የፍልሰታ ጾም ፈለሰ ከሚለው የግዕዝ ግስ የተገኘ ሲሆን ከአንድ ቦታ ወደ ሌላ ቦታ መዛወርን ወይም መጓዝን ያመለክታል። በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ይህ ጾም የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሥጋ ከእረፍቷ በኋላ ከጌቴሴማኒ ወደ ገነት መፍለሱንና በትንሣኤዋ ሥጋና ነፍሷ ተዋሕደው ወደ ሰማይ ማረጓን የምናስብበት ታላቅ የሱባኤ ወቅት ነው። ታሪካዊ አመጣጡም ከሐዋርያት ሱባኤ ጋር የተያያዘ ነው:: እመቤታችን በነሐሴ ፲፭ ቀን በዕረፍት ከተለየች በኋላ አይሁድ ሥጋዋን ለማቃጠል ሲሞክሩ ወደ ገነት በመወሰዱ ሐዋርያት ሥጋዋን ለማግኘት ከነሐሴ ፩ ጀምረው ሱባኤ ገብተዋል። እግዚአብሔር ጸሎታቸውን ሰምቶ በሁለተኛው ሳምንት ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋዋን ሰጥቷቸዋል:: ሐዋርያትም ደስ ብሏቸው በክብር ቢቀብሯትም በሦስተኛው ቀን ተነስታ ስታርግ ሐዋርያው ቶማስ ብቻ ትንሣኤዋን አይቶ የሰበኗን ጨርቅ ተቀብሏል። በኋላም ሌሎቹ ሐዋርያት ቶማስ ያየውን ትንሣኤና እርገት እኛም ለማየት እንድንችል በማለት ሱባኤ በመያዝ ከነሐሴ ፩ እስከ ፲፮ ቀን ሱባኤ የመግባትና የመጾም ስርዓት በመስራታቸው ዛሬም ምዕመናን ያንን አሰረ ፍኖት በመከተል በጉጉት በመጠበቅ በየዓመቱ በታላቅ ተጋድሎ ያሳልፉታል።
አባት እናቶቻችን ከግል ጥያቄያቸው ይልቅ ልክ እንደ አሁኑ ሀገርና ቤተክርስቲያን በሚጨነቁበትና ጥፋት በበዛበት ድቅድቅ ጨለማ ወቅት ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መፍትሔ የሚጠይቁበትና መልስ የሚያገኙበት ዋናው መንገዳቸው ሱባኤና ጾም ነበር። በአሁኑ ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ በጦርነት፣ በደም መፋሰስና በጽኑ መከራ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን የበርካታ ሚሊዮን የንጹሐን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ማለፍና የትውልድ መሳደድ በመብዛቱ እጅግ ተጨንቃለች:: በተለይም በታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በምዕመኖቿና በንብረቷ ላይ የሚደርሰው ስልታዊ ጥቃትና ጫና እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። በተጨማሪም በፖለቲከኞች ጠባብ ፍላጎትና በውጭ አስተሳሰብ ምክንያት ህዝባችን ከባህሉ፣ ከሃይማኖቱና ከትውፊቱ እንዲወጣና እርስ በእርሱ እንዲቃረን የማድረግ አደገኛ ዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል። ስለሆነም በዚህ የተቀደሰ የፍልሰታ ጾም ወቅት እያንዳንዱ ክርስቲያን በቤት ውስጥም ሆነ በተለያየ የሥራ መስክ ላይ ሆኖም ይሁን በበዓት ራሱን በጾምና በጸሎት መስዋዕት ሊያደርግ ይገባል። ሀገርንና ቤተክርስቲያንን ከአምባገነኖች ጥፋት ለመታደግ ጦረኛውም ጦሩን ጸሎተኛውም ጸሎቱን ይዞ በያለበት አቋም ሆኖ ወደ አምላኩ ሊለምን የሚገባበት ሰዓት አሁን ነው። ጾም ከምግብ መከልከል ብቻ ሳይሆን ከሰው ላይ ክፉ ከመመኘት፣ ከቂም በቀልና ከዘረኝነት ነፃ መሆንን የሚጠይቅ ሲሆን የአምባገነኖች ጊዜ እንዲያጥርና እውነተኛው የሰላም መንገድ እንዲገለጥ በጽኑ ልንጸልይ ይገባል። እግዚአብሔር አምላክ የአባቶቻችንን አምላክ እንዲራራልን መከራውንና ድቅድቅ ጨለማውን አስወግዶ ብርሃኑን እንዲያበራልንና ለሀገራችን ሰላሙን እንዲልክልን በዚህ የፍልሰታ ጾም በሙሉ ልባችን ልንማጸነው ይገባል።
ሁላችንም ልናውቀው የሚገባ ነገር ቢኖር ለዚህ ሁሉ ምስቅልቅልና መከራ ሀገራችን ኢትዮጵያ የደረሰችበትና አሁን ያለንበት ዋናው ምክንያት የሃይማኖት አባቶችም ሆነ ህዝብን እንመራለን ብለው የተቀመጡ የፖለቲካ ሰዎች ፈሪሃ እግዚአብሔርን በማራቅ በውስን እውቀታቸውና በጠባብ አእምሮ በመመካት በስህተት መንገድ በመሄዳቸው ነው። ይህ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ችግርና የመከራ መንገድ ፈር ቀዳጅ ሲሆን የሰው ልጅ ከተፈጠረበት የተቀደሰ ዓላማ ውጭ እንዲጓዝ በመደረጉ ነው:: ዓለማችን እግዚአብሔርን ከትውልድ በማራቋ ወደ ያልተፈቀደና አደገኛ የጥፋት መንገድ እየተጓዘች እኛን እያጠፋች ነው:: በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ የሚታየው የእርኩሰት ሥራ፣ የትውልድ መበላሸትና መምከን፣ የንጹሐን ደም መፈሰስ፣ ህዝብ በህዝብ ላይና ሀገር በሀገር ላይ መነሳት፣ እንዲሁም በቋንቋና በጎሳ መከፋፈልና ዘረኝነት መስፋፋት ሁሉ የተፈጠሩበት ዋናው ምክንያት የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ሕግና ሥርዓት በመውጣቱ ነው። እኛ አሁን ካልነቃን ዓለም በራሷ ጥፋትና ፈቃድ በሰራችው መንገድ ብቻ እየተጓዘች በመሆኗ ይህ አካሄድ የሰውን ልጅ መጻኢ እድል እጅግ አደገኛ የሚያደርገውና አሁን ካለንበት መከራ የበለጠ የከፋ አደጋ የሚያስከትል መሆኑን ሁላችንም በጽኑ ልንገነዘበው ይገባል። በመሆኑም አሁን ያለው ትውልድ በተለይም ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስቲያን አማኞች በምንም ዓይነት መንገድ ሳይታለሉና ጊዜያቸውን በዋዛ ፈዛዛ ሳያሳልፉ በንቃት ሊነቁ ይገባቸዋል። ጊዜው በዘፈን፣ በስካር፣ በዝሙትና ከፈጣሪ በሚያርቁ ልዩ ልዩ የኃጢአት ሥራዎች የሚባክን ሳይሆን ከእነዚህ ሁሉ በመራቅና በምግብም በህሊናም በጽኑ በመጾም ወደ አምላክ የሚጮህበት ወቅት ነው። ሀገራችን ኢትዮጵያ ከአምባገነኖች እጅ ነጻ እንድትወጣና ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም በብሉሽ አሰራር ምክንያት ከገባችበት መዓትና መቅሰፍት እንድትወጣ አጠቃላይ ሁለቱም ከወደቁበት እንዲነሱ ሁላችንም የበኩላችንን መንፈሳዊና ሥጋዊ ኃላፊነቶችን መወጣት አለብን። ጸሎት የሚያደርገው በጸሎቱ ለፍትህ የሚዋጋውና የሚታገለው ደግሞ በክንዱና በእውቀቱ በመጽናት ቅድስት ቤተክርስቲያንንና ሀገራችንን ኢትዮጵያን በሕብረት ልንታደጋቸው ይገባል።
በተለይም በአሁኑ ሰዓት ጥቂት እውቀት አለን ወይም የቤተ ክርስቲያን ትምህርት ተምረናል የሚሉ አባቶች ሁሉንም ነገር ከእኩያን መናፍስት ጋር ብቻ በማያያዝ ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚመጣውን ተግሣፅና ጥሪ በማጣጣል ትውልዱ እያንቀላፋ አብሮ ከሚመጣው መቅሰፍት ጋር እንዲጠፋ እያደረጉ ይገኛሉ። በመሆኑም እነዚህን አካላት ባለመስማት የሚጠቅመውንና እውነተኛውን መንገድ በመለየት በሁሉም መስክ ልክ በጦር ግንባር እንዳለ ወታደር ክርስቲያኖች በተጠንቀቅ ልንቆም ይገባል። በጾም፣ በጸሎት፣ እውነተኛ ንስሐ በመግባት፣ መልካም ትሩፋቶችን በመሥራትና እንደ ቀድሞዎቹ ሰማዕታት ለሃይማኖታቸውና ለሀገራቸው በመቆም ቤተ ክርስቲያንንና ሀገርን መታደግ ያስፈልጋል። ሀገርና ቤተ ክርስቲያን የማይለያዩ ሁለት የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች በመሆናቸው ቤተ ክርስቲያንን መታደግ ኢትዮጵያን መታደግ ሲሆን ኢትዮጵያን መታደግም ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን መታደግ እንደሆነ ተረድተን የአምባገነኖችን ኃይልና ዛቻ ሳንፈራ እግዚአብሔርን አስቀድመን ለሁለቱም ትንሣኤ በጽናት ልንቆም ይገባል። በአጠቃላይ አሁን በዓለም ግርግርታና ሆታ እየተታለልን የምንተኛበትና የምናንቀላፋበት ዘመን ሳይሆን በንቃት በመጸለይ፣ በመጾም፣ ንስሐ በመግባትና ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን የሚታደጉ ተግባራዊ ሥራዎችን የምንሠራበት ወሳኝ ጊዜ ነው። አሁን ሀገራችንንና ቤተ ክርስቲያናችንን ወደዚህ ታላቅ ችግርና መከራ ውስጥ የከተቱ አካላት ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚገባቸውን ፍርድ እንደሚያገኙና በታሪክም በመጥፎ ስማቸው አልፈው እንደሚቀሩ በመረዳት አሁን ያስጨነቀንን ዘመን በፈጣሪ እርዳታና ኃይል የምናልፈው እንደሆነ ማወቅ ግድ ይለናል:: ሆኖም ግን ቤተክርስቲያንንና ሀገርን የምናሻግረው ዝም ብሎ ፈዞ ደንግዞ በመቀመጥ በማን አለብኝነት ወይም የኢትዮጵያ ትንሣኤ ወዴት አለ? ስቃያችንስ ለምን በዛ? በሚሉ መሰል የስላቅ ጥያቄዎችና ተስፋ በመቁረጥ በመመላለስ ሳይሆን በጸሎት፣ በጾም፣ ንስሐ በመግባት፣ ዘረኝነትን ከልብ በማስወገድ፣ አውነተኛ አንድነትንና ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን መልካም ነገሮችን በመመኘትና የሚጠበቅብንን ድርሻ በማበርከት ብቻ ነው። ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን ትንሣኤ የእያንዳንዳችን አዎንታዊ አስተዋጽኦ የሚያስፈልግ ሲሆን ይህንን ሳናደርግ ብንቀር ግን የመከራውና የጭንቁ ጊዜ እየረዘመ እንደሚሄድ ተረድተን በሙሉ ልባችን ወደ አምላካችን ልንመለስ ይገባል። ይህንን መልእክት ያስተላለፍኩት አእምሯቸውን ለመልካም ነገሮች ለአዘጋጁት ነው፤ ተሳዳቢዎችና ተችዎች ከአገዛዙ ጋር ቀኑ ይጨልምባቸዋልና ምንም ማድረግ አይቻልም!
ጹሙ ጸልዩ ሀገራችሁንም ቤተክርስቲያናችሁንም ታደጉ! ድል መቼም አይቀርም!
መልካም ጾም!
Blogger Comment
Facebook Comment