✍ መንግሥቱ ጎበዜ
ወቅቱ የሱባኤ በመሆኑ ከዲጂታል መገናኛዎች በመጾም ለመታቀብ አስቤ የነበረ ቢሆንም፣ «የምክክር ኮሚሽን» ከተባለው አካል ጋር በተያያዘ እየተራገበ ያለውን ሀገራዊ አጀንዳ ከወዳጆቸ በመስማቴ ዕረፍት ስለነሳኝ ሐሳቤን እንደሚከተለው ለማካፈል ወደድሁ። ጾም የሚያሽር አጀንዳ!
ታሪክን፣ የስነ-ሕዝብ (ዲሞግራፊ) መረጃዎችን እንዲሁም ዓለም አቀፋዊ የሕግና የዲፕሎማሲ ሁኔታዎችን በጥልቀት ከተመለከትን፤ በኃይል ፍላጎትን ከመጫን ውጭ አዲስ አበባን የአንድ ወገን ወይም ቡድን ብቻ አድርጎ ለማቅረብ የሚደረግ ጥረት ብዙ ርቀት አያስኬድም። በመካከለኛው ዘመን በዐፄ ዳዊት "በርበራ" ተብላ ትጠራ የነበረችው አዲስ አበባና አካባቢዋ፣ በዘመናዊ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆና የተቆረቆረችውና የተደራጀችው በዐፄ ምኒልክና በኢቴጌ ጣይቱ አማካኝነት መሆኑ ይታወቃል።
የሕዝብ ስብጥርን በተመለከተ፣ የቅርቡን የ1999ኙን የሕዝብና የቤቶች ቆጠራ መረጃ እንኳ ብንወስድ፤ አዲስ አበባን ለመዋጥ እያኮበከበ ያለው ቡድን አካሄድ ሕገወጥና ዲሞክራሲያዊ እንዳልሆነ አመላካች ነው። ዲሞክራሲ ማለት የሕዝብ ውክልና ከሆነ፣ በአዲስ አበባ ጉዳይ ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር ያለው ማን እንደሆነ ግልጽ ነው። ድምሩን ብንወስድ እንኳ ከ80% በላይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን፣ ከ20% ባነሰ የሕዝብ ቁጥር ሊዋጡና ሊመሩ የሚችሉበት አሰራር በየትም ዓለም የለም።
• የብሔር ስብጥር፦ አማራ (47.0%)፣ ኦሮሞ (19.5%)፣ ጉራጌ (16.3%)፣ ትግራይ (6.2%)፣ ስልጤ (2.9%)፣ ጋሞ (1.7%)፣ ሌሎች (6.4%)፤
• የሃይማኖት ስብጥር፦ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ (74.7%)፣ እስልምና (16.2%)፣ ፕሮቴስታንት (7.7%)፣ ካቶሊክ (0.8%)፣ ሌሎች (0.6%)፤
• የእናት ቋንቋ አጠቃቀም፦ አማርኛ (71.0%)፣ ኦሮምኛ (10.7%)፣ ጉራጊኛ (8.4%)፣ ትግርኛ (3.6%)፣ ሌሎች ቋንቋዎች (6.3%)።
በአጠቃላይ ከዲሞግራፊ፣ ከታሪክና ከሕግ አኳያ ሲገመገም፦
1. አዲስ አበባ የነዋሪዎቿ ናት፦ ግብር ከፍለው፣ ሰርተውና ሀብት አፍርተው በሚኖሩት በሁሉም ነዋሪዎቿ የጋራ ባለቤትነት የምትመራ መሆን ይኖርባታል።
2. አዲስ አበባ የመላው ኢትዮጵያውያን ናት፦ የኢፌዴሪ ዋና ከተማና የሁሉም ዜጎች መገናኛ በመሆኗ የሀገሪቱ የጋራ ሀብት ናት።
3. አዲስ አበባ የአፍሪካ ማዕከል ናት፦ የአፍሪካ ሕብረትና የበርካታ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች መቀመጫ በመሆኗ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷ ሊጠበቅ ይገባል።
ስለሆነም በኢፌዴሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 49 መሠረት "ልዩ ጥቅም" የሚለውን ቀልድና እንቶፈንቶ አስወጥቶ አዲስ አበባ የፌደራሉ መንግሥት ዋና ከተማና ራሷን በራሷ የምታስተዳድር የራስ-ገዝ አካል መሆኗን አክብሮ መቀበል የተሻለው መንገድ ነው። ከዚህ ውጭ አዲስ አበባን ለአንድ የተወሰነ ስብስብ አሳልፎ በመስጠት ሌላውን ነዋሪ እንደ መጤና እንግዳ መቁጠር ተቀባይነት የሌለውና ዘላቂ ሰላምን የማያመጣ አካሄድ ነው። በኃይል የቡድን ፍላጎትን ለጊዜው መጫን ቢቻል እንኳ፣ ይዋል ይደር እንጂ ማንም መብቱንና ሀገሩን ተቀምቶ ዝም እንደማይል መገንዘብ ያስፈልጋል። አዲስ አበባን ለመሰልቀጥ እያሰበ ያለው ስብስብ፤ አዲስ አበባን፣ ሐዋሳን፣ ድሬዳዋንና መሰል ከተሞችን ከነዋሪዎቻቸው ቀምቶ በሂደት ሀገር የመፍጠር ቅዠት እንዳለው የሚያመላክቱ ነገሮች አሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ "በምክክሩ" ወቅት ነባር ሀገራዊ ዕሴቶችንና የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አሻራዎችን ለመደምሰስ ዓላማ ያደረጉ ሐሳቦች የተንጸባረቁበት መሆኑም ተሰምቷል። ከእነዚህም መካከል፦የሃይማኖት በዓላት ቁጥር ይቀነስ፤ የአደባባይ በዓላት ቀርተው በቤተክርስቲያን ቅጽር ግቢ ብቻ ተወስነው ይከበሩ፣ እሁድ የእረፍት ቀን መሆኑ ቀርቶ በአርብ ይተካ፣ የዘመን አቆጣጠሩ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ስለሆነ ይቀየር፣ የክርስቲያን ስም የያዙ የቦታ ስያሜዎች ይቀየሩ፣ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ይዞታ ሥር የሚገኙ ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ቅርሶችን ለመጠበቅ የሚደረገው መንግሥታዊ ድጋፍ ይቁም፤ ወዘተ የሚሉ ይገኙበታል። ጉድ እኮ ነው!
የሚገርመው፣ «የምክክር ኮሚሽን» ተብዬው ሰብሳቢ፤ "ምክክሩ" ሐሳብ ለማቅረብ እንጂ ውሳኔ ለመስጠት እንዳልሆነ ግልጽ አድርገዋል። በተጨማሪም ከተያዙት ስምንት አጀንዳዎች መካከል "ምክረ-ሐሳብ" እንኳ ሳይሰጥባቸው በይደር የሚቆዩና ለትውልድ ሊሸጋገሩ የሚችሉ እንደሚኖሩ በመጠቆም፣ ለዓመታት የባከነው የሕዝብ ሀብት ውኃ የበላው መሆኑም ታውቋል። ድንቄም የምክክር ኮሚሽን! ኢትዮጵያ ሆይ ጽናቱን ይስጥሽ!!!
Blogger Comment
Facebook Comment