የእግዚአብሄር መልአክ እስከነ ንግስና ስሙ ጠቅሶየመሰከረበትን
ቃል፧
አምላካችን ክርስቶስ በመልካም ልጅነት እናቴ ብሎ የሚያፈቅራትን ድንግል ማርያም ቅዳሴዋን የደረሰው አባ ሕርያቆስንስ
ልትክደው ተነስተሀልን፧ ነው ወይስ ቅዳሴውን ቀድሞም አትቀበለውም ነበር፧ የእዝራሱቱኤል ትንቢታዊ ፅሁፍ ተተርጉሞ ኢትዮጵያውያን
እንድናውቀው በማሰብ ወደሀገራችን አስቦ የላከው እርሱ መሆኑ አልተፃፈምን፧
ነው ወይስ የቁመት የሰአታቱን ውዳሴ አባት አባጊዮርጊስ ዘጋስጫ፧ እሱስ እንግዳ ሆነብህ፧ እሱስ ብዚ ጊዜ ስለዚህ
አልተናገረምን፧ መፅሀፈ ምስጢር ብሎ ፅፎ ባስተማረበት መፅሀፍ ንጉሱን በስም ጠቅሶ እንደውም አልፎ ከነገሰ በኋላ ሮም ድረስ
ሄዶ ስለሚያደርገው ሀይማኖታዊ ድል ሳይቀር በሙሉ ምዕራፍ ተብራርቶ አልተፃፈምን፧
ወይስ የኢትዮጵያ ሊቃውንት መፅሀፍቅዱስ ትርጓሜ ላይ የወደፊት ትንቢት በሰፈሩባቸው ቦታዎች እግዚአብሄር በገለጠላቸው
መንገድ ስለብዙ የወደፊት ተፈፃሚ ትንቢቶች አብራርተው አልፃፉምን፧ ክርስቶስ በዚህ ዘመን ስለሚሆነው የተናገረውን አልፎም
በሀገራችንም የሚሆነውን በሚነግሰው ንጉስ የሚፈፀመውን ጭምር አላሰፈሩትም፧
ራሽን እንድትታዘብ ተባዝተው በእጅህ ያሉትን ለመጥቀስ ነውንጂ በብዙ መፅሀፍት፣ እንደነ ገድለ ፊቅጦር ባሉ፣
በምንኩስና ፋና ፊልክስዩስ፣ በግብፃዊው አባት ሲኖዳ ራዕይ፣ በሳቤላ ራዕይ፣ በተአምረ ኢየሱስ፣ በፍካሬ ኢየሱስ…። በስንቱ
በስንቱ የተጠቀሱትንማ ማን ችሎ ሲዘረዝር ይውላል፧ የተመቸንን ብቻ እየመረጡ መያዙ ክፋት ነው ትርፉ። እስራኤላውያን እንኳን
የጥፋታቸውን፣ የመበተናቸውን የመከራቸውን ትንቢት የሚናገረውን መፅሀፍ ይዘውት ቆይተው ነበር። የእስልምናው መፅሀፍ ቁራን
እንኳን ወደፊት የመካዋ የካእባ በኢትዮጵያዊው ሰው መፍረስ ይናገራል።
አምላክን ስለእውነት የሚፈልግ፣ ልቡ ብሩህ የሆነስ እንደቅዱስ ያሬድ ያለውስ፣ ያለንባብ፣ ያለድምፅ ሰበካ ዛፍ
ከምትወጣ ትል ብቻ አይቶ ይማራል። ያላደለው ግድ መስሎ ስለታየው ብቻ ያለ ፈጣሪ ፍቅር ሀይማኖት የተቀላቀለው ደግሞ፣ አይደለም
በዚህ ሁሉ መፅሀፍ አውርሰውት በሰውነቱ ቢነቅሱት፣ ወይ ደግሞ እንደይሁዳ ከአምላክ ጋር ቢያከርሙትም እንኳን ትርፉ ባዶ ነው።
እኛም አውቀን ልባችንን አንዝጋው። ምን መሀይም ብንሆን በየዋህነት አምላክን ከልባችን ብንፈልገው፣ ስለሱ ልናውቅ
ብንሻ ወዳጅ አባት ነውና የማይገልጥልን፣ የማያደርግልን ነገር ፈፅሞ አንዳችም አይኖርም። ቀድሞስ የሁሉ ፈጣሪና ባለቤት ከኛ
ኢምንት ደቂቃን ከቶ ምን ይፈልግና፧
በዚህ ወሳኝ ጊዜ እንዲህ መሆናችንን ልብ ገዝተን ልናስተውለው ይገባል። ልንነቃ ይገባናል። የተተነበየ ቀን ሲቀርብ
ነገሩ ሁሉ እንዲህ ነውና። ቅዱስ ጴጥሮስ እንኳን “ዶሮ ሳይጮህ ሶስት ጊዜ ትክደኛለህ” ብሎ ለራሱ ትንቢቱን ነግሮትሳለ፣ እሱ
ግን ትንቢቱ እስኪደርስ ከልቡ ተሰውሮ ሁሉ አልቆ የተባለችው ዶሮ ሲሰማ ነበረ ያንን ትንቢቱን ልብ ብሎ በፀፀት ያለቀሰው።
ሌላም ወደፊት ሀሳዊው መሲህ እኔ አምላክ ነኝ እያለ እንደሚመጣ ተብራርቶ ተፅፎ ሳለ ግን ጊዜው ሲደርስ እጅግ እንዲሁ
ልብ ያላሉ የበዙ ተከታዮች፣ አለም ሁሉ አምላኪው እንደሚሆን ሁሉ እኛም ዛሬ በዚህ በተጠቀሰው ትንቢት ደጃፍ ላይ በመሆናችን
ብዙዎች ደንዝዘን ልባችን ታውሮ እንገኛለን። በኢትዮጵያ የብዙ የክርስቶስ ባሪያዎች የሆኑ ቅዱሳን ቃልኪዳን አለና እኛም
አዘውትረን የሱ የክርስቶስ ባሪያዎች በመሆናቸው አክብረናቸው በጥትና የምንለምናቸው ቅዱሳን ልጆቹና መላእክትም ስለኛ ክርስቶስን
ቢለምኑት አልጨከነብንምና አሁንም የተወሰኑም ልብ ብለው ይድኑ ዘንድ ይኸው ባልታሰበ መንገድ ይሄ ፅሁፍ እርስዎም ጋር ደርሷል።
በኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ተጠብቀው ለእምነቷም መሰረት የሆኑ ብዙ መፅሀፍትና ሀብቶች አሉ። ብዙ ምእመኗ ግን በነሱ
የሰፈሩትን እንኳን ተማምኖ ለማመን ይቸግረዋል። ታዲያ መፅሀፍቷን ካላመንክ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ መሆንህ ምኑ ነው፧ ነው ወይስ
እንደ ምእራባውያን እምነት በአፍ ብቻ እግዚአብሄርን እየጠሩ፣ የመረጡትን ብቻ ከመፅሀፍ ቅዱስ እየወሰዱ በርክስና ህይወት
እንደሚኖሩት መኖር ይሻላል፧ ማመን ወይ መካድ እንጂ በሁለቱ መሀል ሆኖ እኔ ክርስትያን ነኝ ማለት ግዴለሽነት ነው። ብዙዎቹ
ለራሳቸው የሚመቻቸውን ብቻ ነው የሚቀበሉት። ሀይማኖት እንደ አጃቢና ማድመቂያ ሆኖ የፈለግናቸውን ብቻ በፈለግነው መንገድ
ወስደን ለምድራዊ ምኞታችን ማዳመቂያ ነው የምንጠቀምበት። ለሰንካላው የአምላክን ህልውና ከምንም ሳንቆጥር በስጋ ፍትወት
ለምንቃዠው አላማችን፣ ከአምላክ የሚያርቅ ይሁን የሚያቀርብ ገድ ሰጥቶን ለማያውቀው፣ በዚሁም ምክንያት ለመፈትፈት ግብዣና ገድ
የማያስፈልጋቸው ልክስክስ አጋንንት ለሚጋልቡት፣ ለዚሁም ምልክቱ ሞትና ደም ለሚቀድመው ፖለቲካችን ማሟሟቂያ ብቻ የኢትዮጵያ
ትንሳኤ የምትለውን ቃል እንዲሁ አጃቢ እናደርጋታለን።
ለመሆኑ ትንሳኤ ማለት ምን ማለት ነው፧
በመነሻነት በቅዱሳት መፅሀፍት የተፃፈውና በብዙው ኢትዮጵያዊ “የኢትዮጵያ ትንሳኤ” ተብሎ የሚታወቀው ይህ ትንሳኤ ግን
እውነታው ምንድነው፧ ሁሉም ማለት እስኪያስደፍር ድረስ፣ መልካም ክርስትያኖችም ጭምር ይህንን ነገር አዛብተው ነው የተረዱት።
ማንም አሁን ቢጠየቅ መልካሙም ክርስትያን ጭምር የኢትዮጵያን ትንሳኤ በአእምሮው ያለው፥
( ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ የበለፀገች ሆና ከአለም ሀገራት ተርታ መሰለፍ፣ በኢኪኖሚዋ ጠንካራ መሆን፣ መከላከያዋ እጅግ
ብርቱ፣ በአለም ሀገራት ላይ ተፅእኖ ፈጣሪ ሆና፣ ህዝቦቿ በሀብትና ደስታ የሚኖሩባት፣ አለም ሁሉ ወደሷ የሚሰደድባት ክብሯ
የተጠበቀ ኢትዮጵያ፣ ዴሞክራሲና ነፃነት እንዲሁም ሳይንስና ህክምና ቁንጮ )
ይህ ነው ሁሉም “የኢትዮጵያ ትንሳኤ” ብሎ የሚገልፀው።
ልክ ይኸው አገላለፅ ፣ ብዙዎች ከአለም የሚሰደድባት፣ የነፃነትና ዴሞክራሲ (ህዝብ በብዛት ሆኖ የፈለገው ማንኛውም
ነገር የሚታወጅበት)፣ የሀብትና ጥንካሬ ቁንጮ የሆነችዋን አሜሪካን አይገልፃትምንዴ፧ እውነት ፪፯ አመት ማንም ሳያስገድዳቸው
በአንዲት ዋሻ ቆመው በፆም በስግደት እንደቅዱስ ዮሀንስ በበረሀ ከምቾት ወደው ርቀው ያለፉት አቡነተክለሀይማኖት ይሄ አጓጉቷቸው
ትንሳኤ አሉት፧
ጣልያን በዚህ መልኩ ያደገች ጠንካራ ብዙዎች ለመድረስ በባህር የሚሰጥሙላት ሀገር ነች። የኛን የትንሳኤ ምኞት ሀገር
ትመስላለች። የአለም ቁንጮ ሆና የጣልያን እቃ ሲባል እራሱ ክብሩ እጅግ ከፍ ያለ ነው። ታዲያ ምነው በአንድ ቀን ተመሳሳይ
ህልም ያዩት መቶዎቹ የሮም ቅዱሳን ስለራሳቸው ሀገር ስለሮም ጣልያን ስለዚህ ትንሳኤዋና ሀያልነትዋ አልታያቸው፧ ምንሆነው ነው
እትብታቸው ስለተቀበረችበት ምድራቸው ይህ ሁኔታ አልተናገሩ፧ ምነው አልፈው ስለ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ተናገሩ፧
የሮሙ ቅዱስ ጳውሎሽ ቢሆን ምነው ስለዚህ የሮም መፃኢ ሀያልነትና አሁን ስላለችበት ትንሳኤ አልተናገረ፧
የቆስጠንጥንያው ዮሀንስ አፈወርቅ አልታየውም ይሆን እንዴ የሀገሩ ትንሳኤ፧ የቆስጠንጥንያ ወደኢስታንቡል መቀየር፣
የቱርክ ሀያል ሀገርነት፣ በኢኮኖሚና ስልጣኔ እጅግ ገዝፋ ከዩሮፕያን ዩኒየን አባል ለመሆን እስከመሰለፍ እንደምትደርስ፧
ከዙሪያዋ ያሉ ዛሬ እንደሚታየው ወደሷ ሊሰደዱ ሲሻሙ፧ አይ ቅዱስ አባታችን፣ አልታየውም ነበር እንዴ የሀገሩ ህዝብ ነፃነት፧
ዴሞክራሲ ነውና ብዙ ህዝብ ስለጠየቀ የወሲብ ንግድ የሚደግፍ ህግ መውጣቱ፧ ቁጥጥር አድራጊ አካል መቋቋሙ አልታየውምን፧
አዪዪ… ምነው የመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቅዳሴዋን የደረሰው የቆስጥንጥንያ ብህንሳው ኤጲስ ቆጶስ አባ
ሕርያቆስ፣ ለእእዝራ ሱቱኤል የተነገረውን የቅዱስ ዑራኤልን ዜና፣ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ትንቢት ወደኢትዮጵያ አስተርጉሞ ያመጣው
እሱ እራሱ አልነበረምንዴ፧ ታዲያ ምነው ስለራሱ ክህነት ቦታ ቆስጠንጥንያ (የዛሬዋ ቱርክ ዋናከተማ ኢስታንቡል) ሀያልነትና
ትንሳኤ፣ ሀብት መትረፍረፍ፣ ከውድቀት ተነስቶ የአለም ሀያል ሀገር መሆን ምንም አልተናገረ፧
ይህ ለምን የሆነ ይመስላችኋል፧
እውነተኛ ክርስትያኖች ሆይ ፈፅሞ አትሳሳቱ፦ እንደዛ ያለ የኢትዮጵያ ትንሳኤ የለም። ትንሳኤ ቃሉ ራሱ የሚያመለክተው
ከነበረበት የወደቀና የተዋረደ ሁኔታ ወደበፊቱ ወደነበረበት ክብር መመለስ ማለት ነው። የኢትዮጵያ የቀድሞ ማንነትም
በእግዚአብሄር በረከትና ሀይል ተጠብቆ መኖርና በመልካም ስራና ክርስትያናዊ ህይወታቸው ምክንያት በአምላክ ተወዶ መኖር ማለት
ነው። ትንሳኤ ማለት “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደእግዚአብሄር ትዘረጋለች” የሚለውና “ኢትዮጵያውያን በፊቱ ይመራሉ” ይሚለው የዳዊት
ትንቢት የሚፈፀምበት በአምላክ መነፅር የታየ ታላቅ የእግዚአብሄር ህዝብነት ነው። ህዝቡ በእምነት ወደአምላኩ የሚመለስበት
ሀገሪቱም በአምላክ የምትባረክበት አኗኗር ነውንጂ በስጋ ሀብት፣ በብረት ሀይል ግዝፈት መመካት፣ በወርቅና ብር መትረፍረፍ ከመቼ
ወዲህ ነው በቅዱሳት መፅሀፍት ትንሳኤ ተብሎ የሚፃፈው፧ ለሱ ለሱማ የነአሜሪካ ይህ ምጡቅ ሀያልነትን አያሰፍረውም ነበር፧
እንዴት ያለ መታወር ነው፧ ከመቼስ ወዲህ ነው መልአክ ትንሳኤ ብሎ ይህንን እንደ አሜሪካ ያለ ስጋዊ ሀያልነት
የምስራች ብሎ የሚናገረው፧ አምላክስ ቢሆን በራእይ የሚገልጠው፧ በነቢያት የሚያስነግረው፧
አሁን እንደሚወራው የኢትዮጵያ ትንሳኤ ተብሎ ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ በልፅጋ፣ ጥሩ መንግስት ይዛ፣ ህዝቦቿ በነፃነት
የፈለጉትን ሆነው፣ የዴሞክራሲና ነፃነት ጥግ የሚባለው ግብረሰዶማዊ ጋብቻ ተፈቅዶባት፣ አምላኳን በካደ ሳይንስ የበላይ ሆኗ…
እውነት ይህ እንዴጽ ይሆናል፧
እምነት ያለው ወደአምላኩ ተመልሶ፣ አውቆ ከሀዲውና ጠማማው በፍፁም ጥፋት ከተጠረገ በኋላ የሚመጣ የቀና የእግዚአብሄር
ህዝቦች ከአምላካቸው ጋር በአንድነት የሚኖሩበት ትንሳኤ ነው የኢትዮጵያ ትንሳኤ።
እንዲጠፋ የፈለጉትን ነገር ማስረሳት እጅግ ከባድ በመሆኑ በሌላ ነገር መተካት ግን ውጤታማ የማጥፋት ስልት ነው።
ለዚህም ነው በውጪ ሀገራት የክርስቶስን ልደት በ ኅ፡ማሽ ትንሳኤውን በ ዐኣስተር በመተካት በአላቱ ደምቀው ቢከበሩም እንኳን
ከሀይማኖታዊ በአልነት ወደ ተራ ፌስቲቫልነት ተቀይረው በመከበራቸው ህፃናት እንኳን ትውልዱ የማ ልደት ነው ሲባሉ እንኳን
በአእምሯቸው የገና አባት እንጂ ክርስቶስ እንዳይታያቸው ድረስ ተገልብጦ ሲወድቅ ይታያል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያ ትንሳኤ በሁሉ የታወቀና በኢትዮጵያውያን የሚጠበቅ በመሆኑ ሊረሳ የማይቻል በመሆኑ ሌላ
መልክ ባለው ሌላ ትንሳኤ ተቀይሮ እንዲታሰብ ሰይጣን የሚያደርገው ውጊያ ነው ይህንን መዛባት የፈጠረብን።
የዚህም ውጤቱ ከትንሳኤው በፊት ለሚመጣው መከራና ጠረጋ በእምነት የተዘጋጀን ሳንሆን በተሳሳተ መልኩ መልኩ ተሰልፈን፣
በመቅሰፍት እንድንወድቅና እንድንጠፋ የታሰበ ትልቅ አደጋ ነው። ይህም ሁሉ የመጣው በሀይማኖታችን እጅግ ደክመን መፅሀፍቶቻችንን
መመርመር በማቆማችንና ይህንንም በማድረግ ለህዝቡ ያገለግላሉ ተብለው የሚጠበቁት የእምነት አባቶች የድርብርብ ጥቃትና ማዳከም
ኢላማ በመደራጋቸው ነው።
ነገርግን ሁላችንም ይህንን አውቀን፣ ከሚመጣው መከራ አምላክ እንዲጠብቀን በመማፀን በእምነትና ንሰሀ ወደአምላካችን
ቢያንስ ለኛም ባይሆን ለቤተሰቦቻችን ልንለምንና እንዲያድነን ምክንያት ልንሰጠው ይገባናል።
በተለያየ መልኩ የሚመጣ ሰይጣን በብዙ መልኩ ሊያዳክመን ብዙ ነገሮችን አድርጓል። በኢትዮጵያና በቤተክርስትያኗላይ
ያደረገውም ውጊያ አሁንም አብሶ የሚያደርገው ውጊያ ከምንም በላይ የበረታ ነው። ለዚህም የውጭ ጠላቶችንና ዘረኛ መንግስታትን
መሳሪያ አድርጎ ተጠቅሞባቸውል።
በዝባዥ ሀያላን ሀገራት ከጥንትም በአፍሪካ ማንነት ያለው ህዝብ መሆን፣ እራሱን ማክበሩ ለመገዛትና ባርነት እንዳይመች
ስለሚያደርገው በኢትዮጵያና እምነቷ እንዲሁም ታሪኳላይ ትልቅ ዘመቻና እቅድ ተደርጎ ለማጥፋት ተሰርቶበታል። ይህም እንዲሁ
በወሬና ለራስ ችግር ሌላን ለመውቀስ ተብሎ የሚነገር ሳይሆን እራሳቸው የዚህ ተግባር ባለቤቶች አይን ባወጣ መልኩ በመፅሀፍ
“ዓብይስሲኒኣ፥ ጥሀ ጶውደር ባርረል” በሚል ርእስ እቅዱን አሳትመው የኢትዮጵያ ዘውድ ክብር፣ የቆየ እንቁ ከህዝቡ የተዋሀደ
ክርስቲያናዊ እምነት፣ ባህል አፍሪካ እንዳይገዛና ቀና ብሎ እንዲሄድ ሊያስተባብር የሚችል አደገኛ ፈንጂ በመሆኑ በዚህ
እንዲተባበሯቸው ለማስተባበር በተለያዩ ሀገራት ሲያሰራጩት የነበረው መፅሀፍ ዛሬ በኢንተርኔት ላይ ምስክር ሆኖባቸው ይናገራል።
ከዚህም ባለፈ በመንፈሳዊ መልኩ፣ ሰይጣን የእግዚአብሄርን ህዝብ ለመበተን፣ ትውልዱን ለማጥፋት ፈፅሞ አይተኛምና
አምላክን በማክበር፣ በራቸውን ዘግተው ወራሪን በእምነት ሀይል በመመከት ለእግዚአብሄር ተገዝተው የኖሩ ህዝቦችን ለመጣል የሚመጣ
ጠላት ሁልጊዜም አይተኛም።
በነዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ክርስትና ላይ እጅግ ከፍተኛ የማይታመን ድብቅ ጥፋት ተሰርቷል። የማጥፋት ሁሉ የመጨረሻው
ተግባር ጥግ ሊባል እስከሚችለው ድረስ በስኬት ሊያደርጉን ተችሏቸው፣ ከህዝቡ መፍዘዝና ለእግዚአብሄር ካለው ቸልተኝነት የተነሳ
ጠላቶች ቤተክርስትያናችንን የማፈራረስ እቅዳቸው እጅግ ወደስኬት ከመድረሱ የተነሳ ለፈሊጣዊ ንጝር እንኳን ለግነት “በቋንቋ
አንግባባም” የሚባለው በአካል እስኪፈፀምብን ድረስ ደርሶ ቤተክርስትያንና ምእመኑን በቋንቋ ጭምር ተለያይቷል። ግእዝን ፈፅሞ
የማይሰማ፣ አባቶች ስንት የደከሙበት የተራቀቁበት ወርቃማ የቅኔ፣ የዝማሬ፣ የቅዳሴ፣ የምስጋና፣ የፈጣሪ ፍቅር ውጤቶች ምኑም
ያልሆኑ ሊረዳቸው የማይችል ትውልድ ተፈጥሯል፣ አሁንም ወደባሰው እጅ እየተሸጋገረች ትገኛለች። የኢትዮጵያ ጠላቶች ይህንን ድንቅ
የሺ አመታት ክርስትና ሀብት ማቃጠልና ማጥፋት ሳይጠበቅባቸው፣ ባልተጠበቀ ስልት የቋንቋውን ትምህርት በማግለል የሚመጣው ትውልድ
ምኑም እንዳይሆኑ፣ እንዳይረዳቸው፣ ስሜት እንዳይሰጡት፣ ባዶ እንዲሆን ተደርጎ ተቀርጿል። በኛ ትምህርት ስርአት እንዳይካተት
አድርገው ሲቀርፁልን፣ በራሳቸው ምድር ግን ልጆቻቸው እስከ ዶክትሬት ደረጃ ተራቀው እንዲማሩበት አድርገውታል። ቅዳሴ እንኳን
ልቁም ቢል ምንም በአእምሮው ሳይረዳ እንዲሁ ከመንፈሳዊ ከበረከቱ ብቻ ተካፍሎ እንዲመለስ የሆነ ምስኪን ወላጅ አልባ ትውልድ
ሆኗል። ያኔ ጥንት እንግሊዞች ከእግዛብሄር ይልቅ ቀድመው በንጉሱ አእምሮ ላይ ሲነግሱ የኢትዮጵያን ትምህርት ስርአት በአዲስ
ሲተካ፣ እንግሊዞች የኢትዮጵያ መሰረት የሆነው የግዕዝ ቋንቋ ለትውልድ እንዳይተላለፍ፣ እንዳይካተት ከፍተኛ ተፅእኖና ተግባር
ነበራቸው። ለማካተት የነበረውንም ጥረት፣ በውጪ አስተሳሰብና ትምክህት ጠምቀው ያመጧቸውን ምሁራን ተብዬዎች በመጠቀም፣
ማንነታቸውን ተጠይፈው ቋንቋውንና ይዘቱን እንደኋላቀርነት ምንጭ አድርጎ በመስበክ እርግፍ አድርገው በመተው፣ ፈረንሳይኛና
ጀርመንኛ የመሳሰሉት ተክተው እንዲሰጡ በማድረግ በስልት ኢትዮጵያዊውን የአፍሪካ ባለታሪክ ኮከብ ህዝብ የእምነትና የጥበብ
ሰንሰለቱ እንዲበጠስ ጥረዋል።
ይህም ሁሉ ሆኖ በአምላክ ቸርነትና ቅዱሳን ፀሎት ከህዝቡ ልብ አምላክን ሊወጡት ስላልተቻላቸው ዛሬ የኢትዮጵያ
ክርስትያን ሁሉም ሲጠየቅ ከሁሉ ነገር የማስቀድመውና የማስበልጠው እግዚአብሄርን ነው ይላል።
ነገር ግን ህይወቱና የሀገሩ አላማ ከዚህ የተቃረነ ሆኖ ተቀርፆበታል። ባላሰበው ባልፈለገው መንገድ የአምላክን ህልውና
የካደ፣ ኢአማኒነትን የሚሰብክ፣ የእምነት መጥፋት መዳረሻው የሆነ የትምህርት ስርአት፣ የአስተዳደር ርእዮት በጥቂት ሰወች
ስልጣን፣ ባልተስማማበት መንገድ ተጭኖበት ይኖራል።
የሰው ልጅ አንድ አእምሮ ነው ያለው። ማንም ቢሆን ከሁሉ የሚቀድምበት ፈጣሪው እንደሆነ ይናገራል። በዛው አእምሮው
ደግሞ በህይወቱና ጉዞው ሌላን ነገር ሙሉ በሙሉ አስቀድሞ ይጓዛል።
የአእምሮ ሁኔታ እጅግ ወሳኝ ነውና፣ እንዲህ መከፈሉ፣ ወደአንድ አለማድረጉ በፈለገው መስክ ውጤታማ እንዳይሆን
አድርጎታል። ወይ አምላኩን እርግፍ አድርጎ ትቶ ሙሉ የአእምሮ ሀሳብና ችሎታውን የኢኮኖሚ እድገት፣ ሳይንስ ልዕቀትን ብቸኛ
ግብና ቀዳሚነት ወዳደረገው ርዕዮት አልገባ ወይ ደግሞ አምላኩን እንደሚለው አስቀድሞ፣ ሁሉን ሌላውን ከሱ በታች አድርጎ ውጤታማ
አልሆነ። በተፈጥሮው በሁለት መሀል መዋለል ላይ ሆኖ በሙሉ ሀይሉ ሊሰራ የማይችለው አእምሮ በትክክል ተንቀሳቅሶ እንድናድግ
ያልሆንነውም ለዛ ነው።
ወይ እንደባቢሎን ሙሉ ክደን ትልቅ ስልጣኔላይ አልተገኘን፣ ወይ እንደሶሎሞን አምላክን አስቀድመን ትልቅ ጥበብና
ስልጣኔ ላይ አልተገኘን፣ ከሁለት ያጣ ሆነን ደርቀን ቀርተናል።
ወይ ፈጣሪን ክደንላቸው አጋንንት የምድርን ሀብትን፣ ብልፅግናን፣ አልሰጡን፣ ወይ ለፈጣሪ አባታችንን ተገዝተንለት
በምድር ባለው ላይ ሁሉ በሾመበት ቃሉ እንደ ጥንታችን ባለጥበብና ፀጋ አላደረገን።
የዛሬ ሁኔታችን ሲገለጥ በትክክል የሚከተለውን ይመስላል።
አንተም የእግዚአብሄርን መኖር ፍፁም የምታምንና፣ አባታችንም ከሁሉ ነገር ይቀድምብኛል የምትል ከሆነ ብቻ ከዚህ ቡሀላ
ያለውን አንብበው። ያንን የተቀበለ በሚከተለው የማይስማማበት አንዳችም ምክንያት የለምና
ለመደህየታችን፣ ለኋላቀርነታችን ግን ቆይ በማን ይሆን የሚፈረደው፧
እስቲ ስለእውነት በሀቀኝነት እንመልከት፣
ዛሬ በሀገራችን ሀብትን ያገኘ ሰው፣ ብር የበዛለት ሰው፣ ይበልጥ ወደእግዚአብሄር ሲቀርብ ነው የምናየው ፧ወይስ ይባስ
ሲርቅና የሚወልዳቸውም ልጆቹን ከእግዚአብሄር በሚያርቅ መልኩ ሲቀርፅ፧
ታዲያ ማን ልጁን የሚወድ ከሱ የሚያርቀውንና ወደ ጠላት እጅ ሚመራ ነገርን ይሰጠዋል፧ ታዲያ እግዚአብሄር እውነት
የሚወደን ከሆነ እንዴት ከሱ እንድንርቅ ያደርገናል፧ ሀብት ሰጥቶ ስለምን ያርቀናል፧
ስነልቦናችን ሀብት ሲያገኝ አምላክን የሚያርቅ አድርገን ከቀረፅነው፣ ይህንን ለመገመግምና ለማስተካከል የማንጥር ከሆነ
ታዲያ አምላክ ምን ያድርገን፧
ትቶን እንዳይተወን ደግሞ፣ በልባችን እንደምናፈቅረው ያውቃል፣ እንደምንወደው ያውቃል፣ ከሱ መራቅን ፈልገን
ተግባራችንን በዛ መልኩ እንዳላደረግን ያውቃል። ታዲያ እንዴት ይተወን፧ በድህነትም ቢሆን ልጆቹ አድርጎን በአለም ለነገሰው
ለሰይጣን እንዳንወድቅ ይጠብቀናል እንጂ።
ነው ወይስ “ዞርበልልን አንፈልግህም፣ ልቅቀን ተወን፣ እንደግበት” እንበለው፧ ቆርጠን በአንድነት እንደዛ ብንለውኮ
ምንም ችግር የለበትም፣ ልክ እንደሌሎቹ ሀገራት በሀብት ገነው፣ የሰዶምን ተግባር አውጀው፣ የሰይጣን አምልኮን ፈቅደው
እንደሚኖሩት ሀገሮች መሆን እንችላለንኮ። ድሮውንስ በግል እንኳን በጥንቆላ የሚገኝ ሀብት እንደዛ አይደልንዴ የሚመጣው፧ ደሞ
ለምድር ሀብት፦
ነገርን ግን ሁለት ሀይል ብቻ ነው ያለው። ይሄኛውን ርቀን ሄደን ጥበቃውን ስናርቅ፣ ሌላኛው አነፍናፊ መዳፍ ውስጥ
ነው ራሳችንን የምናገኘው። ከሁለቱ ሌላ የለም።
አምላክ ከኛ ምን ችግር አለበት፧ ሀብቱን እድገቱን ልዕልናውን ቢሰጠን፧ ምን ቸግሮት፧ ኢምንት ቅንጣት የሆንን ፍጡራን
ምን አገኘን ምን ያዝን ምን ግድ ኖሮት፧ ምንም አይቸግረውምኮ። ጥንት እንደዛ ሆነን የኖርንባቸው ወርቃማ ጊዜያትም ነበርኩንኮ።
በተለያዩ ጊዜያት በ ፩፱፱፯ ጨምሮ ምነው አምላክ በሀገራችን ላይ መልካም እንዲሆን አላደረገም፧ ብለን ስንቴ ይሆን
የወቀስነው፧ ምን ለመሆን፧ እንደ አሜሪካ ባለ የዴሞክራሲ፣ የግለሰብ ነፃነት፣ ሊብራሊዝም፣ የሳይንስ ሊቅነት ወዘተ ለመሄድ፧
በብዙ የአውሮፓ፣ የምስራቅ ክርትያን ሀገሮች ተተግብሮ ያየነው፣ በጊዜ ሂደት ሁሉንም ወደተመሳሳይነት መልክ የሚመራ፣
ባህልን፣ አማኝነትን፣ ሀይማኖትን፣ እጥብ ጥርግ አድርጎ አፅድቶ በአዲስ ማንነት፣ ልቅ ስነልቦና፣ ለስሜት ተገዥነት፣ ቁስ
ገንዘብ አምላኪነት የተመሰረት በሁሉም ቦታ ፍፁም ተመሳሳይ አዲስ ማንነት ሲቀርፅ ያየነው እንደ ኮሪያ እንደ ጃፓን፣ እንደ
ቱርክ የመሳሰሉ በባህል እምነትና አስተሳሰባቸው ፍፁም የተለያዩ የነበሩ ሀገራትን ትውልድ ወደ ፍፁም ተመሳሳይ አሜሪካ መሰል
ስነልቦና ህግጋትና ባህል እየቀየረ እየተመለከትነው ያለውን ርዕዮት
አንዲትም ሳይቀየር በዴሞክራሲ ስም በሀገራችን ነግሶ ስለምን አንተን አጥፍቶ አላሳደገንም ብለን በአይናውጣነት ጠይቀን
እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም።
በዚህ ንጝሬ ኋላቀር፣ ፀረ ዴሞክራሲ፣ ዘመኑን ያልዋጀ… መስዬ ታየሁህ አይደል፧ “አምላክን ከሁሉ የማስቀድም ነኝ”
ብለህ ካልተስማማህ እንዳታነበው አስቀድሜ ነግሬህ ነበረ። ላስቀድም ካልክ ግን እውነታው ይህ ነው።
ጨርሰህ ሳትሰማኝ አትፍረድብኝ ወንድሜ፣ እኔም ዴሞክራሲን እንዲሁ ዝምብሎ መቃወም የያዝኩ አይምሰልህ። በዛ ስም
ሆነንጂ ዴሞክራሲ እራሱ አልነበረምና ቀርቦልን የነበረው፣ ይልቅ በሱ ስም ከትርጉሙ በተቃራኒ ሰይጣናዊነትን ይዞ የመጣ ነውንጂ።
እስቲ ልጠይቕ፣ ዴሞክራሲ ማለት የብዙው ህዝብ ፍላጎትን ማክበት አልነበረምን፧
ብዙ የሰርቬይ ድርጅቶች እንደሚሰሩት ኢትዮጵያውያን ከአለም አንደኛ የሆኑበት ነገር አለ “ለአምላኬ ከሁሉም በፊት ቦታ
እሰጣለሁ” በሚለው አስተሳሰብ። ሙስሊምም ሆነ ክርስትያን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአለም አንደኛ የራሱ እምነት ያለው ህዝብ ነው።
ይህ ሆኖ ሳለ፣ እናሳንሰውና ፺% ህዝቡ ሁሉ ፈጣሪዬ ከሁሉ ዋና አላማዬ ነው የሚል ሆኖ ሳለ ዴሞክራሲ ቢሆን ኖሮ
እንደሀገር የጋራ አላማውን የሚቀርፅለት አስተዳደሩ እንዴት ፈጣሪን አንዲት ጊዜ እንኳን አክብሮ ቦታ ሰጥቶ ሊይዘው አልቻለም፧
ሙስሊምም ሆነ ክርስትያን በአምልኳቸው አንድ የሚያደርጓቸውን ነገሮች ላይ ተመስርቶ ለአምልኳቸው እንዲረዳቸው የሚችል እንዴትም
አንዳች፣ አንዳች ነገር ሊያመቻች ወይ ሊሰራ ተጠየፈ፧ የድፍን ሙሉ ህዝቡን የመጀመርያ ፍላጎት እቅድ አላማ የሆነውን ነገር
እንዴት ሊጠቅስ አልቻለም፧ ይሄ ነው ዴሞክራሲ፧ ጭፍለቃ፧
እሺ ማመቻቸቱ ይቅርና፣ እንዴት ዴሞክራሲ ሆኖሳለ፣ ግን ድፍን ሙሉ ህዝብ የሚቃወማቸውን የረከሱ ተግባራት ሊያውግዝለት
አልቻለም፧ ሙሉ ሀብ እምነት ያለው በሆነበት ሀገር፣ የወሲብ ንግድ (ሴተኛዳሪነት) ሙሉ ህዝቧ የሚጠየፈው ሆኖ ሳለ፣ በህግ
የተፈቀደ እንደማንኛውም ያለ አድርጎ የብዙሀኑን አንገት ማስደፋት ነው የብዙሀኑ ህዝብ አስተዳደር የተባለለት ዴሞክራሲ መስፈን፧
እንደ አሜሪካ፣ ካናዳ ያሉ የርኩሰት፣ የ ሰዶምነት ምልክት ተብለው በሚወሰዱት ሀገራት እንኳን ለትውልድ ስነልቦና
ሲባል በህግ ደረጃ ወንጀል ተብሎ ክልክል የሆነውና በፍርድቤት ክስ የሚያስቀጣው የወሲብ ንግድና ሴተኛዳሪነት እንኳን በሀገራችን
ህጋዊ መብትና ልቅ ስራ ያደረገው ነው የብዙሀኑ አስተዳደር፨ዴሞክራሲ፧
ሁሉ ህዝብ ፈጣሪዬ ብሎ የሚጠራው አምላክ እያለው፣ ይህ የብዙሀኑ አስተሳሰብ ፍላጎት ሆኖ ሳለ ልጆቻቸው “ፈጣሪ
የሚባል ነገር የለም፣ በዝግመት ከቁሳት ወጣችሁ፣ እምነት ኋላቀር ነው” የሚል ትምህርት በመንግስት ደረጃ ከህዝቡ በሚሰበሰብ ታክስ
ወጪው ተሸፍኖ በብቸኝነት እንዲሰጥ ማድረጉ፣ የማይፈልጉት አይነት እምነት ያላቸው ልጆች እንዲኖሯቸው የሚያስገዽ ስርአት ነው
የብዙሀኑ አስተዳደር፨ ዴሞክራሲ ማለት፧
ዝገመተለውጥህ ስለተነካብህ እንደኋላቀር አይተህ እንደምታጉረመርም ይጠበቃል፣ ግን ጥፋትና የተጋፊነት ጫኝ ተግባር
ያደረገው የዝግመተለውጥ ትምህርት መሰጠቱ ሳይሆን፣ በህዝቡ ታክስ በመንግስት ተደግፎ፣ በብቸኝነት መሰጠቱና ሁሉም የሚያምኑበት፣
ከህዝብወሳኝነት፨ዴሞክራሲ ፍፁም ተቃርኖ የኢትዮጵያ አማኝ ህዝቦች ልጆቻቸው እንዲማሩት እጅግ የሚፈልጉት የክርስትና፨እስልምና
የሰው አፈጣጠር ሂደትና የፈጣሪው ማንነት ይህንን ይመስላል ተብሎ ጎንለጎን እንደማስተያያ እንኳን እንዳይሰጥ በጉልበተኝነት
ማገዱ፣ ብሎም ይሄ ሁሉ ከህዝቡ በሚሰበሰብ ገንዘብ የልጆቻቸውን አእምሮ ባልፈለጉት መልኩ ተተኪያቸውን መቅረፁ፣ ህዝቡ
በሚፈልጉት ባህልና እውነት ሳይሆን ቀራጮቹ በፈለጉት ባህልና የአስተሳሰብ መልክ ትውልድ መቅረፁ ነው።
በሰው እምነትና ፍልስፍና ላይ አይደለምንዴ አስተዳደርም፣ ትምህርትም ምንም ነገር በመሰረትነት የሚቆመው፧ ሰዉ ለራሱ
“ሰው ምንድነው፧ ከየት መጣ፧ ሰው ምን ያስፈልገዋል፧ ምን እናድርግ፧” የሚለውን ተመስርቶ፣ ያ ታይቶ ለምሳሌ “ሰው ማለት ሙዝ
ለመብላት የተፈጠረ ነው” ብለው ከደረሱበትና ካመኑ፣ ትምህርት ስርአቶች ሙዝ ማምረት ላይ አተኩረው በመስራት፣ ያንንም ማሻሻልን
አላማና ግብ አድርገው ይቀረፃሉ፤ አስተዳደሮቹም ህዝቡ ያለችግር ሙዝ መብላት እንዲችል ለማስቻል በቻለው መንገድ ሁሉ የሚተጋ
ይሆናል። በዚህም መንገድ ህዝቡ ያለችግር ሙዝ በተሻለ ሁኔታ በመብላት በደስታና ስኬት ይኖራል። ይህ አይደለምንዴ እውነታው
መሆን ያለበት፧ ካልሆነማ ሌላ የተጫነ ከንቱ ነገር ነው ማለት ነው። ማንን ለማስደሰት ብለው ያንን ያደርጉታል፧
እኛስ ከራሳችን እምነትና መንገድ፣ የህይወት ግብ ተፃራሪ የሆነን እዳ ስለምን ብለን እንሸከማለን፧ ሁሉን የፈለግነውን
የማድረግ ሙሉ ችሎታና መብት እያለን፧ ማንን ለማስደሰት ብለን ያንን እናደርገዋለን፧
በ ፩፱፱፯ም ሆነ በሌላ ጊዜያት እንግዲህ ይህን ነው ካልነገሰብን ብለን የምናማርረው። እንዲሁ ሙሉውን ያልተረዳነውን
ነገር በራሳችን ለማወጅ እሽቅዽም። እውነት አለ ካልን ለአምላክ ውዳሴ ምስጋና ነውንጂ ልናቀርብ የሚገባን፣ ባሰብነው መንገድ
ለመንጎድ ስላላስቻለን።
ስለዚህ አምላክህን የምትወደው ከሆነ አሁን ቀና ብለህ ዕበ፱፯ ምርጫም ሆነ በሌሎች ጊዜያት የተመኘሁት እንዲሳካ፣
እንዲፈፀም ስላልሆነ አመሰግንሀለሁዕ ብለህ እስቲ አመስግነው። አምላክህን ለመውደድ መራቅ ላለመፈለግ ልብ ያለህ ከሆንክ እስቲ
ደፍረህ እንዲህ በለው፦
ያ አካሄድ አምላክን እናስቀድማለን፣ ዋናው የህይወት አላማችን እሱ ነው ለምንል በነፍሳችን ለምናምን ህዝቦች ነውንጂ፣
ለሌሎችስ ይጣጣም ይሆናል። ወይ ፍፁም ክደን ቁጭ ማለቱን ማን ከለከለን፧ እውነቱን ስለምናውቅ፣ የፈጠረም የምናመልከው አባት
ስላለን ነውንጂ። እንዲያ ከሆነ ግን እውነቱ ይህ ነው።
ከሱ ከጌታችን የሚያርቅ ያልሆነ የመንግስትና አስተዳደር ስርአትን፣ የትውልድ ልቅነትና ሀይማኖት ቸልተኝነት ላይ
ያልተመሰረተ፣ መቶ አመት ብንኖርበት ከአምላክ ከማራቅ ይልቅ የሚያቀርበን የሆነ የመንግስት ስርአትን ይዘን በፊቱ ብንቆም
አምላካችን ያለአንዳችም ማንገራገር ከአለም ሁሉ በላይ ሊያደርገን ምንም ጥርጥር አልነበረውም ነበር። እሱ እንደሆነ ዝቅ ብሎ
በኛ ምድራዊ ታላቅነትና ሀያልነት ላይ ምን ችግር ኖሮበት ቦታ ሰጥቶ ትሆናላችሁ፨አትሆኑም ይለናል፧ ይህ ለሱ ምኑ ነው፧ ሀገራዊ
ኢኮኖሚያችን በሺ ተቆጠረ፨በትሪሊዮን ተቆጠረ ለሱ ምኑ ነው፧ ለኛ ለልጆቹ ደስ ያለንን የጠየቅነውን ያለምንም ችግር ያደርግልናል
እንጂ። ግን እኛ ከሱ ፍቅርና ቅርበት ይልቅ የመጀመሪያ ግባችን አድርገን የኢኮኖሚ ግዝፈትን ስንይዘው፣ አልፎም በሌሎቹ
በምስክርነት የመንገዱ መዳረሻ በታየ መልኩ ከምንወደው ከሱ በሚያርቀን፣ እንደው በርትተን ከኛም ባይሆን እንኳን ከትውልዶቻችን
የሱን ክብርና ፍቅር፣ ለሱ ያለንን ቅርበት አጥቦ የሚያጠፋ መንገድ መሆኑ ባደጉት ሀገራት የተመሰከረውን አካሄድ ስንይዝ ግን፣
እውነት የሚወደን ከሆነ ሊያቆመን ግድ ይለዋል። ያ ግን ገደብ አለው፣ ብዙዎችቻን ክደን ልቀቀን ብለን ብንታገለው፣ አልመለስ
ብንል ግን ይህች ቅድስት ሀገር የኛ የበዛነው ከሀዲያን ብቻ ሳትሆን የተባረኩ ቅዱሳን ልጆቹ ፀንተው እየኖሩ ያሉባት ናትና፣
ከቅዱሳን አባቶቻችን ቃልኪዳን ያላት ናትና፣ አሉና ስለነሱ ሲል ቤቱን የምንረብሸውን እኛን ለራሳችን አሳል ፎይሰጠናል።
በሀገራዊ ክህደት ጉዟችን ወጣቱ እርስ በርሱ ይበላላል፣ በክህደት ርእዮት ራሱን ያጠመቀ ወጣት ሌላ እርስ በርስ መከፋፈያ ቢያጣ
ዕማሸነፍዕ እና ዕማቸነፍዕ በሚለው ቃል ሳይቀር እርስ በርስ ሲገዳደል አይተናል፣ ያንንም ተግሳፅ አይተን ያልተመለስን የርሬዎቹ
በምናደርገው እንቅስቃሴ ሁሉ ወደውድትቷችን ከቀን ቀን እንነጉዳለን። እኛም ለራሳችን ተላልፈን የተሰጠን እንሆናለን፣ ወጣቱ
በየምክንያቱ ያልቃል፣ ይተላለቃል፣ የቻለው በዘር፣ በመዋለዱ ዘሩ ቢዋሀድበት እንኳን ቋንቋ ለይቶ ይገዳደላል። በዚህም መልኩ
መንግስት ለመመስረት በምናደርገው ምዘናችን፣ መስፈርታችን ሁሉ እስክናመልከው ድረስ ለምናፈቅረውና ለምናስቀድመው፣ እሱም
በአምሳሉ እስኪፈጥረን ድረስ የሚያፈቅረን፣ አልፎም እስኪሰቀልልን ድረስ ከሚያፈቅረን አምላካችን ያርቀናል፧ ወይስ አያርቀንም
ብለን ለአንዲትም ሴኮንድ ቆመን ማሰብ እስከተቻለን ድረስ፣ ወደጥፋታችን የምንነጉድ ይሆናል።
አንድ አገልጋይ ገበያ ሲወጣና የሚገዛውን ሲመርጥ፣ ለራሱ የሚመች ሚመቸውን ብቻ እየመረጠ፣ “ጌታዬ ይወደው ይሆን፧
ጌታዬን ያስቀይመው ይሆን፧” ሳይል ቢያደርግ፤ የጌታው ምላሽ ምን ይሆን፧ ይህ ተግባር አገልጋዩ በጌታው ላይ ራሱን ሲያነግስ
እንዴት ያለ ንቀትና ትእቢት ነው የሚያመለክተው፧
የሰው ልጅ እንግዲህ፣ የአምላኩ የበታች አገልጋይ ነው። አምላኩም ፍፁም የተቀበለው ጌታው ነው።
መሪ ብሎ ወይ ለሀገሬ ገዥ ልምረጥ ሲል፣ ስርአት ልምረጥ ሲል ከፈጣሪው የሚያርቀው፣ የሚለየው ይሁን፨አይሁን ለጌታው
ተስማሚ ይሁን፨አይሁን ምንም ግድ ሳይሰጠው አምላክ እንደሌለው ኢአማኒ ፈጣሪውን ፈፅሞ ከሀሳቡ ቢያደርገው፣ ምን ይሆን ውጤቱ፧
ትርጉሙ፧
ምን ይሆን ከጌታው የሚኖረው ምላሽ፧ እኛስ ከጌታችን ምን ምላሽ ይሆን የምንጠብቀው፧ ነው ወይስ ጭራሹኑ ስለመኖሩም
ክደነዋል፧
በመፅሀፍት ባህሪውን የምናውቀው ያ ፈጣሪ የፈጣሪ ምላሹ ፀጥ ብሎ ወደሰዶማዊነት፣ ወደ ኢአማኒ ትውልድ ማፍራት፣ ወደ
ሰይጣናዊ ባህል መመረዝ ስንገባ ዝም ብሎ መመልከት ነው ብለን የምናስብ ከሆነ እጅግ እንገርማለን።
እውነት የሚወደን ቢሆን፣ መቼም ወደዚህ አይነት ልቅነት፣ አጥፊ ትውልድ ቀረፃ፣ አምላክን አስረሽ አስተዳደር
እንድንገባ አይፈቅድልንም። በ ፱፯ም ሆነ በሚመጣው ዘመን በድህነትና በችግር ሆነን ራሳችንን ሳንለውጥ፣ ልጅነታችንን ሳንክድ
ቢቆይልን የተሻለ ይሆንልናልና ልጆቹ አድርጎ ያቆየናል።
እኛ ባልነው ሆኖ እድገት ብለን ወደምንጠራው፣ ዴሞክራዊ ብለን እንደናፈቅነው ወደምኞታችን በስኬት ገብተን ቢሆን ኖሮ፣
ከአምላክ ፈፅሞ የምንርቅበት ስለመሆኑ ለማንም አእምሮ ላለውና ፈጣሪ እውነትም አለ ብሎ ለሚያስብ ሰው የማይካድ ሀቅ ነው።
ሁላችሁም የምታውቁት በዚሁ ተፅእኖ ከእምነት የተለያየው በውቀቱ ስዩምም ሁኔታችንን መርምሮ እውነታውን ተናግሯል፣ “የጊዜ ጉዳይ
ነውንጂ ሁላችንም በፍጥነት ወደዛው ነው የምንሄደው” ብሎ ያለንበትን ሁኔታና መዳረሻችንን ገልፆታል። ፈጣሪ የሚባል ነገር የለም
ብሎ አምኖ ለተነሳው ይህ የማይካድ እውነት ነው። ነገር ግን እሱ ስላለና ጣልቃም ስለሚገባም ይህ አይሆንም። ወይ በቅጣት፣ ወይ
በንሰሀ ወደእውነት እንመለሳለን። አይቀርም። ይህንን የምታነበው የፈጣሪን መኖር የምታምን ብቻ ሳይሆን የምታውቅ ስለሆንክ
ይህንን ፈፅመህ አትቃወመውም።
እኛ ጠልተነው ዝም ቢለን፣ የጥንት ቅዱሳን አባቶች፣ ለራሳቸው ህይወትና እድሜ ሳይሆን ፪፯ አመት ቆመው ቢፀልዩ
ለሀገራቸ፣ ለሚመጣው ትውልድ ጭምር ነውና፣ ስለነሱ ስለገባው የማይታጠፍ ቃልኪዳን ብሎ አምላክ እጁን ያነሳል።
ታዲያ በትንቢቱ እንዳለው እንዲህ የፀና መከራ እንዴት ይደርስብናል፧ የተሻለ እምነት ኖሮን፧
በቅድስት ሀገር ይህንን የመሰለ እድል ይዘን ብንወለድ፣ እድልን ብቻ ሳይሆን እዳንም ይዘን እንደተወለድን እንዳንረሳ።
ከመጀመርያው በወንጌል ተጠማቂ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ጀምሮ መቶ አይደለም፣ ሺዎች አመታትን በክርስትና፣ በእግዚአብሄር
ተአምራት መሀል የኖርን፣ ምሳሌ በሚሆኑ የክርስቶስ ቅዱሳን ገድልና ታሪክ በዝቶ በሚነገርበት፣ ቅዳሴ ያለማቋረጥ በሚፈስበት
ሀገር ላይ ሆነን በክህደት መንገድ ስንጓዝ፣ በውድቀት በርክስና መንገድ ስንነጉድ ሌላው ያጠፋ ሲባል፣ እኛ ደግሞ “አውቆ
ያጠፋ” በሚል ይሆናል የምንታየው። ሌላው አለም የማያውቅ ሲባል፣ እኛ ግን ፈጣሪን አግኝቶት ከፊቱ ቆሞ የካደው ነው
የምንባለው። ታዲያ መከራውና ቅጣቱ በማን ይፀና ይሆን፧ በቅዳሴ፣ በስብከት፣ በቃልኪዳን በበረከት መሀል እየኖርን የአምላክን
ስራና ክብር በአይናችን እያየን በግዴለሽነት የካድነው መከራችን እንዴት አይፀና፧ ይህም ሁሉ ቅዱስን አንብቦ ለሚያውቅ
ክርስትያን ሁሉ እንግዳ አይሆንበትም። ምክንያቱም በመፅሀፍ ቅዱስ ወንጌል አንዴ ብቻ ሳይሆን ሁለቴም ሳይሆን ሶስት ቦታ ላይ
በማቴዎስ በሉቃስ በማርቆስ ወንጌል ላይ ይኸው ቃል ተደጋግሞ የተፃፈ ነውና
<< በእናንተ የተደረገው ተአምራት በጢሮስና በሲዶና ተደርጎ ቢሆን፥ ማቅ ለብሰው አመድም ነስንሰው ከብዙ
ጊዜ በፊት ንስሐ በገቡ ነበርና።
ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከእናንተ ይልቅ ለጢሮስና ለሲዶና ይቀልላቸዋል።
በአንቺ የተደረገው ተአምራት በሰዶም ተደርጎ ቢሆን፥ እስከ ዛሬ በኖረች ነበርና።
ነገር ግን እላችኋለሁ፥ በፍርድ ቀን ከአንቺ ይልቅ ለሰዶም አገር ይቀልላታል። >>
በአይናችን ፊትለፊት ያየነውን አባታችንን ብንክደው፣ እነሱ ግን ሲወለዱ ጀምሮ ያልሰሙትን ያላወቁትን ነው የካዱት።
በዚህም መከራው በኛ ይፀናል። ከልባችን ተመልሰን በፅኑ ልመና አምላካችንን ከሚመጣው እንዲጠብቀን ብንለምነው ግን ፈፅሞ
ሊጨክንብን አይችልም።
ዛሬም በደላችን የፀና ነውና፣ መዳን ከፈለግን የቅዱሳን አባቶቻችንን፣ እናቶቻችንን ቃልኪዳን በሙሉ አንብበን ልናውቅ
ይገባናል። ቃልኪዳናችንን እንወቅ፦፦ ስለቅዱሳን አባቶቻችን ቃልኪዳን ብሎ እንዲምረን ፈፅመን ልንለምነው ይገባናል። ይህ እጅግ
ታላቅና ፍፁም የአምላክ ተግባር ነውና
በመዝሙረ ዳዊት
፲፭፥፰ ቃል ኪዳኑን ለዘላለም፥ እስከ ሺህ ትውልድ ያዘዘውን ቃሉን አሰበ፥ ለአብርሃም ያደረገውን፥ ለይስሐቅም
የማለውን
ብሎ አምላካችንን ቢገልፀው
ዘፀአት ፳፥፮ ላይ “ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ
እግዚአብሔር…” ብሎ አምላክ እራሱ ተናግሯልና
ትእዛዙን ጠብቀው በፅድቅ ኖረው ቃልኪዳንን ለመጪው ትውልድ የተቀበሉትን እያሳሰብክ ከአምላክህ ፊት በንሰሀ ወድቀህ
ራሽን ታድን ዘንድ ይህ ፅሁፍ መጥቶልሀል።
ቅዱሳን አባቶችና እናቶች ስለአንተ ዛሬ ስላለኸው ብለው ነውና ቃልኪዳኑን የተቀበሉት። አቡነ መልከፄዴቅ እንኳን ቀጥታ
በዚህቺ ሰአት ላይ ያለነውን በፀጋቸው ያውቁን ነበርና አምላክ ለስጦታው ቢጠይቃቸው “ከዚህ በኋላ የሚመጣው ትውልድ ተጠራጣሪ
መርማሪ ሆኖ የሚቃወም ነውና፣ እነሱ ይድኑበት ዘንድ በአይን የሚታይ እንድትሰጠኝ እለምንሀለሁ” ቸሩ አምላክ ቢፈቅድላቸው ይኸው
በቅፅራቸው የተቀበረ አስከሬን ሳይፈርስ ሳይበሰብስ እስከቅንድቡ ፀንቶ እየኖረ በሳንቲሜትር ልዩነት ከፊል አካሉ ወጣ ያለው
በስብሶ እስኪታይ ድንቅ ስጦታን አልብሷቸው ሄደ።
አዪዪ… ደጉ አባታችን፣ ለማያውቁን ልጆችዎ በፍቅር ይህንን ቢሰጡን፣ እያየን ለመዳን ከማመን፣ ብዙዎቻችን እያየነው
ለመካዳችን መፋረጃ እንዳይሆነብን አቤቱ እንዴት ያስፈራል፧
ጥንት አባቶቻችን ጠላት ቢመጣ በገድሉ በሰፈረው ከአምላክ የተቀበለው ቃልኪዳኑ መሰረት በእምነት ሶስት ጊዜ “አምላከ
ጊዎርጊስ” ብለው ስለገባው ቃልኪዳን እግዚአብሄርን ቢለምኑት ከድልም ደማቅ ድል አልብሶ አድኗቸዋል።
ይህ ለጥፋት የተነገረ የትንቢት ቃል አይደለም። የዘመኑ ሰወች ሰምተው ይድኑበት ዘንድ ነውና። አዲስም አይደለም።
በትርጓሜ ወንጌል ላይ እንደተመሰከረው በግራኝ ዘመን የነበረውን የ ፵ አመት የመከራ ትንቢት ሳይቀር በህዝቡ ልመናና
መመለስ፣ በድንግልማርያም ምልጃ እንዳጠረ ሰፍሮ ይገኛል።
ስለአባቱ ዳዊት ቃልኪዳን ብሎ ንግሱ ሶሎሞን ከባድ ክህደት ቢሰራ ከዙፋኑ ያልነሳው አምላክ፣ ዛሬም በዝተው ስላሉት
ስለውድልጆቹ ቃልኪዳን ብሎ እንዲምረን ፈፅመን ልንማፀነው ይገባናል።
ከሁሉ ከሁሉ ከሁልሉ በላይ ዛሬ ያለነው ትውልድ እንደስፖርት ደጋፊ በስም ብቻ የያዝነውን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነታችንን
እንወቀው እንወቀው እንኑረው። በከፊል መርጠን የምንይዘው የምንንጠባጠብበት ሳይሆን፣ ወይ ፈፅመን እንሁነው፨ ወይ ፈፅመን
እንካደው። ከሁለቱ መሀል ቦታ የለምና፣ ያም ሆኖ በመሀል መሆን እጅግ የከፋ ነው። ጥንትም ቢሆን በሰማይ በመላእክት መካከል
በነቅዱስ ሚካኤል ሰራዊትና በሳጥናኤል ሰራዊት ጊዜም ቢሆን መሀል መሆን አልጠቀመም። መሀል ላይ የሆኑት ተፈርዶባቸው ያየር
አጋንንት በመባል የሚታወቁት ዛሬም ድረስ የሚያሰቃዩን እጅግ ክፉ የሰው ጠላቶች ሆነው የሚገኙት ናቸውና። የአየር አጋንንትነትን
እንተው።
እግዚአብሄርን ከሁሉ አስቀድማለሁ፣ ከሁሉ እወደዋለሁ የሚል ሰው
ለኑሮም፣ ለሀገሩም፣ በየትም በሚያደርገው ጉዞ ከሁሉ ነገር የአምላኩ ፍላጎት የሚቀድምበት፣ ለሁሉ ነገር ቅድሚያ
መስፈርቱ ለዛ ለሚወደው አምላኩ መመቸት፨አለመመቸት የሆነ፣ ከዛ በኋላ ባለው እንደፈለገው በነፃነት በሀያልነት መኖር የሚችል
ሰው መሆን አለበት። ከዛ ውጪ ግን በአፉ ብቻ እንደይሁዳ እየሳመ ልቡን የሚያደማ የደግ አምላክ እግዚአብሄር ጠላት ነው።
አባቱን ሳያውቀው ከረከሰው ሌላው አለም ይልቅ፣ አውቆት የሚክደው ነውና ልቡን የሚያደማው ቅጣቱ ፍርዱ እጅግ እጅግ የከፋ ነው።
እግዚአብሄር ፈትኑኝ እንዳለ ታውቃለህን፧
ደግሞ አምላክ እንድንፈትነው ይጠይቃልን፧
አዎን። እግዚአብሄር አድርጎታል። መዳኛችን የሆነች ቤተክርስትያናችን ትፀና ዘንድ ልጆቹን ትሰበስብለት ዘንድ እሱው
ከሰጠን ገቢ አስራት እንድናስገባ አፅንቶ፣ አዎ አፅንቶ ሲነግረን ይህንን ቃል ተናግሯል። “በቤቴ ውስጥ መብል እንዲሆን
አሥራቱን ሁሉ ወደ ጎተራ አግቡ የሰማይንም መስኮት ባልከፍትላችሁ፥ በረከትንም አትረፍርፌ ባላፈሽላችሁ በዚህ ፈትኑኝ፥ ይላል
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር” ብሎ በመፅሀፍ ቅዱስ ላይ ተፅፏል።
ይህንን ፀንቶ የተፃፈ ቃሉ ሆኖ ሳለ አይናችንን አፍጠን የማንተገብር ህዝቦች ነን የኦርቶዶክስ ተዋህዶ አማኞች ነን
ዛሬ የምንለው።
የካድን መሆኑን ማወቅ በራሱ ትልቅ ነገር ነውና ከሀድያን እንደሆንን እንወቀው። ቀድሞስ እንዲህ ያለውን ፅኑ ቃል
እየካዱ ሌላ ከዚህ የከፋ ክህደት እንደው ከየት ይመጣል፧ ኧረ እንደው ከዚህ የከፋ ክህደት መቼ አለና ነው ራሳችንን ክርስትያን
ብለን ለማሾፍ የተነሳነው፧ እስከዚህ ድረስ ታውረናል፧ በእሳት መሀል ሆነን ሳለን እንዳንወጣ ራሳችንን ዕአቤት ብርዱ፣ ቅዝቃዜው
ደስ ሲልዕ እያልን ነዶ ማለቅን ያክል ነው የዚህን አይነት ብዙ ፅኑ ቃሎችን እየካዱ ክርስትያን ነኝ ማለት። ለበለጠ ቃጠሎ
መንደርደር፦
በኢትዮጵያ ገዳማት፣ የገጠር አብያተክርስትያናት ተዘጉ፣ መናንያን ተፈናቀሉ፣ ገዳማት ችግር ውስጥ ሆኑ የሚል ቃል
የተለመደ ምንም ስሜት የማይፈጥርብን ሆኗል። እጅግ አስደንጋጭ ነው፣ ይህን ተላምደነዋል፦ ትናንሽ ማህበራት አንዳንድ ጊዜ
ቁንፅል የቤተክርስትያን አገልግሎት ቁሶች፣ እጣንና ሻማ ሲያበረክቱ እንኳን የራሳቸውን ትተው የእግዚአብሄርን ስም መቀደሻ
እንኳን የመስእዋት እጣን ስላገኙ በረዥም ምርቃት በደስታ አልፎም በእንባ የሚያመሰግኑ መነኮሳትና ካህናትን በቪዲዮ ማየት ለኛ
ተራ ልማዳችን ሆኖልናል።
ይህም ሁሉ እኛው ቤተክርስትያናት የሚገባቸውን ዘርፈናቸው ለዚህ አብቅተናቸዋል። ዛሬ ክርስትያን ብለን ራሳችንን
እየደለልን ግን ያላመንነው መፅሀፍ ቅዱስ እንዲህ ስለክፉር ዝርፊያችን ይናገራል። በአግራሞት ሆኖ ስለእኛው እንዲህ ይላል።
“ሰው እግዚአብሔርን ይሰርቃልን፧ እናንተ ግን እኔን ሰርቃችኋል። እናንተም። የሰረቅንህ በምንድር ነው፧ ብላችኋል።
በአሥራትና በበኵራት ነው።
“እናንተ፥ ይህ ሕዝብ ሁሉ፥ እኔን ሰርቃችኋልና በእርግማን ርጉሞች ናችሁ።”
ይህን ሁሉ እንዲሁ የተባለ ሳይሆን በመፅሀፍ ቅዱሱ ቃል በቃል ያለው የእግዚአብሄር ቃሉ ነው። የመፅሀፍ ቅዱስን ቃል
ወይ እውነት ወይ ሀሰት በል ከሁለቱ መሀል የሆነ ቦታ የለም። ለራሳችን ብለን የምንመርጠው፣ የምንለዋውጠውም አይደለም። ዛሬ
ያለነው እንደምናወራው ቅዱስ ህዝብ አይደለንም፣ በዚህ መፅሀፍቅዱሳዊ ቃል መሰረት የተረገምን እርጉማን ህዝቦች ነን። አዎ
እንደለመድከው “እኔኮ ክርስትያን ነኝ፣ ያውም ከጥንት ያልተለወጠችው ተዋህዶ” ብለህ ራሽን ደልለው። በስሟ ከመጠራት ያለፈ
ህግጋቷንና ስርአታን አክብረህ፣ ኑሮህን በሷ እንቁዎች ካላደረጀኸው እውነተኛ ማንነጥ አንተ ያልከው ሳይሆን በእግዚአብሄር ቃል
መሰረት እውነተኛው ማንነጥ ያ ነው። ከልዑል እግዚአብሄር ቃል ሌላ ከፍ ያለ መለኪያ አለኝ ካልክ እንግዲህ አንተ ታውቃለህ።
ይኸው ይህንን ዛሬ አነበብከው፣ ነገር ግን ከአሁን በኋላ እንኳን እንደማትቀየር እነግርሀለሁ። ግን የተፃፈ የራሱን
ቃል በመካድ አይን ያወጣ ክህደትን እንደያዝክ እወቀው።
ለሀዋርያቱ “ለሠራተኛ ደመወዙ ይገባዋል” ብሎ በአንደበቱ የተናገረላቸውን ሀዋርያቱን ያስራብክ፣ እነሱ እንደሆነ ዝም
የሚሉ አባቶች ቀሳውስት በየቦታው ያሉ ሊቃውንትን ከሰማይ አይወርድላቸው ነገር የነፈግክ አይደለህምን፧
ርጉማን ያላቸውን ህዝብ ተግባር አምላክ ፅፏል። ከሱ ተገዳድረህ እኔ ቅዱስ ነኝ ብለህ ብትከራከረው፣ መብጥ ነው።
ነገርግን በዚህ መንገድህ መጨረሻህን ማንም አይቀይርልህም፣ እሱም ውድቀት ነው።
ሰበብ ልትሰጥ ትችላለህ፣ ሰበብ የሌለው ክህደትና ጥፋት እንደሌለ ግን እወቅ፤ ማንም በድሎ ሰበብ የማይሰጥ የለም፤
ያንተም ሰበብ ከዚሁ አይለይም፤ አያድንህምም። ምናልባትም ዕበዘመናችን ቤተክርስትያን አስተዳደር ውስጥ ብዙ አጥፊዎች ተመድበው
አሉ፣ ብሰጥም በትክክል አይውልም።።።ዕ ብዙ ልትል ትችላለህ። ግን ይህንን የምታደርገው ስለአምላክህ፣ ስለእሱ የጥያቄ ቃል
ብለህ እንጂ የትኛው ተራ ምድራዊ ፍጡር ሰበብ ሆኖህ አምላክህን ልታሳዝን ተቻለህ፧ እምነት ጎድሎ እንጂ፣ ለምሳሌ አንድ የዋህ
ደሀ ካለችው ቆርሶ ሄዶ ዕይህቺስ ለአባቴ ቤት ትሁንልኝ፣ አምላኬ ሆይ ለሚዘርፈው እሳት ትሁንበት፣ ለቤጥም ዋጋ አድርግልኝዕ
ብሎ ለአምላኩ ነግሮ ቢሰጥ፣ እምነቱ ተአምር በሰራ ነበር። ከገንዘቡ ይልቅ ፀሎቱ ቤተክርስትያኗን ባጠራት ነበር፣ ይህ ጥቂት
ስጦታ ለቤተክርስትያናችን መድሀኒቷ በሆነ ነበር። ወይ ካልሆነ እንኳን እንደ ማህበረ ቅዱሳን ላሉት፣ በአይን ለሚታዩት ማን
አስገብቶ ይሆን፧ በገንዘብ ካላመነ እንኳን ማን ይሆን የአምላኬ ቤት ብሎ በማህበር ሆኖ በተግባርና ቁሶች በማድረግ ያስገባ፤
የቤቱ ቅናት በልቡ ያለ፧
ቤተመቅደሱን ቤተመቅደሱን በገንዘብ ልውውጥ ገበያ ቢያረክሱት ክርስቶስ በቤቱ ቅናት ጅራፍ አነሳ። እኛ የአባታችን ቤት
ቅናት ሊኖረን ሲገባ ጭራሽ ላልናቸው ሰወች አስረከብናት፣ አልፈንም በንፍገት ቤተክርስትያኒቷን የዱር ቅዱሳንን መበደል ምን
ይባላል፧ ከጦር፣ ከእሳት የበረታ ፀሎትንና እምነትን የታጠቅን ሆነን ሳለን፧
ምን ታደርግ ወንድሜ ከእውነተኛው የተዋህዶ የቀናች ህይወትና አኗኗር መንገድ በምን ያህል የራቕ፣ ወይ የቀረብክ
እንደሆነ ወይ እንግዲህ በጊዜ ወደኋላ ተመልሰህ አታይና ራሽን አታወዳድር ነገር፣ ምን ማድረግ ይቻላል፧ የተፃፉ መፅሀፍትን
እንኳን በክርስቶስ ፍቅር አምላኬን ልወቀው ብለህ የምታነብ አልሆንክ።
ደክመህ ለአምላክህ መገዛት አልተቻለህምንጂ ስለእውነት ግን እምነጥን እንደምታፈቅራት አንተ ታውቃለህና እባክህን
ቢያንስ ቢያንስ እውነቱን ከሰማህ፣ ወይ በመሰል አጋጣሚዎች ባወቅክ ጊዜ ራሽን አቅና። በእውነትም ቅድስት ናትና የምትወዳት
የምትወድህ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ልጇ ሁን። ፈትነኝ ያለህን አምላክህን ያጎልብኛል ብለህ አላመንከውም፧ ነው ወይስ
ቃሉ ውሸት ነው፧ ወይስ ከዚህ በላይ ምን ይበልህ፧
መቼስ ደክመን ነውንጂ፣ ለኦርቶዶክስ እምነታችን፣ ለአምላካችን ፍቅራችን ልዩ ነው።
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሆኖ አምላክ ክርስቶስን የማያፈቅር፣ አይደለም እሱን የወለደቺው ሚወዳት እናቱን ድንግል ማርያምን
ሳይቀር በፍቅርና በሽት የማይመለከት የለምና፣ ስለፍቅራችን ድንግል ማርያም ብለን እንኳን እንመለስ።
መቼም ግን የድንግል ማርያም ፍቅሩ በልባችን አለና፣ እስቲ ቢያንስ የምንወዳትን ቅድስት ድንግል ማርያም እንመናት፣
እመብርሀን የተናገረችን እስቲ እኛ ኢትዮጵያውያን ልጆቿ እንኳን እንመናት፦
ሰላም ለኪ እንል የለምንዴ፧ በመፅሀፍ ቅዱስ በሉቃስ ላይ የሰፈረው ቃሏ ነውኮ ሰላም ለኪ፦
በዛ ቃሏ የአምላክን ሀይልና አድራጊነት የመሰከረችው በምድር የሚያደርገውንም ጭምር ነውና
ኧረ እስቲ እንወዳታለን የምንላትን ድንግል ማርያም የተናገረችውን እንኳን እንመናት፦
ሰላም ለኪ ፀሎቷ ላይ “ዘረዎሙ ለእለ ያብዩ ህሊና ልቦሙ” ማለትም “በልባቸው ሀሳብ የሚታበዩትን ሁሉ በተናቸው” ብላ
የተናገረችው፣ እኛ አምላክን የያዝን እንደሆነ፣ በሴራም በስልጣንም በሀይልም ከፍ ብለው የሚታዩት ሁሉ ከእግራችን በታች
እንደሚበታተኑ ቃል በቃል የሷ ንጝር ነው።
“ነሰቶሙ ለሀያላን እም መናብርቲሆሙ” ሀያላን የተባሉት ሁሉ በቅፅበት ከየመንበሮቻቸው ሊያነሳ የሚቻለው አምላክ
“አበዮሙ ለትሁታን” ለተዋረዱትና ዝቅ ዝቅ ያሉትን ሁሉ ከማንም በላይ ታላቅና ከፍ የሚያደርግ አምላክ
“አፅገቦሙ እምበረከቱ ለርሁባን” ይዘውነው ተርበን የማናድር አምላካችን። ፀሎት ሲያስተምረን “የአመት ወይ የወር
ቀለባችንን” ሳይሆን “የእለቷን” ብቻ እንድንጠይቅ ያስተማረን፣ ነገን በሙሉ መተማመን በሱ አምነነው እንድንጥል የነገረን፣
በዛም መንገድ የሆነ የቃልኪዳን ፀሎትን ያስተማረን እኛ ግን ያላመንነው አባታችን።
“ወ ፈነዎሙ ራእቆሙ ለብኡላን” ባለፀጋዎችን በአንዲት ቅፅበት ራቁታቸውን ሊያስቀር የሚቻለው
በምድር እንኳን ይህን ሁሉ የሚቻለው አምላክ ነው ፈጣሪያችን እያለች ድንግል ማርያም በፀሎቷ የተናገረችውን የምትወደን
ልጆቿ አላምናት አልን። ድንግል ማርያምን አላምንሽም አልናት።
ይሄ መሪ ፀናብን፣ እነህዚ ሀይልን የያዙ አሴሩብን፣ ባለስልጣናት ሊያጠፉን ነው፣ ይሄን መሾም አቃተን ወዘተ እያልን
እንተራመሳለን። ዘወትር እናለቅሳለን፣ ፖለቲካ እያልን ስንደናቆር ስንፍጨረጨር እንውላለን። ነገር ግን አንዲትም ጊዜ እንኳን
እንዲህ ድንግል ማርያም የነገረችንን ያንን ሁሉ የሚቻለውን አምላካችንን በሀገራችን ጉዳይ መፍትሄ አድርገን በህብረትና በጋራ
ይዘነውአናውቅም።
ኧረ እስቲ ቢያንስ ያለችን ሀብታችንን ድንግል ማርያምን እንመናት።
ይህቺን እጅግ አጭር ፀሎቷን በቀን አንዴ ብናደርሳት፣ ሁሌ ስንላት እያንዳንዷን ቃል ትርጉም በየተለያየ ቀን ልብ
ብለን እናደንቅ ነበር። ይሂቺ አጭር ፀሎት እምነታችንን ባጠነከረችው ነበር። ከቀን ወደቀን ባላሰብናቸው መንገዶች ህይወታችንን
ወደእምነትና አምላካችን በመራችን ነበር። እናም ይህችን ፭ መስመር አካባቢ ፀሎት በቀን አንዴ ማለት ቀላል ናትና፣ እስቲ
እንሞክራት።
ቢያንስ ያለችን ሀብታችንን የፍቅር እናት ድንግል ማርያምን እንመናት። እሷን እንኳን ማመን ያቅተን፧፧፧
አስራት ሀገሯ ቆይ የትኛው ነው፧ ኢትዮጵያ አይደለችምንዴ፧
ነገር ግን በዚህ ዘመን ከኛ ይልቅ በእጥፉ ለግብፅ ኦርቶዶክስ ምእመናን ስለምን ይሆን አብዝታ የምትገለጠው፧
ስለምንድነው እንደዛ በአደባባይ ሁሉ ከምእመኑ የማትለየው፧
ይህንን ስናይ እንኳን እንዴት ልብ አንልም፧
እጅግ ብዙዎቻችን በአፍ ብቻ እምነት ያለን መሆኑ፣ አንደኛ ነን በማለት ብቻ፣ በስም አማኝ ብቻ የሆንን መሆኑ እንዴት
አይታወቀንም፧ በህይወት በተግባራችን ፈፅሞ ሀይማኖት አልባ መሆናችንን እንዴት ልብ አንልም፧ እንዴት ያንን ስናይ እንኳን ልብ
አንልም፧
ከዛሬ ጀምሮ እንደምትወደው የእውነት ክርስትያን ሁን መኪና ስትሳፈር እንኳን “በሰላም አስገባኝ” አትበለው፣ ይልቅ
እስቲ ደፍረህ አምነኸው “ፈፅሞ ያንተው ፈቃድህ ይሁንልኝ” በል ክርስትና ያ ነውና፣ ፈቃዱን ማስቀደምን፣ መቀበልን ተለማመድ ፦
፦ ፦ “ፈፅሞ ፈቃድህ ይሁንልኝ፣ ግን ከተቻለ የይቅርታና ቸርነጥ እንዲሆን እለምንሀለሁ” ብለህ አምነኸው ራሽን ስጠው፣ ፈቅዱ
ሞጥም ከሆነ በደስታ ለመቀበል እስካልቻልክ እውነተኛ እምነት የለህምና ራሽን በዛ መንገድ አንፀው፣ ይህንን ሳትረሳ በመኪናም
ሆነ በስጋጥ ጊዜ አትዘንጋው፣ ራሽን ወደአምላክህ አለማምደው። አባት ሆኖ ሳለ ደካማ ልጁ አምኖት ከእግሩ ስር ሲሸጎጥ ልቡ ችሎ
የሚጎዳ፣ ችሎም ዝም የሚል አባት የለምና፣ እሱስ እንደሆነ ከኛ ልጅነትን እንጂ ጎሎበት ለሱ ልንሰጠው የምንችል እሱም
የሚፈልገው አንዳችም የሌለው ደግ አባት ልጁ ሁንለት እንጂ ሁሉን እንዳይሰጥህ ቀድሞስ ምን አጋጅ ምክንያት አለውና፧
የብዙ ገንዘብ እጣ ሊወጣልህ ቢል፣ ጌታህን እንደባሪያህ “ለኔ አድርገው” ብለህ ትእዛዝን አጽጥ፣ “እባክህን አምላኬ
ያንተ ፈቃድ ብቻ ይሁንልኝ፣ ለኔ ፈቃድህ እሱ ከሆነ ባዶ እጄን እንድትመልሰኝ፣ አንዳችም እንዳላገኝ አብዝቼ እለምንሀለሁ፣ ለኔ
ያልከው ፈቃድህ ከሆነ እንደፈቃድህ ይሁንልኝ” ብለህ ፈጣሪህን ማመኑን የህይወጥ መርህ አድርገው።
ለሌላው ተግባር ብትሰንፍ ይህቺን፣ ይህቺን ብቻ አድርጋት፣ በቀን ፫ ጊዜ ፪፭ ሴኮንድ የማትሞላውን ዕአባታችን ሆይዕ
ፀሎት በላት፣ እጅግ ቀላል ነውና፣ እንድታስታውሳትም ከ፫ቱ ምግቦች በኋላ ከቁርስ፣ ከምሳ።። በኋላ፣ ወደመስሪያቤጥ ወይም
ወደትምህርትቤት በምትሄድበት ጊዜ በመንገድህ ላይ፣ ወይም በሌላም መልኩ ራሽን ሳትጫን እንኳን እንዲሁ ብትላት ትልቅ እርምጃ
ይሆንልሀል፤ በዚህ መልኩ በቀን ፫ቴ ማለቱ እጅግ ቀላል ነውና በዚቺ እንኳን ጀምር፤ አታጓድላት እንጂ እንዲሁ እንደዋዛ
የምትላት አጭር ቀላል ፀሎት እየቆየ በምናውቀውም፣ በማናውቀውም መንገድ በስነልቦናህና በህይወጥ ላይ ተፅእኖ እየያዘች
ትመጣለች፣ በጊዜ ሂደት ልብህ ናፍቆ፣ ፈልጎ ጊዜ ሰጥተህ አተኩረህ የምትላት ትሆናለች። በመልካም መንገድም ህይወጥ መልክ
ይይዛል። ይህቺን በቀን የሴኮንዶች ፀሎት በአፈፃፀሟ ላይ ሳትጨነቅ ቁጥሯን ብቻ ሳታጓድል በላት፣ ይህቺን ቀላሏን እንኳን
ለማድረግ ፈቃደኛ ሁን። በእምነት ወደፊት ትልቅ እርምጃ ትሁንልህ።
ተፈጥረሀልና በእውነት ህይወት ኑር። ሁሉ በጅህ ሆኖልህ፣ ምንም ካንተ የማይጠብቅ ወዳጅ አባት አምላክ፣ ልክ አንተኑ፣
አዎ ራሽ አንተኑ አስቦና ፈልጎ ፈፅሞ ሳይሳሳት የፈጠረህ ጌታ እያለልህ ወደእሳት፣ ወደተራ ስጋ መንገድ አትጓዝ። ይህ ሀያል
አምላክ፣ ከምንም በላይ በሚያከብረው፣ በማያልፈው ቃሉ ላንተ ፍቅሩን ገልጧልና፣ ወደሱ በተመለስን ጊዜ እንደአዲስ የተወለደ ልጁ
በፍቅር እንደሚያቅፈን ደጋግሞ በቃሉ ነግሮናል። ከመንገዱ ገብተህ በደስታ ትኖር ዘንድ ፈልጎ ፈልጎህ ፈጥሮሀልና በዛው ኑር።
ቀኑ ደርሶ ከሚመጣው መከራ ሁሉ ትድን ዘንድ በንሰሀ ፀድተህ፣ በፍቅር ፀንተህ፣ በእምነት ጠይቀው። ትኖርበት ዘንድ ከተሰጠህ
ምድርህ በመቅሰፍት አትጥፋ።
ካልሆነ ግን ሞት እንደሆነ በፊታችን ፀንቶ ቆሟልና ምርጫው የኛ ይሆናል።


Blogger Comment
Facebook Comment