መልዕክት ለ ሙስሊሞች




በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤ከቃሉ አንዲቷም ፈፅሞ በማትታበል በአንድ አምላክ ስም

ሀይማኖት ሁሉ ስለ ህይወት፣ ስለመፈጠርና መኖር ምክንያትና ግብ፣ ስለ ቀጣይ ታላቅ ፍርድ የሚናገር በመሆኑ ማንም ሰው በሀይማኖቱ የሚያሾፍና የሚቀልድ ባለመሆኑ ሁሉም ሰው በሙሉ አእምሮው አመዛዝኖ፣ ከልቡ በመሻት ነው ሀይማኖቱን የሚይዘው። ዛሬ በኢትዮጵያ እንዳለነው ትውልድ ልል፣ ቸልተኛ አማኞች ሳይሆን።

ቅን ሙስሊሙ በተቻለው ሁሉ ሊቀርበውና ለማምለክም የሚተጋው የክርስትያኖችን ፈጣሪ ነው። ቅን ክርስትያኑም ሁሉ በተቻለው መጠን ሊቀርበውና ሊያመልከው የሚተጋው የሙስሊሞችን ፈጣሪ ነው።

የአንድ ቤት የአንድ ፈጣሪ ልጆች አንዱን የጋራ አባታችንን ለማመስገንና ለማምለክ ስለእውነት በመሰለን መንገድና አምልኮ ስንተጋ ቆይተናል። የጋራ አባታችን አንዱን የሚጥር ቅን ልጁን ከሌላው አብልጦ ወይ አሳንሶ አያየውም። በእውነት ልብ ፈልገው አባቴ ብለውት ቢፈልጉት እንደአብርሀም ወደቤቱ መንገድ ይመራቸዋል እንጂ። ማንኛውም በቅን ልቦና ስለእውነት ከልቡ ፈልጎ አምላኩን ለማግኘት በፍቅር የሚተጋ ሰው የጋራ አባታችን አይጨክንበትም።

ነብያትና ትንቢቶች በክርስትናም ሆነ በእስልምና ሀይማኖት ያሉ፣ በደንብ የሚታወቁ የእምነቶቹ ክፍሎች ናቸው። ቅዱሳን ለሆኑ ሰወችም ስለወደፊቱ እውነት ገልጦ የሚነግራቸው እንዳሉ ይታመናል። በክርስትና ብዙ የተፈፀሙ፣ ወደፊት ገና የሚፈፀሙ ትንቢቶች በፍርድ ቀን ስለሚፈፀመው፣ ስለ እስራኤላውያን መበትንና መሰብሰብ ወዘተ በደንብ ግልፅ ሆነው የተፃፉ እንዳሉ ሁሉ፣ በቁራኑም ስለወደፊቱ ፍርድ ቀን ምን እንደሚሆን፣ ስለ ሀይማኖት ክህደት መስፋፋት፣ መልካም ሰው መጥፋት ወዘተ ተፅፏል። በዚህም መልኩ ትንቢት ለሁላችንም አዲስ ነገር አይደለም።

ዛሬም በእኛ ዘንድ ተፅፈው ያሉትንና ከፍፁም ጥፋትና ውድቀት፣ ክፉ መከራ እልቂት እንድንባቸው ዘንድ ከሺ አመታት ጀምሮ በብዙ የተለያዩ ቅዱሳን በአንድነት እኛን በሚገልፅ መልኩ የተገለጡ፣ ዛሬ ያለን ህዝቦች ይሄኛው ያኛው ሳይል ሁላችን በንሰሀና ተመልሰን በፀሎት ፀንተን እንድንባቸው ዘንድ የተፃፉልንን አቅርበንላችኋል።


በተመሳሳይ በአሁኑ ወቅት ልንድንበት የተፃፉ መልእክቶች በናንተ ዘንድ ቢኖሩ ልክ እንደኛው በወንድማዊ ፍቅርና፣ በእውነት ካመኑበት አደጋ ሁሉ ይድን ዘንድ በወንድማዊ ፍቅር እንዳቀረብንላችሁ እናንተም በለሁላችን ታሳውቁንና ታቀርቡልን እንደነበረ በፍፁም አንጠራጠርም።

ይህም የተፃፈው ለሁላችንም የአባታችን ልጆች ነው። ከእናንተም ሆነ ከኛ ከማንኛችንም መሀል ከሚመጣው ለመዳን ከሁሉም የሚጠበቀው ወደ ፈጣሪ ተመልሶ፣ በፍፁም ልብ ለሰራው ሀጢያት በፀፀትና ንሰሀ ፀድቶ ያቅርታንና ጥበቃን ከፈጣሪያችን መለመን ነው።

በዚህ ፅሁፍም ሌላ የሚጠየቅ ነገር ከቶ የለም። ይህንንም አመናችሁትም አላመናችሁትም ብታደርጉት የምትክሰሩበት ነገር የለም። ንሰሀ በመግባት፣ ይቅርታና ጥበቃን ከፈጣሪ ከመለመን

ንሰሀና ፀሎት እንደሆነ አያከስር፨አያሰክር

አይደለም በዚህ ወቅት በማንኛውም ጊዜ ጥያቄ የሌለው ጠቃሚ ነገር ነውና። ይህንንም አንብቦ ያንን ተግቶ የሚያደርግ ሰው ምን ሊጎዳ፧ ይህንን ካነበቡ በኋላ ሞት በስንት አመት ወይ ወር ወይ ቀን ወይ ሰአት ወይ ደቂቃ እንደሚመጣ ምን መተማመኛ የሌለን በመሆኑ ቢያዘጋጀን እንጂ ሌላ ምንም ጉዳት እንደሌለው ግልፅ ነው። ቀድሞም ወደአምላክ ለመመለስ ዛሬ ነገር የለውምና።

ከምንም በላይ ደግሞም የትንቢቶቹ የቀደሙ ክፍሎች በትክክል ቃል በቃል የተፈፀሙ እውነቶች ስለመሆናቸው በማስረጃዎች ተደግፎ ታሪክ የሚመሰክርላቸው በመሆኑ፣ ቀሪዎቹም ክፍሎች በዛው መልኩ መፈፀማቸው ይቀጥላል።

ማወቅ አለማወቅ መዳኛ ሆኖ አያውቅም። ነገርግን እምነትና የህይወት ተግባር ነው ለድህነት ምንጭ። ይህንን ይወቁም አይወቁም በመልካሙ መንገድ ለፈጣሪያቸው ቀርበው፣ ሀጢያትን አርቀው፣ በንሰሀ ፀድተው የተገኙ ሁሉ በፈጥአሪ ጥበቃ ስር ይሆናሉ። በኛም በተለያዩ ቦታዎችና መንገዶች የኖርንና ያደግን ሆነን በፈጣሪያችን ህግጋትና አገላለፅ፣ ቀድሞም በፈጣሪያችን ዙሪያ በተሰሩ ታሪኮች አቀባበል ብንለያይም፣ የሱ መገለጫ በሆነው ፍቅርና መልካም ተግባራት፣ ባህሪያት በአንድነት የምንስማማ በመሆኑ፣ በፍቅር አንድነት ሆነን በየገባንና በያመንንበት መንገድ ፈጣሪያችንን ለመቅረብ በመሞከር ልንኖር፣ በመፀለይ ልንገኝ ይገባናል። በሚመጡትም አስፈሪ ጊዜያት በብዙዎች መሀከል ጠላትነት በመፍጠር የተለያዩ ፀቦችና ግፊቶች ቢመጡም ከሁሉ በላይ ፍቅርና ሰብአዊ መተሳሰብን በማስቀደም በምናምነው ፈጣሪ ህግጋት ከምንም በላይ ለመፅናት በመሞከር ልንታግስ ይገባናል። ሁላችንም ወደእውነተኛው የፈጠረን አምላካችን ለመቅረብ መጣር፣ በሱም ፈቅድና ትእዛዛት ለመኖር ይበልጥ መጣር ይጠበቅብናል።

በተዋህዶ ክርስትናም ቢሆን የአምላክ ፍርድ እንዲሁ በኛ አይን ፈርደን የምናውቀው፣ ሀይማኖ ለይተን እንኳን ይህ ይፀድቃል ይህ ይሞታል ፈፅሞ የምንለው አይደለም። አዲስ ነፍስ፣ ህፃን ሲወለድ መወለጃውን ስፍራ እሱ መርጦ ሳይሆን ፈጣሪ በወሰነው ቦታ ነፍሱ ትመጣለችና፣ ወይ በጥንታዊ እስልምና በምትታወቀው መካ፣ ወይ በጥንታዊዋ ተዋህዶ ክርስትና ምትታወቀው በላሊበላ፣ ወይ ደግሞ ምናልባትም ከአለምና ሰውልጆች ጋር ተያይተው የማያውቁ የአማዞን ጫካ ጎሳዎች መሀል ሊወለድ ይችላል። መርጦ አልመጣምና በዚህ ምክንያት ብቻ በፈጣሪው ፊት ከሌላው የሰው ፍጡር ተቀድሶ ወይ ረክሶ በውልደቱ የሚፈረድበት ሳይሆን ለኛ ደቃዎቹ የ ፍትሀዊነትንእውቀት የሚያመዛዝን አእምሮ የፈጠረው ፈጣሪ እሱ ደግሞ በእፁብ ልኡል ፍትሀዊነት ፍርዱን እንደሚሰጠው ይታመናል። መፅሀፍትም በባዶ ኖረው ከሞቱት ይልቅ ፈጣሪ በይፋ በሚሰበክበት መሀል ኖረው ራሳቸውን ያረከሱና የካዱት ላይ ፍርዱ እንደሚፀና ይናገራሉ።

በዚህም መሰረት የሰው ልጅ የተም ሆነ የት ፈጣሪውንና አባቱን ለማወቅ እጅግ በመጣር፣ በቅንነት በተገለጠለት መልኩ ወደ አባቱ ለመቅረብ ቢጥር፣ ፈጣሪውን ለማግኘት በቅንነት፣ ለህሊናውና ላመነበት ራሱን አስገዝቶ ልባዊ ቅን ትኩረት ወደፈጣሪው አድርጎ ዘወትር ቢጣራ ፈፅሞ የሚመለከተው ፈጣሪ አባቱ እንደማይጨክንበት እሙን ነው። ስለዚህም ሁላችንም እርስበርስ በቅንነትና ሁሉም እምነት በሚሰብካት በፍቅር ሆነን ልንፀና ይገባናል።ካልሆነ ግን ሞት እንደሆነ በፊታችን ፀንቶ ቆሟልና ምርጫው የኛ ይሆናል።

በተዋህዶ ክርስትናም ሆነ በኢስላም አንድ፣ ፍፁም ከአንድ አምላክ ሌላ አምላክ ፈፅሞ የለም። እሱም ሁላችንንም በጥበቡ በአንድነት ያፀናን ፈጣሪ አንድ እሱ ነው።

በግለሰብ ደረጃ የዋህና በቅንነት እውነትን ብቻ ፈላጊ ሙስሊም ሆነህ፣ እሱም የዋህና በቅንነት እውነትን ብቻ ፈላጊ የሆነ ክርስትያን ወንድምህ ጋር ስትታዩ ሁለት አባታቸውን የሚፈልጉ የአንድ አባት ወንድማማቾች እንጂ ሌላ መልክ ልትሰጣጡ አይገባችሁም። በእኩል አመዛዛኝ አእምሮ ተፈጥሮ ያላችሁ እኩል ፍጡራን ናችሁና በቅንነት ስለእውነት በአባት ፍቅር እስከሆነ ድረስ ይህን ልባችሁን የሚመለከት እውነተኛ አንድ አባታችሁ ወደ እቅፉ መርቶ እንደሚወስዳችሁ ጥርጥር የለውም።

ይህም መልእክትና ፅሁፍ በፍቅርና በቅንነት ብቻ ሆኖ ሁላችን እንድን ዘንድ ለእርስዎ የደረሰ ነው።

ከሚመጣው ሁሉም እንደ እምነታችን ድክመትና ምግባራችን ውድቀት ሳይሆን እንደ ይቅርታውና ቸርነቱ ሁላችንንም በጋራ ይጠብቀን።

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment