✍ ቆሞስ አባ ጳውሊ | ከግንባር
የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን በየካቲት ወር 2014 ዓ.ም. በአዋጅ ቁጥር 1265/2014 ሲቋቋም በጦርነትና በማኅበራዊ መከራ ለደቀቀችው ሀገር መከራ ማራዘሚያ ለአገዛዙ ስልጣን ጠባቂ ሆኖ ነው:: የኮሚሽኑ ዋና ዓላማና ተልዕኮ ሥር የሰደዱ የታሪክ፣ የፖለቲካ እና የማኅበረሰብ ጥልቆችን በውይይት መፍታት፣ በዋና ዋና አገራዊ ጉዳዮች ላይ የጋራ መግባባትን ማምጣት እና ዘላቂ ሰላምን ማስፈን የሚመስል ቢሆንም ሂደቱ ከህዝቡ እውነተኛ ፍላጎትና ሰቆቃ ጋር ፈጽሞ የራቀ ነው። ይህ ጉባኤ በአገዛዙ ዘንድ ለሀገሪቱ የመጨረሻዋ የድኅነት በር ተደርጎ ቢደሰኮርም በተግባር ግን በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው መንግሥት ሥልጣኑን ለማራዘም፣ ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊና ፋይናንሳዊ ጫናዎችን ለማለፍ እና የራሱን ስልታዊ የበላይነት ለማረጋገጥ የሚጠቀምበት የፖለቲካ ቁማር እና የይስሙላ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ ነው። ዛሬ ኢትዮጵያ የምክክር ኮሚሽኑ በድራማ በሚያቀርበው ትረካና መሬት ላይ ባለው እጅግ አስፈሪ ነባራዊ እውነታ መካከል ሴራና የህዝብ ንቀት ፍትንትው ብለው ገነው ይታያሉ::
አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መንግሥት የምክክር ኮሚሽኑን ገለልተኝነት ከድብብቆሽ አውጥቶ ይፋዊ በማጉላትና የጉባኤውን ስውር ተልእኮ በመግለጥ ለህዝብ ያውና ምን ታመጣላችሁ በሚል ፈሊጥ ሂደቱን የራሱን ፍላጎት የሚያስፈጽሙ ሰዎችን ብቻ መርጦ የሚያሳታፍበት የካድሬዎች ስብሰባ አድርጎታል። እውነተኛና አሳታፊ ምክክር ሊባል የሚችለው የችግሩ ባለቤቶችና ትክክለኛ የሕዝብ ድምፅ የሆኑ አካላት ሲካተተበት ብቻ ነበር። ነገር ግን የዚህ ጉባኤ የሀሳዊነት ዋናው ማሳያ በግጭትና በጦርነት ማዕበል ውስጥ የሚገኙት የሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል ህዝቦች በዚህ የምክክር ሂደት ውስጥ በአግባቡ አለመካተታቸው ነው። እጅግ ከፍተኛ ስቃይ፣ መፈናቀልና ሰቆቃን እያስተናገዱ ያሉ አካባቢዎችን እንዲሁም ክፍለ ሀገሮችን በገጠር የሚኖረውን ህዝብ ድምጽ ሙሉ በሙሉ ሳያካትቱ እንዲሁም ያኮረፉና በግጭት መካከል የሚገኙ ወገኖችን እውነተኛ ተሳትፎ ሳያረጋግጡ የሚደረግ ማንኛውም ምክክር ነባሩን ችግር ከመፍታት ይልቅ ይበልጥ ማባባሱ የማይቀር ሀቅ ነው።
ከዚህም በላይ በመንግሥት በኩል ስልታዊ ጥቃትና ሁለንተናዊ ጫና እየደረሰባት ያለችው ታሪካዊቷ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና ሌሎችም ድምፅ አልባ የተደረጉ ወገኖች በዚህ ሂደት ውስጥ ትክክለኛ ውክልና አልተሰጣቸውም:: ምክክር ብሎ ያቀረባቸው ሰዎች ሆሉ ከሁሉም አካታች ሆነው የተውጣጡ ሳይሆን የብልጽግና አመራርና የስርዓቱ ተጠቃሚ የሆኑ ብቻ ናቸው:: እንደሚታወቀው በአሁኑ ሰዓት ቅድስት ቤተክርስቲያን ግፍ እየተደረገባት ሲሆን አሁን ምክክሩ ላይ ያየናቸው የሃይማኖት አባት ተወካይ ሆነው የቀረቡት ከአገዛዙ ጋር ሆነው የችግሯ መንስኤ የነበሩትና አሁንም እየሆኑ ያሉት ናቸው:: ይህ የሚያሳየው አገዛዙ ቤተክርስቲያንን ምን ያክል እንዳቃለላትና እንደናቃት ነው:: የበርካታ ሚሊዮኖችን ህዝብ መንፈሳዊና ማህበራዊ ህይወት የምትመራው እና ሀገራዊ አንድነትን ስትጠብቅ የኖረችው ይህቺ ታላቅ ተቋም በመንግሥት አካሄድ ባለመስማማቷና በምክክሩ አለመካተቷ ሂደቱ የህዝብን እውነተኛ ድምጽ እንደማይወክል ፍጹም ማሳያ ነው። ይልቁንም በመንግሥት መዋቅር የተመለመሉ የገዥውን ፓርቲ ብልሹ የሆነ የፖለቲካ መስመር የማይቃወሙ አድርባይና ጥቅመኛ አካላት ብቻ እንዲሳተፉ በማድረግ ሂደቱ መንግሥት ራሱ አጀንዳ ቀርጾ፣ ራሱ ተሳታፊ መርጦና ራሱ አጽድቆ ምክክር አካሄድኩ የሚልበት የይስሙላ ቲያትር ነው።
ይህ የማስመሰል የፖለቲካ ድራማ የሚካሄደው ደግሞ አገሪቱ በታሪኳ አይታው በማታውቀው እጅግ አስከፊ የጦርነት እና የውድመት አዙሪት ውስጥ እያለች መሆኑ እጅግ ያሳዝናል። ሀገራችን እነዚህ ሰዎች እጅ ላይ መውደቋ እንቅልፍ ይነሳል! በአሁኑ ሰዓት አቢይ አሕመድ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል እያካሄደው ያለው ግልጽ ጦርነት የአገሪቱን ማኅበራዊ መዋቅር ፈጽሞ እያፈራረሰው ይገኛል። ወደ ስልጣን ከመጣብን ጀምሮ ሕዝብ ላይ የሚወርደው ከባድ መሣሪያ፣ የድሮን ጥቃት፣ የከተሞች መከበብ እና የንጹሐን ዜጎች እልቂት ሀገሪቱን ወደማትወጣበት የደም ገንዳ ውስጥ ከቷታል። መንግሥት በአንድ በኩል በአዲስ አበባ አዳራሾች ውስጥ የሰላምና የምክክር ፕሮፓጋንዳ እየሰበከ በሌላ በኩል ግን በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በገዛ ሕዝቡ ላይ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችንና ያለ የሌለ ኃይሉን አሰማርቶ የጥፋት እልቂት እያዘነበ ግብዝነቱንና ህዝብ መናቁን ቁልጭ አድርጎ እያሳየን ነው።
ዛሬ ኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ አቅጣጫዋን የሳተች እና በከፍተኛ ስጋትና ምስቅልቅል ውስጥ ያለች ሀገር ሆናለች። ትክክለኛ ቢሆን የጉባኤው የምክክሩ ዋና ትኩረት መሆን የሚገባው የዜጎች መፈናቀል፣ የኢኮኖሚ ውድቀት፣ የጸጥታ እጦት እና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መሆን ነበረባቸው፤ ይሁን እንጂ ሂደቱ ከህዝቡ እውነተኛ ስቃይ ይልቅ ከላይ የታዘዙ እና የፖለቲካ አጀንዳዎችን በማስፈጸም ላይ ብቻ የተመሰረተ ነው። ህዝቡ በነጻነት ሃሳቡን የሚገልጽበት፣ ያለ ስጋት የሚወያይበት ትክክለኛ ምህዳር ሳይዘጋጅ የሚደረግ የውሸት ውይይት ፍሬ ቢስ እና ጊዜንና ገንዘብን ማባከን ብቻ ነው። ጉባኤውን አገዛዙ ለፕሮፖጋንዳ እንዳይጠቀምበት ህዝብ ነቅቷል! ስለዚህ ገንዘብን ማባከን ብቻ ይሆናል ትርፉ! በአንድ በኩል የኢኮኖሚው ውድቀትና የኑሮ ውድነቱ ሕዝቡን ለከፋ ረሃብና ስደት ዳርጎታል በሌላ በኩል ደግሞ የሕግ የበላይነት ሙሉ በሙሉ በመጥፋቱ ምክንያት እገታ፣ ግድያና ዘረፋ የዕለት ተዕለት ክስተቶች ሆነዋል። በዚህ ዓይነቱ እጅግ አስፈሪ ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ስለ ብሔራዊ ምክክር ማውራት የሕዝብን በደልና ቁስል መሳለቂያ ማድረግ ነው። የዐቢይ አሕመድ መንግሥት ይህንን የሕዝብ መከራ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እና ለለጋሽ ድርጅቶች «እያማከርን ነው የዴሞክራሲ ሥርዓት እየገነባን ነው» በሚል የውሸት ገጽታ ለመሸጥና የገንዘብ እርዳታ ማግኛ የዲፕሎማሲ ጋሻ አድርጎ እየተጠቀመበት ይገኛል። ይህ ዓይነቱ የማስመሰል እና የፕሮፓጋንዳ ፖለቲካ የኢትዮጵያን መከራ የሚያራዝም እና አገሪቱን ወደ ፍጹም መበታተን የሚወስድ እንጂ ፈጽሞ እውነተኛ ሰላምን ሊያመጣ የሚችል አይደለም።
የምክክር ኮሚሽኑ አካሄድ የብልጽግናን ስርዓት ስህተቶች ለማስመሰል የሚያገለግል ጊዜያዊ መዋቅር ከመሆን የዘለለ ትርጉም የለውም። የችግሩ ዋና ምንጭና ፈጣሪ የሆነው ገዥው አካል ራሱን እንደ መፍትሔ አቅራቢ አድርጎ ለመሳል የሚጫወተው አደገኛ የቁማር ጨዋታ የኢትዮጵያን ቁስል ይበልጥ እያመረቀዘው ይገኛል። ይህ የህጻን ልጅ አይነት አኩኩሉ ጨዎታ ሀገሪቱን ይበልጥ የሚጎዳ አደገኛ ፕሮፖጋንዳ ነው:: ሀገሪቱ የምትፈልገው እውነተኛና ገለልተኛ የሆነ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ድምጽ በእኩልነት የሚሰማበት ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ያካተተ ብሔራዊ ሰላም ውይይት እንጂ የአንድ ወገንን ጠባብ ፖለቲካዊ ፍላጎት የሚያስፈጽም ሂደት አይደለም።
እውነተኛ መረጋጋትና ሰላም ሊመጣ የሚችለው የሴራ የባለጊዜነት ፖለቲካው ቆሞ በጦርነት ውስጥ ያሉ የተበደሉ በአገዛዙ ስልታዊ ዘር ማጥፋት የታወጀባቸው ህዝቦች እውነተኛ ወኪሎችና የመከራው ገፈት ቀማሽ የሆኑ እንደ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ያሉ ታሪካዊ ተቋማትንና በአጠቃላይ በግጭት ውስጥ ያሉ አካባቢዎችን ፍትሃዊ ውክልና ያካተተ እውነተኛ መድረክ ሲፈጠር ብቻ ነው። በኢትዮጵያውያን ባህልና ወግ ሥርዓት መሰረት የተጣሉ ሰዎችን ሽማግሌዎች ሲያስታርቁ የበደለው ክሶ የተበደለው ተክሶ ከሁሉም ጎራ ቀርበው ጥፋት በማዬትና በመመርመር ዳግመኛ ጥፋት እንዳይፈጥሩ ሁለቱን አካላት አስማምተው ነው:: ጥፋት የተገኘበት ድጋሚ ጥፋት እንዳያጠፋ የተበደለውም እንዳይበቀል በመካከላቸው የስምምነትና የቃልኪዳን ህግ ያስቀምጣሉ:: የምክክር ኮሚሽኑም እውነተኛ ቢሆን ኖሮ የሀገሪቱን ችግሮች በጥልቅ መርምሮ ሁሉን አካታች በሆነና የፖለቲካ ወገኝተኝነቱንና ጥቅምን አስወግዶ ለህዝብ እርቅና ሰላም እንዲፈጠር ያደርግ ነበር:: በመጀመሪያ ደረጃ የሰላም ጉባኤ የሚካሄደው ህዝብ የሚያነሳውን ጥያቄ ለማስመለስ ነው:: ሆኖም ግን ኮሚሽኑ ከአገዛዙ ጋር ሆኖ የመንግሥትን ቀጣይ የዙፋን መጽናትና የስልጣን መራዘምን እያበረታታ እያገዘ ነው:: ትክክለኛ የህዝብ ውክልና ሳይኖራቸው የሀገሪቱን ከፍተኛና አንገብጋቢ ጉዳዮችን ከአገዛዙ ጎን ሆነው ለአገዛዙ እየፈጸሙ ነው:: አሁን እየተካሄደ ያለው የምክክር ኮሚሽን ሂደት የኢትዮጵያን ሕዝብ መከራ የሚያባብስና ታሪካዊ ተጠያቂነትን የሚያስከትል የመንግሥት ስልታዊ ሴራ ነው። በዚህ ጉባኤ ውስጥ የሚሳተፉ ሁሉ በቀጣዩ የሚመጣው ስርዓትም ይሁን የህዝብን ግፍ በሚመረምረው በእግዚአብሔር ዘንድ ከፍርድ አያመልጡም! በመጨረሺያ መልእክቴም በጀግኖችና በተመረጡ ልጆቿ ኢትዮጵያ መነሳቷ ግድ ነው አይቀርም! ሁላችንም አንድ ሆነን ሀገርን ከገባችበት አዘቅት ውስጥ ለማውጣት በጽኑ እምነትና ጽናት ልንነሳ ግድ ይለናል:: ኢትዮጵያውያን ሆይ የቀድሞ ታሪክን ከማወደስ ብቻ ይልቅ ታሪክንም እንስራና በነገ ትውልዶች እንዘከር!
በሴራ ሰላም አይመጣም ፤ በአፍራሾችም ሀገር አይገነባም! ድል ለኢትዮጵያ ድል ለቤተክርስቲያን!
Blogger Comment
Facebook Comment