«ሞዐ ተዋሕዶ» የማነው?

✍ መንግሥቱ ጎበዜ   

ከወቅታዊ የሀገርና የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ጎልተው ከሚነሱ አጀንዳዎች መካከል አንዱ «ሞዐ ተዋሕዶ» ነው። ስለ ንቅናቄው ግልጽና የጠራ ግንዛቤ ይኖረን ዘንድ በተረዳሁት መጠን የሚከተለውን ምልከታ ማጋራት ወደድሁ።

«ሞዐ ተዋሕዶን» በተመለከተ ብዙ ግራ መጋባቶች ይስተዋላሉ። አንዳንዶች ሆን ብለው በሚመስል ሁኔታ ከዐውዱና ከዓላማው ውጭ የሆነ መረጃ በማሰራጨት፣ ንቅናቄው የፖለቲካ ዓላማ እንዳለው አድርገው በመሳል ብዙዎችን ያሳስታሉ። እንዲያውም «ሞዐ ተዋሕዶ» በአንዳንድ የመንግሥት አካላትም ሆነ በሌሎች የቤተ ክርስቲያን ተቃዋሚዎች በኩል የሚለጠፍበት አሉታዊ ስም፣ በተግባር ከሚሠራው በጎ ሥራ ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም። ከዚያም አልፎ ስሙን የመምቻ ዱላ በማድረግ፣ ኦርቶዶክሳውያንን ለማሳቀቅ፣ ለማሰር፣ ለማሳደድና ለማጥቃት እንደ ምክንያት ሲጠቀሙበት ይስተዋላል።

ሆኖም «ሞዐ ተዋሕዶ» ምንም ዓይነት የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌለውና ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን ሊጋሩት የሚችሉትን ዓላማ ሰንቆ የሚጓዝ ግብረ-ኃይል ነው። ዋና ግቡም ቤተ ክርስቲያንን ከጥቃት፣ ከስደትና ከጥፋት መከላከል ብቻ ነው። አንዳንዶች ሞዐ ተዋሕዶን ከ«ሞአ አንበሳ» ጋር በማመሳሰል ንቅናቄውን ከንጉሣዊ ሥርዓት መመለስ ጋር ለማያያዝ የሚያደርጉት ጥረት ፈጽሞ መሠረት የለውም። የግብረ-ኃይሉን ርእይ፣ ተልዕኮ፣ ግብና ተግባር ከግለሰቦች ማንነት ጋር ማያያዝም ትክክል እንዳልሆነ ተገንዝቤአለሁ።

የ«ሞዐ ተዋሕዶ» መነሻ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥቅምት 2013 ዓ.ም. የምልዓተ ጉባኤው ለመላው ኦርቶዶክሳውያን ያደረገውን ጥሪ መሠረት ያደረገ ነው። ሲኖዶሱ በምእመናንና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ የሚፈጸመውን ጥቃት በመመልከት፣ ምእመናን ቤተ ክርስቲያናቸውን እንዲጠብቁ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የካቲት 2 ቀን 2014 ዓ.ም. በአዲስ አበባ በይፋ ተመሠረተ። 

ሞዐ ተዋሕዶ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ የሚሰነዘሩ መዋቅራዊ፣ አስተዳደራዊና ርዕዮተ-ዓለማዊ ጥቃቶችን ለመመከት የሚሠራ የጥብቅና ንቅናቄ (Advocacy Movement) ነው ማለት ይቻላል። ግብረ-ኃይሉ ለዘመናት የነበረውን «የዝምታ ስልት» በመስበር፣ የቤተ ክርስቲያኗን መብትና ድምፅ በግልጽ የሚያሰማበትን ሰላማዊ መንገድ ቀይሷል። ይህም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ከዝምተኛ ተከታይነት ወደ «ንቁ ተሟጋችነት» የተሸጋገሩበትን አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ያመላክታል።

«ሞዐ ተዋሕዶ» ከምሥረታው ዕለት ጀምሮ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለሚመለከታቸው አካላት ያቀረባቸው ሰባት ዋና ዋና ጥያቄዎችን በማስተጋባት ላይ ይገኛል። እነዚህም በትምህርት፣ በሚዲያና በልማት ስም የሚሰራጩ ጸረ-ኦርቶዶክስ ትረካዎች እንዲቆሙ፣ በመንግሥት መዋቅርና በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸም መዋቅራዊ ማግለል እንዲያበቃ፣ ቤተ ክርስቲያንን በብሔርና በቋንቋ የመከፋፈል ፖለቲካዊ ሴራዎች እንዲገቱ፣ በምእመናን ላይ የሚፈጸሙ አካላዊና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃቶች እንዲቆሙ፣ በጥፋተኞች ላይ ሕጋዊ እርምጃ ተወስዶ ለተጎጂዎች ካሳ እንዲሰጥ፣ የተፈናቀሉ ምእመናን ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ፣ እንዲሁም «አዲሲቷን ኢትዮጵያ» በመገንባት ሰበብ የሚካሄዱ ኦርቶዶክሳዊ አሻራዎችን የማጥፋት ዘመቻዎች እንዲቆሙና መንግሥት ይፋዊ የይቅርታ መግለጫ እንዲሰጥ የሚጠይቁ ናቸው።

በአጠቃላይ፣ መገንዘብ እንደቻልሁት ሞዐ ተዋሕዶ በየትኛውም ዓይነት የፖለቲካ አሰላለፍ ያልወገነ፣ ዋና ዓላማውና ትኩረቱ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻና ብቻ የሆነ ንቅናቄ ነው። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ የታሪክ እውነታ ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ተነጣጥለው ስለማይቆሙ፣ በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ አወንታዊ አስተዋጽኦ ከማበርከት ወደ ኋላ አይልም። ሁሉም ኢትዮጵያውያን በፍቅርና በመከባበር የሚኖሩባት፣ ፍትሕ፣ እኩልነትና ነጻነት የሰፈነባት ሀገር እንድትገነባ የበኩሉን ድርሻ ይወጣል።

እንደ እኔ መረዳት፣ በቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ዘርፈ-ብዙ ጥቃት ለመከላከል ሁሉም ኦርቶዶክሳውያን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ የሚያበረክቱበት የትብብር መረብ በመሆኑ «ሞዐ ተዋሕዶ» የማንም ሳይሆን የሁሉም ነው። በአሁኑ ወቅት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በህልውና አደጋ ውስጥ የምትገኝ በመሆኗና ይህንን ሰፊና መዋቅራዊ ፈተና ለመመከት ይመጥናል ተብሎ የሚታመን ጠንካራ ተቋማዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ፣ የጎደለውን ሞልቶና የጎበጠውን አቃንቶ እንደ «ሞዐ ተዋሕዶ» ያሉ ንቅናቄዎችን መደገፍ፣ ማበረታትና ማሳደግ ከመላው ኦርቶዶክሳውያን የሚጠበቅ ኃላፊነት ነው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ።



Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment