✍ በኃይሉ ታየ ደበላ
በጎንደር መንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ከታላቁ መምህር ሊቀ ሊቃውንት መንክር መኰንን ወንበር ተምረው አኽለውና መስለው የወጡት ብፁዕ አቡነ እንድርያስ፣ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና ተጠያቂ የሊቃውንት ሰብሳቢ የቅዱስ ሲኖዶስ አባል ጉባዔውን ጥለው ወደ ጫካ ከመመነናቸው በፊት በቅዱስ ሲኖዶስ ምልዐተ ጉባኤ በተደጋጋሚ እንዲህ እያሉ ይጮኹ ነበር።
...
“ቤተ ክርስቲያን መነገጃ አይደለችም! ሌቦች ከቤተክርስቲያን አጥር ግቢ ይውጡ! ከማህበራችን ጉበኞች ይውጡ! ንዋይን የናፈቁ ሠርተው ይብሉ! በቤተ ክርስቲያን አውደልዳይ አይብዛ፤ ቦታ ይሰጠው፤” “በጎጥ እና በቋንቋ የምንመራው እስከ መቼ ድረስ ነው?”ቢሮው የማን ነው?በጉቦ የገባ ማን ነው? ወንጌሉ የሚሰበከው ለማን ነው? ሕዝቡ ተሰብኮ፣ ተሰብኮ ዐውቆታል፤ ከቢሮ ውስጥ ነው ችግሩ፤ ጥያቄው ሲጎርፍ አለመመለስ ነው ችግሩ፤ በዚኽ ዓለም ያልታመነ በእግዚአብሔር መንግሥትስ ቦታ አለው እንዴ? ትምህርቱ የጆሮ ቀለብ ኾኗል፤ ውስጥ ገብተው ሲያዩት ያስለቅሳል፡፡” “ምርጫ በሞያ ይኹን ፤ምርጫ በእውቀት ይሁን፤ምርጫ ሱባኤ ትይዞ በቀኖና ቤተክርስቲያን ይሁን፤ምርጫ በክርስቶስ ይሁን ምርጫ በጎጥ በብሔር አይደለም፤ የተመረጠው ሲጠየቅ መልስ የሚሰጥ የሕዝብ አባት ይኹን፤ ድኻ ተበደለ፤ ፍርድ ተጓደለ የሚል አባት ከሌለ ትርጉሙ ምንድን ነው መሰብሰባችንም በክርስቶስ ምንም ነው”
“አእምሯችን ሳይገራ፣ ለሕጉ ተገዥ ሳንኾን ከየትም ከየትም መጥተን እግዚአብሔርን የምናስቀይም ነው የምንኾነው፤ ያልተቀጣ ልጅ ኹልጊዜ እንደሰረቀ ይኖራል፤ ልቡናው በእግዚአብሔር ቃል እና ምስጢር ያልተቀጣ ሰውም ኹልጊዜ እንደበጠበጠ ይኖራል፤ – ፖሊቲካ ከቤተ ክርስቲያን ይውጣ፤ እውነት ይገለጥ አባቶቸ፤ ስለእውነት እንቁም፤ በአራቱ ማዕዝን ጥያቄ ተቀስሯል፤ ስለ ሃይማኖት ጥያቄ እየተነሣ ነው፤ ጥያቄውን የሚመልሰው ማን ነው?በብሔር የተመረጠው! በጎሳ የተመረጠው! በእውቀት የተመረጠው! በክርስቶስ የተመረጠው !የቱ ነው...?ብዙ ችግሮች ቀርበዋል፤ የሚፈታቸው ማን ነው?
አእምሮ ያስባል፤ ጆሮ ይሰማል፤ ድኻ ተበደለ፤ ፍርድ ተጓደለ፤ የሚል አባት ከሌለ ትርጉሙ ምንድን ነው? ዙሪያውን ሰይፍ ተመዞ እየተብለጨለጨ የደነዘዘውን አእምሮ እናስወግደው፤ ቃሉን እንጠይቀው፡፡ ሕጉ ይከበር፤ ስም ብቻ አንያዝ፤ ሕጉን ወደ ኋላ አሽቀንጥረን ትተን እንዴት መምራት እንችላለን? ተንኰል ይቅር፤ በውሸት አንመን፤ በዝባዥ ይጋለጥ፤ ጨርሻለኹ፡፡"
ይሉ ነበር ቆራጡ ሊቅ ጥበብን፣እውቀትን ከምናኔ ጋር አጣምረው የዋጁት ቆራጡ የክርስቶስ አርበኛ አራት ዐይናው ሊቅ ብፁዕ አቡነ እንድርያስ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ኃላፊ ሊቀ ጳጳስ ከትርጓሜው ባሻገር ማሕሌተ ያሬድን በትርጓሜያቸው ያሳምሩታል፤ በረከታቸው ይደርብን።
አባቴ ለደካማው ልጅዎት በረከትዎ ይደርብኝ🙏
......
አባታችን ለምን ከጉባኤው ተነጥለው ገዳምን እንደመረጡ ከዓመታት በፊት የተናገሩት አሳማኝ ነው።
አባታችን ያሉበትን ቦታ ያልጠቀስኩ ለደኅንነታቸው ነው።
Blogger Comment
Facebook Comment