የኢትዮጵያ መንግሥት ከጤፍ ባለቤትነት ጋር በተያያዘ የሆላንድ ድርጀትን በዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት በዚህ ሳምንት መክሰሱ ይታወቃል።
ድርጅቱና የኢትዮጵያ መንግሥት ከአስር ዓመታት በላይ የባለቤትነት ይገባኛል ንትርክ ውስጥ የቆዩ ሲሆን የዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት በዛሬው እለት የሆላንዱን ኩባኒያ የባለቤትነት ጉዳይ ውድቅ አድርጎታል።
ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጤፍ ጉዳይ ፍርድ ቤት የተሟገተው 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል' የተባለው የሆላንድ ድርጅት እንግሊዝ፣ ጣልያን፣ ቤልጂየም፣ ኦስትሪያና ሆላንድ ውስጥ የጤፍ ባለቤትነት ፈቃድ አለው።
በፈረንጆቹ 2000 አካባቢ ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ስምምነት ስትፈራረም የጤፍ ምርትን ማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር። ነገር ግን ለድርጅቱ የተሰጠው ፈቃድ ኢትዮጵያ የጤፍ ምርትን ወደ ውጪ ከመላክ ያግዳታል።
ይህን በተመለከተ አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው። "በኔዘርላንድስ ኤምባሲ በኩል ከድርጅቱ ጋር ለመደራደር ሞክረናል። ነገር ግን አንድ ግለሰብ በመሆኑ ተቀባይነት ሳይገኝ ቀርቷል። እስካሁን ስንሰራው የቆየነው የባለቤትነት ፈቃዱ መጥፎ እንደሆነ ማሳየት ነው" ይላሉ።
በስተመጨረሻም ጤፍ የኢትዮጵያ ንብረት መሆኑን ፍርድ ቤቱ አጽንቷል።
Blogger Comment
Facebook Comment