- ❖ ናዛዚ (የሚናዝዝ)
- ❖ መጽንዒ (የሚያጸና)
- ❖ መስተፍሥሒ (የሚያስደስት) ማለት ነው።
መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት በወረደበት ዕለት በቤተ ክርስቲያን የሚከበረው ይህ በዓል ‹በዓለ ጰራቅሊጦስ› ወይም ‹በዓለ ጰንጠቆስጤ› በመባል ይታወቃል። ‹ጰንጠቆስጤ› በግሪክ ቋንቋ በዓለ ኀምሳ፣ የፋሲካ ኀምሳኛ ዕለት፣ በዓለ ሠዊት (የእሸት፣ የመከር በዓል) ማለት ነው (ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፣ ገጽ ፱፻፮-፱፻፯)።
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ካረገ በኋላ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ዐሥራ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት፣ ሰባ ሁለቱ አርድእት፣ አምስት መቶው ባልንጀሮች እና ሠላሳ ስድስቱ ቅዱሳት አንስት በኢየሩሳሌም ከተማ በአንድነት ኾነው በጸሎት ይተጉ ነበር።
ጌታችን በሚያርግበት ጊዜ "እነሆ አባቴ የሰጠውን ተስፋ እኔ እልክላችኋለሁ፤ እናንተ ግን ከላይ ኃይል እስክትለብሱ ድረስ በኢየሩሳሌም ከተማ ቆዩ፤" ሲል ለሐዋርያቱ በሰጣቸው የተስፋ ቃል መሠረት በዐረገ በዐሥረኛው ቀን መንፈስ ቅዱስን ልኮላቸዋል (ሉቃ. ፳፬፥፵፱)። ዅሉም በአንድ ቦታ ተሰባስበው ሳሉ በበዓለ ጰራቅሊጦስ ማለዳ እንደ ዐውሎ ነፋስ ያለ ድምፅ ድንገት ከሰማይ ወርዶ የነበሩበትን ቤት ሞላው። ከዚያም የተከፋፈሉ የእሳት ላንቃዎች በዅሉም ላይ አረፉባቸው። በዚህ ጊዜ ዅላቸውም መንፈስ ቅዱስ ባደላቸው መጠን በየአገሩ ቋንቋዎች ዅሉ ተናገሩ (ሐዋ.፪፥፩-፬)።
ጌታችን መንፈስ ቅዱስን ለሐዋርያት የላከበት ይህ ዐቢይ በዓል ዐሥራቱን፣ በኵራቱን፣ ቀዳምያቱን ካህናተ ኦሪት ስለሚቀበሉበት በብሉይ ኪዳን በዓለ ሠዊት ተብሎ ይከበር ነበር። በሐዲስ ኪዳን ደግሞ ቅዱሳን ሐዋርያት መንፈስ ቅዱስን ስለ ተቀበሉበት በበዓለ ሠዊት ምትክ በዓለ ጰራቅሊጦስ ገብቶበታል። የበዓለ ትንሣኤ መነሻው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ማለትም በግብጽ፣ እስራኤል ከሞት የዳኑበት የመታሰቢያ በዓል እንደ ኾነው ዅሉ፣ ለበዓለ ጰራቅሊጦስም መነሻው ይኸው የአይሁድ የፋሲካ በዓል ነው። የአይሁድ ፋሲካ ከተከበረ ከሰባት ሳምንታት በኋላ በኀምሳኛው ቀን የሩቆቹ ከከተሙበት ወጥተው፣ የቅርቦቹ ከተሰባሰቡበት ተገናኝተው ለበዓሉ ፍጻሜ የሚኾነውን በዓለ ሠዊት (የእሸት በዓል) ያከብሩ ነበር።
ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ተሰባስበው ሳሉ መንፈስ ቅዱስ በእሳት አምሳል ወርዶ ሰማያዊ ሀብትን፣ ዕውቀትና ጸጋን አድሏቸዋል። መንፈስ ቅዱስ ከወረደላቸው በኋላም በአእምሮ ጐልምሰዋል፤ ጥቡዓን (ቈራጦች)፣ ጽኑዓን ኾነዋል፤ ለስብከተ ወንጌል የሚፋጠኑበትንና ለሰማዕትነት የሚዘጋጁበትን ልቡና ታድለዋል።
ቅድስት በኾነች በጽርሐ ጽዮን በሐዋርያት ላይ የወረደው የእግዚአብሔር አብ ጸጋ፣ የእግዚአብሔር ወልድ ፍቅር፣ የእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ አንድነት በዅላችን ላይ ይደር፤ እጽፍ ድርብም ይኹን።
Blogger Comment
Facebook Comment