ይህ ትውልድ ግን አዲስ ግኝትና ታሪክ ከመስራት ይልቅ የቀድሞዎቹን ማጥፋት ለምን ይቀለዋል?

✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር

አፍራሽ የሆነ ትውልድ አንሁን እባካችሁን እንንቃ! ይህን ያክል ለሀገርና ለቤተክርስቲያን ጠላት መሆን ያዋጣልን?  ጸባችሁ ከእውነት ጋር ስራችሁም ግፍ ስለሆነ  ዋጋ እንደሚከፈላችሁ አትዘንጉ::  ደግሞ የዘመን አቆጣጠር ቢቀራችሁ እሱንም የጥፋት እጃችሁን ልትዘረጉበት አሰባችሁ? በነገራችን ላይ የውጩ ዘመን አቆጣጠር ስህተት ከመሆኑም በተጨማሪ የወራቱ ስያሜዎች ከባዕድ አምልኮና ከጣዖት ስሞች ጋር የተያያዙ ናቸው! የእኛ የዘመን አቆጣጠር ግን ወራቶቹና ስያሜዎቹ መንፈሳዊ የሆኑና የሀገራችንን የወቅቶች ጸባያትንም የያዙ ግሩም የሆነ  መልእክት ያላቸው ናቸው:: 

የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ከሰው ልጅ የጊዜ መለኪያ ታሪክ ውስጥ በጥንታዊነቱ፣ በልዩነቱ እና በቀጣይነቱ የሚጠቀስ ታላቅ የሥልጣኔ አሻራና ብሔራዊ ቅርስ ነው። የታሪክና የስሌት መሠረቱ በቅዱሳት መጻሕፍት በተለይም በመጽሐፈ ሄኖክ እና በመጽሐፈ ኩፋሌ ላይ ከተገለጸው የፀሐይ፣ የጨረቃ እና የከዋክብት ዑደት ጋር ተዋህዶ በኢትዮጵያ ሊቃውንት አማካኝነት የባሕረ ሐሳብ (የቁጥር/የስሌት ትምህርት መዋቅር ሆኖ እስከዛሬ ድረስ ተጠብቆ የመጣ ፍጹም እውነተኛ ሥርዓት ነው። ዓመቱን በ12 የ30 ቀናት ወራት እና በ1 ተጨማሪ የ5 ወይም 6 ቀናት ወር (ጳጉሜን) በመክፈል 365 (በየአራት ዓመቱ 366) ቀናትን የሚቆጥረው ይህ ሥርዓት ከጎርጎርዮሳዊ ዘመን አቆጣጠር  በ7 ወይም 8 ዓመታት ዘግየት ማለቱ የክርስቶስን ልደት ዓመት ለመወሰን በጥንት ሊቃውንት መካከል በነበረው የስሌት ልዩነት መሠረት የተጠበቀ ታሪካዊ እውነታ ነው። ቤተክርስቲያኗ የመንፈሳዊ ሕይወቷን መዋቅር በሙሉ በዚህ የቀን አቆጣጠር ላይ መሠረት ታደርጋለች።  ሁሉም በዓላት ማለትም ፋሲካ፣ ገና፣ ጥምቀት፣ ሆሳዕና፣ አጽዋማት እና የቅዱሳን መታሰቢያ ቀናት ሁሉ በዚህ የባሕረ ሐሳብ ስሌት መሠረት የሚወሰኑ በመሆናቸው የቀን አቆጣጠሩ እምነትን ከእለት ተእለት ሕይወት ጋር በማያያዝ ረገድ ታላቅ መንፈሳዊ ሚና ይጫወታል። አብዛኞቹ ዓለማት የራሳቸውን የቀድሞ ሥርዓት ትተው የጎርጎርዮሳዊ ካሌንደርን በተቀበሉበት ዘመን ኢትዮጵያ የራሷን የወራት ስሞች፣ የራሷን የሰዓት አቆጣጠር እና የዘመን መለወጫ በዓል ጠብቃ መኖሯ በዓለም አቀፍ ደረጃ ልዩ የማንነት ምልክቷ ነው።

ይህንን ትክክለኛ የቀን አቆጣጠር ሰርታ ለሀገር በማስረከቧ ቤተክርስቲያን ልትወደስ ሲገባት እንደ ጠላት እየታየች ጥርስ ተነክሶባት ለበርካታ ዘመናት ቆይታለች:: የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የቤተክርስቲያኗ ሀብት ብቻ ሳይሆን የጠቅላላዋ ሀገር የታሪክ፣ የኪነ-ሕንጻ፣ የሥነ-ጽሑፍ እና የማንነት መገለጫ ነው። ዘመን አቆጣጠሩ እንዲቀየር የሚቀርቡ ጥያቄዎች በሙሉ መንፈሳዊውን ሥርዓት ለማበላሸትና ትክክለኛ በዓላት የሚውሉበትን ቀናት በማዛባት አማኞች ከጸጋና ከበረከት እንዲርቁ ለማድረግ የታለሙ ናቸው። ቅዱሳን በዓላትና አጽዋማት በመጽሐፋዊ ስሌት በታወቁበት ቀንና ሰዓት መከበራቸው መንፈሳዊ ይዘታቸውን የሚጠብቅ በመሆኑ ይህንን አቆጣጠር መጋፋት የሀገሪቱን ጥንታዊ መሠረትና መንፈሳዊ ውርስ የሚያናጋ አደገኛ አካሄድ ነው። አሁን የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እንዲቀየር ጥያቄ የሚያቀርቡት ቤተክርስቲያንን  ለመጉዳት የተነሱ አካላት ናቸው:: ከዚህ በፊትም ለበርካታ ዘመናት ይህ ሴራ ተሞክሮ የነበር ቢሆንም በአያቶቻችን ብርታት ተጠብቆ ኖሯል:: 

ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያን የዘመን አቆጣጠር መቀየር የሚፈልጉ ዋነኛ አካላት ኢትዮጵያ በአዲሱ የዓለም ስርዓት (ኢሉም*ናቲ) ስር በትክክል እንድትገባ የሚፈልጉና  እንዲተገበርም እየሰሩ ያሉ ናቸው::  የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ለሀሳዊ መሲሁ መንገድ ጠራጊዎች ለአዲሱ ዓለም ስርዓት ፍጹም አይመቻቸውም::  ሌሎች ጸረ ክርስቶስ የሆነ ሃይማኖት ያላቸውም ሁሉም እንዲሁ በእጅጉ ይጠሉታል!  አጠቃላይ ኢትዮጵያን ከትክክለኛው መንገድ የማስወጣት ጉዞ እንደሆነ ሁላችንም መገንዘብ አለብን::  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ከምዕመናን መጨፍጨፍ እስከ ቤተክርስቲያን መቃ*ጠልና አስተዳደራዊ መዋቅሯን ማፍረስ ድረስ እየሰሩ ያሉ አካላት በተጠናና በእቅድ እንደሆነ ሁላችንም ማወቅ አለብን:: በገዳማት በታሪካዊ ቅርሶች እና በአማኞች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች፣ መፈናቀሎች እና የቅርስ ውድመቶች የዚሁ የታሪክና የማንነት መሸርሸር አካል ናቸው። ይህ አገዛዝ ታሪክን ከመስራት ይልቅ ማፍረስ የሚቀለው ነው!  ወደ ስልጣን ከመጣ ጀምሮ የኢትዮጵያንና የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን መሰረቶች እያፈረሰ እያናወጻቸው ነው::  የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊ ቅርሶቿን፣ የባሕረ ሐሳብ ስሌቷን እና ታሪኳን ጠብቃ ለትውልድ በማስተላለፍ ረገድ የተጫወተችው ሚና የሀገሪቱ ታሪክ ትልቅ መሠረት ነው:: ኢትዮጵያ የ13 ወራቶች ባለ ጸጋ እየተባለች በዓለም የምትታወቅበትን ሀብቷን ጠብቃ ማቆየት ሲገባት የራሷን ሀብት ትታ ወደ ውጭ መመልከቷ ውድቀት መሆኑን ማወቅ አለባት:: እነዚህን ታሪካዊና መንፈሳዊ ሀብቶች ሳይበረዙ በጥንቃቄ መጠበቅ የሀገርን ማንነትና አንድነት ለማጽናት ወሳኝና ወደር የሌለው ብቸኛ መንገድ ነው።  ይህንን ቅርሳችንን እንዲሁም ትክክለኛና ብቸኛ የሆነውን የዘመን አቆጣጠር ሁላችንም መጠበቅ ግድ ይለናል:: ሆኖም ግን  በጥመት አካሄዳችሁን አበርትታችሁ ይህንን የማንነታችን አንዱ አካል የሆነውን የዘመን አቆጣጠራችንን ለመቀየር ብታስቡ እንደማይሳካላችሁ እወቁ!  

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment