አለቃ አያሌው ታምሩ ያስተላለፉት ግዝትና ምክንያቶቹ‼️


በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አመራር ላይ ያዩትን ችግር በማስመልከት የቤተ ክርስቲያኒቱ የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ የነበሩት አለቃ አያሌው ታምሩ ችግሩ ሥር ሳይሰድ ገና ከጅምሩ እንዲታረም ማሳሰቢያና ተማጽኖ ካቀረቡ በኋላ በማስከተልም ቃለ ግዝት አስተላልፈዋል። ቃለ ግዝታቸው በመጀመሪያ የወጣው ሰኔ ፳፯ ቀን ፲ ፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በ«መብሩክ» ጋዜጣ ላይ ነበር። ይኽም እንደሚከተለው ይነበባል።

«👉ሀ፤ በቤተ ክርስቲያን የደረሱ ልዩ ልዩ ችግሮች ሁሉ በሲኖዶስ ተመክሮባቸው እንዲወገዱና እርምጃቸውም እንዲገታ በ፲ ፱፻፹፯ ዓመተ ምሕረት ጥቅምትና ኅዳር ወር ለሲኖዶሱ ማመልከቻ ስጽፍ መልእክቴ በጌታዬ በአምላኬ ትእዛዝ የተደረገ መሆኑን ገለጨ በአፈጻጸሙ ቸልተኝነት እንዳይታይበት ሲኖዶሱን በሾመ በመንፈስ ቅዱስ ዳኝነት ተማጽኜ አቤቱታዬ የእኔ ብቻ ሳይሆን በዐጸደ ሥጋና በዐጸደ ነፍስ ያሉ የኦርቶዶክሳውያን አበውና ምእመናን አቤቱታ መሆኑን ገልጬ ነበር ያቀረብኩት። ነገር ግን የሲኖዶሱ ዋና ጸሓፊ አባ ገሪማና ፓትሪያርኩ ሐሳባቸው እስከ አሁን በቤተ ክርስቲያን የኖረውን የመንፈስ ቅዱስ መሪነት ሽረው የራሳቸውን ጣዖታዊ መሪነት ለመተካት ኖሮ በጥቅምት ወር ፲ ፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት በተደረገው አጠቃላይ ጉባኤ ላይ ያቀረብኩትን አቤቱታ ጭምር ሳይቀበሉ ከመቅረታቸውም በላይ የመንፈስ ቅዱስን ዳኝነት፥ የሲኖዶሱን ሥልጣን ለግል አድመኞቻቸው ኮሚቴ አሳልፈው በመስጠትና በነሱ ውሳኔ ተደግፈው የኑፋቄ መጽሐፍ ማውጣታቸውና መበተናቸው አንሶ ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባኤ አፍርሰዋል።

👉ለ፤ ይህ በዚህ እንዳለ ሲኖዶሱ ተሰብስቦ ጉዳዩን እንዲያይ በግል ማመልከቻ፤ በነጻ ፕሬሱ በኩልም ተቃውሞዬን በማሰማት ላይ እያለሁ ሚያዚያ ፲ ፰ ቀን ፲ ፱፻፹፰ ዓመተ ምሕረት የቅሬታ አስወጋጅና የሰላም ኮሚቴ በሚሉት የግል ኮሚቴያቸው ድጋፍ እኔን ካባረሩ በኃላ ከሚያዚያ ፳፪ እስከ ግንቦት ፮ ባደረጉት በአፈና የሲኖዶስ ስብሰባ ሕግ አስወጥተው በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ ራሳቸው ፓትሪያርኩ ሲኖዶሱ ወንጌልን ለሚሰብክበት፥ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ለሚያስተምርበት ጉዞ አመራር ሰጪ (ጣዖት) ወደ መሆን አድገዋል። በቤተ ክርስቲያን ስም ተሰይመው እግዚአብሔርንና ቤተ ክርስቲያንን ሊያገለግሉ የተሾሙ ኤጲስ ቆጶሳት፥ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት የሲኖዶሱ ዋና ጸሓፊ ሳይቀር ለቤተ ክርስቲያን ተጠሪ መሆናቸው ቀርቶ ለፓትሪያርኩ ተጠሪዎች እንዲሆኑ ሲያደርጉ ሚያዚያ ፴ ቀን ተፈርሞ ጸድቋል፤ የተባለውና በጽሕፈት ቤቱ አማካኝነት ለሚመለከተው ሁሉ እንዲተላለፍ በቃለ ጉባኤ ትእዛዝ የተሰጠበት ሕገ ቤተ ክርስቲያን እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን ስትሠራባቸው የኖሩት ሕጎችና ደንቦች ሁሉ በዚህ ሕግ ተሻሽለው ከስፍራቸው ሲወገዱ፥ አባ ጳውሎስ በመንፈስ ቅዱስ ፈንታ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአመራር ሰጪነት ቦታ ሲይዙ በቤተ ክርስቲያን ላይ የአምልኮ ጣዖት ዐዋጅ ዐውጀውባታል። 

ፓትሪያርኩ በሾማቸው በእግዚአብሔርና በቤተ ክርስቲያን ላይ በፈጸሙት ተግባር ታላቅ በደል ፈጽመዋል። ከራሳቸው ጋር ቃላቸውን ለማጽደቅ፥ ምኞታቸውን ለሟሟላት በሕጉ ላይ ፈርመዋል ተብሎ ስማቸው የተመዘገበላቸው ፴፬ቱ ጳጳሳትና ሊቃነ ጳጳሳት እንደ ተባለው አድርገውት ከሆነ ለፈጸሙት በደል ተባባሪዎች ናቸው።

ይህም እጅግ የሚያሳዝን ነው። የሚገርመው ደግሞ በዚሁ ሕግ አንቀጽ ፲ ፬፤ «ፓትሪያርኩ የተዋሕዶ እምነትን፥ ሕግጋተ ቤተ ክርስቲያንን የማይጠብቅ፥ ማዕረጉን የሚያጎድፍ ሆኖ መገኘቱ በተጨባጭ ማስረጃ ሲረጋገጥ በምልአተ ጉባኤ ያለአንዳች የሐሳብ ልዩነት በቅዱስ ሲኖዶስ ከተጠና በኋላ በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት ከማዕረጉ ይወርዳል፤» የሚል ቃል አስፍሮ ሲኖዶሱን በአፈና ልዩ ሥልጣን ተጠቅመውና እንደ ሌለ አድርገው ካሳዩ በኋላ የኑፋቄ መጻሕፍት በማሳተም የተዋሕዶ ሃይማኖትን አፋልሰዋል፤ ሕገ ቤተ ክርስቲያንን ሳይጠብቁ ቤተ ክርስቲያን ከምታወግዛቸው ጋር የጸሎተ ቅዳሴና የማዕድ ተሳትፎ አድርገዋል፤ ቤተ ክርስቲያኒቱ ከምታወግዘው ፓፓ ቡራኬ ተቀብለዋል፤ እያልን እየተቃወምን ለተቃውሟችንንም ተጨባጭ ማስረጃ እያቀረብን፤ ራሳቸውም ይህንን ሳይቃወሙ ይህ እንዳይቀጥል በሥልጣናቸው ተጠቅመው ኦርቶዶክሳዊውን የሊቃውንት ጉባኤ ሲያፈርሱ ጉዳዩን አይቶ ውሳኔ በመስጠት ፈንታ እንደገና በሕግ፥ በመንፈስ ቅዱስ ስፍራ ተተክተው ለሲኖዶሱ ሥልጣንና ተግባር አመራር ሰጪ ይሆናሉ። የሲኖዶሱ አባሎች ሁሉ ለፓትሪያርኩ ተጠሪ ይሆናሉ ሲል የወጣው አዋጅ አፈጻጸም ነው። 

ይህ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ የታወጀው ሕግ፤ «እስመ ሜጥዋ ለዐመፃ ላዕሌከ፤» «ዐመፅን ወደ አንተ መለሷት፤» ተብሎ እንደ ተጻፈ ቤተ ክርስቲያንን መካነ ጣዖት፥ ምእመናንን መምለኪያነ ጣዖት የሚያሰኝ ስለ ሆነ በሙሉ ድምፅ እንድትቃወሙት በእግዚአብሔርና በቤተ ክርስቲያን ስም እጠይቃለሁ።

👉ሐ፤ ከአሁን ጀምሮ ማለት ይህ ቃል በነጻው ፕሬስ ከተላለፈበት ጊዜ ጀምሮ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቃልና እጅ፥ በሲኖዶሱ ጸሓፊ በአቡነ ገሪማ ቃልና እጅ፥ ይህን የተጻፈውን ሕግ የቤተ ክርስቲያን ሕግ ብለው አጽድቀው በተባባሪነት አሳልፈዋል የተባሉ ጳጳሳት እውነት ሆኖ ከተገኘ የነሱ ተባባሪዎች ናቸውና በነሱ ቃልና እጅ ቡራኬ እንዳትቀበሉ፥ እንዳትናዘዙ፤ ስማቸውን በጸሎተ ቅዳሴ የሚጠሩ አለቆች፥ ቀሳውስት፥ ካህናት ካሉም አምልኮ ጣዖት አራማጅ ናቸውና ተጠንቅቁባቸው፤ ምክር ስጧቸው፤ እንቢ ካሉም ተለዩዋቸው።
እንዲሁም ሐምሌ ፭ ወይም ፮ ቀን ይከበራል ተብሎ ሽርጉድ የሚባልለት በዓለ ሢመት የአሮን የወርቅ ጥጃ መታሰቢያ ሆኖ በቤተ ክርስቲያን ሊከበር የማይገባው ስለ ሆነ በዓሉ ከመድረሱ በፊት የሲኖዶሱ አባላት በአስቸካይ ተሰብስበው ሕጉን ካልሻሩና በጣዖትነት የተሰየሙትን አቡነ ጳውሎስን ከሥልጣናቸው ካላነሡ ይህንን በዓል እንዳታከብሩ ለቤተ ክርስቲያን ደሙን ባፈሰሰ አምላክ ስም፥ ቤተ ክርስቲያንን በሚመራና በሚጠብቅ በመንፈስ ቅዱስ ስም ጥያቄዬን አስተላልፋለሁ።

ምናልባት የሕጉን ጽሑፍ አንብቦ መረዳት የተሳነው፥ ግን በልዩ ልዩ ደጋፊዎቻቸው ተጭበርብሮ በቸልታ የሚመለከተው፤ ከዚያም ዐልፎ በሥልጣናቸው እየተመኩ ለቤተ ክርስቲያን ጥያቄ ጆሯችንን አንሰጥም ብለው ይህን በደል ያደረሱትን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን፥ በሦስት የሹመት ስም የሚንቀባረሩትን አባ ገሪማን፥ ለነሱ ድጋፍ የሚሰጡትንም ሁሉ፤ ጌታዬ አምላኬ፤ «በምድር ያሰራችሁት በሰማይ የታሰረ ይሆናል፤» ሲል በሰጠው ቃል በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን፤ በጴጥሮስ፥ በጳውሎስ፥ በማርቆስ፥ በቄርሎስ፥ በባስልዮስ፥ በቴዎፍሎስ፥ በተክለ ሃይማኖት ዘደብረ ሊባኖስ ቃል፤ ኃጥእ ደካማም በምሆን በእኔም በቀሲስ ወልደ ጊዮርጊስ ቃል አውግዣለሁ።
ይህን ሕግ የተቀበሉ፥ ከሥራ ላይ ያዋሉ ሁሉ እንደ አርዮስ፥ እንደ መቅዶንዮስ፥ እንደ ንስጥሮስ፥ እንደ ፍላብያኖስ፥ እንደ ኬልቄዶን ጉባኤና ተከታዮቹ እሱራን፥ ውጉዛን ይሁኑ። በማይፈታው በእግዚአብሔር ሥልጣን አስሬአለሁ። 

ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋና ይሁን አሜን። 

🔴 ማስጠንቀቂያ፤ አምላኬ ሂድ ተናገር ያለኝን ትእዛዝ ለናንተ አድርሻለሁ። ሩጫዬን ጨርሻለሁ። ከእንግዲህ ተጠያቂነቱ የእናንተ የምእመናንና ታሪክ ተጠያቂ ያደረገው የመንግሥት ነው። ለዚህም ምስክሬ ራሱ እግዚአብሔር፥ ቅዱሳን መላእክት፥ ሰማይና ምድር ናቸው። 

አለቃ አያሌው ታምሩ ዘዲማ ጊዮርጊስ።»


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment