✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር
ሰሞኑን አህ*መዲን ጀ*በል የተባለ ሰው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ሲያጣጥጥል እያየሁ በጣም እየገረመኝ ነበር:: "አይጥ ዝሆንን አክላለሁ ብላ ፈንድታ ሞተች" ብለው ምሳሌ የሚናገሩ አባቶቻችን ምንኛ እውነተኞች ናቸው! ደግሞ የሚጽፈው ጽሑፍ አማርኛ ሆኖ እንኳን ከቀኝ ወደ ግራ የተጣመመ ነው:: በመጀመሪያ ይህ ሰው ተልእኮ ያለው ሲሆን ከብልጽግና ጋር ሆኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ተግቶ የሚሰራ ነው:: ለሀገራችን ኢትዮጲያና ለኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ጠላቶች አሳልፈው ለመስጠት ቃልኪዳናቸውን ለመፈጸም የጥፋት መንገዳቸውን የጀመሩ መሆናቸውን በሚገባ እናውቃለን:: ይህ ሰው ነግቶም መሽቶም ከቤተክርስቲያን ላይ እጁን ሊያነሳ አልቻለም:: በቤተክርስቲያን ላይ ለሚደርሱት ጥፋቶች ሁሉ በተዘዋዋሪ መልኩ እጁ እንዳለበት እንዳትጠራጠሩ! ለማንኛውም ሰሞኑን ለሚናገራቸው አንጃ ግራንጃዎች ህጻናት ልጆች ቢመልሱለትም ክርስትና እንደ ሌሎቹ የሃይማኖት ድርጅቶች መጤ እንዳልሆኑ አጭር መልእክት ለማስተላለፍ እወዳለሁ::
ኢትዮጵያ ክርስትናን ከመቀበሏ ክፍለ ዘመናት በፊት ባዶ የጣዖት አምላኪ ሀገር አልነበረችም። ይልቁንም ከአብርሃም፣ ከሙሴና ከንግሥተ ሳባ ዘመን ጀምሮ የነበረውን የብሉይ ኪዳን የአንድ አምላክ አምልኮ ትከተል የነበረች ሀገር ናት። መጽሐፍ ቅዱስም ስለ ኢትዮጵያውያን የብሉይ ኪዳን እምነትና ቅድስና በርካታ ማስረጃዎችን ይሰጣል። የልዑል እግዚአብሔር ካህን የነበረው መልከ ጼዴቅ እንዲሁም በብሉይ ኪዳን ታሪክ ውስጥ ታላቅ መንፈሳዊ ቦታ የነበረው አቤሜሌክ (ነቢዩ ኤርሚያስን ከጉድጓድ ያወጣውና በእግዚአብሔር ዘንድ የታመነው ኢትዮጵያዊ) ኢትዮጵያውያን ገና ከጥንት ጀምሮ የእውነተኛው አምላክ አገልጋዮችና ቅዱሳን እንደነበሩ ያሳያሉ። በትንቢተ አሞፅ ፱፥፯ ላይ እግዚአብሔር በነቢዩ አማካኝነት "የእስራኤል ልጆች ሆይ እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላችሁምን?" ብሎ የተናገረው በወቅቱ እስራኤላውያንን ከኢትዮጵያውያን ጋር በማወዳደር ኢትዮጵያውያን በብሉይ ኪዳን እምነታቸውና በመታዘዛቸው ለእግዚአብሔር ይበልጥ ይመቹ የነበሩ እውነተኛውን አምላክ ያመልኩ የነበሩ ሕዝቦች ስለነበሩ ነው። ይህን ጥቅስ ላስተዋለው ሰው በእግዚአብሔር ዓይን ኢትዮጵያውያን ምን ያክል የከበሩ እንደሆኑ ግልጽ አድርጎ ያሳያል! በተጨማሪም በዘኍልቍ ፲፪፥፩ ላይ የሕግ መሪው ነቢዩ ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ሲፓራን ማግባቱ ትልቅ የብሉይ ኪዳን ማስረጃ ነው፤ ምክንያቱም በኦሪት ሕግ መሠረት እስራኤላውያን የባዕድ አምላክ የሚያመልኩትንና አሕዛብ የሆኑትን ማግባት በጥብቅ የተከለከለ ስለነበር። ሙሴ ኢትዮጵያዊቷን ያገባው ኢትዮጵያውያን በወቅቱ ተመሳሳይ የአንድ አምላክ (የብሉይ ኪዳን) እምነት ይከተሉ ስለነበር ነው። በመዝሙረ ዳዊት ፷፰፥፴፩ ላይ የተጻፈው "ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ታዘረጋለች" የሚለው ትንቢትም ኢትዮጵያውያን ሁልጊዜም ቢሆን አምልኮታቸውንና ጸሎታቸውን ወደ እውነተኛው አምላክ ያቀረቡና የሚያቀርቡ ሕዝቦች መሆናቸውን ያረጋግጣል። ይህ የመዝሙረኛው ዳዊት ስለ ኢትዮጵያ የተናገረው ቃል ኢትዮጵያ ልዩ እንደሆነች የቅዱሳን ሀገር እንደሆነች ለምንናገረው ፍጹም የሆነ ምስክር ነው:: እስራኤል እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች አላለም፤ አያችሁ ኢትዮጵያ ነው ያለው! መታደል ነው! የተዋህዶ ልጆች ሆይ ጠላት እንዴት አይቀናብንም ብላችሁ ታስባላችሁ?
ኢትዮጵያ የብሉይ ኪዳንን ሕግና ሥርዓት በሃይማኖቷ ብቻ ሳይሆን በባህሏና በዕለት ተዕለት ሕይወቷ ውስጥ በጥልቀት የተከለች ሀገር ናት። በሰሜን ኢትዮጵያ (በተለይም በአክሱም፣ በየሐ፣ በላሊበላና በጣና ሐይቅ ዙሪያ) በርካታ ኮረብታማና ተራራማ ቦታዎች የብሉይ ኪዳን የኦሪት መስዋዕት ይሠዋባቸው የነበሩ ቦታዎች ናቸው። እንደ አብርሃምና እንደ ሙሴ ሁሉ ኢትዮጵያውያንም በየኮረብታው ላይ መሠዊያ እየሠሩ ለእግዚአብሔር መስዋዕት ያቀርቡ የነበረ ሲሆን በጣና ቂርቆስና በብርካታ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ተራራማ ቦታዎች የሚገኙት የኦሪት መስዋዕት ማቅረቢያ ድንጋዮችና የመስገጃ ኮረብታዎች እስከዛሬ ድረስ የሚገኙ ቁሳዊ ማስረጃዎች ናቸው። አብዛኛዎቹ ጥንታዊ ገዳማት የተገነቡት በእነዚያ ቅዱስ ስፍራች ላይ ነው:: በንግሥተ ሳባና በንጉሥ ሰሎሞን ዘመን ታቦተ ሕጉ (ታቦተ ጽዮን) ወደ አክሱም መምጣቱ ደግሞ ሀገሪቱን በሰፊው የብሉይ ኪዳን እምነትና ሕግ ዋና ማዕከል አድርጓታል። የሕዝቡ የአመጋገብና የአለባበስ ሥርዓትም የዚሁ ሕግ መገለጫ ነው፤ ኢትዮጵያውያን የሚመገቡት የእንስሳት ዓይነት በኦሪት ዘሌዋውያን ምዕራፍ ፲፩ ላይ ከተጠቀሰው የንጹሕና የርኩስ እንስሳት ሕግ (እንደ በግ፣ በሬ፣ ፍየል መብላትና እርያ አለመብላት ወዘተርፈ ) ጋር ሙሉ በሙሉ አንድ ሲሆን ባህላዊው ነጭ ልብስና ነጠላ ማጣፋትም የኦሪት ካህናትና ምእመናን የንጽሕና ሥርዓት መገለጫ ነው። አጠቃላይም የኢትዮጵያ የአለባበስ ስርዓት ቀጥታ ብሉይ ኪዳናዊ ነው:: ሌላው ቀርቶ ኢትዮጵያ አጠቃላይ ሽታዋ ብሉይ ኪዳን ነው! ታቦትን በካህናት እሸክም ማውጣት፣ ዝማሬው እልልታና ከበሮ፣ ቅዳሜና እሑድ ሰንበትን አክብሮ መጠበቅ ሁሉ ንጉሥ ዳዊት በታቦተ ሕጉ ፊት ይዘምር የነበረውን የብሉይ ኪዳን ሥርዓት (፪ኛ ሳሙኤል ፮) ቀጥታ የሚያሳይ ነው።
ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን ስንሸጋገር የአህዛብ ሀገራት አጠቃላይ ከኢትዮጵያና ከእስራኤል ውጭ ያሉት (ጣዖት አምላኪ የነበሩ) ክርስትናን ሲቀበሉ የነበሩትን የጣዖት ምስሎች ሰብረው አዲስ እምነት ከባዶ በመጀመር የተቀበሉ ሲሆን ኢትዮጵያ ግን ከብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን በተደረገ ቀጥተኛ መንፈሳዊ ሽግግር ነው ክርስትናን የተቀበለችው። በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፰ ላይ የተጠቀሰው የኢትዮጵያ ንግሥት ሕንደኬ ጃንደረባ ወደ ኢየሩሳሌም ሄዶ ይሰግድ የነበረው ኢትዮጵያ አስቀድማ የብሉይ ኪዳን እምነት ተካፋይ ስለነበረችና የክርስቶስን መምጣት በጉጉት ትጠባበቅ ስለነበር ነው። ጃንደረባው በሰረገላው ላይ ሆኖ ያነብ የነበረው በራሱ ቋንቋና ፊደል የተቀዳውን የነቢዩ የኢሳይያስን መጽሐፍ መሆኑ በወቅቱ የነበረውን የጽሑፍ፣ የቋንቋና የትምህርት እድገት ያሳያል። ጃንደረባው ሲያነበው የነበረ ኢትዮጵያውያን ሲጠብቁት የነበረውን ትንቢት ነበር:: ይህም እንዲህ ይላል:- "ተጨነቀ ተሣቀየም አፉንም አልከፈተም፤ ለመታረድ እንደሚነዳ ጠቦት በሸላቾቹም ፊት ዝም እንደሚል በግ እንዲሁ አፉን አልከፈተም።" ኢሳ. ፶፫፥፯ ይህን ስለ ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተንገረውን ትንቢት ሲያነብ የነበረ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ የጌታችንን መምጣት (መወለድ) በተስፋ ስትጠብቅ እንደነበረ ያሳያል:: ያኔም ጃንደረባው አዲስ ሃይማኖት ፈጥሮ ወይም ይዞ የመጣ ሳይሆን ኢትዮጵያውያን አስቀድመው ያውቁት የነበረውን የነቢያቱን ትንቢትና የመሲሑን መምጣት ተስፋ በሐዋርያው ፊልጶስ አማካኝነት መፈጸሙን ተረድቶ ተጠመቀ፤ ወደ ሀገሩም ተመልሶ የክርስቶስን መወለድ፣ መሰቀልና መነሳት የምስራች አበሰረ። ይህ ታሪክ የሚያሳየው ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ በውጭ ኃይል ወይም በባዕድ አካል ተጭኖ ሳይሆን አስቀድሞ በነበረው የብሉይ ኪዳን እምነትና ተስፋ ላይ የተመሠረተ ሽግግር መሆኑን ነው። ትንቢቱ መፈጸሙን ምስክር ሆኖ መጣ አበሰረ እንጅ አዲስ ሃይማኖት እኛ የማናውቀውን እንግዳ ትምህርት አላመጣም! ይህ የሚያስብ አእምሮ ያለው ሰው በቀላሉ ሊረዳው የሚችል በጣም ቀላል ጉዳይ ነው:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእውነት መንገድ ስለሆነች የሚቀኑባት ጠላቶቿ ባይቀበሉትም እውነታው ይህ ነው:: ይልቁንስ የነፍስ ጉዳይ ስለሆነ እውነትን መርምራችሁ ከጥፋት ተመለሱ ወደዚች እውነተኛ የብርሃን መንገድ ወደሆነች ወደ ብቸኛዋ የመንግስተ ሰማያት መግቢያ በር ኑ!
በ1ኛው ክፍለ ዘመን በጃንደረባው የምስራች አበሳሪነትና ምስክርነት መሠረት የተጣለው የሐዲስ ኪዳን እምነት እየተስፋፋ ሄዶ በአባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃንና በንጉሥ ኢዛና ዘመነ መንግሥት (በ፬ኛው ክፍለ ዘመን/፫፻፴ ዓ.ም) የሀገሪቱ የመንግሥት ሃይማኖት ሆኖ ታወጀ። ይህ የሆነው አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ገና በጣዖት አምልኮ ውስጥ በነበረበትና ክርስቲያኖችን ያሳድድ በነበረበት ዘመን ነው። በኋላም በ፭ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ከሮምና ከሶርያ የመጡት ዘጠኙ ቅዱሳን (አባ አረጋዊ፣ አባ ጰንጠሌዎን፣ አባ ገሪማ፣ አባ አፍጼ፣ አባ አሌፍ፣ አባ ጉባ፣ አባ ሊቃኖስ፣ አባ ጽሕማ፣ አባ ይስሐቅ/ገሪማ) ወደ ኢትዮጵያ የመጡት አህ*መዲን ጀ*በል እንደሚለው ለሀገሪቱ አዲስ እምነት ይዘው ሊመጡ ወይም ሊያስተምሩ አይደለም። ይልቁንም የኢትዮጵያን ታላቅ ቅድስና፣ የአንድ አምላክ አምልኮ መሠረትና መንፈሳዊ ሰላም ዝናንም ሰምተው በሀገሪቱ ቅድስና ተሳብበው ለመባረክና በዚህ ለመኖር ፈልገው ነው። መጻሕፍትን ወደ ግእዝ በመተርጎምና ገዳማትን በመሥራት የነበረውን እምነት አበለጸጉት እንጂ አዲስ እምነት አላመጡም። በመሆኑም ኢትዮጵያ በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ "ምድራዊቷ ብሔረ ሔዋን" (የቅዱሳንና የጸሎት ምድር) በመባል የምትታወቅ ሲሆን በጥንት ዘመንም ሆነ በአሁኑ ዘመንም በዓለም ዙሪያ ያሉ ቅዱሳን አባቶችና ባሕታውያን በረቂቅና በመንፈስ የሚሰበሰቡባትና የሚያመልኩባት የተቀደሰች ምድር ናት።
"የክርስትና ሃይማኖት በኢትዮጵያ መጤ ነው" የሚለው አባባል የታሪክ፣ የአርኪኦሎጂና የሃይማኖት እውነታዎችን ካለመገንዘብ እንዲሁም ከበታችነትና ከጥላቻ ስሜት የሚመጣ የተሳሳተ ትርክት ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የጊዜ ቀዳሚነትን ስንመለከት የሐዲስ ኪዳን እምነት መያያዝ የጀመረው በ፩ኛው ክፍለ ዘመን በጃንደረባው ምስክርነት ሲሆን የመንግሥት ሃይማኖት የሆነው ደግሞ በ፬ኛው ክፍለ ዘመን ነው፤ ይህም በ፯ኛው ክፍለ ዘመን (በ ፮፻፲-፮፻፳፪ ዓ.ም አካባቢ) ከተመሠረተው የእስልምና ሃይማኖት አመሠራረትና ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቱ በበርካታ ክፍለ ዘመናት የሚቀድም ታሪክ ያለው ነው። በታሪክ፣ በዘመናት ስሌትና በአስተምህሮ ይዘት እጅግ ዘግይቶ በ፯ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳ እምነት ከክርስቶስ ልደት በፊት ጀምሮ በብሉይ ኪዳን አምልኮ የጸናችውንና በ፩ኛው ክፍለ ዘመን ሐዲስ ኪዳንን የተቀበለችውን የሺዎች ዓመታት ታሪክ ያላትን ጥንታዊት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን "መጤ" ብሎ ለማንቋሸሽ መሞከሩ እጅግ የሚያስቅ ነው! በዘመናት ረጅም እርቀትና በሥልጣኔ ቀዳሚነት ረገድ ይበልጥ ዘግይቶ የመጣ እምነት ጥንታዊቷንና ሀገር በቀሏን ቤተ ክርስቲያን የመተቸት ታሪካዊም ሆነ አርኪኦሎጂያዊ መሠረት የለውም። በተጨማሪም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የራሷ የሆነ ፊደል፣ ዜማ (ያሬዳዊ ዜማ)፣ የቀን አቆጣጠር ፣ ሕግ (ፍትሐ ነገሥት) እና ሥነ-ሕንጻ ያላት ሀገር በቀል ተቋም ናት፤ ኢትዮጵያም ክርስትናን የተቀበለችው በቅኝ ግዛት ወይም በውጭ ኃይሎች ተፅዕኖ ሳይሆን፣ ከብሉይ ኪዳን ወራሽነቷ በመነሳትና በፍቃደኝነት በመሆኑ እምነቱ የሀገሪቱ ብሔራዊ ማንነትና ሥልጣኔ መሠረት ሆኖ ኖሯል። ትክክለኛው መጤ ሃይማኖቶች ብለን የምንጠራቸው ከኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ውጭ የሆኑትን ነው:: የኢትዮጵያ ህዝብ ይመጣሉ ብሎ አልጠበቃቸውም በትንቢት በተስፋ አልጠበቃቸውም:: እነዚህ ሃይማኖቶች በእንግድነትና በልዩ ልዩ መልኩ ወደ ኢትዮጵያ ገብተው ተቀብለናቸዋል:: ከዚህ በዘለለ ሀሰቱን እውነት እውነቱን ሀሰት ብትሉ ነባራዊ እውነታው የሚቀየር አይደለም!
በአጠቃላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱ የታሪክ፣ የባህል፣ የሥልጣኔና የማንነት መሠረት እንጂ በምንም ዓይነት የታሪክና የሃይማኖት መስፈርት ወደ ሰማይ ብትወጡ ወደ ምድር ጥልቅ ብትወርዱ "መጤ" ልትባል አትችልም። ኢትዮጵያውያን ለበርካታ ዘመናት በብሉይ ኪዳን አምልኮ ኖረው ሐዲስ ኪዳንን በተስፋ ይጠብቁ ነበር እንጂ ክርስትና ከውጭ የተጫነባቸው ባዕድ እምነት አይደለም። የብሉይ ኪዳኑ መስዋዕት፣ የተራራዎች አምልኮ፣ የመልከ ጼዴቅና የአቤሜሌክ ቅድስና፣ የነቢዩ ሙሴ ጋብቻ፣ በርካታ የመዝሙረ ዳዊትና የነቢዩ አሞፅ ትንቢቶች፣ የጃንደረባው ምስክርነት፣ እንዲሁም የዘጠኙ ቅዱሳን ወደ ቅድስቲቱ ምድር መምጣት ወዘተርፈ ሁሉም የሚያረጋግጡት ኢትዮጵያ የኦሪትና የወንጌል ባለቤት መሆኗን ነው። ስለዚህ የኢትዮጵያ ክርስትና ሀገር በቀል ከጥንት አምልኮ የቀጠለና የታሪክ መሠረት ያለው እንጂ በምንም ዓይነት መንገድ መጤ ሊባል የማይችል ታላቅ መንፈሳዊ ውርስ ነው።
ኑ ወደ ብቸኛዋና እውነተኛዋ መንገድ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ፤ ኑ በብርሃኗ ተመላለሱ!
Blogger Comment
Facebook Comment