✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር
በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ በኦርቶዶክሳውያንና በታሪካዊ ገዳማት ላይ እየተፈጸመ ያለው ውድመትና ጭፍጨፋ ይፋዊ በሆነ መልኩ የተቀናጀ አካሄድ ነው:: ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ክርስትና ሃይማኖት ጠል በሆነው አምባገነን አገዛዝ ቤተክርስቲያኗን ለማዳከምና ለማጥፋት የተቀመረና አደገኛ ዘመቻ ነው::
በዛሬው ዕለት በምዕራብ ወሎ መካነ ሰላም አጠገብ በዓባይ ወንዝ ዳርቻ በሚገኘው የዓባይ ገዳመ አስቀጤስ የሰማእቷ ቅድስት አርሴማ አንድነት ገዳም ላይ የተፈጸመው የድሮን ጥቃት የዚሁ አረመኔያዊ ዘመቻ አካል ነው። ጥቃቱ የተፈጸመው የዕለቱን መቁኑን በማዘጋጀት በተግባር ቤት ላይ በነበሩ ንጹሐን መነኮሳይት ላይ ነው:: በዚህ አሰቃቂ ጥቃት ካህናትንና ዲያቆናትን ጨምሮ በርካታ መነኮሳይት ተገድ*ለዋል:: በዚህ የድሮን ጭፍጨፋ ከ፳ በላይ መነኮሳይት በጽኑ ቆስለዋል::
ይህ በንጹሐን ለሀገር በሚጸልዩ መነኮሳይት ላይ የተፈጸመ ጭፍጨፋ በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በደብረ ኤልያስ ገዳም ላይ ከተፈጸመው ዘግናኝ ጭፍጨፋና ውድመት የቀጠለ አደገኛ አካሄድ ነው። በዚያን ወቅት በገዳማትና በመነኮሳት ላይ ያን ያህል አሰቃቂ ጥቃት ሲፈጸም ምእመኑም ሆነ የቤተክርስቲያኗ ከፍተኛ አባቶች የጠበቀና ጠንካራ ምላሽ አለመስጠታቸው እንዲሁም የሕዝቡ ዝምታ በመንግሥት ዘንድ እንደ ድክመት ተቆጥሯል። የሥርዓቱ መሪዎች የሕዝቡን የልብ ትርታና ምላሽ በጥንቃቄ ከለኩ በኋላ ያለምንም ፍርሃትና ተጠያቂነት ገዳማትን የማፍረስና አባቶችን የማሳደድ እርምጃቸውን አጠናክረው ቀጥለውበታል።
ይህ አካሄድ ቀደም ሲል በከፍተኛ የጦር ጄኔራሎቻቸው አንደበት ገዳማትም ቢሆኑ ይመታሉ ሕዝቡም ይመታል ተብሎ በይፋ እንደተነገረ ሁላችንም እናውቃለን:: በሁሉም ገዳማት እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ምንም ዓይነት የፋኖ አባላት ወይም የመሳሪያ ታጣቂዎች በሌሉበትና በፍጹም መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ በሚገኙ ገዳማት ላይ "የፋኖ አባላት አሉበት" የሚል ሀሰተኛ ምክንያት እየተፈበረከ ጥቃት ይፈጸማል። ከአሩሲ ጭፍጨፋ እስከ ወሎ መካነ ሰላም ገዳም ድረስ እየተካሄደ ያለው ይህ እርምጃ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንን መዋቅርና ታሪካዊ ቅርስ ለማጥፋት የተቀረፀ አደገኛ ስትራቴጂ በተግባር እየዋለ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሕያው ማስረጃ ነው። መንግሥት አላማው ቤተክርስቲያንና ኢትዮጵያ ላይ ነው! ሁለቱን ካላፈረሰ አዲሲቷን አብይ በህጻንነቱ እናቱን ሲታዘዝ በምናቡ መኪና እያሽከረከረ ሱቅ ከንፎ በደቂቃ ይመለስ እንደነበረው አይነት ሀገር ለመመስረት ከንቱ ቅዠት ላይ ስለሆነ ነው:: አብይ ያሰባት ሀገር ባትመጣለትም አሁን ቤተክርስቲያንና ኢትዮጵያን ወደማይወጡበት አዘቅት ስለከተታቸው የምናንቀላፋበት ሰዓት ማብቃት አለበት::
በዚህ ብልጽግና ወደ ስልጣን ከመጣብን ጀምሮ ከኦሮምያ እስከ አማራና ትግራይ ክልል የተጨፈጨፉ ክርስቲያኖችና የወደሙ አብያተ ክርስቲያናት ስፍር ቁጥር የላቸውም:: ህዝብ የሚያውቀው ሚዲያ ላይ የሚወጣውን ብቻ ሆኖ እንጂ ለኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በታሪክ እንደዚህ ያለ አስከፊ ዘመን ገጥሟት አያውቅም:: የተዘረፉ ንዋየ ቅዱሳቶቿን እግዚአብሔር ይቁጠራቸው! የተዘጉ ገዳማትና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት ስፍር ቁጥር የላቸውም:: ኧረ የግፍም እኮ ልክ አለው! ውድ ኦርቶዶክሳዊያን ወጣቶች ሆይ ቤተክርስቲያን መጠበቅ የእኛ አደራ ነውና አንዘናጋ:: አንድ ከሆን ቤተክርስቲያን እንጠብቃለን የሚጨፈጨፉ ወገኖቻችንን እንታደጋለን:: እንደ እስከ አሁኑ እያንቀላፋን ከቀጠልን ለቀጣይ ትውልድ የምናስተላልፋት ቤተክርስቲያንም ሆነ ሀገር አይኖሩም ፤ የጥፋት በትሩም በሁላችን በር እያንኳኳ ይመጣል! የመንግሥት ደጋፊ የሆኑ አባቶች ክርስቲያኑ ሁሉ ሽባ እንዲሆን የሚያደነዝዝ ትምህርት በየ አውደ ምህረቱ እየሰበኩ እያገዙት ነው:: ክርስቲያኑ ነጠላ ለብሶ ብቻ ጻዲቅ ጻድቅ እንዲጫዎት እያደረጉ ያሉ መምህራን ከመንግሥት ጋር ሆነው ቤተክርስቲያንን ለማጥፋት እየተባበሩ እንደሆነ መገንዘብ አለብን:: ክርስቲያን የመዳኑ ቀን ዛሬ ሰዓታችንም አሁን ሲሆን ታሪካዊ የአደራ ስራችንም እንዲሁ በጊዜ ልንፈጽም ግድ ይለናል:: ለነገ በስንፍና አናልም ፤ ዛሬ አሁኑኑ ልባችን ይነሳ እጃችን ስራ ይጀምር!
ማሳሰቢያ:- በየገዳማቱ ያላችሁ አባቶች ጥንታዊና ምትክ የሌላቸው ንዋየ ቅዱሳትን እንደ ቀድሞ አባቶቻችን ሰውራችሁ ማስቀመጥ ይኖርባችኋል:: ከግራኝ መሀመድና ከዮዲት ጉዲት የላቀ አጥፊ አብይ መጥቶብናልና! ሁላችንም አባቶች የታሪክ አደራ አለብንና እንደ ቀድሞ አባቶቻችን ብልጥ እንሁን:: ብዙ ገዳማት ውስጥ ያሉ ንዋየ ቅዱሳት ጥንታዊ ታቦታትን ጨምሮ አገዛዙ እያወደመ ነው:: ስለዚህ ወቅቱን በመዘነ መልኩ ከጠላት በሁሉም መልኩ ረቀን መገኘት ያለብን ሰዓት ላይ ነን! እንንቃ!
Blogger Comment
Facebook Comment