"ኢትዮጵያዊ ነን” በሚለው ብዙኃንና “ኢትዮጵያዊ አይደለንም” በሚሉ ኦነጋውያን መካከል የሚካሄደው “አገራዊ ምክክር ጉባዔ”

✍ አቻምየለህ ታምሩ

ቢቢሲ ስለ ምክክር ኮሚሽን ተብዮው መሰንበቻ ዛሬ ያወጣው ዘገባ፣ መድረኩን በየዋህነት “አገራዊ ምክክር” የሚደረግበት ገለልተኛ መድረክ ነው ብለው ለሚያምኑት ሁሉ፣ በውስጡ እየተፈጸመ ያለውን ዐቢይ አሕመድ መር ኦነጋዊ ሸፍጥ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው።

ዘገባው እንደሚያሳየው፣ ምክክር ተብዮው እየተደረገ ያለው “ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን፤ አዲስ አበባም የኢትዮጵያ ዋና ከተማና፣ በአስተዳደሯም ራሷን የቻለች የሁሉም ኢትዮጵያውያን የፌዴራል ከተማ ትሁን” በሚሉ ብዙኃን ኢትዮጵያውያን እና “አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሳትሆን የኦሮሞ ብቻ ናት፤ ስለሆነም የኦሮሚያ አካል መሆን አለባት” የሚል አቋም በያዙ፣ ኢትዮጵያዊ አይደለንም በሚሉ ኦነጋውያን መካከል ነው። በእነዚህ ሁለት አቋሞች መካከል ያለው ልዩነት ተራ የሐሳብ ልዩነት ሳይሆን፣ መሠረታዊ የሀገር ማንነት ጥያቄ ነው።

ከሁሉም ይበልጥ አስገራሚው ደግሞ፣ “አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሳትሆን የኦሮሞ ብቻ ናት፤ ስለሆነም የኦሮሚያ አካል መሆን አለባት” የሚል አቋም የሚያራምዱትን፣ ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚሉትን የኦነጋውያን ቡድን የሚመራው፣ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትርነት የተሰየመው ዐቢይ አሕመድ የሚባለው ጉድ መሆኑ ነው።

በሌላው ዓለም፣ የአንድ ሀገር መሪ ዋናው ተግባር የዚያችን ሀገር የጋራ መሠረት፣ የጋራ ዋና ከተማና የጋራ ማንነት ማጠናከር ነው። ዐቢይ አሕመድ የሚባለው ኦነጋዊ ጉድ ግን፣ በጠቅላይ ሚኒስትርነት ተሰይሞ የሚገዘግዛትን አገር “አላውቅሽም” ብሎ፣ “ኢትዮጵያዊ አይደለንም፤ አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ሳትሆን የኦሮሞ ብቻ ናት፤ ስለሆነም የኦሮሚያ አካል መሆን አለባት” የሚለውን ኦነጋዊ ቡድን ይመራል።

መስፍን አርአያ የሚባለው የዐቢይ አሕመድ ከዳም በተደጋጋሚ ኮሚሽኑ “ተመካካሪዎች የሚመካከሩበት መድረክ ነው” ሲል ይሰማል። ይህ ከሆነ ታዲያ፣ “አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ መሆኗን ዕውቅና ይሰጣት” የሚለው ጉዳይ፣ ከታች ጀምሮ በተካሄደው ምክክር ተብዮው ያልተነሳ፣ ያልተወያዩበትና “ተመካካሪዎቹ” ያልጠየቁት ጉዳይ ሆኖ ሳለ፣ ድንገት “ከበላይ የመጣ ሐሳብ” ተብሎ በቃለ ጉባኤ ውስጥ እንዴት እንዲገባ ተደረገ?

በእውነቱ ይህ ብቻ የምክክር ተብዮውን ኦነጋዊ ማጭበርበሪያ መሆኑን ለማሳየት ከበቂ በላይ ነው። ከታች ያልተነሳን ጉዳይ ዐቢይ አሕመድ ከላይ ስላወረደው ብቻ፣ ተመካካሪዎቹ ተብዮዎች ያልጠየቁትን እንደጠየቁ አስመስሎ፣ ያልተወያዩበትን እንደተወያዩበት አድርጎ በቃለ ጉባኤ ማስፈር ምክክር አይደለም። ይህ አብነት የሚያሳየው ምክክር ኮሚሽን ተብዮው ምድረካ ኦነጋዊ የማይጠረቃ ፍላጎትን በሕዝብ ስም ለማስፈጸም የተዘረጋ ኦነጋዊ ማጭበርበሪያ ስለመሆኑ በተደጋጋሚ የተናገርነውን የሚያረጋግጥ ብቻ ነው።

የነ ዐቢይ አሕመድ ኦነጋዊ ቲያትር በዚህ ብቻ አያበቃም። አብዛኞቹ “ተመካካሪዎች” አዲስ አበባ ራሷን የቻለች የፌዴራል ከተማ ትሁን ሲሉ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ የኦሮሚያ ትሁን ማለታቸውን የቢቢሲ ዘገባ ያሳያል። ይህ እውነታ “አብዛኞቹ እንዲህ አሉ፣ ጥቂቶቹ ደግሞ እንዲህ አሉ” ተብሎ በቃለ ጉባኤ እንዲሰፍር ሲባል ግን፣ “አብዛኞቹ” እና “የተወሰኑ” የሚሉት ቃላት እንዲጠፉና ሁለቱም “አማራጭ አንድ፣ አማራጭ ሁለት” ተብለው እንዲመዘገቡ ተደርጓል።

ይህ ተራ የቃላት ምርጫ አይደለም። ይህ ብዙኃኑን ከቃለ ጉባኤ ላይ የማጥፋት፣ ጥቂቶችን ወደ ብዙኃን ደረጃ የማሳደግ፣ እውነተኛውን የድምፅ ሚዛን ደብቆ የጥቂቶቹን ፍላጎት ሕዝባዊ አማራጭ አስመስሎ የማቅረብ ኦነጋዊ አሻጥር ነው።

ቁጥርን አጥፍቶ፣ የብዙኃኑንና የጥቂቶቹን ልዩነት ደብቆ፣ ሁለቱንም እኩል “አማራጭ” ብሎ መመዝገብ እውነታን መዝግቦ ማስቀመጥ አይደለም፤ እውነታን ቀይሮ ለተፈለገው ፖለቲካዊ ውጤት ማመቻቸት ነው። መስፍን አርአያ “ሁሉም ነገር በቃለ ጉባኤ ተይዟል” የሚለን ሆዳም ስለኾነ እንጂ ቁጥር እየተደበቀ፣ የብዙኃኑና የጥቂቶቹ ልዩነት እየተፋቀ፣ ሁለቱ እኩል አማራጭ እየተደረጉ ከተጻፈ፣ የእውነታ መዝገብ ሳይሆን እውነታ የተጣመመበት ድሪቶ መሆኑ ጠፍቶት አይደለም።

ከዚህ በተጨማሪ፣ ቢቢሲ ባቀረበው ዘገባ መሠረት፣ “አጠናቃሪዎች” የተባሉት ሰዎች ራሳቸው እንደ ተመካካሪ ሆነው ኦነጋዊ ሐሳብ እንደሚሰጡ፣ “ይህ መሆን አለበት” ብለው እንደሚከራከሩ መስፍን አርአያ ራሱ አምኗል። ኦነጋዊ ፍላጎታቸውን በተመካካሪው ላይ እንዲጭኑ የተሰማሩ ኦነጋውያንን መስፍን አርአያ  የሚባለው ጉድ ግን እንደ ባለሙያ ነው የሚቆጥራቸው።

የኦሮሞ ባለሥልጣናት በአካልና በስልክ ጭምር ጫና ለመፍጠርና ጣልቃ ለመግባት ሞክረዋል የሚል አቤቱታ በተሳታፊው ሁሉ ቀርቧል። ከታች ያልተነሳ አጀንዳ “ከበላይ” እየወረደ፣ አጠናቃሪዎች ከአጠናቃሪነት ወጥተው ተከራካሪ እየሆኑ፣ በባለሙያነት ስም ኦነጋዊ ፍላጎትን እየጫኑ፣ ባለሥልጣናትም ጫና ያደርጋሉ የሚል ቅሬታ እየቀረበበት ያለው የመስፍን አርአያ ኮሚሽን አሁን መጠየቅ ያለበት “ሂደቱ ችግር አለበት ወይ?” የሚል ሳይሆን፣ “ከዚህ ውስጥ ምክክር  ሊባል የሚችል የቀረው ምንድን ነው?” የሚል ነው።

ይህ ሁሉ አንድ ላይ ሲታይ፣ ምክክር ኮሚሽን ተብዮው የሕዝብን ፍላጎት በገለልተኝነት የሚመዘግብ መድረክ ሳይሆን፣ ቀድሞ የተያዘን ኦነጋዊ አጀንዳ በ“ሕዝባዊ ምክክር” ማኅተም ለማጽደቅ የተዘጋጀ መሣሪያ መሆኑን ነው። ከታች ያልመጣን ከላይ አውርዶ፣ ያልተባለን እንደተባለ ጽፎ፣ የብዙኃኑን ድምፅ አጥፍቶ፣ የጥቂቶቹን ፍላጎት ከብዙኃኑ ጋር እኩል አማራጭ አድርጎ ማቅረብ ከሆነ፣ ይህንን “ምክክር” ማለት ለቃሉ ራሱ ስድብ ነው።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment