በዚህ ዓለም በእውነት መንገድ ላይ ያለ ሰው ሁሉ ዕጣ ፈንታው መነቀፍና መሰደድ ነው! በክርስትና ሕይወት ውስጥ በመልካም ሥራ መጽናት፣ እውነትን መመስከርና በትክክለኛው የሃይማኖት መስመር ላይ መጓዝ ሁልጊዜም ዋጋ የሚያስከፍል ጽዋ ነው። ከመጽሐፍ ቅዱስ መጀመሪያ ከዘፍጥረት ጀምሮ እስከ መጨረሻው የራዕየ ዮሐንስ መጽሐፍ ፍጻሜ ብንቃኝ እንዲሁም በቅድስት ቤተክርስቲያን ታሪክ ውስጥ እስከ ዛሬዋ ቀን ድረስ የተገለጠውና የማይታበለው ትልቅ እውነት ቢኖር በእግዚአብሔር ዘንድ ትክክለኛ፣ ታማኝና ፍጹም ሃይማኖታዊ የሆነ ሰው ሁሉ የዓለምን ጥላቻ፣ ነቀፌታ፣ ስድብና ስም ማጥፋት ሳይቀበል ያላለፈ ማንም የለም። ይህ ለምን እንደሚሆን ሁላችንም የምናውቀው ጉዳይ ሲሆን ይኸውም መልካም የሚሠራ ሰው እውነትንና በጎነትን እያበረከተ እንደሆነ የሚታወቀውና ትክክለኛ ማረጋገጫ የሚገኘው ነቃፊዎችና ተቃዋሚዎች ተነስተው በሀሰት ሲነቅፉትና ስሙን ሲያጠፉት ብቻ በመሆኑ ነው። ይህ ታላቅ የመከራና የክብር መደራረብ ታሪክ መነሻውን ያደረገው ገና በብሉይ ኪዳን ዘመን በሰው ልጅ ታሪክ መጀመሪያ ላይ ነው። ጻድቁ አቤል ለእግዚአብሔር ያቀረበው እውነተኛና መልካም መሥዋዕት በተቀበለለት ጊዜ በዘፍጥረት 4፥3-8 ላይ እንደተጻፈው ወንድሙ ቃየን በቅናትና በክፋት ተሞልቶ በሜዳ ላይ ገደ*ለው። ይህ በቅንነትና በመልካም ሥራ ምክንያት የመነቀፍና የመሰደድ የመጀመሪያው የታሪክ መነሻ ነው።
ከዚያም በኋላ የተነሱት የእግዚአብሔር ነቢያት በሙሉ ማለት ይቻላል በእውነት ቃልነታቸው ምክንያት በሰዎች ዘንድ አልተወደዱም፤ ይልቁኑ ተንቀዋል፣ ተሰድበዋል፣ በግፍም ተሰደዋል። ነቢያቱ የእግዚአብሔርን ሕግ ይዘው ገዥዎችንና ነገሥታትን በድፍረት ሲገሥጹ ሕዝቡ ግን ከመሪዎቻቸውና ከነገሥታቱ ጎን በመቆም የእግዚአብሔርን ሰዎች ያጣሏቸው፣ ያሳድዷቸውና አሳልፈው ይሰጧቸው ነበር። ነቢዩ ኤልያስ የጣዖት አምላኪዎችንና የነገሥታቱን ሐሰተኝነት አጋልጦ እውነተኛውን አምልኮ በመመለሱ ምክንያት በ1ኛ ነገሥት 19፥1-4 እንደምናገኘው በንግሥት ኤልዛቤል ዛቻና በሕዝቡ መገለል ነፍሱን ለማዳን ወደ ምድረ በዳ ተሰደደ፤ በዚያም በነቀፌታው ብዛት የተነሳ «አቤቱ አሁን ይበቃኛል እኔ ከአባቶቼ አልበልጥምና ነፍሴን ውሰድ» ብሎ እስኪጸልይ ድረስ ተጨንቆ ነበር። እንዲሁም ደግሞ «የልቅሶው ነቢይ» እየተባለ የሚጠራው ኤርምያስም ነገሥታቱንና ሕዝቡን ንስሐ እንዲገቡ በመገሰጹና የእግዚአብሔርን እውነት በመናገሩ ምክንያት በኤርምያስ 20፥1-2 ላይ እንደተጠቀሰው የካህናቱ አለቃ ፋስኮር እንዲደበድቡትና በኢየሩሳሌም በምትገኘው በላይኛው በቤንያም በር እንዲያስሩት አድርጎ ነበር። እርሱም መራራውን ስደትና መነቀፍ ሲገልጽ በኤርምያስ 20፥7-8 ላይ «ቀኑን ሙሉ መሳቂያ ሆኜአለሁ፥ ሁሉም ይዘብቱብኛል ...የእግዚአብሔር ቃል ቀኑን ሙሉ መሳደቢያና መሳለቂያ ሆኖብኛልና» ብሏል። አልፎ ተርፎም በኤርምያስ 38፥4-6 መኳንንቱና ሕዝቡ በትክክለኛው ምክሩ ተቆጥተው «ይህ ሰው የዚህን ሕዝብ ክፉ እንጂ መልካሙን አይፈልግም» በሚል የሐሰት ክስ ከንጉሡ ጋር አጣልተውት ውኃ በሌለበትና ጭቃ በሞላበት ጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ በገመድ አውርደው ጥለውታል። በተመሳሳይ መልኩ ነቢዩ አሞጽ እውነትን በመናገሩ ምክንያት በአሞጽ 7፥10-13 ላይ በሐሰት ተከሶ «ባለ ራእይ ሆይ ሂድ ወደ ይሁዳ ምድር ሽሽ» ተብሎ በነገሥታቱና በሕዝቡ መሪዎች ተንቆ ከአገሩ ሲሰደድ ነቢዩ ሚክያስ ደግሞ በ1ኛ ነገሥት 22፥24-27 እግዚአብሔር የገለጠለትን እውነት ብቻ በመናገሩና ንጉሡን በመገሠጹ ምክንያት ጉንጩን ተመትቶ በመከራ እንጀራና ውኃ እንዲቀጣ ወደ ወህኒ ቤት ተጥሏል። በ2ኛ ዜና መዋዕል 24፥20-21 የካህኑና የነቢዩ የዘካርያስ ታሪክም ሕዝቡ ከክፉው ንጉሥ ጋር በማበር ስለ መተላለፋቸው በገሠጻቸው ጊዜ በእግዚአብሔር ቤት አደባባይ መካከል በድንጋይ ወግረው እንደ*ገደሉት ይነግረናል። እነዚህን ቅዱሳን ነቢያት በሙሉ የዓለም ክፋት እንዴት እንዳሰቃያቸው ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በዕብራውያን 11፥36-38 ላይ ሌሎችም መዘበቻ በመሆንና በመገረፍ ከዚህም በላይ በእስራትና በወኅኒ ተፈተኑ በድንጋይ ተወግረው ሞቱ ተፈተኑ በመጋዝ ተሰነጠቁ በሰይፍ ተገድለው ሞቱ ሁሉን እያጡ መከራን እየተቀበሉ እየተጨነቁ የበግና የፍየል ሌጦ ለብሰው ዞሩ ዓለም አልተገባቸውምና በምድረ በዳና በተራራ በዋሻና በምድር ጕድጓድ ተቅበዘበዙ" በማለት ይገልጸዋል። ሐዋርያት ሥራ 7፥52 ላይ አይሁድን «ከነቢያትስ አባቶቻችሁ ያላሳደዱት ማን ነው? የጻድቁንም መምጣት አስቀድመው የተናገሩትን ገደሏቸው» በማለት የነቢያትን የስደትና የመነቀፍ ታሪክ የእውነተኛነታቸው ማኅተም አድርጎ አቅርቦታል።
ይህ የመነቀፍ፣ የስድብና የስም ማጥፋት ጽዋ ትልቁንና ፍጹሙን ምሳሌነቱን ያገኘው ግን ራሱ በፈጣሪያችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው:: እርሱ ፍጹም ኃጢአት የሌለበት እውነት፣ ፍቅርና ብርሃን ሆኖ ሳለ የዘመኑ ሰዎች ትክክለኛ ትምህርቱንና አምላክነቱን በክፉ ልባቸው ሳይቀበሉ ቀርተው የስም ማጥፋት ዘመቻ ከፈቱበት። በዮሐንስ 8፥48 ላይ «ጋኔን አለበት» አሉት፤ ድንቅ ተአምራት ሲያደርግና ሰዎችን ከደዌና ከበሽታ ሲፈውስ በማቴዎስ 9፥34 ላይ «በአጋንንት አለቃ በብዔል ዜቡል አጋንንትን ያወጣል» እያሉ ቅዱስና ሰማያዊ ሥራውን ሲያቃልሉ ነበር:: በላተኛና የወይን ጠጅ ጠጪ የኃጢአተኞችና የቀራጮች ወዳጅ እያሉ ስሙን አጠፉት። ሕዝቡም ከሮም ገዥዎችና ከካህናት አለቆች ጋር በማበር የእውነትን ጌታ ሰቅለው ህዝቡም የነፍሰ ገዳዩን የበርባንን መፈታት መረጡ። አሁን ያለነው ትውልድ ብንሆን አስቡት! ከመስቀል በላይ ሌላ ነገር ቢኖር የባሰ ነበር የምናደርገው:: ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከመወለዱ ጀምሮ በንጉሥ ሄሮድስ ምቀኝነትና ክፋት ምክንያት ወደ ግብፅ ምድር የተሰደደው በአደባባይም ያለ በደሉ ተገርፎ ፊቱ ላይ ተተፍቶበትና ተሰድቦ በመጨረሻም ህይወቱን ለእኛ ቤዛ አድርጎ በመስቀል ላይ ተሰቀለ።
ጌታችን አምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እውነተኛ እረኞች የእርሱ መልእክተኞች በሰው ዘንድ እንደሚሰደቡ ሲነግረን በማቴዎስ 5፥12 ላይ እንዲህ ብሎናል! «ደስ ይበላችሁ ሐሴትም አድርጉ ዋጋችሁ በሰማያት ታላቅ ነውና፤ ከእናንተ በፊት የነበሩትን ነቢያትን እንዲሁ አሳድደዋቸዋልና» በማለት የተከተሉት ሁሉ ይህንን መንገድ እንዲጠብቁት አስተምሯል።
ጌታን የተከተሉ ቅዱሳን ሐዋርያትም ያረፉት በዚህ በክርስቶስ የስደትና የመነቀፍ ጎዳና ላይ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ በ1ኛ ቆሮንቶስ 4፥9-13 ላይ የሐዋርያትን ስለ ክርስቶስ ወንጌል ብሎ ስለ መከራ መቀበል፣ መገለል እና ትሕትና የሚያወሳ ድንቅ መልእክት አስቀምጧል:: «እኔ እንደማስበው እግዚአብሔር እኛን ሐዋርያትን እንደ ሞት የተፈረደብን ሰዎች አድርጎ በመጨረሻ አስቀመጠን፤ እኛ ለመላእክትና ለሰዎች ዓለም ማሳያ ሆነናል። እኛ ስለ ክርስቶስ ብለን ሞኞች ነን፤ እናንተ ግን በክርስቶስ ብልሃተኞች ናችሁ፤ እኛ ደካሞች ነን፥ እናንተ ግን ብርቱዎች ናችሁ፤ እናንተ የተከበራችሁ ናችሁ፥ እኛ ግን የተናቅን ነን። እስከዚህ ሰዓት ድረስ እንራባለን፥ እንጠማለን፥ እንራቆታለን፥ እንደበደባለን፥ እንሰደዳለን፤ በእጃችን እየሠራን እንደክማለን፤ ሲሰድቡን እንመርቃለን፤ ሲያሳድዱን እንታገሣለን፤ ሲያሙን በለዘብተኛ ቃል እንመልሳለን፤ እስከ አሁንም እንደ ዓለም ቆሻሻ፥ የሁሉ መጣያ ሆነናል » በማለት በዓለም ፊት የተናቁና የትገፉ መሆናቸውን ይናገራል። በሐዋርያት ሥራ 5፥40-41 ላይም አይሁድ ሐዋርያትን አግኝተው በግፍ ከገረፏቸውና በኢየሱስ ስም እንዳይናገሩ ካዘዟቸው በኋላ እነርሱ ግን ስለ ስሙ ይናቁ ዘንድ የተገባቸው ሆነው ስለ ተቆጠሩ ከሸንጎው ፊት ደስ እያላቸው ወጥተዋል። ቅዱስ ጴጥሮስና ቅዱስ ዮሐንስ ሽባ የነበረውን ሰው በጌታ ስም ፈውሰው ፍጹም በጎ ሥራ ሲሠሩ ሕዝቡ ከሃይማኖት መሪዎቹ ጋር በማበር ሕዝቡን ስላስተማሩና ትክክለኛውን ትምህርት ስለሰበኩ ተበሳጭተው ወስደው በወህኒ ጥለዋቸዋል:: ሐዋ. 4፥1-3 እንዲሁም ደግሞ ንጉሥ ሄሮድስ አግሪጳ ቤተክርስቲያንን ለማሳደድ እጁን ዘርግቶ ሕዝቡን ደስ ለማሰኘት ሲል ጴጥሮስን በወህኒ ቤት ዘጋው። ሐዋ 12፥ 1-19
የቅዱስ ጳውሎስም ስደትና መነቀፍ ወደር አልነበረውም። በ2ኛ ወደ ቆሮንቶስ 11፥ 23-24 ላይ «...በድካም አብዝቼ በመገረፍ አብዝቼ በመታሰር አብዝቼ በሞት ፊት ብዙ ጊዜ ሆንሁ። ከአይሁድ አርባ ግርፋት አንድ ሲጎድል አምስት ጊዜ ተገረፍሁ» በማለት ይገልጻል። በየሐዋርያት ሥራ 14፥19 ላይ አይሁድና ሕዝቡ ተባብረው በድንጋይ ወግረውት የሞተ መስሏቸው ከአገር ውጭ ሲጎትቱት እንዲሁም ደግሞ በሐዋርያት ሥራ 16፥22-24 ደግሞ በፊልጵስዩስ ከተማ መልካም ሲያደርግ መኳንንቱና ሕዝቡ በአንድነት ተነስተው ልብሱን ቀደው በበትር ገረፉትና ወደ ወህኒ ጥለውታል።
የመጀመሪያው ዲያቆንና ሰማዕት ቅዱስ እስጢፋኖስም በጸጋና በኃይል ተሞልቶ ድንቅ ሥራዎችንና ተአምራትን በሕዝቡ መካከል ሲያደርግ ሰዎቹ ግን ከነገሥታትና ከፈሪሳውያን ጋር በማበር በትክክለኛ ትምህርቱ ተቆጥተው «በሙሴ ላይ በእግዚአብሔርም ላይ የስድብን ነገር ሲናገር ሰምተነዋል» ሐዋ. 6፥11-13 የሚሉ የሐሰት ምስክሮችን አቁመው ስሙን አጠፉት በመጨረሻም በሐዋርያት ሥራ 7፥57-59 ላይ እንደተጠቀሰው በአንድ ልብ ሆነው ጆሯቸውን ደፍነው ከአገር ውጭ አውጥተው በድንጋይ ወግረው ገድለ*ውታል። የዮሐንስ ወንድም ያዕቆብም በንጉሥ ሄሮድስ እጅ በሰይፍ ተሰይፎ ሰማዕት ሆኗል። ሐዋ. 12፥1-2
ከሐዋርያት በኋላ የተተኩት እንደነ ቅዱስ አትናቴዎስና ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያሉ የቤተክርስቲያን አባቶችና ሊቃውንትም ነገሥታቱንና ንግሥታቱን ስለ ክፉ ሥራቸው በመገሠጻቸውና የእምነትን ዶግማና ቀኖና በመጠበቃቸው ምክንያት ሕዝቡ ከነገሥታቱ ጋር በማበር አሳልፎ ሰጣቸው ተሰደቡ በህዝቡ ተወገዙ ከአገር አገርም ተሰደዱ። ወደ ሀገራችን ታሪክ ስንመጣም በርካታ የቀድሞ አባቶቻችን በየዘመኑ በኖሩበት አካባቢ መከራን ቀምሰዋል:: እንደ አሁኑ ጊዜ ሚዲያ ቤይኖር ሁሉም ሆ ብሎ ባያወግዛቸውም በሚንቀሳቀሱበት ቦታ እየተነቀፉ እየተሰደቡ ነው የኖሩት:: የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትልቅ ዓምድ የሆኑት ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት የዚሁ የመነቀፍና የመሰደድ እውነተኛ ማሳያ ናቸው። ጻድቁ አባታችን ገና በወጣትነታቸው ወንጌልን ለማስተማር ፣ ሰዎችን ከኃጢአት ለመመለስና ጣዖታትን ለመስበር በቆራጥነት ሲነሱ በወቅቱ የነበሩ ክፉ ነገሥታትና ጣዖት አምላኪዎች እንዲሁም ከእነርሱ ጋር ያበሩ የገዛ ወገኖቻቸው ከፍተኛ ስድብ፣ ዛቻና ዶፍ ነቀፌታ አውርደውባቸዋል። ለአምላካቸው ካላቸው ፍቅር የተነሳም ትውልድ አገራቸውን ጥለው ለመሰደድ ተገደዋል። ለአንድ እግራቸው መሰዋት ምክንያት የሆነውን ያህል ረጅም ዘመን በትጋት፣ በጾምና በጸሎት በትሕትናና በቅድስና ሲኖሩ በወቅቱ የነበሩ ሥጋውያንና ማስተዋል የሌላቸው ሰዎች «እብድ ነው» እያሉ ይንቋቸውና ይሳለቁባቸው ነበር። አቡነ ተክለ ሃይማኖትም ሆኑ ሌሎች ቅዱሳን አባቶቻችን ያሳዩን ፍጹም እውነት በክርስቶስ ዘንድ ትክክለኛና ፍጹም ሃይማኖተኛ የሆነ ሰው ሁሉ ከዓለም ዘንድ ምድራዊ ክብርን ሳይሆን ነቀፌታን፣ ስድብንና ስም ማጥፋትን እንደሚቀበል ነው። እዚህ ላይ ልናስተውለው የሚገባ ትልቅ የሰው ልጅ ጸባይና የታሪክ እውነት አለ፦ እርሱም አጠቃላይ ሕዝብ መልካም የሚሠሩትንና እውነትን የሚናገሩትን ሰዎች በሕይወት እያሉ ከቶ አይወዳቸውም፤ ይልቁኑ ያሳድዳቸዋል፣ ያገልላቸዋል፣ ያጠለሻቸዋል እንጅ። የሰው ልጅ ምድራዊ ጸባይ ክፉን ነገር ስለሚለምድ ብርሃን ይዞ የሚመጣውንና ለእግዚአብሔር የሚታዘዘውን ሰው እንደ ጠላት ነው የሚያየው። ይሁንና የሚገርመው ነገር ሕዝቡ እነዚህን መልካም ሰዎች ማድነቅ፣ ማክበርና ማመስገን የሚጀምረው ከሞቱ በኋላ ነው። በሕይወት እያሉ ድንጋይ የወረወረባቸው ሕዝብ ከሞቱ በኋላ መቃብራቸውን ይገነባል በሕይወት እያሉ ስማቸውን ያጠፋው ትውልድ ከሞቱ በኋላ ታሪካቸውን በትውፊት ያወድሳል። ለዚህ ነው ማቴ. 23፥29 ላይ እናንተ ጻፎችና ፈሪሳውያን ግብዞች ወዮላችሁ! የነቢያትን መቃብር ትሠራላችሁና የጻድቃንንም መቃብር ታጌጡናላችሁ በአባቶቻችን ዘመን ብንኖር ኖሮ የነቢያትን ደም በማፍሰስ የአባቶቻችን ተካፋዮች ባልሆንን ነበር ትላላችሁ። እንዲህም የነቢያትን ደም ያፈሰሱ የገዳዮቻቸው ልጆች እንደሆናችሁ በራሳችሁ ላይ ትመሰክራላችሁ። እናንተ የአባቶቻችሁን ልክ ትፈጽማላችሁ።» የሚለው! ይህ የሚያሳየው ሰዎች በሕይወት እያሉ በጎ ሰሪዎችን ማየት እንደማይፈልጉ ነገር ግን የእነዚያ ቅዱሳን እውነተኛነትና የመልካም ሥራቸው ፍሬ በጉልህ የሚበራውና የሚመሰገነው ታሪካቸው በሞት ከተደመደመ በኋላ መሆኑን ነው።
በኢትዮጵያዊያን አባባል «የሚሠራ ሰው ይሳሳታል የማይሠራ ሰው ግን የሚሠሩትን ይነቅፋል» እንደሚባለው ሁሉ የአንድ ሰው መልካም መሥራትና በትክክለኛው መንገድ ላይ መጓዝ ትልቁ ማረጋገጫ የነቃፊዎች መነሳት ነው። ምንም የማይሠራ ዝም ብሎ የተቀመጠ ወይም ከጅረቱ ጋር አብሮ የሚፈስ ሰውን ማንም ትኩረት አይሰጠውም:: ምክንያቱም እርሱ ለማንም ሥጋት ወይም እንቅፋት ስለማይሆን። ነገር ግን አንድ ሰው መልካም ሥራ መሥራትና እውነትን መያዝ ሲጀምር ጨለማውን የሚገልጥ ብርሃን ስለሚሆን የብዙዎችን ትኩረት ይስባል። ነቃፊዎችና ተሳዳቢዎች ቀስቶቻቸውን የሚወረውሩት በሚንቀሳቀሰውና ለውጥ በሚያመጣው ፍሬ ባለው ዛፍ ላይ ብቻ ነው። ይህ መልካም ሥራ የሰነፎችንና የክፉዎችን ማንነት ያጋልጣል ሌላው ሰው በጎ ሲሠራና ህዝብን እንዲሁም ቤተክርስቲያን ሲታደግ ሲያዩ የራሳቸውን ደካማነት ስለሚያስታውሳቸው ያንን መልካም ሥራ ለማጠልሸትና ሰሪውን ለመስበር ነቀፌታን፣ ስድብንና ስም ማጥፋትን እንደ መሣሪያ ይጠቀማሉ። ክሳቸው ደግሞ ፍጹም በሬ ወለድ ሲሆን ደግሞ ተመሳሳይ ነው:: ካህናትን መንኮሳትን ሲተቹ ክህነታቸው ፎርጅድ ነው... እንትን አላቸው... ያ ናቸው... ወዘተርፈ ዘወትር ተመሳሳይ ትችት ነው:: ሁሉንም ተችዎች ብትሰሟቸው ከዚህ አይዘሉም! እነዚህ ከድሮ ከጥንት ጀምረው የነበሩ ናቸው:: እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን በጥልቅ ማየት የማይችሉ ግብ*ዞች ናቸው:: «በወንድምህም ዓይን ያለውን ጕድፍ ስለምን ታያለህ? በዓይንህ ግን ያለውን ምሰሶ ስለምን አታስተውልም? ወይም በዓይንህ ምሰሶ ሳለ፥ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጕድፍ አውጣ ልትለው እንዴት ትችላለህ? አንተ ግብዝ አስቀድመህ ከዓይንህ ምሰሶውን አውጣ፥ ከዚያም በኋላ በወንድምህ ዓይን ያለውን ጕድፍ ታወጣ ዘንድ አጥርተህ ታያለህ።» ማቴ. 7፥3-5 የሚለውን ቃል ማስተዋል የተሳናቸው ናቸው::
ያም ሆነ ይህ አንድ ሰው በመልካም መንገድ ላይ እያለ ነገሥታት ቢቆጡበት ሕዝቡ ከነገሥታቱ ጋር አብሮ ቢያማው ነቀፌታ፣ ስድብና መሰናክል ቢበዛበት ሥራው ፍሬ እያፈራ መሆኑንና ጠላት ዲያብሎስ እንደደነገጠ የሚያሳይ ትልቅ ምልክት ነው። ነቃፊዎች መኖራቸው መልካም ሰሪው ይበልጥ እንዲጠነክር፣ በትሕትና እንዲጸና እና ወደ እግዚአብሔር ይበልጥ እንዲጠጋ ያደርገዋል።
በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ መሠረት አንድ ክርስቲያን በእውነተኛው እምነት ጸንቶ ሲኖርና መልካም ሥራን ሲሠራ የሚደርስበት ስድብና ስም ማጥፋት የእምነቱና የሥራው ትክክለኛነት ማረጋገጫና የጽድቅ አክሊል እንጂ የውድቀት ምልክት አይደለም። ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ በ1ኛ ጴጥሮስ 4፥14 ላይ እንዳለው፦ «ስለ ክርስቶስ ስም ብትነቀፉ የክብር መንፈስ የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ላይ ያርፋልና ብፁዓን ናችሁ» ብሎ ተናግሯል። ስለሆነም ከዘፍጥረት እስከ ራዕይ ከሐዋርያት እስከ አሁንም በዚህ ዘመን በመልካም ሠራተኞች ላይ የሚደረገው ነቀፌታ ሁሉ እነዚያ ሰዎች በእውነትና በብርሃን መንገድ ላይ መሆናቸውን የሚያሳይ ትልቅ የእግዚአብሔር ምስክርነት ነው። ዓለም በሕይወት እያለህ ባያመሰግንህም ታሪክህ ግን ከሞት በኋላ በወርቅ ቀለም ይጻፋል፤ ስለዚህ ሰዎች ቢነቅፉህም ስምህንም ቢያጠፉት መልካም ሥራህን ከቶ አታቁም! ምክንያቱም የሥራህ ትክክለኛ መታወቂያውና ማህተሙ የነቃፊዎች መነሳት ነውና:: ስራ መስራት ያለብን ይነቅፉናል ይሰድቡናል ብለን ሳይሆን እግዚአብሔር የሰጠኝ ኃላፊነት ምንድን ነው? ብለን መሆን አለበት! በአሁኑ ሰዓት ወሬ በፍጹም አያስፈልገንም::
ቤተክርስቲያንና ሀገራችን ችግር ላይ በወደቁበት ሰዓት ዋዛ ፈዛዛ መጫዎት አያዋጣንም የታሪክ ተወቃሾችም ያደርገናል:: ይልቁንስ አንድ ሆነን ይህን ዘመን ታሪክ ሰርተን እንለፍ:: ትልቅ ኃላፊነት እጃችን ላይ ወድቋል! እንንቃ! በመጨረሺያም ወዳጄ ሆይ ዝም ብለህ ሥራህን ሥራ እንዳሉህ ታላቁ አባታችን አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ እንዳትዘናጋ! በል ሥራህን ሥራ!
ድል ለኢትዮጲያ ድል ለቤተክርስቲያን!
Blogger Comment
Facebook Comment