ያለ ወላዲተ አምላክ ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም! አራት ነጥብ!


✍ እስራኤል ዘነፍስ 

እንኳን አደረሰን አደረሳችሁ

ግንቦት 21 | አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በደብረ ምጥማቅ በስሟ በተሠራች ቤተ ክርስቲያን ጉልላት ላይ በብርሃን መርከብ ተቀምጣ ፊቷ በግልጥ ስለመታየቱ ታላቅ በዓል ነው።

እርሷም በልጅዋ የመለኮት ብርሃን የተጎናጸፈች ናት። በዙሪያዋም የመላእክት ሠራዊት የመላእክት አለቆችም በየማዕረጋቸው ክንፋቸውን ዘርግተው ይቆሙ ነበር፤ ይጋርዷታልም። ሱራፌልም ማዕጠንታቸውን ይዘው ለንግሥዋ ገናናነት ይሰግዳሉ። በየስግደታቸውም እንዲህ እያሉ ያመሰግኗታል።

አብ በሰማይ ሁኖ ተመለከተ እንደ አንቺ ያለ አላገኘም አንድ ልጁንም ልኮ ከአንቺ ሰው ሆነ። ሁለተኛ ሰማዕታትም በየማዕርጋቸው ረቂቃን በሆኑ ፈረሶቻቸው ተቀምጠው እየመጡ፥ መጀመሪያ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአምባላይ ፈረሱ ወርዶ ይሰግድላታል እንዲሁም ባልንጀሮቹ ሰማዕታት መጥተው ይሰግዱላታል ከእርሱ በኋላ የሚመጣው በዱሪ ፈረስ የሚቀመጥ ይህ መርቆሬዎስ ነው። ከዚህም በኋላ ሰማዕታት ሁሉ በመከታተል መጥተው ይሰግዱላታል ምስጋናም ያቀርቡላታል። ደግሞ ጻድቃንም እንዲሁ።

ሄሮድስ የገደላቸው ሕፃናትም መጥተው ይሰግዱላታል። በፊቷም እየዘለሉ አንዱ በአንዱ ላይ እየዘለለ በመተቃቀፍም ይጫወታሉ።

እናትና አባቱም የሞቱበት ቢኖር ወይም ከዘመዶቹ ወይም ባልንጀራዉ "ቅድስት ድንግል እመቤቴ ሆይ ዕገሌን አሳዪኝ" ብሎ በሚለምናት ጊዜ ቀድሞ በነበረበት መልኩ ያን ጊዜ ታመጣዋለች። ደግሞ መሀረባቸውን ወደላይ ይወረውሩላታል።

የወደደችውንም በእጇ ተቀብላ መልሳ ትጥልላቸዋለች። ለበረከትም በየጥቂቱ ይካፈሉታል።

እንዲህም አምስት ቀን ሁሉ ክርስቲያንም እስላሞችም አረማውያንም ያይዋታል። ወደ ቤታቸውም ለመሔድ ሲሹ በፊቷ ሰግደው ይሰናበቷታል። እርሷም ትባርካቸውና ይመለሳሉ።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment