ይድረስ ለድሮናውያን



✍ መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) | ዮቶጵያ

ገዳማትን፣ መነኮሳትን፣ አብያተ ክርስቲያናትን፣ በጥቅሉ ክርስቲያኖችን ኾን ብሎ፡ በሃይማኖታቸው ምክንያት ማሰቃየት ወይም መግደል፡ በኢትዮጵያ ላይ ታላላቅ ቅዱሳን እንዲወለዱ ከማድረግ ውጪ፡ የእናንተን የማስለም ወይም የማመንፈቅ አጀንዳ የሚደግፍ ውጤት አያመጣምና፡ አትድከሙ።

ከዮዲት ጉዲት ጭፍጨፋ በኋላ፡ 300 ዓመት፡ የቅዱሳን ነገሥታትን (Prester John) ዘመን አየች እንጂ፡ ኢትዮጵያ አልሰለመችም፥ ወይም አልመነፈቀችም።

ከሞተሎሚ በኋላ፡ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና ሌሎች ብዙ ቅዱሳን ተወልደው ጠንቋዩን፣ ባለዛሩን፣ እስላሙን፣ አይሁዱን ኹሉ አጥምቀው ክርስቲያን አደረጉት እንጂ፡ ኢትዮጵያ አልሰለመችም፥ ወይም አልመነፈቀችም።

ከግራኝ ጭፍጨፋ በኋላ፡ ብዙ ቅዱሳን ከየበረሃው፥ ከየዋሻው ወጥተው ሕዝቡን እያጽናኑ በግልፅ ታዩ እንጂ፡ ኢትዮጵያ አልሰለመችም፥ ወይም አልመነፈቀችም።

አሁንም፡ ተቀናጅታችሁ በምትሠሩት ጥፋት፡ ልጆቻችሁን አጥምቀው ወደ ጥንቷ ቤታቸው፡  ወደ ፅዮን (ቅድስት ቤተክርስቲያን) የሚመልሱ ቅዱሳን በዝተው እንዲወለዱ ኺደቱን ታፈጥኑት ይኾናል እንጂ፡ "የሰለመች ወይም የመነፈቀች ኢትዮጵያ" አታዩም። ትንቢቱም የለም።

እንኳንስ አሁን ወይም ድሮ፥ ለወደፊትም ዓለሙን የሚያስተው ሐሳዌ መሢህ መጥቶ እምነትን ካጠፋ በኋላ እንኳ፡ ጌታ እንደተናገረው፡ ንግስተ ሳባ (የዐፄዎቹ እናት)፡ የክርስቶስን የባሕሪ አምላክነት ካልተቀበሉ ትውልዶች ጋር ስትፋረድ ትታያለች እንጂ፡ ምንፍቅና ወይም እስልምና አሸንፎ የሚታይበት ትንቢት የለም።

እና፡ ለምን ልታጠፉ የማትችሉትን መለኮታዊ እውነት ለማጥፋት ትደክማላችሁ? 

እንኳን ለእናንተ፡ ለእኛም አልተሳካልንም እኮ? ከእግዚአብሔር ጋር ለመዋጋት ያልሞከረ ጥጋበኛ የለም። እኛም እንደናንተ ያደርገናል አንዳንዴ። ገርፎ ወደመሥመር እየመለሰን እንጂ።

እና.... የምትጸድቁበትን በጎ ሥራ ብታስቡበት አይሻልም? 

ደግሞ ችግሩ፡ ከእናንተ መሃል፡ "በጎ ሥራ አያጸድቅም" ብሎ የሚያምነው ብዙ መኾኑ ነው። እንደምገምተው "ክፉ ሥራም አያስኮንንም" ብሎም ያምናል።

ምን ይሻላችኋል ግን? 

የCritical Theory ተንታኞች፡ ስለ oppressor እና oppressed ፖለቲካ ሲተነትኑ፡ "ብዙውን ጊዜ፡ ግፍ የሚሠሩ ሰዎች (oppressors)፡ ግፍ ከሚሠሩባቸው (oppressed) ይልቅ አደጋ ላይ ናቸው፤ ግን አያውቁትም" ይላሉ። ፕሮፌሰሮቼ እንዲህ ሲሉ መቀበል ይከብደኝ ነበር። አሁን ፍንትው ብሎ አየሁት። እውነትም አደጋ ላይ ናችሁ።

እግዚአብሔር ይኹናችሁ።

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment