✍ አብነት ባሶሬ
"ጽዮን ማለት አንተ እንድትላበሰው የተዘጋጀልህ ማንነት ወይም ስብዕና ማለት ነው።"
1 ጽዮን ንፁህ ናት- ለዛም ነው እናቱን(ማሪ ሃም) ወይም ቤተክርስትያንን በጽዮን ምንመስላቸው
2 ጽዮን የህግ መፍለቂያ ናት- ለዛም ነው ከበዓለ 50 በኃላ እነሱም ፅዮን ሆነው ወንጌላውያኑ ህግን የፃፉልን(መፅሐፍ ቅዱስን የፃፉልን)።
የምታውቃቸው ወንጌልን የፃፉ ፃድቃን ጴጥሮስ በለው ጳውሎስ ወይም ሉቃስ በበዓለ 50 መንፈስ ቅዱስ ወርዶላቸው አዲሲቱን ሰብዕና(ጽዮንን) በመላበስ ነበር ህግን የፃፉልን(ቃሉም ህግ ከፅዮን ይወጣል አይደል የሚለው) እነሱ ጽዮን ሲሆኑ ህግ ከነሱ ወጣች ወይም ተፃፈች።
ስለዚህ የየትኛውም ሰው የመጨረሻ ግብ ፅዮናዊነት ነው። ምን አልባት በተለያየ አቅጣጫ ሊያስበው ይችላል እንጂ የመጨረሻ ግቡ ፅዮናዊነት ነው።
ስለዚህ ስምህ አበበ ወይም ከበደ ከሆነ የምታደርገው የህይወት ጉዞ ጽዮን ተብሎ ወደመጠራት ይሆናል።
ምን አልባትም ይህን ክብር ሳታገኘው የነፍስህ ህላዌ መሻት ሳይገባህም ቀርቶ የዚች ምድር የህይወትን ጊዜ ልትጨርስም ትችላለ።
አንድ ሰው ጽዮን ያልነው ስብዕና ላይ ደረሰ ማለት፦ ከሙሽራው ጋር ጋብቻ መስርቷል ማለት ነው።
ጋብቻ መሰረተ ማለት ደግሞ ሙሽራው በእርሱ ውስጥ ይኖራል ማለት ነው።
ማነው ሙሽራው?
ሙሽራውማ፦ ተወዳጁ፣ መድሐኒቱ አየሱስ ክርስቶስ ነው።
በምድር ቆይታው በአንተ ባህሪ በመግባት ህይወትን ተወለደ ፣ ኖረ ከዛን ሞተ ከመባል አውጥቶ ለአዲስ ሰማይ እና ምድር ወይም ለጽዮን ክብር አብቅቶ ሄዷል።
እርሱ ሙሽራው በሰጠህ እና በገባልህ ቃል አማካኝነት ሙሽራይቱን ነብስህን ለሰርጉ ክብር እንድታበቃለት ወይም እርሱ መኖሪያውን በዓንተ ለማድረግ በአምላካዊ ፍቅር ይጠብቅሐል።
ጋብቻውን ፈፅመህ በጽዮን የተመሰሐችውን ስብዕና ያዝክ ማለት አየለ ወይም ከበደ መባልህ ይቀራል፡ ስትኖርም እንደአየለ እና ከበደ መሆኑ ይቀራል። በውስጥህ ያለው እኔ የምትለው ሥጋዊ ፈቃድ ይሞትና በፈጣሪ ፈቃድ መኖር ትጀምራለህ፣ የፈጣሪ መኖሪያው ትሆናለህ፣ ይሁን ያልከው ይሆናል፡ አይሆንም ብለህ የዘጋኸውን ማንም አይከፍተውም፤ የምታዘው አንተ ሳትሆን በውስጥህ ያለው መንፈስ ነው።
ጽዮን ያልናትን ሰብዕና ባለማግኘት እና በማግኘት ውስጥ ያለፈ አንድ ቆንጆ ሰው ምሳሌ ልስጥህ ፦
"ጴጥሮስ" ይባላል
መቼም ጴጥሮስን የማያውቀው የለም፣ ቢያንስ ዶሮ 🐓 እንኳን ሲጮኸ ትዝ ሊለን ይችላል።
ታዲያ ይኼ አትሙት፣ጌታ ሆይ አይሁንብህ፣ ማንም ቢክድህም እኔ አልክድህም.. ምናምን ብሎ እንዳልዘበዘበ፣ ሐሙስ ማታ ተወዳጁ ተይዞ ሲወሰድ፣ አንዲት ገረድ ጴጥሮስን አይታው 'አንተም ከእርሱ ወገን ነህ ንግግርህ ይገልጥሐል' ስትለው እሱም መልሶ 'የምትይውን ሰው እኔ በጭራሽ አላውቀውም' በማለት ክዶት ነበር...
ምንም እንኳን ቢከዳውም በጊዜውም ቢሆን ጴጥሮስ ተወዳጁን እጅግ ይወደው እንደነበር አበው ይናገራሉ፣ ነገር ግን በጴጥሮስ ውስጥ ጴጥሮስ እንጂ የተወዳጁ መንፈስ አልነበረም ፣ጋብቻው አልተከናወነም ወይም በውስጡ ያለው ስጋዊ ፈቃድ አልሞተም ነበር ማለት ነው።
ነገር ግን ይሄው ጴጥሮስ ነበር ከትንሳኤው በኃላ እያስተማረ እያለ ሊገድሉት ከመጡት ሮማውያን ፊት ለመሸሽ አልሞከረም፤ ሞትን እስገመጋፈጥ ደረሰ፣ ራሱን ዘቅዝቀው እንዲሰቅሉትም ፈቀደላቸው። ከትንሳኤው በኃላ ጴጥሮስ የቀድሞውን ጴጥሮስ አልነበረም፤ በስጋ ፈቃድ ሳይሆን በውስጡ ባለው የፈጣሪ መንፈስ ነበር የሚመራው።
ጽዮን ስትሆን በወለደችህ እናት እና ድንገት መንገድ ላይ በምታያት የሌላ ሰው እናት መሐከል ምንም ልዮነት አይታይህም፡ ለሁለቱም ሴቶች የሚኖርህ ስሜት ተመሳሳይ ነው። ይህ ነው ስጋዊ ፈቃድ በውስጥህ ሞቷል የሚያሰኘው!
እንደኔ መሰረታዊ ሰው የመሆን ደረጃዎችን ያልጨረሰ እና በስጋዊ ፍትወት በሚሰቃይ ሰው፡ እንደዚህ መለኮታዊ የሚመስል ነገር ሲያወራ እና ሲፃፍ ሲገኝ ሊያስገርም ይችላል፤
ነገሩን የኃሊት ለተመለከተው ታሪክን ላነበበ ሰው ግን እንደ ሐገር መሰረታዊ እሳቤዎቻችን የተሰሩት ከላይ ባነሳኃቸውና መሰል አውነት ላይ መሆኑን ይታዘባል፤
ልክ እንጀራን ለመጋገር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ነገሮችን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ሊያውቀው እንደሚችለው ሁሉ፡ የጥንት ኢትዮጵያውያን ከላይ ለእንዳነሳሁት አይነት መንፈሳዊ እዉነቶች እንግዳ አልነበሩም። ለኛ ትውልድ ነው ነገሩ ሩቅ የሆነብን።
Blogger Comment
Facebook Comment