✍ ዘርአዳዊት ዘ-ኢትዮጵያ
በግሌ በጣም ከምወዳቸው ሐዋርያት መካከል ቅዱስ ማቴዎስ አንዱ ነው!
የጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን አምላካዊ ትእዛዝ ተቀብለው ወንጌልን ለመላው ዓለም በማብሠር መምለክያነ ጣዖትን ወደ አሚነ እግዚአብሔር፣ አሕዛብን ወደ ክርስትና ከመለሱ ቅዱሳን ሐዋርያት መካከል ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ አንደኛው ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስ አገሩ ናዝሬት፣ የዘር ሐረጉም ከይሳኮር ነገድ ሲኾን አባቱ እልፍዮስ (ዲቁ)፣ እናቱ ደግሞ ካሩትያስ ይባላሉ፡፡
ለደቀ መዝሙርነት ከመመረጡ በፊት ‹ሌዊ› ይባል ነበረ፤ ከተጠራ በኋላ ግን ‹ማቴዎስ› ተብሏል፡፡ ‹ማቴዎስ› ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ‹ጸጋ እግዚአብሔር (የእግዚአብሔር ስጦታ)› ማለት ሲኾን ስሙን ያወጣለትም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡ ለወንጌል አገልግሎት የተጠራውም በቅፍርናሆም ከተማ ከቀራጭነት ሥራ ላይ ነው /ማቴ. ፱፥፱-፲፫፤ ሉቃ. ፭፥፳፯-፴፪/፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ ቍጥሩ ከ፲፪ቱ ሐዋርያት ሲኾን ከ፬ቱ ወንጌሎች አንደኛውን የጻፈው እርሱ በመኾኑ ‹ወንጌላዊ› እየተባለ ይጠራል፡፡ ወንጌሉን የጻፈውም ጌታችን ባረገ በ፰ኛው ዓመት መጨረሻ በ፵፩ /፵፪ ዓ.ም፣ ቀላውዴዎስ ቄሣር በነገሠ በመጀመሪያው ዘመን በዕብራይስጥ ቋንቋ ነው /ማቴ.፳፰፥፳/፡፡ ጽሕፈቱንም በፍልስጥኤም ጀምሮ በህንድ ፈጽሞታል፡፡
እንደ መምህራነ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ወንጌሉ በውስጡ ከ፻፶ በላይ የብሉይ ኪዳን ጥቅሶችን ማካተቱ አይሁድን ለማሳመን የተጻፈ ለመኾኑ ማስረጃ ነው፡፡ የማቴዎስ ወንጌል ከኦሪታዊ ይዘቱ አኳያ በመጀመሪያ ተቀመጠ እንጂ የተጻፈው ግን ከማርቆስ ወንጌል ቀጥሎ እንደኾነም መምህራን ይናገራሉ፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ በሀገረ ስብከቱ በፍልስጥኤም ጌታችን ከፅንስ ጀምሮ እስከ ዕርገቱ ድረስ ያደረጋቸውን ተአምራት፣ ያስተማረውን ትምህርትና የሠራቸውን ትሩፋቶች ሲያስተምራቸው ብዙ አሕዛብ ከኦሪት ወደ ወንጌል፤ ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ተመልሰዋል፡፡ ምእመናኑ ‹‹በቃል ያለ ይረሳል፤ በመጽሐፍ ያለ ይወረሳልና ያስተማርኸንን ጻፍልን›› ብለውት፤ አንድም እንደ አባትነቱ ከራሱ አንቅቶ /አመንጭቶ/፤ አንድም አይሁድ ክርስቲያኖችን ‹‹ክርስቶስ ወልደ ዳዊት ወልደ አብርሃም መኾኑን ሠፍራችሁ፣ ቈጥራችሁ አስረዱን›› ቢሏቸው ለማስረዳት የዕውቀት ማነስ ነበረባቸውና እርሱ ጽፎላቸዋል፡፡
ወንጌሉን ከጻፈ በኋላም ወደ ኢየሩሳሌም ተመልሶ አፓንጌ በሚባል አገር ወንጌልን በመስበክ ብዙዎችን በክርስቶስ አሳምኗል፡፡ የማቴዎስን ወንጌል ወንጌላዊው /ሐዋርያው/ ዮሐንስ በእልአንሳን፣ በህንድና በኢየሩሳሌም አገሮች እየተረጐመ አስተምሮታል፡፡ የእርሱ ስብከት በመጽሐፍ ቅዱስ አለመጠቀሱም መላ ሕይወቱን ለክርስቶስ አገልግሎት የሰጠ ሐዋርያ መኾኑን እንደሚያሳይ መምህራን ይመሰክራሉ፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ በወንጌሉ ‹‹ወልደ ዳዊት፣ ወልደ አብርሃም›› በማለት የክርስቶስን ምድራዊ ልደት /ሰው መኾን/ ጽፏልና ከአራቱ የኪሩቤል ገጽ መካከል በአንደኛው በገጸ ሰብእ ይመሰላል፡፡ የኤፌሶን ወንዝ ፈለገ ሐሊብ ይባላል፤ ርስትነቱም ለሕፃናት ነው፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም በዘር የሚወለዱ አበውን ልደት ጽፏልና፤ ዳግመኛም ሄሮድስ ስላስፈጃቸው ሕፃናት ተናግሯልና በኤፌሶን ወንዝ ይመሰላል፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ ወንጌልን አስተምሮ ብዙዎችን ወደ አሚነ እግዚአብሔር ከመለሰ በኋላ ጌታችን ወደ ካህናት አገር እንዲሔድና የካህን ልብስ ለብሶ፣ ፀጉሩንና ጺሙን ተላጭቶ፣ በቀኝ እጁ ዘንባባ ይዞ ወደ አገሩ ቅፅር እንዲገባ ስላዘዘው በደመና ተጭኖ ሔዶ ወደ ቤተ ጣዖታቱ ገብቶ በጸለየ ጊዜ መብረቅ የመሰለ ብርሃን ወረደ፡፡ የአምላክን ከሃሊነት ለመግለጥ በተከሠተው ርዕደ መሬትም የአገሩ ጣዖታት ኹሉ ወድቀው ተሰባበሩ፡፡ አርሚስ የሚባለው የጣዖቱ ካህንም ካየው አምላካዊ ብርሃንና ድንቅ ተአምር የተነሣ በክርስቶስ አምኖ ከተጠመቀ በኋላ የቅዱስ ማቴዎስ ረድእ ኾኗል፡፡
ይህ ክሥተትም በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙዎችን በክርስቶስ እንዲያምኑ አድርጓቸዋል፡፡ ያማኞች ቍጥርም ፬ ሺሕ እንደ ነበረ በገድለ ሐዋርያት ተጠቅሷል፡፡ ከዚህ በኋላ የንጉሡ ልጅ በሞተ ጊዜ ቅዱስ ማቴዎስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ ከሞት ቢያስነሣው ንጉሡ፣ ቤተሰቦቹና የአገሩ ሰዎች ኹሉ በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው አጵሎን የተባለውን ጣዖት በእሳት አቃጥለው ቤተ ጣዖቱን የአምልኮተ እግዚአብሔር መፈጸሚያ ሥፍራ አድርገውታል፡፡ ቅዱስ ማቴዎስም አርሚስን ኤጲስ ቆጶስ በማድረግ ቀሳውስትንና ዲያቆናትን ሾሞላቸዋል፡፡
በገድለ ሐዋርያት እንደ ተጠቀሰው ቅዱስ ማቴዎስ ከማረፉ በፊት በደመና ተነጥቆ ብሔረ ብፁዓን ገብቷል፤ በዚያም ሄሮድስ በግፍ በጨፈጨፋቸው ሕፃናት ክብረ በዓል ጌታችን ወደ እነርሱ ሲመጣ፣ መላእክትም በዙሪያው ከበው ሲያመሰግኑት ያይ ነበር፡፡ ከዚያ ተመልሶም በየአገሩ እየዞረ ወንጌልን አስተምሯል፤ ካስተማረባቸው አገሮችም ፍልስጥኤም፣ ፋርስ፣ ባቢሎን፣ ኢትዮጵያና ዓረቢያ ይጠቀሳሉ፡፡ የማስተማር ተልእኮው የተከናወነውም በታንሿ እስያ ውስጥ ነው፡፡ ግሪካውያን አሕዛብ «አምላካችንን ሰደበብን» ብለው አሥረውት በነበረ ጊዜም ወኅኒ ቤት ኾኖ ይሰብክ ነበር፡፡
ቅዱስ ማቴዎስ በ፵ ዓ.ም በአገራችን በኢትዮጵያ እየተዘዋወረ ወንጌልን እንደ ሰበከና በዘመኑ የነበሩ ኦሪታውያን ነገሥታትን ጨምሮ በርካታ አሕዛብን አስተምሮ በማጥመቅ ወደ ክርስትና ሃይማኖት እንደ መለሰ፤ እንደዚሁም ለምጻሞችን በማንጻት፣ አንካሶችን በማርታት፣ ሕሙማንን በመፈወስ፣ ሙታንን በማስነሣት ድንቅ ድንቅ ተአምራትን እንዳደረገ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንትና በትግራይ ክልል በማኅበረ ጻድቃን ዴጌ ገዳም የሚገኙ የብራና መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡
በአገልግሎቱ መጨረሻም በትርያ በምትባል አገር ሲያስተምር አገረ ገዥው አሠረው፡፡ በወኅኒ ቤቱም ጌታው ለንግድ የሰጠውን ገንዘብ ማዕበል ወስዶበት በዕዳ ምክንያት የሚያለቅስ አንድ እሥረኛ አገኘና አጽናንቶ መኰንኑ ገንዘቡን ከሕዝቡ ለምኖ እንዲከፍለው በመሻት ከእሥር እንደሚፈታው፤ ከባሕር ዳርቻም የወደቀ ወርቅ የተሞላ ከረጢት እንደሚያገኝ፤ ያንንም ለጌታው ከሰጠ በኋላ ከዕዳና ከእሥር ነጻ እንደሚኾን አስረዳው፡፡ ሰውየውም ቅዱስ ማቴዎስ የተናገረው ኹሉ ስለ ተፈጸመለት ለቅዱስ ማቴዎስ እየሰገደ፤ ‹‹በኢየሱስ ክርስቶስ አምናለሁ›› እያለ ሃይማኖቱንና ደስታውን ገለጸ፡፡ ይህንን ድንቅ ተአምር የሰሙ ብዙ አሕዛብም በጌታችን አምነዋል፡፡ በዚህ ምክንያትም አርያኖስ በሚባል ንጉሥ ትእዛዝ ጥቅምት ፲፪ ቀን አንገቱን በሰይፍ ተቈርጦ በሰማዕትነት ዐርፏል፤ ምእመናንም ሥጋውን በክብር ቀብረውታል፡፡ ትርጓሜ ወንጌል ደግሞ ብስባራ በምትባል አገር በደንጊያ ተወግሮ በሰማዕትነት ካረፈ በኋላ የቂሣርያ ክፍለ ዕጣ በምትኾን በቅርጣግና መቀበሩን ይናገራል፡፡
ለእግዚአብሔር ምስጋና ይኹን፡፡ እኛንም በሐዋርያው በቅዱስ ማቴዎስ ጸሎት ይማረን፤ በረከቱም ይደርብን፡፡
ምንጭ፡-
መጽሐፈ ስንክሳር፣ ጥቅምት ፲፪ ቀን፤
የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት፤
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፤
የማቴዎስ ወንጌል አንድምታ ትርጓሜ፤
ገድለ ሐዋርያት፡፡
Blogger Comment
Facebook Comment