ግንቦት ፳ | እንኳን ለታላቁ መናኝ ንጉሥ ቅዱስ አፄ ካሌብ ዓመታዊ የዕረፍት በዓል/ መታሰቢያ አደረሰን።

✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ 

ቅዱሱን ንጉሥ አፄ ካሌብን በዓለም ያሉ አብያተ ክርስቲያናት በትልቁ ያከብሩታል። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን አክሱም አካባቢ ካልሆነ ከነ ስም አጠራሩ እንኳ እየተዘነጋ ይመስላል።

ነገር ግን ጀግንነቱ፣ ውለታው፣ ምናኔውና ቅድስናው የማይረሳ ነውና እንኳን በእምነት የሚመስሉን ይቅርና የማይመስሉን ምሥራቅ ኦርቶዶክሶችና ካቶሊኮች ዓመታዊ በዓሉን በወርኀ ጥቅምት ያከብራሉ።

ከአክሱም ነገሥታት በኃይሉም ሆነ በሃይማኖታዊ ቅድስናው አፄ ካሌብ ዋናው ነው። ቅዱሱ የነገሠው በ485 ዓ/ም አካባቢ ሲሆን እስከ 515 ዓ/ም ድረስ በዙፋኑ ላይ ቆይቷል። ከመልካም ትዳሩ አፄ ገብረ መስቀልን ጨምሮ ልጆችን ወልዷል።

ስለ ቅዱስ አፄ ካሌብ የሚከተሉትን ነጥቦች ብቻ እናንሳ፦

፩ኛ. በንግሥና ዙፋን ከመቀመጡ በፊት የሚገባውን መንፈሳዊ ትምሕርት ጠንቅቆ ተምሯል።፪ኛ.ሃይማኖቱ የጠራና እጅግ የሚደነቅ ነበር። በእርሱ ዘመን ሃይማኖት ለነገሥታቱ የፖለቲካ ማስፈጸሚያ ነበር። እርሱ ግን እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ አምልኳል።፫ኛ.ለእመቤታችንና ለቸር ልጇ የነበረው ጥልቅ ፍቅር የተገለጠና የሚያስቀና ነበር።፬ኛ.ገና በዙፋኑ ሳለ ጸሎትን ያዘወትር ነበር።፭ኛ.ዛሬም ድረስ ሁሉም ክርስቲያኖች የማይረሱትን መንፈሳዊ ቅንዓትን አሳይቷል።

ይሕስ እንደ ምን ነው ቢሉ:-

በወቅቱ ዐመፀኛው የአይሁድ መሪ ፊንሐስ በሃገረ ናግራን(የዛሬዋ የመን) ውስጥ የነበሩ ክርስቲያኖችን ክርስቶስን ካዱ በሚል ጨፈጨፋቸው። ከተማዋንም ለአርባ ቀናት በእሳት አነደዳት። ዜናው በመላው ዓለም ሲሰማ በርካቶቹ ቢያዝኑም የተረፉትን ለመታደግ የሞከረ አልነበረም።

ቅዱስ አፄ ካሌብ ግን የሆነውን ሲሰማ ወደ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብቶ በግንባሩ ሰገደ። ወደ ፈጣሪም ጸለየ:- "ጌታዬ ሆይ! የክርስቲያኖችን ደም እመልስ ዘንድ እርዳኝ? እኔ በጦሬ ብዛት አልመካም። እኔ ተሸንፌ ክርስትና ከሚናቅ እዚሁ ግደለኝ" ብሎ በበርሃ ላሉ መነኮሳት እንዲጸልዩ ላከባቸው።

ጊዜ ሳያጠፋ በመርከብና በፈረስ : በበቅሎና በግመል ናግራን (የመን) ደረሰ። ፊንሐስን ገድሎ ሠራዊቱንም ማርኮ ክርስቲያኖችን ነጻ አወጣ። ደምና እንባቸውንም አበሰ። አብያተ መቅደሶችን አንጾላቸው ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ።

ወዲያው እንደተመለሰ ወደ አክሱም ጽዮን ገብቶ "ጌታየ ኢየሱስ ክርስቶስ ስላደረክልኝ የምሰጥህ ሰውነቴን እንጂ ሐብቴን አይደለም" ብሎ መንግስቱን ለልጁ ገብረ መስቀል አውርሶ ከዙፋኑ ወጣ። የወርቅ አክሊሉን ወደ ኢየሩሳሌም ልኮ እርሱ በአባ ጰንጠሌዎን እጅ መንኩሶ መነነ።

ከዚሕች ዓለም ከአንዲት ረዋት(ኩባያ)፣ ከአንዲት ሰሌንና ከአንዲት ቀሚስ በቀር የወሰደው አልነበረም። ከዚያም በበዓቱ ውስጥ በጾምና በጸሎት ተወስኖ አንድም ሰው ሳያይ በሰባ ዓመቱ (በ፭፻፳፱/529 ዓ/ም) ዐርፏል።  ጌታችንም በሰማይ ክብርን አጐናጽፎታል።

ንጉሥ ካሌብን ሳስብ ዛሬ በመላዋ ሃገራችን ሥልጣኑን ይዘው ኢትዮጵያን እየበደሏት ያሉት የኦነግ/ብልጽግና፣ የሻዕቢያ፣ የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኢዜማ፣ የአብን መስለ ወንጀለኛ ፓርቲዎች መሪዎች በደብረ ዘይት ሆራ ሐይቅ የተፈለፈሉ ተባዮች/ቁንጫዎች ሆነው ነው የታዩኝ።

እንደ ንጉሥ ካሌብ ያለ ምርጥ የዓለም መሪ ለሃገራችን ያምጣልን። ለቅዱስ አፄ ካሌብ የተለመነ አምላክ ለእኛም ይለመነን። በጻድቁም ጸሎት ከመከራ ይሠውረን።

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment