መጽሐፍ ዣንሸዋ | የአዲሰ ዓመት አከባበር ታሪክ ድንቅ ምስጢር



✍ መሪራስ አማን በላይ

የሚከተለው ምስጢራዊ ታሪክ የተገኘው፡ ክቡር መሪራስ አማን በላይ፡ ተርጉመው ካቀረቡልንና “መጽሐፍ ዣንሸዋ“ የሚል ስያሜ ከተሰጠው ድንቅ መረጃ ጽሑፍ ነው። 
_________________________________________

ናህኤል የተባለው ኖህ እንደቅድመ አያቱ ሄኖክ በትውልዱ ዘመን ከቤተሰቦቹ ጋር እግዚአብሔርን የሚፈራ ጻድቅና ፍጹም ሰው ነበረ።

ኖህም ከሚስቱና ከልጆቹ ከልጆቹም ሚስቶች በምድር ለዘር እንዲተርፉ ከሰበሰባቸው አራዊትና እንስሳ አእዋፋትና አሞራዎች ጋር በመሆን ከጥፋት ውሃ የእግዚአብሔር ትእዛዝ ከመፈጸሙ የተነሣ በመርከቢቱ ውስጥ ገብቶ እንዲሁ ሌሎቹንም አስጠግቶ አድኖአል።

አዳም ከኤዶም ገነት ስለወረደ ንስሐ በመግባቱ እግዚአብሔር የተስፋውን ዘር ከሴት ልጁ ተወልዶ እንደገና የተነጠቀውን የእግዚአብሔርን ልጅነት እንደሚመልስለት ቃል ኪዳን አድርጎለት ከነበረችው ቀን እስከ ጥፋት ውኃ ድረስ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ አምሳ ዓመተ ፍዳ ነበረ። ውኃው ከጎደለና ከደረቀ በኋላ ምድር ፀጥ ብላ በለመለመ ዛፍና በአትክልት ቅጠል በሳርም ተሸፍና ነበር። እንደዚሁ ከአሥራ ሁለቱ ወራቶች መካከል በመጀመሪያው ውር በመስከረም ምድሪቱ በአበባ ተሸፍና ነበር።

እንደዚህም ሆነ፡ ኖህና ቤተሰቦቹ መርከቢቱ በአራቱ መንኮራኩር መካከል በአንደኛው /አራራት/ በአሉባር ተራራ በአረፈችበት በመጀመሪው ወር በመስከረም ከወሩም በመጀመሪያው ቀን እርግቢቱ ለኖህ ለግላጋ ቀንበጥ የሆነ የወይራ ቅጠል እንደሰጠችው ሁሉ እንዲሁ መካከለኛው ልጁ ካም የአደይ አበባና የጽጌረዳ አበባ አምጥቶ እንቁ–ዮጳሺ (እንቁጣጣሽ) ብሎ ሰጣቸው። እንደጠራ እንቁ ሁኑ ሲል ነው። በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር ከጥፋት ውኃ እንድንድንና እንድናመልጥ መርከቢቱን እንድንሰራ በማድረጉና ለዘር እንድንተርፍ በማስቀረቱ መርከቢቱን በዚህች ቀን ምድር እንድትነካ በማድረጉ የእግዚአብሔርን ስምና ቸርነት ከትውልድ ወደ ትውልድ የምናስተላልፍበት ቀን ነው።

ስለዚህ ለአዲሱ ዘመን ቀኑም ለወሮች መጀመሪያ ለሆነው ወር ለመስከረም የመጀመሪያው ቀን ይሆናል፡ ወሩም የወሮች መጀመሪያ ይሆናል ሲል ካም ለቤተሰቦቹ እንቁጣጣሽ አላቸው። እነርሱም በየአመቱ የአጣህ አሉት።

ኖህም መርከቢቱ ምድር የነካችበትን መስከረም አንድ ቀንን ለወሩ የመጀመሪያው ቀን ለዓመቱ ወራቶች የመጀመሪያው ወር እንዲሆን ለልጅ ልጅ ከልጅም ወደ ልጅ እንዲተላለፍ በመጽሐፍ ዣንሸዋ ጽፎና መዝግቦ አስቀመጠው።

ኖህ የክህነቱ ስም ናህኤል የተባለው ልጆቹን አል፦ እግዚአብሔር የምናደርገውን ያሳየን ዘንድ ምሕረቱና ቸርነቱ ለዘለዓለም ከኛ ጋር መሆኑን እናውቅ ዘንድ ቃሉን ስምተን ትዕዛዛቱን እንፈጽም ዘንድ ሁለት ሰባት በሰው ልጅ በደል ምክንያት በጥፋት ውኃ የነገለውን የዛፍ ግንድና የደረቀውን እንጨት ሁሉ ሰብስቡ ከምርቱም፡ በዚያም አቃጥለን ለእግዚአብሔር የሚቃጠልና ንጹህ የሆነ የእህል መስዋእት እናቀርባለን አላቸው።
ልጆቹም የልጆቹም ሚስቶች ደከመን ሳይሉ ለሁለት ሰባት ተራራ ያክል አድርገው ግንዱን አመሳቅለው እንጨቱንም በበላዩ ከመሩት፡ አባታቸው የአላቸውን ሁሉ አደረጉ።

ናሆም ለእግዚአብሔር ዳግመኛ ከንጹህ እንስሳና ከንጹህ እህል ፍሬ መስዋእትን በአሉባር ተራራ ላይ በሰራው መሠዊያ ላይ ደመራውን አቃጥሎ አቀረበ።

እግዚአብሔር ናህኤል የተባለው ኖህ የአቀረበውን መስዋእትና መአዛ የአለውን ሽታ ተመለከተና ተቀበለው። እንደዚህም አለው፦ አንተ ከጠፋው ትውልድ ተለይተህ በፊቴ ጽድቅ ሁነህ በመገኘትህ እንደ ሄኖክም አካሄድህን ከእግዚአብሔር ጋር ስለአደረክ ከጥፋት ውኃ ልትድን ችለሃል፡ አሁንም እልሃለሁ፦ ከእኔ ከፈጠረህ ሌላ አምላክ ላልፈጠረህ እንዳታመልክ እንዳታምንም የልጅ ልጆችህም እንዲሁ ያደርጋሉ።

እኔም እነሆ ቃል ኪዳኔን ከአንተ በኋላ ከሚመጣው ከዘርህ ጋር አቆማለሁ፡ ከእናንተ ጋር ላሉትም የሕይወት ነፍስ ላላቸው ሁሉ በምድር ለሆኑ ሁሉ ይሆናል።

በእኔና በእናንተ መካከል ከእናንተ ጋር ደማዊ ነፍስና ልባዊ ነፍስ ሕያው ነፍስ በአለው መካከል ሁሉ ለዘለዓለም የማደርገው የቃል ኪዳን ምልክትና ሰንደቅ አላማ የሚሆን ይህ ነው።

ቀስቴን በደመና አድርጌአለሁ፡ የቃልኪዳኑም መታሰቢያ ምልክት በእኔና በምድር መካከል ይሆናል። በምድር ላይ ደመናን በጋረድሁና ዝናብ በአወረድሁ ጊዜ ቀስቲቱ በደመናውና በብርሃኑ መካከል ትታያለች፡ በእኔና በእናንተ የአለው የመታሰቢያውን ቃል ኪዳን አስባለሁ።
ሥጋ ያለውን ሁሉ ያጠፋ ዘንድ ዳግመኛ የጥፋት ውኃ አይሆንም፡ ቀስቲቱ በደመናና በፀሐይ ብርሃን መካከል እንደሆነች ሁሉ እንዲሁ በእኔና በምድር ላይ በሚኖረው ሥጋ በለበሰው ደማዊ ነፍስና ልባዊ ነፍስ መካከል የአቆምኩትን የዘለዓለም ቃል ኪዳን ለማሰብ አያታለሁ፡ የቃል ኪዳኔ መታሰቢያ የሰንደቅ ዓላማ ምልክት ይህ ነው አለው።

ኖህም ከእግዚአብሔር መልአክ ከሱርያኤል የሰማውንና የተማረውን የእግዚአብሔርን ትእዛዛት ቃል ኪዳኑን ሁሉ ልጆቹና የልጆቹ ልጆች ሁሉ እንዲጠብቁትና እንዲፈጽሙት አስተማራቸው።

ከመጽሐፈ ሄኖክና ከትንቢተ ሄኖክ ቀጥሎ ኖህ ስላለፉት አባቶቹ ታሪክና ስለጥፋት ውኃ ስለ እንሳስትና ስለአራዊት ስለሰማያትና በውስጣቸው ስላሉት ዓለሞችና ከዋክብት ስለባህር አሦችና ስለሰማይ ወፎች በምድር ስለሚሳቡ ተንቀሳቃሾች ስለድንጋዮችና ስለ እፀዋት ስለ ንፁህነትና ስለ እርኩሰት ስለ መድኃኒትና ስለ መርዝነት የሚገልጹትን ሁሉ ከኖህ በፊት ያልታወቁትን ምስጢሮች ገልጾ ጽፎአል። ይህም መጽሐፍ በመጽሐፈ አበው ወመጽሐፈ ኖህ ይባላል።

ከመጽሐፈ ኖህ በፊት የነበረውን ዜና አዳምንና መጸሐፈ ሄኖክን ጨምሮ ለልጆቹ እንዲያጠኑትና ለልጆቻቸው እንዲያስተላልፉት አስረክቦዋቸዋል። ነገር ግን ተከታዩ ትውልድ ከመልካሙ ተግባር (ስነ ምግባር) ይልቅ መጥፎውን ሥራ (ግብረ እኩይ) እየመረጡ ያጠኑበትና ጠላታቸው የሆነውን ሁሉ ይበቀሉበት ጀመር። ነገር ግን መርከቢቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ምድርን የነካችበት መስከረም አንድ ቀን ሁለተኛ ህዳር መባቻን ከመርከቢቱ ወጥተው የብስን የረገጡበትን ሦስተኛ ሚያዝያ በኋላ ፋሲካና ትንሣኤ የሆነበትን ወደመርከቢቱ የገቡበትን ቀን መታሰቢያ በዓል አድርገው ያከብሩታል። ይሄም በካም ልጆች ዘንድ አዲስ ዓመት አዲስ አዝመራ ሲመጣና ክረምቱ ገና ሳይመጣ እስከ አሁን የሚያከብሩና የሚያስታውሱ አሉ።

ኖህ ለልጆቹና ለልጆቹ ልጆች ለተከታዩ ትውልድ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍና መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በዓላትን አዘጋጀላቸው።

ኖህ መርከብ ለመስራት ግንድን መጥረብ የጀመረበት መርከቢቱ በአሉባር ተራራ ላይ የአረፈችበትን እግዚአብሔር ከኖህ ጋር ቃል ኪዳን የአደረገበትን የመጀመሪያውን ወር መስከረም ከወሩም የመጀመሪያውን ቀንና የአሥራተኛው ቀን የመታሰቢያ የደስታ ቀን እንዲሆን አዟል።

ኖህና ልጆቹ ከመርከቢቱ የወጡበትና አብረውት የነበሩትን እንስሳዎችና አራዊቶች ሌሎችንም ብዙ ተባዙ ምድርን ሙሉዋት ብሎ ባርኮ የአሰናበታቸው የህዳር መባቻን በየዓመቱ መታሰቢያ በዓል እንዲሆንና እንዲከበር ሲል ሥርዓት አድርጎ ሠርቶላቸዋል።
ኖህና ልጆቹ የልጆቹ ሚስቶች ለዘር እንዲቀሩ አብሮ ከሰበሰባቸው ፍጥረታት ጋር ሁሉ ከጥፋት ውኃ ይድኑ ዘንድ ወደ መርከቢቱ የገቡበት ሚያዝያን ወር ከወሩም ሁለተኛውን ቀን መታሰቢያ በዓል እንዲሆን በሥርዓት እንዲከበር አዟል። ይህም ወር በአቢብ ወር እስራኤሎች ከግብፅ የወጡበት ቀን ስለሆነ የፋሲካ በዓል ይደረግበታል። እነዚህም መታሰቢያዎች ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ከመቃብር ይነሣ ዘንድና ዓለምን ያድን ዘንድ ስለ አለው ምስጢሩን በምሳሌ አስቀደመው፡ ይህም የትንሳኤ በዓል ነው።

ኖህ ሦስቱን በዓላቶች ከሌሎች በዓላት ይልቅ እንዲከበሩና እንዲታሰቡ ሥርአት አድርጎ በመጽሐፉ ጽፎ ለልጆቹ ሰጥቷል።

እነዚህንም በዓላት የእግዚአብሔር ኪሩብ ገብርኤል በሰሌዳ ላይ ጽፎ ለመላእክትና ለሰው ልጆች በሰማይና በምድር መታሰቢያ ይሆናቸው ዘንድ በእግዚአብሔር ተራራ ሥር ባለው የውኃ ምንጭ ራስ አስቀምጦ አተመው።

እንደዚሁ ከዚህች ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ በሰማይና በምድር መካከል በእግዚአብሔርና በሰው ልጆችም መካከል እግዚአብሔር የአደረገውን ቃል ኪዳን ያስታውሱት ዘንድ የእግዚአብሔር መልአክ ሱርያኤል በደመናውና በፀሐዩ ብርሃን መካከል ይታይም ዘንድ የቃል ኪዳኑን መታሰቢያ ምልክት የሆነው ቀስት በእንቁዮጵ ላይ ጽፎ ከሕይወት ምንጭ ውኃ ራስ አትሞ አስቀምጦታል።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment