✍ አቢይ ሰይፉ
መቼም ዛሬ ሀሳብን እንደፈለጉ አድርጎ በፈለጉት ግዜና ቦታ ለማስተላለፍ ቴክኒዎሎጂው ያወላዳል፡፡ ስለዚህም ሁሉም እየተነሳ የፈለገውን ከሚጽፍበት የድህረ መረብ ውስጥ እኛም የራሳችን ቁምነገር ብናሰፍር መልካም ነው በማለት ይህቺን ጽሁፍ ላንባቢያን አቀረብ፡፡
በመጀመሪያ ጥያቄ ነገር እናንሳ፡፡ እስቲ ስንቶቻችሁ ናቸው በቋንቋችን በፊደላችን ብንማር ብንመራመር ኖሮ የበለጠ እውቀትን አውቀንና ተረድተን ተግባራዊ እሆን ነበር የምንል፡፡ ወይንም በራሳችን ቋንቋና ፊደል ብንማር ኖሮ ቋንቋችን አድጎና ሰፍቶ፤ መጥቆና ገዝፎ ዛሬ ታላላቅና የሰለጠኑ ከሚባልሉት ሀገራት እኩል ተሰልፎ እናየው ነበር የምንል፡፡
እኛን ግን ሁሌም የሚያሳስበን የነበረው የዚህ ጥያቄ መልስ ነው ብንል አልተሳሳትንም፡፡ በራሳችን ቋንቋና ፊደል እየጻፍንና እያነበብን እያሰብንና እያሰላሰልን እየተከራከርን ሳይንስን ብንማረው፤ ታሪኬን ብንመረምረው፤ ሀይማኖትን ብንቃኘው፤ ስነ ጽሁፋችን ብንመለከተው እንደው ሁሉንም ብንተነትነው የት እንደርስ ነበር እያልን ሁሌም ይቆጨናል፡፡
ግን ለምን በራሳችን ቋንቋና ፊደል ጽፈን አንብበንና ተናግረን መማር ተከለከልን፡፡ መልሳችሁ ምንም ይሁን ምንም ይሄንን ያደረገ ኢትዮጲያዊ በኢትዮጲያ ላይ በሀበሻ ህዝብ ላይ የዘመናት የማንነት ስህተት ተክሎ ያለፈ የፈረንጅ ቅጥረኛ ለመሆኑ ልናረጋግጥ እንወዳለን፡፡ ምክንያቱም ከጥንት እስከ ዛሬ የያዝነውን ታላቁን ጥበባችንን እውቀት አድርገን እንዳንጠቀምበትና በአለም መድረክ ላይ ተወዳዳሪ ሆነን እንዳንገኝ አውቆ በድፍረት ሳያውቅ በስህተት በማንነታችን ላይ የተጫወተብን ዋነኛና ቀደኛ ቀንዳም ነው፡፡
ለዚህም ነው በራሳችን ቋንቋና ተናግረን በራሳችን ፊደል ጽፈንና የተጻፈን አንብበን ሳይንስን መረዳትና ማስረዳት እንደምንችል በማመን በራሳችን ተነሳሽነት በራሳችንና ባካባቢያችን በሚገኙ ልጆች ላይ ትንሽ ሙከራ አኪያሂደን ነበር፡፡
ሳይንሳዊና አለማቀፍ ይዘት ያላቸውን ፈረንጃዊ ቃላትን እንደወረዱ በመውሰድ ቃሉን በቀጥታ በአማርኛ በመጻፍ ትንታኔውንም በቀጥታ በአማርኛ በመስጠት ልጆችን ለማስተማር የተደረገ ሙከራ ነው፡፡
ያደረግነው ሙከራ እጅግ አስደናቂ ውጤት አስመዘገበ፡፡ ልጆች በቋንቋቸውና በፊደላቸው ከተማሩ ማንኛውንም ቃል በፍጥነት እንደሚይዙ ለመረዳት በቅተናል፡፡ ልጆቹ የሰጠኋቸውን ቃል በአጭር ግዜ ከማያዛቸው ሌላ ማወቅ ያለባቸውን እውቀት በደንብ በማወቅ በፈለጋቸው መልኩ በፈለጋቸው ግዜና ቦታ ቃሉን ሳይረሱ አጠራሩን ሳያሳስቱ ሊናገሩት ሊያስረዱት ሊጽፉት መቻላቸው አመንን፡፡
አዎ፡፡ ለምሳሌ ፎቶሲንተሲስ የተባለውን ቃል ሳይንስ ስለ እጽዋት ለማስተማር ሲነሳ የሚጠቀምበት የእንግሊዘኛ በቀጥታ በመውሰድ በእንግሊዘኛ ፊደላት ጽፎ ልጆቻችንን ከማደናገር በአማርኛ ፊደላት ቁልጭ አድርገን tቃሉን ጽፈን እውቀቱን በአማርኛ ለልጆቻችን ማስጨበጥ ነበር ተግባራችን፡፡
ይህንን ቃል ወደ አማርኛ ቃል እንተርጉመው ቢባል እጅግ ይከብድ ይሆናል፡፡ ይሁንና እንግሊዘኛውን ቃል ቁልጭ አድርገን በአማርኛ ፊደላት በመጻፍ አለማቀፋዊዉን ሳይንሳዊ ቃል የራሳችን ቃል አድርገን ልጆቻችንን ማስተማር እንደምንችል በዚህ ሙከራች ለመረዳት በቅተናል ለማለት ነው፡፡ ዋናው ማድረግ ያለብን ሳይንሳዊና የውጪ ቋንቋ የሆነው ቃል እንዳለ ወስዶ በራሳችን ፊደል ልቅም አድርጎ በመጻፍ ልጆቻችንን ማስተማር ብቻ ነው፡፡ ከግዜ ከዘመን በኋላ ቃሉን የራሳችን ቃል አድርጎ ማስቀረት፡፡ በመጨረሻም ቋንቋችን ሰፊ ጥልቅና ግዙፍ አድርጎ በራሳችን የቃል ሀይል መንቀሳቀስ ማለት ይሆናል፡፡
ለዚህ ሀሳባችንና ተግባራችን ስኬት ዋናው የጠቀመንና የሚጠቅመን አባቶቻችን አበው ይህንን እውነታና ሚስጥር ተረድተው ቫውልን ከኮንሰናንት ጋር ያጣመረና ለአንድ ድምጽ አንድ የፊደል ቅርጽ የያዘ ፊደል በሰባትዮሽ ወይንም በኦክታቭ ሎው የሚተዳደር እጅግ አስደናቂ ተፈጥሮዋዊ የሆነ ፊደል አስቀምጠውልን ማለፋቸው መሆኑን መረዳት አለብን፡፡
የተፈለገውን የእንግሊዘኛ ቃልና አረፍተ ነገር አማርኛና የአማርኛ ፊደል ቁልጭ አድርጎ አስተካክሎ ጽፎ ሲያነብ በአንጻሩ እንግሊዘኛ ቋንቋና አልፋ ቤት ወይንም ፊደሉ የአማርኛን ቃልና አረፍተነገር በፍጹም በትክክል መጻፍና ማንበብ አይችልም፡፡
ይህ የሆነበት ምክንያት የእንግሊዘኛ ቋንቋ እንደ አማራኛው ቀቋንቀቋና ፊደል በሰባትዮሽ ተፈጥሮዋዊ ህግ ስለማይተዳደርና ስፋትና ሙሉነት ስለሌለው ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም እውነትን በአንክሮ በመርመር ከገባንበት ጅልነት መውጣት አለብን፡፡
አዎ፡፡ ይህንን በማድረጋችን ብቻ ልጆቻችን ከገልባጭነት፣ ከጥገኝነት፣ በራስ ካለመተማመንና በዋናነት የሰው ቋንቋ ሲያጠኑ ግዜና ዘመናቸውን ከሚያሳልፉ እንታደጋቸዋለን እንላለን፡፡ ስርአትና ህግ በሌለው የእንግሊዘኛ ቋንቋ ፓራዶክስ ልጆቻችን ብሎም ሀገርን ባዶ ማድረጋችንን ከምንቀጥል እስቲ ቆም ብለን አስበን በቋንቋችን ሀይል እንጠቀምበት እንላለን፡፡
መላው ስልጡን ሀገራት በራሳቸው ቋንቋና ፊደል ተምረው ሲሰለጥኑ ለምን እኛ ኢትዮጲያዊያን የራሳቸው ቋንቋና ፊደል እያለን በራሳችን ቋንቋና ፊደል እንዳንማር የታገድን ይመስላችኋል፡፡
አዎ፡፡ ለምን በሰው ሀገር ቋንቋ ፊደል ትምህርትን እንድንማር ተፈለገ፡፡ በቀኝ ግዛት አልተያዝን፤ ነጻነታችን ከጥንት እስከ ዛሬ አላጣን፤ የራሳችን ቋንቋ ፊደል እያለን፤ ለምን... መልሱ እሩቅና እረቂቅ ሚስጥር ነው፡፡
ችግሩ ዛሬም እውነቱን ለመረዳት አለመቻላችንና አለመፈለጋችን ነው፡፡ ይሁንና ተፈለገም አልተፈለገም ቋንቋና ፊደል ያለው ህዝብ ጥንታዊ ማንነቱን በዙሪያው አትሞ አስቀምጧል በማለት ዛሬ ሳይንስ መደንፋቱ የተረዳውና ያወቀው ነገር ቢኖር፡፡
በእርግጥ ጥበባቸው እውቀት ሆኖ ያልተፈታላቸው ኢትዮጲያዊ ጠበብታት ቋንቋ ብርሀን ነው ፊደል ሀይል ነው ማለታቸው ለዋዛ ፈዛዛ አይደለም፡፡ ቋንቋና ፊደል ያላቸውን ከባቢያዊ ሀይልና ማንነታችንን እንደሚቆጣጠሩ ቢያውቁና ቢያምኑ ነው፡፡
አንደ የራሺያዊው ጠበብት ትንታኔ ከሆነ ከህዋሳዊ ማንነታችን ጀምሮ እስከ ሀገራዊ ማንነታችን ድርስ ቋንቋና ፊድል የአንድ ህዝብ ማንነቱ የተቆለፈባቸው እውነታዎች ናቸው፡፡ ከሚታየው ከሚሰማው አለም ጀምሮ እስከ የማይታየውና የማይሰማው አለም ያለውን ስነ ፍጥረት የሚያገናኘ ብርሀናዊና እሳታዊ ሀይል ነው በማለት ለብዙ አመታት ያደረጉትን ምርምርና ጥናት አስመልክተው አስተያየታቸውን ሰተዋል፡፡
አዎ፡፡ አብዛኞቻችን ቋንቋችንን ፊደላችንን ንቀነዋል አዋርደነዋል ቋንቋ ፊደላችን ግን እኛን መናቁንና ማዋረዱን አልተገነዘብን፡፡
ልንግባባው ያልፈለግነው የማይታየውና የማይሰማው ማንነታችንን እሱም ሊያየንና ሊሰማን አልፈለገም፡፡ እንደናቅነው ንቆናል እንደጠላነው ጠልቶናል፡፡
አዎ፡፡ ቋንቋና ፊደላችን ከልባችንና ካካባቢያችን ጋር የተሳሰረ ጥበብ መሆኑን መረዳት አለብን፡፡ ሳይንስ ያላወቀውና ያላረጋገጠው ድብቅ ሚስጥራዊ ሀይል እንዳለው አምነን መቀበል አለብን፡፡ ቋንቋ የሚታየውን ከማይታየው የሚሰማውን ከማይሰማውና እርስ በእርስ የሚያግባባ ታላቅና እረቂቅ ጥበብ እንጂ በራሱ የእውቀት መለኪያ አይደለም የሚሉን እራሺያዊ ጠበብት ፡፡
አንድ ቋንቋ ከአፋዊ መግባቢያነት አልፎ ፊደል መስርቶ በፊደሎቹ መጻፍና ማንበብ ከቻለ፤ ያለውንና የሚመጣውን አዲስና ጥንታዊ ከባቢያዊ ማንነትን በትክክል አምልቶና አግዝፎ መዝግቦ ማስተላለፍና ማስቀመጥ ከበቃ ያቋንቋ ለዛ ህዝብ የአስተሳሰቡ መአከል ወይንም ሰርቨር መሆኑን ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ:
አምነን መቀበል አለብን ይላሉ፡፡
ወይንም የራሺያ ቋንቋና ፊደሉ ለሩሲያዊያን የማንነታችን፣ የአስተሳሰባችን የባህሪያችን የጀግንነታችን ሀገር የመውደዳችን ብሎም ያለን የተፈጥሮ ሀብታችን የሀያልነታቸው መአከል ወይንም ሰርቨር ነው በማለት አምልተውና አስፍተው ይናገራሉ፡፡ ሰርቨራችን ከተቀመረበትና ከቋንቋችንና ፊደላችን ከወጣን ወይንም ከባቢያችንን በመጤ ቋንቋና ፊደል ከሞላነው ይሄ ሁሉ አሁን ያለን ይጠፋል ይሰወራል ይሉናል፡፡
ምእራብ አውሮፓዊያኖች በጠቅላላ ከላቲን ፊደል አስተሳሰባዊ ቅኘት ወይንም ባህሪ ሊወጡ ፈጽሞ አይችሉም፡፡ ስለዚህም አስተሳሰባቸው ሁልግዜም አንድ ነው፡፡ ምክንያቱም የሁሉም ፊደል የተፈለቀቀው ከላቲን ቋንቋ በመሆኑ ነው፡፡የአረብ ህዝብም የአስተሳሰብ ሰርቨሩ አረብኛ ቋንቋና ፊደሉ እንደሆነ ሁሉ የአይሁዶች ማንነት የታሰረው በቋንቋቸውና ፊደላቸው ቅኝት ውስጥ ነው፡፡
በመጨረሻም እኛም ኢትዮጲያዊያን የአስተሳሰባችን የስልጣኒያችን ብሎም የሀብታምነታችን ሰርቨር ግእዝና የያዝነው ቋንቋና ፊደል መሆኑን አምነን ተቀብለን ከገባንበት ጅልነትና ጥገኝነት በመውጣት እራሳችንን እንፈልግ አሁንም ግዜው ገናነው እንላለን፡፡
Blogger Comment
Facebook Comment