መጥምቁ ዮሐንስን የምናከብረው ከስጋና ከደም ጋር ስለተጋደለ አይደለም!



[ወደ ኤፌሶን ሰዎች ምዕራፍ ፮፥፲፪]

"መጋደላችን ከደምና ከሥጋ ጋር አይደለምና፥ ከአለቆችና ከሥልጣናት ጋር ከዚህም ከጨለማ ዓለም ገዦች ጋር በሰማያዊም ስፍራ ካለ ከክፋት መንፈሳውያን ሠራዊት ጋር ነው እንጂ።"

እያንዳንዳችን ከጥምቀታችን ቀጥሎ በሚፈጸምልን ምሥጢረ ሜሮን አማካኝነት መንፈስ ቅዱስ ያድርብናል፡፡ ይህንን ተጠቅመን ሥራ ለመሥራት እኛም እንደ መጥምቁ የራሳችን በረሃ ያስፈልገናል፤ በትህርምትና ራስን በመግዛት መኖር አለብን፡፡

ይህንን ማድረግ የሚገባቸውና የሚችሉት በገዳም ያሉ ሰዎች ብቻ አይደሉም፡፡ በዓለም የምንኖር ሰዎችም ብቻችንን የምንሆንበትና በጸሎት፣ በተመስጦ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ፣ ራሳችንን በመመርመር የምናሳልፈው ጊዜ በመመደብ መኖሪያ ቤቶቻችንን ገዳማት ማድረግ እንችላለን፡፡ ሁኔታዎችን እያመቻቸን ወደተለያዩ ገዳማት እየሄድን ጊዜ ማሳለፍም ጠቃሚ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ምግባችንን፣ መጠጣችንን እና ልብሳችንን በልክ እያደረግን መጥምቁን ባለ ብዙ ፍሬ በሆነበት ጎዳናው ልንከተለው ያገባናል፡፡

ሲሰርቁ፣ ሲያመነዝሩ፣ በዝሙት ሲወድቁ፣ ሲሰክሩ፣ ሲዘሉ፣ ሲያብዱና ሲያጨበጭቡ ከመሞት እግዚአብሔር ሁላችንንም ይጠብቀን!

የቅዱስ ዮሐንስ ጸሎቱና በረከቱ ይደርብን! አማላጅነቱ ይደረግልን!

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment