የኢትዮጵያ የጊዜ አቆጣጠር ሃይማኖታዊ ስለሆነ አንፈልግም ለምትሉ ሁሉ!


✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር

አያ ጅቦ ሆይ ሳታመካኝ ብላኝ የሚለውን የሀገራችንን ምሳሌያዊ አነጋገር እዚህ ብጠቀም ቦታው ይመስለኛል:: የኢትዮጵያና የቤተክርስቲያን ጠላቶች የኢትዮጵያን የጊዜ አቆጣጠር ለመቀየር ምክንያት የሚያቀርቡት የቤተክርስቲያኗ ነው በሚል ተልካሻ አስተሳሰብ ነው::  ይህ ሁሉ ምክንያት ድርደራ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖትን ከመጥላት የመነጨ ነው! ለመሆኑ የአውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠርስ የካቶሊክና የሌሎች የጣዖት አምላኪዎች አቆጣጠር እንደሆነ ስለማታውቁ ነውን?  የቀን አቆጣጠራቸውን እኛ ከምንጠቀመው ከእውነተኛው ቀመር አስወጥተው ለዚህ ዓለም ገዥ ለሆነው ለዲያብሎስ እንዲመች አድርገው የሰሩ ሲሆን የቀናትና የወራትን ስያሜንም ከመንፈሳዊ አውድ አርቀው በጣኦታት ስም ነው የሰየሙት:: የጎርጎርዮሳውያንን አቆጣጠር ያጸደቀው እና ዓለም አቀፍ ትዕዛዝ ያስተላለፈው በወቅቱ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበረው ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ጎርጎርዮስ XIII (Pope Gregory XIII) ነው። ይህም የአውሮፓዊያን የቀን አቆጣጠት ባለቤትነቱ የካቶሊክ ሃይማኖት ነው:: ስለዚህ የኢትዮጵያን የቀን አቆጣጠር የቤተክርስቲያን አቆጣጠር ነው እያሉ ማጣጣል ፍጹም ጥላቻ የወለደው ታሪክን የማጥፋት በቤተክርስቲያኗም ላይ ግልጽ ጦርነት መክፈት እንደሆነ ማወቅ አለብን::  ይህን ፍጹም ጥላቻ ሁላችንም ልናወግዘው ግድ ይለናል! ቤተክርስቲያን ባቀናችው ሀገር እየኖሩ ሊያጠፏት ሆ ብለው ተነስተዋል:: በሁሉም መልኩ እየተዋጓት ስለሆነ በጣም መንቃት ያለብን ጊዜ ላይ ነን::  በነገራችን ላይ በየመስሪያ ቤቱ በአውሮፓዊያን መቁጠር ከጀመሩ ቆይተዋል::  ቀስ በቀስ በአዋጅ ማወጅ ብቻ ነው የቀራቸው:: ስለዚህ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ቅርስ ስለሆነ   እንደ ሀገር መላው ኢትዮጵያውያን እንደ ሃይማኖት ደግሞ እኛ ሳይረፍድ ይህን ሴራ ልናከሽፍ ግድ ይለናል:: 

የዘመን አቆጣጠር የሰው ልጆች የዕለት ተዕለት ሕይወት መለኪያ ብቻ ሳይሆን የአንድ ማኅበረሰብ የዓለም እይታ፣ የእምነት ሥርዓት፣ የባህል ማንነት እና የፍልስፍና መሠረት ነው። የኢትዮጵያ የቀንና የወራት አቆጣጠር ሙሉ በሙሉ ከጥንታዊው የግዕዝ ቋንቋ፣ ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው የፍጥረት ታሪክ እንዲሁም ከግብርናና ከተፈጥሮ ዑደት ጋር የተቆራኘ ነው። ከዚህ በተቃራኒው የምዕራባውያን (የጎርጎርዮሳውያን) አቆጣጠር ሥረ-መሠረቱ በጥንታዊ የጣኦት አምልኮዎች፣ በአፈታሪኮች እና በሮማውያን ንጉሠ ነገሥታት ስም የተገነባ ነው። የኢትዮጵያ የሳምንቱ ቀናት ስያሜዎች መነሻቸው እግዚአብሔር ዓለምን በፈጠረባቸው ቀናት ቅደም ተከተል ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ፍጹም መንፈሳዊ ናቸው። መነሻውም "አሐዱ" (አንደኛ) ተብሎ ከሚጠራው እሁድ ይጀምራል። እሁድ በግዕዝ "አሐዱ" ማለት ሲሆን ብርሃን የተፈጠረበት የመጀመሪያው የፍጥረት ቀን ነው። በክርስትናው ዓለም ጌታ ከሞት የተነሳበት የትንሣኤ ቀን በመሆኑ "ሰንበት ክርስቲያን"  ተብሎ የክርስቲያኖች ዋና የዕረፍትና የአምልኮ ቀን ሆኗል። ቀጥሎ የሚመጣው ሰኞ በግዕዝ "ሰኑይ" (ሁለተኛ) ማለት ሲሆን እግዚአብሔር በሁለተኛው ቀን ጠፈርን (ሰማይን) የፈጠረበት የሥነ-ፍጥረት መታሰቢያ እና ሳምንቱ ሥራ የሚጀመርበት ቀን ነው። ማክሰኞ "ሠሉስ" (ሦስተኛ) በመባል ምድርን፣ ዕፅዋትንና አትክልትን የፈጠረበት ቀን ሆኖ ይጠራል። ረቡዕ "ረቡዕ" (አራተኛ) ተብሎ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትን የፈጠረበት ቀን ሲሆን፣ በክርስትናው ትምህርት አይሁድ ክርስቶስን ለመያዝ ምክር የጀመሩበት በመሆኑ የጾም ቀን ነው። ሐሙስ "ሐሙስ" (አምስተኛ) ተብሎ በውኃ ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታትና በሰማይ የሚበሩ አዕዋፋት የተፈጠሩበት እንዲሁም ጌታ ሥርዓተ ቁርባንን የመሠረተበት ዕለት ነው። አርብ "ዐርብ" (መሰብሰብ/ማብቂያ) ማለት ሲሆን እግዚአብሔር አዳምና ሔዋንን የፈጠረበት እና የፍጥረት ሥራ የተጠናቀቀበት ቀን ነው። በሐዲስ ኪዳንም ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን በመስቀል ላይ የተሰቀለበት ቀን በመሆኑ በታላቅ ጾም ይታሰባል። በመጨረሻም ቅዳሜ "ቀዳሚት ሰንበት" (ሰባተኛው ቀን) ተብሎ እግዚአብሔር ፍጥረታትን ፈጥሮ ያረፈባት የመጀመሪያዋ የዕረፍት ቀን ናት። 

ለዚህ የኢትዮጵያ መንፈሳዊና ቅዱስ ስያሜ በተቃራኒው የምዕራባውያን የሳምንቱ ቀናት ስሞች ሙሉ በሙሉ በጥንታዊ የጣኦትና የከዋክብት አምልኮ ላይ የተመሠረቱ ናቸው። Sunday (እሁድ) ለፀሐይ አምላክ (Sol Invictus) መታሰቢያ የተሰጠ ሲሆን፣ Monday (ሰኞ) ደግሞ ለጨረቃ አምላክ (Luna) የተሰየመ ነው። ቀጥሎ ያሉት Tuesday, Wednesday, Thursday እና Friday ለኖርስ (Norse) አፈታሪክ አማልክት ማለትም ለTiw (የጦርነት አምላክ)፣ ለWoden (የጥበብ አምላክ)፣ ለThor (የነጎድጓድ አምላክ) እና ለFrigg (የፍቅር አምላክ) የተሰጡ ስሞች ናቸው። Saturday (ቅዳሜ) ደግሞ የሮማውያን የእርሻና የጊዜ አምላክ ለሆነው ለSaturn መታሰቢያነት የተሰየመ ጣኦታዊ ስም ነው።

ወደ ዓመቱ ወራት ስያሜዎች ስንሄድ ደግሞ የኢትዮጵያ አቆጣጠር ከምድር ገጽ ላይ በሚታየው የተፈጥሮ ለውጥ፣ በእርሻ ዑደትና በሕይወት እንቅስቃሴ ላይ የተመሠረተ ነው። መስከረም ከክረምት ማብቂያና ከብርሃን መግቢያ (ከረመ) የተወሰደ ሲሆን ጥቅምት አዝመራው እሸት የሚሆንበት (ጠቀመ)፣ ኅዳር እህሉ ደርቆ ወደ ጎተራ የሚገባበትና ቅጠሎች የሚረግፉበት (ኀደረ) ወር ነው። ታኅሣሥ ላሞች ግጦሽና ውሃ ፍለጋ የሚጓዙበት (ኀሠሠ) ሲሆን በመንፈሳዊው የክርስቶስ ልደት የሚታሰብበት ነው፤ ጥር እህሉ የሚከመርበትና ብርዱ የሚጸናበት (ጠረረ)፣ የካቲት አዝመራው ሙሉ በሙሉ ተሰብስቦ የሚከተትበት ወር ነው። መጋቢት ገበሬው ቤተሰቡን የሚመግብበት የጸደይ ወቅት ሲሆን ሚያዝያ አጭር ዝናብ የሚጀምርበትና ፋሲካ የሚከበርበት ነው። ግንቦት መሬት ለአዲስ ዘር የምትዘጋጅበትና የልደታ በዓል የሚታሰብበት ሲሆን ሰኔ ምድር በዝናብ የምታምርበትና አዝመራ የሚጀመርበት ነው። ሐምሌ የልምላሜና የዝናብ ወር ሲሆን ነሐሴ ገበሬው ጎተራውን የሚጠግንበትና ጾመ ፍልሰታ የሚጾምበት ወር ነው። ጳጉሜ ደግሞ የዓመቱን ማጠናቀቂያ የምታሳይ የሽግግር 13ኛ ወር ናት።

በምዕራባውያን በኩል ያሉት የወራት ስሞች ግን በሙሉ በሮማውያን አማልክት እና በንጉሠ ነገሥታት ስም የተሰየሙ ናቸው። January ባለ ሁለት ፊት የመግቢያ አምላክ ለሆነው ለJanus፣ March ለጦርነት አምላክ ለMars፣ May እና June ደግሞ ለሮማውያን አማልክት ለMaia እና ለJuno የተሰጡ ናቸው። July እና August በታላላቆቹ የሮም መሪዎች በጁሊየስ ቄሳር (Julius Caesar) እና በአውግስጦስ ቄሳር (Augustus Caesar) ስም ተሰይመዋል። September እስከ December ያሉት ደግሞ በጥንቱ የሮም ካላንደር መሠረት የላቲን ቁጥሮችን (7ኛ እስከ 10ኛ ወር) የሚያመላክቱ ሲሆን አጠቃላይ ይዘታቸው ፍጹም ዓለማዊና ጣኦታዊ መሠረት ያለው ነው።

በአሁኑ ወቅት ዓለም አቀፍ ግብይትን እና ቴክኖሎጂን ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያን የቀን አቆጣጠር እንዲቀየር የሚሠሩ በርካታ አካላት አሉ። ይህ ድርጊት የሀገሪቱን መንፈሳዊ፣ ታሪካዊ እና ባህላዊ እሴቶች በመናድ በጣኦታዊ እና በዓለማዊ ስያሜዎች የተሞላውን የምዕራባውያን ሥርዓት በግድ ለማስገባት የሚደረግ ሙከራ ነው።  የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር ትክክለኛ ሲሆን የቀናቱና የወራቱ ስያሜዎቹም ከጣኦት አምልኮ ፍጹም የራቁ መንፈሳዊያን ናቸው::  የኢትዮጵያ አቆጣጠር ጊዜን የሚለካበት መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የሕዝብ ማንነት፣ የጥንታዊ ሥነ-ከዋክብት እውቀት እና የመንፈሳዊ ፍልስፍና ማሳያ በመሆኑ ይህንን ልዩ ሥርዓት ጠብቆ ማቆየት የዘላለም የባህልና የታሪክ ኃላፊነት ነው። ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በጥላቻ ሳይሆን አስበን እንጓዝ! ከዚህ በዘለለ ግን በቤተክርስቲያን ላይ ልክ ያለፈ ጥላቻችሁ የትም እንደማያደርሳችሁ እወቁልን::  ውድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ልጆች ሆይ ነቃ በሉ አትፍዘዙ! ጠላት እንደ እኛ አያንቀላፋም!

 
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment