ያን ጊዜ ወንድም ወንድሙን ጎረቤትም ጎረቤትም የሰዉ ጠላቱም የቤቱ ሰዉ ይኾናል ። ያን ጊዜ የመከራዉ መጀመሪያ ይኾናል።


አሕዛብ በስሜ የተጠራችሁትን ለመግደል ይሽቀዳደማሉ አዉሬ ርግብን እንደሚያድን አድነዉ ይይዟችኋል።አሳልፈዉም ለመከራ ይሰጧችኋል።ይደበድቧችኋል። በሰይፍና በሜንጫ በሌላም መግደያ ይገድሏችኋል ። በስሜ አምናችሁ ስለኖራችሁም በአሕዛብ ዘንድ ትጠላላችሁ።
በዚያን ወራት በአራቱም የዓለም ዳርቻዎች ወንጌል ትሰበካለች ። ያንጊዜም የመጀመሪያይቱ የጽድቅ መገኛ የሃይማኖት ከተማ የሳባ ምድር ትታወካለች ። የራሔልን ስምም እየጠራች ፤ ስለ ልጆቿም እጆቿን ዘርግታ ታለቅሳለች ። ከወንዞቿ ግዮንና ተከዚ ዳርቻም እሾህ ይነቀላል ። አሜከላም ይነጥፋል ። ከዚያ በኋላ ግን ፀሐይ በሌሊ ጨረቃም በቀን ይወጡባታልና ምሽቷ እንደ ንጋት ያበራል እንጂ አይጨልምም ።

በዚያን ወራት የሚድኑትስ በዚኽች መጽሐፈ ጸሎት ሰምተዉ የጾሙ የጸለዩ ይኽች የመከራ ሰዓት ሳትደርስባቸዉ ንሥሓ ገብተዉ የተጠበቁ ብቻ ናቸዉ ። ከዚያም በኋላ ምድር ባዶ ትኾናለች አይጥና ፍልፈል ይሠለጥኑባታል  እንጂ በዓለም የአሉ ኹሉ ይጠፋሉና እስከ ኻያ ዘጠኝ አመት ድረስ ምድር ያለሰዉ ምድር በዳ ትኾናለች ።

ከዚያ ኹሉ በኋላ ግን ፈቃዴን የአደረጉትንና የአተረፍኋቸዉን የሚሰበስብ ፤ ስሙ ቴዎድሮስ፤ የተሰኘ ደገኛ ንጉሥን አስነሣለሁ ።ምድርን በጸሎቱ የሚዋጅ ደግ ጳጳስንም አመጣለሁ ። ዳግመኛም  አብያተ ክርስቲያናት ይበዛሉ ። ከዚያ ዘመን በቀር ቁጣዬን አልመልስም ። ይቅርታዬንም አልሰጥም ። ሰላሜንም በምድር ላይ አላወርድም ። ሰላሜን እንደ ሰጠኹም የአተረፍኋቸዉ ወዳጆቼ ብቻ ያዉቃሉ ። ያለ ደመናም ጠለ በረከት የአለዉ ዝናምን እስከ ስምንት ቀን አወርዳለሁ ።
በዚያን ወራትም ሽብር የዓመፃ ነገርም ቢኾን አይኖርም ።ኹሉ በምሥራቃዊው ደግ ንጉሥ ቴዎድሮስ ቃል ይስተካከላል ። በምድር ዉስጥ ኹሉ በረከት የመላል ። የፈረሱትም መንደሮች ኹሉ ይታደሳሉ ። የእግዚአብሔር አምላክን ስም በመፍራት በምድር ላይ ፍጹም ደስታ ይትረፈረፋል። በዚያ ዘመን ጥልና ክርክር የጦር ወሬም አይኖርም ። ዝርፊያና ግድያ የለም በምድር ኹሉ ፍቅርና ሰላም ይሰፍናል ። ሕዝቡና ካህናትም እስከ አርባ አመት እግዚአብሔርን በማመስገን ይኖራሉ።"

ለማንበብ ማስተዋሉን ያድለን አሜን።

ከመጽሐፈ ፍካሬ ኢየሱስ  --------በአማረኛ
ከገጽ 75 እስከ 79 የተወሰደ
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment