✍ መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) | ዮቶጵያ
ገና ከጥንቱ፡ "ከልጅ ልጅህ ተወልጄ አድንሃለሁ" ብሎ ቃል ኪዳን ከገባበት ጊዜ አንሥቶ፡ "አምላክን ወልዳ ታድነናለች" ብሎ፡ ድንግል ማርያምን በተስፋ ሲጠባበቃት የኖረው፡ የሴም፣ የካም፥ የያፌት ድብልቅ ሕዝብ ያለባት አገር ናት።
አብያተ መቅደሶች በምድሪቱ መታነጽ ሲጀምሩ፡ 7500 ዓመት አለፋቸው።
ይኽ እንደመልከ ጼዴቅ ድብልቅ የኾነ አዳማዊ የአምላክ ሕዝብ፡ በዘመናት ሂደት፡ የአሁኗን ኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን፡ አብዛኛውን አፍሪካ እና የእስያ መካከለኛና ደቡብ ክፍሎች ጨምሮ የያዘ ሕዝብ ነው። ለዚህም ማረጋገጫ፡ በጄኔቲክ ጥናቶች እንደሚታየው፡ ከዚህ አዳማዊ የውሕደት የዘር ግንድ ጥንታዊ ዘረ መል ጋር የማይገናኝ የሰው ዘር የለም። "ኢትዮጵያውያን በጣም ጥንታዊ ዘረ መል አሁንም በሰውነታቸው ተሸክመዋል" ይላሉ - አጥኚዎች።
ይኽ አዳማዊ ሕዝብ፡ "እግዚአብሔር በሴም ድንኳን ይደር" የተባለውን ምርቃታዊ ትንቢት ወድዶና አፍቅሮ፡ የአብርሃምን ዘር በመውደድ፣ በመዛመድ፣ በመዋለድ፣ ርስታቸውን በመጠበቅና በማስጠበቅ፡ ከሴቲቱና ከመሢሁ ገብቶ የተቆጠረ ትውልድ ለመኾን በቅቷል።
ዲያቢሎስ፡ ኢትዮጵያዊውን የዓለም ሕዝብ የተዋጋው፡ በዘረኝነት ነው። በቅድሚያ፡ ነጩን የያፌት ዘር፡ "አንተ እኮ በኦሊምፐስ ተራራ ይኖሩ የነበሩ አማልእክት ዘር ነህ። እንዴት ከጠይም፣ ጥቁር፣ ቡኒ ሕዝብ ጋር ትቀላቀላለህ? ዘርህን አጥራ፤ አንተ እንደአማልእክት፡ ቆዳህ ነጭ፥ ዓይንህ ሰማያዊ፥ ጠጉርህ ቢጫ ነው። ይኽን ከምታጣ፡ እርስ በርስ ከቤተሰብ ተዋልደህም ቢኾን ዘርህን አስቀጥል" በማለት፡ ተቀላቅሎ መጠየምን እንዲጠየፍና የቆሸሸ እንዲመስለው በማድረግ፡ እስከ Nazi Aryan Race theory ድረስ ለዘለቀ ዘረኛ አስተሳሰብ አስተማቸው። የጥቁርን ሕዝብም ባርያ ማድረግ ሥራቸው መስሏቸው ቀረ።
የእስያን ሕዝብ ደግሞ፡ "እናንተ እኮ ቀይ ሕዝብ ናችሁ? ከአማልእክት የተቀዳችሁ፡ የተለየ መንፈሳዊ ዘሮች ናችሁ። በመንፈሳዊ ጥበብ እናንተን የሚተካከል የለም። እንዴት ከድብልቅልቅ ኢትዮጵያውያን ጋር ትቀላቀላላችሁ? እናንተ ጥቁር ፀጉራችሁ ረዥም፥ ቆዳችሁ ቀይ፥ የሴቶቻችሁ ወገብ እንደደራጎን መጥመልመል የሚችል ቀጭን፥ ባሕላችሁና አምልኮታችሁ እስከ ፀሓይና ጨረቃ የሚደርስ ነው። እርስ በርስ በቤተሰብ ውስጥ እየተጋባችሁም ቢኾን፡ ዘራችሁን አጥሩ" እያለ፡ አዳማዊውን ኢትዮጵያዊ የውሕደት ዘር እንዲጠሉ፥ ጥቁር ሕዝብን እንዲጠየፉ፥ "የጠራን ዘሮች ነን" ብለው እንዲኮፈሱ አድርጎ ጣዖታት ሥር ገተራቸው።
ጥቁሩን ሕዝብ ደግሞ፡ "እናንተ ጥቁሮች፡ የፀሐይ ኃይል በደማችሁ ያለ፡ የተለያችሁ ጠንካራ፡ ተፈጥሮ ብዙ ዓቅምና ችሎታ ያደለቻችሁ ሰፊ ሕዝቦች ናችሁ። እነዚህ አንዴ ጥቁር፥ አንዴ ቀይ፥ አንዴ ጠይም እየኾኑ ከሚዋለዷችሁ ኢትዮጵያውያን ጋር ምን ጉዳይ አላችሁ? እናንተ እኮ ኢትዮጵያውያን አይደላችሁም? አፍሪካውያን ናችሁ! ከዐረብ፥ ከፈረንጅ ከጥቁር እንደሁኔታው ከሚመሳሰል ድብልቅ ሐበሻ ጋር ምን ትሠራላችሁ?የነርሱ ዓላማ እኮ፡ ከቀያዮቹና ነጫጮቹ ጋር ተመሳጥረው እናንተን ባርያ አድርጎ መግዛት ነው? እናንተ ሙሉ ጥቁር ሕዝብ ናችሁ። ከግዛታችሁ ፈካ የሚሉትን አስወግዱ። እነሱ አቢሲንያውያን ናቸው" እያለ፡ እስከ ሩዋንዳው የቱትሲዎች ጭፍጨፋ ድረስ የዘለቀ የ"ሐበሽን ማጥፋት"ና በምትኹ የ"ንፁህ ኩሻዊነትን" የማስቀጠል ዘረኝነት አስተማራቸው።
እንዲህ አድርጎ፡ እግዚአብሔር በዳግማዊው አዳም፥ በአማናዊው መልከጼዴቅ በክርስቶስ ሰውነት ውስጥ አንድ ያደረገውን ኢትዮጵያዊ ዘር፡ መልሶ ወደ ሴም፣ ካም፣ ያፌት ዘረኝነት ከፈለው።
ከተዋሕዶ ውጭ የተመሠረቱ እምነቶች በሙሉ፡ ዲያቢሎስ፡ እንዲህ ላለ የዘረኝነት ፖለቲካ እንዲመቸው የፈጠራቸው ናቸው። ሃይማኖት ፖለቲካ ነው፤ ፖለቲካም ሃይማኖት ነው። ካቶሊክን ለነጩ ሕዝብ ፈጠረለት። እስልምናን ለዐረቡ ፈጠረለት። ባሕላዊ እምነትን ለጥቁሩ ሰጠ። አይሁዶችን፡ ወደ እውነተኛዋ ፅዮን እንዳይመጡ፡ በሌላ ፅዮናዊነት ለከፋቸው። ተዋሕዶ፥ እውነተኛዋ አዳማዊ የዓለም ሕዝብ ሃይማኖት ግን፡ ኢትዮጵያዊነታቸውን መካድ በማይፈልጉ ኢትዮጵያውያን ተይዛ ቀረች።
ያሁኑ "እኔ ንፁሕ ኩሽ ነኝ"፥ "እኔ ንፁሕ ሴም ነኝ"፥ "እኔ ንፁሕ ያፌት/ጣልያን ነኝ" የሚያስብላቸው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች ጠብ፡ ራሳቸውን፡ ልክ እንደ ሌላው ዓለም፡ ከዚህ ኢትዮጵያዊ ዘርነት ለማውጣት የሚታገሉበት ኺደት የወለደው የመጨረሻው መፍጨርጨር ነው።
ግን፡ በእውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን፥ ነብር ዝንጉርጉርነቱን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?
የሚገርመው፡ አንድነቱን የሚጠሉት፡ በእግዚአብሔር ሥር ሲኾን እንጂ፡ ለዓመፃ ሲኾን ግን፡ ኹሉም ጽንፈኛ ብሔርተኞች ኅብረት ይፈጥራሉ።
ኦነግና ሻዕቢያ፥ ሕወኃትና ጀብሃ፥ ምንጥስና ምንጥስ፡ ኢትዮጵያዊነትን ለመዋጋት አንድ ላይ መቆም አይከብዳቸውም።
ማፍያና አልቃይዳ፣ አልሻባብና ሲ አይ ኤ፣ ቦኮ ሃራምና ኒዮ ናዚ... ለጥፋት ሲኾን የኾነ ቦታ ይገናኛሉ። መንገዱ አይጠፋቸውም።
በእግዚአብሔር ሥር በተዋሕዶ አንድ መኾን ግን፡ የሚገድላቸው ይመስላቸዋል።
እኛ ፅዮናውያን ግን፡ የምናውቀው ንጹሕ ዘር፡ የድንግልን ዘር ነው። ኢየሱስ ክርስቶስን ነው።
Blogger Comment
Facebook Comment