የኢትዮጵያ ታሪካዊ ዘውድ ተመለሰ


ከመቐለ 16 ኪሎ ሜትር በደቡብ ምሥራቅ አቅጣጫ የሚገኘውና ረዥም ዕድሜ ያስቆጠረው የሥላሴ ጨለቆት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በርካታ ንዋየ ቅድሳት እንዳሉ ይነገራል። በተለይም ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስትያኑ እልፍ ንዋየ ቅዱሳን ማበርከታቸውን ቤተ ክርስትያኑ ግቢ ውስጥ ለዓመታት የኖሩ አባቶች ምስክርነታቸውን ይሰጣሉ።

ለአሥራ ስድስት ዓመታት መንነው በቤተ ክርስቲያኗ የሚኖሩት የ82 ዓመት የዕድሜ ባለፀጋ አባ ገብረሥላሴ፤ ሦስት ዘውዶችን ራስ ወልደሥላሴ ለቤተ ክርስቲያኗ መስጠታቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።

በጎርጎሳውያኑ አቆጣጠር ከ1745-1865 በወቅቱ የእንደርታ ዙሪያ የሚባለውን ሰፊ ግዛት ያስተዳደሩት ራስ ወልደሥላሴ በአራት ቦታዎች ማለትም በጨለቆት፣ በሕንጣሎ፣ በፈለግዳዕሮና በመቐለ ቤተ መንግሥቶችን ገንብተው ነበር። በአንድ ወቅትም ጨለቆትን ዋና ከተማቸው አድርገዋታል።

ራስ ወልደሥላሴ ካበረከቷቸው ዘውዶች መካከል አሁን በኔዘርላንድ የተገኘው ዘውድ አንዱ ሲሆን፤ ከ24 ዓመታት በፊት መሰረቁንና ከዚያም መሰወሩን ተናግረዋል።

ከኢትዮጵያ ተሰርቆ የተወሰደው ዘውድ ኔዘርላንድ ውስጥ መገኘቱንና በዛሬው ዕለት ወደ አገሩ መመለሱን ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሳውቀዋል።
ይህ ዘውድ ንብረትነቱ የጨለቆት ሥላሴ መሆኑ የማያጠራጥር በመሆኑ ወደቦታው ተወስዶ በክብር ሊቀመጥ ይገባዋል።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment