የኦህዴድ ብልፅግና ፓርቲ ፀረ-ሴሜቲክ እንቅስቃሴና በግዕዝ ሥልጣኔ ላይ ያለው ቅናት
✍ አስማረ ብሩህ
በኦህዴድ ብልፅግና ፓርቲ የሚመራው መንግስት በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ላይ የጀመረው ጦርነት (በመጀመሪያ ከትግራይ ጋር፣ በመቀጠል ደግሞ ከአማራ ጋር) ከላይ ከላይ ስናየው ፓርቲው የሥልጣን የበላይነቱን ለማስጠበቅ ያደረገው ጦርነት ሊመስለን ይችላል፡፡ ሆኖም ግን፣ ይህ ምክንያት ትክክል አለመሆኑን የምንረዳው የነገሩን ሥረ መሰረት በጥልቀት ቆፍረን ስናየው ነው፡፡ መነሻ ምክንያቱም ‹‹የግዕዝ ሥልጣኔ ቅናት›› ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
‹‹የግዕዝ ሥልጣኔ›› የሚለውን ቃል የተዋስኩት ዶ/ር ተሻለ ጥበቡ ‹‹The Making of Modern Ethiopia 1896 – 1974›› በሚል ርዕስ ካሳተሙት መፅሐፍ ነው፡፡ ዶ/ር ተሻለ ‹‹የግዕዝ ሥልጣኔ›› ሲሉ የግዕዙ ዓለም ወይም አቢሲኒያ የሚባለው የሰሜኑ ኢትዮጵያ ክፍል በሥነ መንግስት፣ በሃይማኖት፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በኪነ ጥበብና በኪነ ህንፃ፣ በተቋማት ግንባታ እንዲሁም በታሪክና በቅርስ ያካበተውን ሐብት ለማመላከት ነው፡፡ ‹‹እኛም የብዙ ሺ ዓመታት ታሪክ አለን›› የሚለው የኦህዴድ ብልፅግና ግን እነዚህ የሥልጣኔ ሐብታትን አለማፍራቱ በቅናት እንዲንገበገብ እያደረገው ይገኛል፡፡
በታሪክ ሂደት የኢትዮጵያ አካል የሆኑት የደቡብ፣ የምዕራብና የምስራቅ ህዝቦች እነዚህን የሥልጣኔው ሐብቶች የተቀበሉ ቢሆንም፣ ኦህዴዳውያን ግን ከሥልጣኔው ተቋዳሽ ከመሆን ይልቅ ቅናትና ጥላቻ አድሮባቸዋል፡፡ እናም ሥልጣን እስኪይዙ ጠብቀው፣ በአሁኑ ወቅት ሥልጣኔው ላይ ያላቸውን ቅናትና ጥላቻ በተግባር እየገለፁት ይገኛሉ፡፡ ይሄንንም ድርጊታቸውን የኦህዴድ ብልፅግና አባላትና አክቲቪስቶች በተለያዩ ወቅቶች ከሚፅፏቸው፣ ከሚናገሯቸው ንግግሮችና ከድርጊታቸው መረዳት እንችላለን፡፡ ለዚህም የሚከተሉትን ስድስት ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡
የመጀመሪያው ማሳያ፣ በለውጡ ማግስት የጠ/ሚ አብይ አህመድ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩትና በኋላም በሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት አቶ ሌንጮ ባቲ የፖለቲካ ለውጡ በመጣ በ7ኛ ወሩ ላይ በጥቅምት 4/2011 ላይ በይፋዊ የፌስቡክ ገፃቸው ላይ እንዲህ ብለው መፃፋቸው ነው ‹‹ያለፉት 3ሺ ዓመታት የኢትዮጵያ ፖለቲካ በትግራይና በአማራ የተቀረፀ ነበር፤ የሚቀጥሉት ሦስት ሺ ዓመታት ደግሞ የኢትዮጵያ ፖለቲካ በኦሮሞ የሚመራ ይሆናል፡፡›› ይህ የሌንጮ አስተሳሰብ በ‹‹ሴሜቲክና ኩሺቲክ›› የሁለትዮሽ የተቃርኖ ሐሳብ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ከዚህ ሐሳብ በመመስረት ነው ‹‹ሥልጣኑ አሁን ከሰሜን (ከሴሜቲኩ አቢሲኒያ) ወደ ደቡቡ ኩሽ ሄዷል›› የሚል አቋም የያዙት፡፡
ሁለተኛው ማሳያ፣ ከ2010ሩ የፖለቲካ ለውጥ በኋላ የኦህዴድ አክቲቪስቶች ‹‹የኩሽ ህዝቦች ትብብር (Kushitic Alliance) መመስረት አለብን›› የሚል እንቅስቃሴ ውስጥ መግባታቸው ነው፡፡ ሐሳቡ ደቡብ ላይ ያሉትን ህዝቦች በማስተባበር ፀረ-ሴሜቲክ የሆነ እንቅስቃሴ ለማስጀመር ነው፡፡ ለዚህ ግብ እንዲረዳቸውም ‹‹ኩሽ ሚዲያ›› የሚባል የማህበራዊ ሚዲያ መድረክ ከፍተው ‹‹የግዕዝ ሥልጣኔ›› ያፈራቸውን ባህሎችን፣ ምልክቶችንና እሴቶችን ማንቋሸሽ የዕለተለት ተግባራቸው አድርገውታል፡፡
3ኛ፣ የግዕዝ ፊደላትን ላለመጠቀም የሚያደርጉት ጥረትና እነሱ ‹‹ኩሽ›› ከሚሉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክፍል የግዕዝ ፊደላትን የማስወገድ እንቅስቃሴያቸው ሌላኛው ነው፡፡ ከፀረ-ሴሜቲክ ስሜታቸውና ከግዕዝ ሥልጣኔ ቅናት የመነጨውን ይሄንን ተግባራቸውን ደቡብ ላይ የግዕዝ ፊደላትን ሲጠቀም የነበረው የቀቤና ህዝብ ላይ ተግባራዊ አድርገውታል፡፡ በዚህም የቀቤና ህዝብ የላቲን ቋንቋ እንዲጠቀም አስገድደውታል፡፡ ይሄንንም እርምጃ በግንቦት 2015 ይፋ አድርገውታል፡፡
4ኛ፣ የኦህዴድ ብልፅግና አመራሮች የግዕዙ ሥልጣኔ ያፈራቸውን እሴቶችና ባህሎች በአደባባይ እንዳይታዩ የሚያደርገው ጥረት ነው፡፡ ለምሳሌ፣ የመስቀል፣ የጥምቀትና የአድዋ በዓላት ላይ ህዝቡ ላይ የሚያደርሱት ክልከላና ወከባ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
5ኛው ማሳያ፣ የግዕዙ ሥልጣኔ ምልክት የሆነችውን ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያንን ለማዳከምና ለመከፋፈል የሚያደርጉት ጥረት ነው፡፡ ይሄንንም ተግባራቸውን በመጀመሪያ በቄስ በላይ መኮንን፣ በመቀጠል ደግሞ በአባ ሳዊሮስ በኩል ለማድረግ ሞክረው አልተሳካላቸውም፡፡ በእነሱ የጳጳሳት ምደባ ዝርዝር ውስጥም አቢሲኒያ (ትግራይና አማራ ክልል) አልተካተተም፡፡ ከሰሜኑ ይልቅ፣ ዋነኛ ትኩረታቸው ‹‹የኩሽ ምድር›› የሚሉት አካባቢ ስለነበረ ነው ‹‹የኦሮሚያና ‹‹የብሄር ብሄረሰቦች›› ሲኖዶስ›› የሚለውን አገላለፅ ሲጠቀሙ የነበረው፡፡
6ኛው ማሳያ፣ የግዕዝ ሥልጣኔ ሐብታትን በፀጋ የተቀበሉ ህዝቦችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው በግድ እንዲፈናቀሉ ማድረጋቸው ነው፡፡ ይሄንንም ጭካኔያቸውን በወለጋ፣ በአዲስ አበባና በሸገር ከተማ ተግባራዊ አድርገውት አሳይተውናል፡፡ ይህ ጭካኔያቸው የተወለደው በግዕዝ ሥልጣኔ ላይ ካላቸው ቅናትና ብስጭት ነው፡፡
ባጠቃላይ፣ ኦህዴዳውያን ሀገር እየመሩ ያሉት በፀረ-ሴሜቲክ ስሜት እና በግዕዝ ሥልጣኔ ቅናት ነው፡፡ በእነሱ የሥልጣን ዘመን፣ ኦርቶዶክ ቤ/ክ መከራዋን እያየች ያለችውና ሰሜኑን በየተራ የጦርነት አውድማ እያደረጉ ያሉት በዚህ ስሜት፣ ቅናትና ብስጭት ተነሳስተው ነው፡፡
Blogger Comment
Facebook Comment