በምዕራብ ጎጃም ዞን ቋሪት ወረዳ በቋሪት እየሱስ ቀበሌ ልዩ ስሙ ዳሞት ተራራ በተባለ ጎጥ በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ዝናብ በመኖሪያ ቤቶች፣በእንስሳትና በሰብል ላይ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ትናንት የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም ከቀኑ 9፡00 ሰዓት ገደማ በረዶ ቀላቅሎ የጣለው ከባድ ዝናብ በሰብሎች ላይ ማለትም ሽምብራና ጓያ እንዲሁም በውሃገብ ልማቶች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱን የአካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ሙላቴ ደሳለው ገልፀው፤ በቤቶች እና በእንስሳት ላይም ጉዳት አድርሷል ብለዋል፡፡
በእለቱ ከዘነበው በረዶ ጋር አሳ ከሰማይ ወርዷል ሲሉ ነዋሪዎች በጠቆሙን መረጃ መሰረት እኛም በቦታው ተገኝተን እንደተመለከትነው በቁጥር ከስድሰት ያላነሱ መጠናቸው መለስተኛ የሆኑ አሳዎችን ተመልክተኛል ሲል የቋሪት ወረዳ ኮሙኒኬሽን ዘግቧል፡፡
አሳዎች በሰዎች የመጡ እንዳይሆኑ ብለን ስንጠይቅ በዚያ ሰዓት ማንም ያመጣል ተብሎ አይታሰብም በእርግጠኝነት ከበረዶ ጋር የወረደ ነው ሲሉ የአካባቢው ነዋሪ አቶ ላቀው እጅጉ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የቋሪት ወረዳ ኮምኒኬሽን ነው፡፡
በዘንድሮው ዓመት ከሰማይ ላይ የወረደ እሳትን ጨምሮ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብም ሆነ ከተለመዱ ተፈጥሮአዊ ክስተቶች የተለዩ ብዙ ሁነቶች እየተፈጠሩ መሆኑ ይታወሳል።
ምንጭ፦ አማራ ሚድያ ማዕከል/አሚማ
Blogger Comment
Facebook Comment