ዲያብሎስ ሰላሙን፣ ፍቅሩን እና ደስታውን ሊነጥቀን ይሠራል፤ ቅዱስ ሩፋኤልን ግን ሊነጥቀሊነጥቀን አይችልም


✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ

በየዓመቱ ጳጕሜን ፫ ቀን የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሩፋኤል ዓመታዊ ክብረ በዓል በመላው የኢትዮጵያ ርትዕት ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት፣ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥነ ሥርዓት ይከበራል፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሩፋኤል ከከበሩት ቅዱሳን መላእክት ሦስተኛው ነው፡፡ "ከከበሩ ከሰባቱ አለቆች አንዱ አለቃ እኔ ሩፋኤል ነኝ" እንዲል /ጦቢት ፲፪፥፲፭/፡፡

ያለማቋረጥ ፈጣሪያቸውን ልዑል እግዚአብሔርን ከሚያመሰግኑ ቅዱሳን መላእክት መካከል አንዱ መልአከ ጥዒና ወሰላም /የሰላምና የጤና መልአክ/ የሚባለው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ "ሩፋኤል" የሚለው የስሙ ትርጓሜ ደስ የሚያሰኝ፣ ቸር፣ መሐሪ፣ ቅን የዋህ ማለት ነው፡፡

የሰው ልጆች ከተያዙበት የኀጢአት ቁስል ይፈወሱ ዘንድ በአማላጅነቱና በጸሎቱ የማይለይ መልአክ ነው፡፡ "በበሽታ ኹሉ ላይ በሰው ልጆችም ቍስል ላይ የተሾመው ቅዱስ ሩፋኤል ነው" በማለት ሄኖክ ከእግዚአብሔር መልአክ ያገኘውን የምስክርነት ቃል ጽፏል /ሔኖክ ፲፥፲፫/፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል በሰውነታችን ላይ የሚወጣውን ደዌም ኾነ ቍስል ይፈውስ ዘንድ ከልዑል እግዚአብሔር ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ "በሰው ቍስል ላይ የተሾመ ከከበሩ መላእክት አንዱ ቅዱስ ሩፋኤል ነው" እንዳለ ሄኖክ /ሔኖክ ፮፥፫/፡፡

ለቈሰሉ ፈውስን የሚያሰጣቸው ለማኅፀን ችግር ኹሉ ለሴቶች ረዳታቸው ቅዱስ ሩፋኤል ነው፡፡ ሴት በፀነሰችበት ወቅት ቅዱስ ሩፋኤል አይለያትም ሕፃኑ ዐርባ ቀን ሞልቶት፣ በማኅፀን እያለ "ተሥዕሎተ መልክዕ" (በ አርአያ መልኩ መሳል) ከጀመረበት ቀን አንሥቶ እስከሚወለድበት ቀን ድረስ ቅዱስ ሩፋኤል አይለየውም፡፡ በወሊዳቸው ቀን ሴቶች ከሚደርስባቸው ጭንቀትና ሕመም ስሙን ጠርተው ይማጸኑታል፡፡ ፈታሔ ማኅፀን ነውና ቅዱስ ሩፋኤልም ጭንቀታቸውን ያቀላል፡፡

አስማንድዮስ የተባለ ጋኔን በወለተ ራጉኤል ላይ አድሮ ባሎቿን እየገደለ ቢያሰቃያት ቅዱስ ሩፋኤል ጋኔኑን አስጨንቆ አስወጥቶላታል /ጦቢት ፫፥፰-፲፯/፡፡ ቅዱስ ሩፋኤል "ዳግመኛም እግዚአብሔር ሩፋኤልን፣ አዛዝኤልን እጁን እግሩን አስረህ በጨለማ ውስጥ ጣለው አለው" ተብሎ እንደ ተጻፈ /ሔኖክ ፫፥፭-፯/ ለቃየን ልጆች ሰይፍና ሾተል መሥራትን፣ የምንዝር ጌጥ ማጌጥን፣ መቀንደብን ያስተማረ አዛዝኤል የተባለውን ጋኔን በእሳት ሰይፍ እየቀጣ በረቂቅ አስሮ ወደ ጥልቁ የጣለው ይኸው መልአክ ቅዱስ ሩፋኤል ነው /ሔኖክ ፪፥፲፰/፡፡
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment