ይህ ከክፍል ፬ ላይ ተቋርጦ የነበረው ክፍል ፭ ነው። መልካም የማስተዋል ክትትል ይሁንላችሁ።
ሌላው ደግሞ ክርስቲያን ወገኖቼን በተጨማሪ የማሳስባችሁና የማስጠነቅቃችሁ ጉዳይ፦ በዘፈናችሁ ጊዜ ከላይ ዘርዝሬ እንደነገርኳችሁ ሁሉ ለዘፈናችሁ ሰአት ይኑራችሁ። ማለትም፦ ለምሳሌ ያህል በጥምቀት ጊዜ ስትዘፍኑ ታቦቱ ከቤተ መቅደሱ ሲወጣና ወደ ማደሪያው ባሕረ ጥምቀቱ ስትሸኙት ወደ ድንኳኑ እስክታስገቡት ድረስ፣ እንዲሁም በበነገታው ጽላቱ ከአደረበት ድንኳን ተነስቶ ወደ መቅደሱ እስኪገባ ድረስ ወንዱም ሴቱም ሁላችሁ በአለባበሳችሁ አሸብርቃችሁና ደምቃችሁ፣ በዘፈናችሁ ውዝዋዜ፣ በዘፈናችሁ ግጥም፣ በዘፈናችሁ ዜማ፣ በዘፈን ሆታችሁ፣ በዘፈን እልልታችሁ፣ በፊት በኋላ፣ በቀኝ በግራ ፣ በሩቅ በቅርብ እየሆናችሁ በማጀብ አስነኩት እላችኋለሁ። ይህ ደግሞ ለእናንተ ለምእመናኑ በሃይማኖታችን ትምህርትና እምነት መሠረት ከራሱ ከእግዚአብሔር፣ ከነብያት፣ ከሐዋርያት፣ ከሊቃውንት የተፈቀደላችሁ እና ፍጹም መብታችሁ መሆኑን በፍጹም እውነትና ትምህርት፣ በኩራት መንፈስ ተሞልቼ ነው የምነግራችሁ እንጅ እንደ አልጫ ወሬኞችና ሰባኪዎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥሬ ቃልና ጥሬ ንባብ፣ ነጠላ ቃልና ነጠላ ንባብ ብቻ እያነበብኩ ለራሴ ነጠላ እና ጥሬ ሁኜ እናንተንም ነጠላ እና ጥሬ አድርጌአችሁ የምቀር በአእምሮየና በልቦናየ ደንቆሮና ዕውር ሰባኪ አይደለሁም። ታቦቱ ከማደሪያው ድንኳን ተነስቶ ወደ መቅደሱ ከገባና፣ ፲፪ ሰአት ከሞላና ካለፈ በኋላ ግን፣ ማለትም፦ ፀሐይ የዙረት ሰአቷን ጨርሳ ብርሃኗን ነስታ ከገባችና ተራውን ለከዋክብት ካስረከበች በኋላ ግን በምንም ምክንያት፣ በምንም ተአምር ዘፈን አያስፈልግም። ዋ! ዋ! ዋ! ይህን የሰአት እላፊ ዘፈን የሚያደርገው ጎንደር ከተማ ላይ መስቀል አደባባይ ላይ ድንኳን ተክሎ ካርኒቫል በማለት ዘመናዊያን የፍቅር ዘፋኞችን ከየትም እያመጣ ከማታ ጀምሮ እስከ ሌሊት ድረስ የሚያዘፍኑትና የሚዘፍኑት የአጋንንት ዘፋኝ የሆነው የአማራ መንግሥት ተብየው በድኑ ብአዴን ነው። ስለዚህ የእኔ ትምህርትና መልእክት እነዚህን የአጋንንት ዘፋኞችን አይመለከትምና አስተውሉ። ዘፈናቸው ምንም ይሁን ምን የሰአት እላፊ ዘፈን የአጋንንት ዘፈን ስለሆነ ለመስማት እንዳትሄዱላቸው። የእናንተ የጽዮናዊያን ክርስቲያኖች ሀገራዊይና ሃይማኖታዊ ዘፈናችሁ ፀሐይ ከመግባቷ በፊት በሰአታችሁ ነው መሆን ያለበት። ታቦቱ ከገባና ፀሓይ ከገባች በኋላ በቃ በቃ ነው። አቁም አቁም ነው። ሰአት ካለፈ በኋላና በዓሉ ከተፈጸመ በኋላ በጨለማና በሌሊት የሚዘፍን ሥርዓትና ሰአት የሌለው ዘፈን ሃይማኖታችን አይፈቅድም። እኛም አንፈቅድም። ጠቢቡ ሰሎሞንም ለሁሉም ጊዜ አለው ብሎ ያስተማረንንና ሐዋርያው ጳውሎስም ሁሉን በሥርዓትና በአገባብ አድርጉት ብሎ ያስተማረንን ማሰብና መፈጸም አለብን። ከዚህ መልእክቴ ወጥታችሁ ግን ያለ ሥርዓትና ያለ ሰአት እንዘፍናለን ብትሉ ግን ከፈጣሪ ጋር ለመጣላት ኃላፊነቱ የራሳችሁ ይሆናል እንጅ የኔና የእኛ አይሆንምና ተጠንቀቁ እላችኋለሁ። ከዚህ የበለጠ ነፃነትስ ምን ትፈልጋላችሁ?? የረሳሁትና አሁን ትዝ ያለኝ ደግሞ፦ አንዳንዴ ታቦት ወደ ማደሪያው ድንኳን ሆነ ወደ መደበኛ መቅደሱ በጊዜ ላይገባና እስከ ጨለማ ሰአት ድረስ ሊያመሽ የሚችልበት ሁኔታ አለ። ለምሳሌም ጎንደር ከተማ የፊት ሚካኤል ታቦት በምንም ይሁን በምን ምክንያት እኔ ባላውቅም በጨለማ ነው የሚገባ። ስለዚህ ይህ አይነት ሁኔታ ሲያጋጥማችሁ ግን ታቦቱ እስኪገባ የግድ በዘፈን ማጀብና ማድመቅ አለባችሁ። ፀሓይ ገብቷል፣ ጨልሟል ብላችሁ ታቦቱን እንደ ሬሳ በዝምታ ልታስገቡት አትችሉም እላችኋለሁ። በዚህ እውነተኛ ትምህርትና መልእክት መሠረት አውቃችሁና ጸንታችሁ መኖር አለባችሁ። የመናፍቃን ሰልፈኞች የሆኑትን አልጫዎችን ሰባኪዎችና አልጫ ስብከታቸውን ወደዛ በሏቸው። ምእመናን ሆይ! እስቲ አንድ ጥያቄ ልጠይቃችሁና አስተውሉ። ይኸውም፦ የመጽሐፍ ትርጓሜ መምህራን ሊቃውንት ከሆኑት አንዳቸውም በየትኛውም ሀገርና በተስኪያን ውስጥ ዘፈን ፍጹም ኃጢአት ነው ስለዚህ እንዳትዘፍኑ ብለው ሊገዝቱ ይቅርና ሲያስተምሩና ሲናገሩ እንኳ በሕይወታችሁ ዘመን ሰምታችሁና አይታችሁ ታውቃላችሁን? በፍጹም በፍጹም። ምክንያቱም ትምህርቱንና ምስጢሩን በደንብ ያውቁታልና። የዕውቀቱ ባለለቤት እነማን ሆኑና? ሊቃውንቱ ናቸዋ!! እንደ ሰካራም እና እንደ በሽተኛ ሰው ድንገት ብድግ እያለ የሚረብሻችሁና የሚያስቸግራችሁ እኮ የወንጌል ደላላ የሆነው አልጫ ሰባኪው ነው። ከዚህ ላይ አስተዋይ አእምሮና ልቦና ያላችሁ ምእመናን ታዲያ ይህ ከሆነ ሊቃውንቱ የወንጌል ደላላ የሆኑትን አልጫ ሰባኪዎቹን ለምንድን ነው ተዉ እረፉ የማይሏቸውና የማይከለክሏቸው? ልትሉኝ ትችላላችሁ። መልሱ ግን በጣም አጭር ነው። ይኸውም፦ ""ሊቃውንቱ አልጫዎቹን ከእነ አልጫቸው በጣም በጣም ይንቋቸዋል። ሊያነጋግሯቸውም አይፈቅዱም አይወዱም። እኩያዎቻቸው አይደሉምና። ሰባኪ ነኝ የሚለው ሁሉ በአልጫ ወሬው ምንም ስለማያመጣ ተወው ይጩህ እያሉ ዝም ይሏቸዋል"" እላችኋለሁ። ከዚህ ላይ ግን ሊቃውንቱ የረሱት ወይም አውቀው የተውት ነገር አለ። ይኸውም ፦ በአልጫ ስብከታቸው ምእመናንን እንደሚያሳስቷቸውና እንደሚጎዷቸው እያወቁ ችላ ማለታቸው ትልቅ ስሕተትና ጥፋት ነው። እናም ሊቃውንቱ ሆይ! ለምእመናኑ ስትሉ አስቡበትና ዝምታችሁን ስበሩ። ንቀታችሁንም አስወግዱ እላችኋለሁ። እናማ በዚህ ዙሪያ እኔ አምኃ ኢየስስ ብቻ ነኝ እናንተን ምእመናንን በአጉል አልጫ ስብከታቸው እንዳያበላሿችሁ እያልኩ በማሰብ የምደክመው እላችኋለሁ።
በሉ ጤናኛ አድማጮቼ የሆናችሁት ጽዮናዊያን ክርስቲያን ቤተሰቦቼ ሁሉ፦ ስለ ዘፈን የጀመርኩትን የዛሬን መደበኛ መልእክቴንና ትምህርቴን የማጠቃልልላችሁ፣ የወንጌል ደላላ አልጫ ሰባኪዎች ለሆኑት ተከታያቸው ከሆኑት መካከል አንድ ቱቦ አፍ ከዚህ በፊት ስለ ዘፈን የሰጠውን የድንቁርናውን ኮሜንት በማንሳትና ድንቁርናውን በመግለጽ ይሆናልና ተከተሉኝ። ከዚህ በፊት በድምፅና በጽሑፍ ዘፈን ኃጢአት ስላለመሆኑና ስለመሆኑ ባጭሩ ያስተላለፍኩትን መልእክቴን ያንብበው አያንብበው፣ ከሰው ይስማው አይስማው ባላውቅለትም አነጋገሩ ግን በወሬ ከመስማትና ከመናገር በቀር እንዳላነበበውና እንዳልሰማው ያስታውቅበታል። ያንን ቃል የተናገረው አንብቦትና ሰምቶት ከሆነም ምንም የማይገባው ደንቆሮ ነው ማለት ነው። እናንተየዋ! ይኸ ማኅበራዊ ድረ ገጽ የሚባለውን ግን ጭንቅላት የሌለው ሁሉ ነው እንዴ ትራስ ለማድረግ የሚሞክረው? ጭንቅላት ሳይኖረው እንዴት ትራስ ይጠቀማል? እናማ ያ ቱቦ አፍ የሆነ የስም ክርስቲያን የሆነው ሰው ቃሉን ምን ብሎ እንደለጠፈ ሳየው በድንቁርናው አዘንኩለት። ለነገሩ አልጫ ሰባኪ ከሆኑት አባቶቹ የሰማው ስለሆነ አልፈርድበትም። የለጠፈውም ቃል እንዲህ ይላል፦ ""አማራ ዘፈን ስለሚወድ ነው እንጅ እኔ በግሌ ዘፈን መቼም ቢሆን ጽድቅ ነው ብየ አላምንም"" አለ። አንተ ደንቆሮ የስም ክርስቲያን ሆይ፦ በል እንግዲህ በተናገርከው ድንቁርናህ ምክንያት መልሸ በጥያቄ ልገርፍህ ነውና ተቀበል። ፩ኛ/ ዘፈን ጽድቅ ነው ብየ የጻፍኩበትና የተናገርኩበት መልእክቴ ከየትኛው ቁጥር ላይ ነው? እስቲ ተናገራት። ""ዘፈን ኃጢአት አይደለም፣ ኃጢአትም ነው"" ብየ በርእስ ያስቀመጥኩትንና ትክክል የሆነ ጥቂት ገለጻ ከማድረጌ በቀር ገና ራሱን የቻለ ብዙ የትርጉም ትምህርት ያለበትንና ያልተሰጠበትን ርእስ ሰምተህም ይሁን አይተህ የጻፍኩትንና የተናገርኩትን እንኳ በደንብ ሳታዳምጥና ሳታስተውል ቸኩለህ ስሜታዊ ቱቦ አፍህን ከፈትክ። ደንቆሮ! ደሞ ዘፈን ጽድቅ ይኑርበት አይኑርበት ገና አልተናገርኩም። የቀጠሮየ ጊዜው ሲደርስ ስለ ዘፈን ምንነት በድንቁርናህ ተቃውሞ የተናገርክ ምናምንቴ ሁሉ ያኔ እያንዳንድህ ከጠረጋው ከተረፍክ በአካል በአደባባይ ላይ እንደ ሐምሌ ዝናብ ስለማወርድብህ ጠብቀኝ። ፪ኛ/ ""ዘፈንን የማይቃወም አማራ ዘፈን ስለሚወድ ነው"" ብለሃል። አዎ ልክ ነህ። በአግባቡ፣ በሥርዓቱ፣ በወጉ፣ በልማዱ፣ በጊዜው፣ በምክንያቱ፣ በቦታው ሲሆን እንወዳለን። የማንነታችን መታወቂያችን፣ መገለጫችን፣ ቋንቋችን፣ ታሪካችን ወዘተ ወዘተ ነውና። እንዳንተ እኮ ማንነት አልባ አይደለንም። እናማ አሁን ተጨማሪ ጥያቄየን የማቀርብልህ፦ ""አንተ ግን ነገደ ትውልድህ ምንድን ነው?"" እስቲ ተናገር። ትግሬ ነህን? ምንም እንኳ ትግሬ የሚለው ስም የነገድ መጠሪያ አለመሆኑ የታወቀ ቢሆንም! ታዲያ የምን መጠሪያ ነው ካልከኝ? ይቆየን እልሃለሁ። እንግዲህ ትግሬ ይህን ሲሰማ ደሞ ይኸ ሰው ምን ሊለን ፈልጎ ነው? ብለው ቧ ማለታቸው አይቀርም። እናማ ትግሬ ከሆንክ ትግሬስ ዘፈን አይወድምን? ዘፈንስ የለውምን? እንዲያውም ትግሬ ከሆንክ ከአማራ ይልቅ ዘፈን የሚወድ ትግሬ ነው። ይህንንም እንዴት እንደሆነ አንተ አታውቀውም። እኔ ግን ስለማውቀው ልንገርህ። ትግሬ መድረክ ላይ የሚቆመው ድምጻዊው ዘፋኝ አንድ ሆኖ ገና መሰንቆውን መግረፍ ሲጀምርና በድምፁ ከበሮ ከበሮ ከበሮ ሲል እና ማዜም ሲጀምር የተቀመጠው ተመልካች ትግሬ ሁሉ፣ ልጅ ያዘለችው ሳትቀር ነው ከመቀመጫቸው ብድግ ብለው እየተሽከረከሩና እየዘለሉ የሚያስነኩት። ተቀምጦ የሚመለከት የሌለ እስከሚመስል ድረስ ነው ብድግ የሚሉ። በደርግ ጊዜ መስከረም ፪ ቀን በአደባባይ ላይ እንደሚደረገው የድል ሰልፍ ማለት ነው። ያኔ መስከረም ፪ ቀን ሁሉም የከተማው ሕዝብ በየቀበሌው የሰልፍ ትርኢት አቅራቢ ይሆንና ተመልካቹ ማን እንደሆነ አይታወቅም ነበር። እናም ተመልካች የሌለው ሰልፍ እስከሚሆን ይደርስ ነበር እልሃለሁ። የትግሬ ዘፈን ወዳድነትም እንዲሁ ተመልካች እስከሚያንስበት ድረስ ነው ሁሉም ተነስቶ በመድረክ ላይ የሚያስነካው። በዚህ መሠረት እንዲያውም ትግሬ ከሆንክ አንድ እውነታ ታሪክ ልንገርህና ዕወቅ። ይኸውም፦ በእነ መለስ ዜናዊ ምክንያት ዛሬ በጸያፍ ቃል የብሔር ብሔረ ሰቦች ቀን እየተባለ በየሀገሩ በዘፈን እና በአለባበስ ብቻ እንደሚከበረው የዘፈን በዓል በንጉሥ ኃይለ ሥላሴ ዘመን አንዴ የኢትዮጵያ ነገዶች ሁሉ የየራሳቸውን ዘፈን ሊያቀርቡ ተዘጋጅተው ከያሉበት ሀገር ወደ አዲስ አበባ ሄዱና ንጉሡ ተጋብዘው እሳቸው ባሉበት የሁሉንም ነገድ ዘፈናቸውን በየተራ አዩ አዩ አዩ እና መጨረሻ ሲያበቃ ንጉሡ ከመቀመጫቸው ብድግ ሲሉ ""ከአበደ አይቀር ትግሬ ይበድበት"" ብለው ሄዱ አሉ። ንጉሡ ይህን ማለታቸው ለምን እንደሆነ አሁንስ ገባህ ይሆን? መቸም አይገባህምና ልንገርህ አዳምጥ። የሁሉም ነገዶች ዘፈናቸውን ለዘፈኑ የተመደቡት ሰዎች ብቻ በመድረክ ላይ ሆነው እየዘፈኑ ሲያሳዩ ሌላው የየራሳቸው ነገድ የሆነው ተመልካች ወገናቸው ሁሉ እንደ ንጉሡ በክብር ተቀምጦ ዝም ብሎ ነበር የሚመለከት። የትግሬ ዘፋኞች ተራቸው ደረሰና ለዘፈኑ የተመደቡት ዘፋኞች ከመድረክ ላይ ሆነው ገና የመሰንቋቸውን፣ የዜማቸውንና የከበሮአቸውን ድምፅ ማሰማት ሲጀምሩ ተቀምጦ ተመልካች የነበረው ሕዝባቸው እንዲያው ባንድ ጊዜ ከየተቀመጠበት እየተነሣ ወደ መድረኩ በመሄድ እየተሽከረከረና እየዘለለ ከዘፋኞቹ በልጦ ሲያስነካውና ሁሉም ሲደበላለቅ ንጉሡ ሲያዩ ዘፋኙ የትኛው፣ ተመልካቹ የትኛው እንደሆነ ለመለየት ግራ ስለገባቸው ተደንቀው ነው እንደዛ ያሉት እልሃለሁ። ስለዚህ አንተ አእምሮ ቢስ ሆይ! ዘፈንን ከአማራ ይልቅ ማን እንደሚወድ አሁንስ ገባህ? ትግሬዎቹም እስካሁን ድረስ በዘፈናቸው ጊዜ እንዲህ መሆናቸው ኃጢአትም አይደለም፣ ጸያፍም አይደለም፣ ነውርም አይደለም። እንዲያውም ይህ ሁኔታቸው ለሌሎች ነገዶች የሚያሳየን ዘፈንንና ዘፈናቸውን እንዴት እንደሚወዱትና እንደሚያከብሩት፣ እንዴት እንደሚኮሩበትና እንደሚደሰቱበት ነው። ትግሬ ሆይ! ጎበዝ! ጎበዝ! በርቱ! በጣም ደስ ይላል። ሆኖም ግን እኔ በበኩሌ ትንሽ ቢስተካከል ለማለት የምሞክረው የማኅሌት ዜማ፣ የሰአታት ዜማ የመሰለውንና ሆድ የሚበላውን የድሮውን የመሰንቆ ዘፈናችሁን ዘፋኙ ብቻውን ወይንም ከተወሰኑ ተወዛዋዦች ጋር ሆኖ ሲዘፍኑ ቢታዩ እና ቢደመጡ፣ ቀሪው ተመልካቹ ሁሉ እየተነሣ የድምጻዊውንና የተወዛዋዦቹን ዘፈን በመዋጥ ውበቱን ባይቀንሰው የበለጠ ደስ ይል ነበር እላለሁ። ሆኖም ግን የዘፈናችሁን ምንነት አዋቂዎች እናንተ ባለቤቶቹ ናችሁ እንጅ እኔ አይደለሁም። ስለዚህ ሙሉ አስተያየትና ሐሳብ ከመስጠት እቆጠባለሁ እላችኋለሁ። ወደ ሰውየው ልመለስና፦ ኦሮሞ ከሆንክ ደሞ ኦሮሞስ ዘፈን አይወድምን? ዘፈንስ የለውምን? አሁንም ከትግሬ አስለጥቆ ከአማራ ይልቅ ዘፈን የሚወደው ኦሮሞ ነው ማለት ይቻላል። ምክንያቱም የኦሮሞ አንዱ ዘፋኝ ገና በመድረክ ላይ መዝፈን ሲጀምር አብዛኛውን ተመልካች እየገባ በመዝለል ነው የሚያስነካው። በተለይ በተለይ ደሞ የሸዋ ኦሮሞዎች። ደሞ ዜማቸውም ውዝዋዜአቸውም ያምራል። ወደ ሰሜነኞቹ ዜማና ውዝዋዜ ይቃረባል። አማራ ግን ዘፋኙ ቆሞ ሲዘፍን ሕዝቡ አብዛኛውን ተቀምጦም ሆነ ቆሞ ያያል እንጅ ከጥቂቶች በቀር አብዛኛው ሰው ወደ ዘፋኞች እየገባ ስሜቱን አይገልጥም። ዘፋኞቹንና ዘፈኑንም አይውጠውም። እናማ አንተ ሰው! ጉራጌ ከሆንክ ደሞ ጉራጌስ ዘፈን አይወድምን? ዘፈንስ የለውምን? ወላይታ ከሆንክ ደሞ ወላይታስ ዘፈን አይወድምን? ዘፈንስ የለውምን? በጥቅሉ የኢትዮጵያ ነገዶች ሁሉ አፋር፣ ጌዲኦ፣ ሲዳማ፣ ኵናማ ወዘተ ወዘተ የየራሳቸው ዘፈን የላቸውምን? ዘፈናቸውንስ አይወዱምን? እኮ በል! ከየትኛው ነገድ እንደሆንክና ዘፈን እንደሌለህ ንገረን። ወይስ የትውልድ ነገድ የሌለህ፣ ማንነትና የማንነት መታወቂያና መገለጫ የሌለህ ምናምን ነህ? እኮ ንገረና? በል ምንም ሳትማርና ሳታውቅ መናገር እንዳይለምድብህ ቱቦ አፍህን ወይ ዝጋው፣ ወይም አጥብበው እልሃለሁ።
እውነተኛ ጽዮናዊያን ክርስቲያን አድማጭ ቤተሰቦቼ ሆይ! የዛሬውን ጊዜአዊ እና መደበኛ የነበረውን የዘፈን ትምህርታዊ መልእክቴን ከዚህ ላይ ቋጨሁ፣ አበቃሁ። ይሁንና በክፍል ፬ መልእክቴ መጨረሻ ላይ ክፍል ፭ መጨረሻየ እንደሚሆን ማሳሰቢያ ሰጥቼ ነበር። ሆኖም ግን እግረ መንገዴን ከዘፈኑ ትምህርታዊ መልእክት ውጭ የሆነ ሌላ አጭር እና ለጊዜው ባጭሩ የግድ መቅረብ ያለበት ትምህርታዊ መልእክት ተጨምሮብኛል። ስለሆነም ይህንን መልእክት ደግሞ ማስተላለፍ ያለብኝ የግድ ከዘፈኑ መልእክት አውጥቼና ለይቼ ለብቻው ነው። ስለዚህ አሁን ባጭሩ የማሳስባችሁ ትምህርታዊ መልእክቴ ወደ ክፍል ፮ አሻቅቧል። እናማ የመጨረሻውንና መቋጫ የሆነውን ክፍል ፮ "ን" የፍልሰታ ጾም ከመግባቷ በፊት ስለምለቀው ተከታትላችሁ እንድታነቡ አሳስባችኋለሁ።
በእውነተኛው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖታዊ አስተምህሮ ""ዘፈን ኃጢአት አይደለም፤ ኃጢአትም ነው"" የሚለውን የማይለወጠውን፣ የማይቀነሰውንና የማይጨመርበትን የዛሬውን ክፍል ፭ የዘፈን ትምህርታዊ መልእክቴን ከዚህ ላይ ቋጨሁ። ቀሪውና የመጨረሻ መዝጊያ የሆነው ክፍል ፮ መልእክቴ ስለሚለጥቅ ተከታተሉና ተመልከቱ።
Blogger Comment
Facebook Comment