በክርስቲያኖች መካከል ለምን ጠብ በዛ?


✍ መስከረም ለቺሳ (ዶ/ር) | ዮቶጵያ

ቁም ነገር ተባብረው በመሥራት ፈንታ፡ ለምን ቡድንተኝነት፣ ክርክር፣ ክፍፍል ወዘተ ያዘወትራሉ?

ይኽን ጥያቄ የሚጠይቁ ሰዎች፡ ሰላምና ፍቅር ወዳድ ሰዎች ተብለው ይሞገሱ ይኾናል። አዎ፤ ሰላም ይወዳሉ። ነገር ግን፡ ብዙ ጊዜ፡ ሰነፎች ናቸው። የነገሮችን ጥልቀትና የውትብትቡን ዓይነት ጊዜ ወስደው ለመረዳት ተነሳሽነቱ የላቸውም። በደፈናው ብቻ "ቤተእግዚአብሔር ውስጥ ቁጭ ብለው ይጣላሉ" እያሉ መታዘብ ደስ የሚላቸው ናቸው። "ሃይማኖተኛ ነኝ እያሉ ይጨቃጨቃሉ" እያሉ ያማሉ፤ ያላግጣሉ፤ ይታዘባሉ። "እኔ'ኮ ብዙም አልቀርብም፡ ከውጪ ተሳልሜ ብቻ ስለምኼድ፡ ነገር ውስጥ አልገባም" በማለትም በስንፍናቸው ይመካሉ። በውስጥ ኾኖ ግን፡ የተለያየ ሠርጎ ገብ ዓላማ ይዘው ከገቡ ፖለቲከኞች፣ መናፍቆች፣ ጠንቋዮችና ሌቦች ጋር ትንቅንቅ የገጠመ መኖሩን አይረዱም። ትክክለኛውን ሥርዓተ ቤተክርስቲያን ለማጥናትና በጠብ የተጎዱትን ወይም ተስፋ ቆርጠው ዝም ያሉትን ለማገዝ ፈቃደኝነት የላቸውም። ብቻ ግን ኹሉ ነገር ሰላም ኾኖላቸው፡ ሆቴል ሲኼዱ ጥሩ መስተንግዶ አግኝተው እንደሚወጡ ኹሉ፥ ቤተክርስቲያንም ሲመጡ ጥሩ መስተንግዶ አግኝተው መውጣት ነው የሚፈልጉት። ጠጋ ብለው ግን አያዩም። Tourist ናቸው። 

ብዙ ኦርቶዶክሳውያን እንዲህ ናቸው። ጠጋ ብለው፥ ጊዜ ወስደው፥ የቤተክርስቲያንን ትምህርት አጥንተው፥ ነገሮችን በጽሙና ቢገመግሙ ግን፡ ቤተክርስቲያን ብዙም ሰው እንደሌላት ይረዱ ነበር። ግልጽና ሥውር የኾነ ብዙ የዲያቢሎስ ተንኮል መኖሩን ያዩ ነበር።

እንደ አገር፡ ከሦስቱ የኢትዮጵያውያን ዋና ዋና መርኆች መካካል አንዱ፡ "ጥበብን እያጠኑ መኖር" ነው። ይኽ፡ ሃይማኖትንና ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን በሚችሉት ዓቅም ሲማሩና ሲያጠኑ መኖርን ያካትታል። ሐዋርያት እንዳስተማሩን፡ ይኽ፡ ለልጅ ልጅ የሚተርፍ ብዙ በረከትን የሚያስገኝ የኹሉ ክርስቲያን ግዴታ ነው።

ብዙ ክርስቲያኖች ግን፡ አንድም ነገር ሳይገነዘቡ "ውይይይ! ኹል ጊዜ ጠብ ብቻ! በናታችሁ ተስማሙ?!" እያሉ እየታዘቡ ይኼዳሉ። ሰው በከፈለው መሥዋዕትነት እየኖሩ እንዳሉም አያውቁም። የጥፋት ርኩሰት፡ በተቀደሰው ቦታ፡ ነጠላ ለብሶ፡ ተመሳስሎ፡ ቆሞ ነገሮችን አንቆ እንዳለ አያስተውሉም። በእውነተኛውም፣ በሐሰተኛውም ላይ እኩል ፈርደው ይኼዳሉ። ከዚያም አልፈው፡ ሳያውቁት፡ ክፉውን ወገንም ሊያግዙ ይችላሉ። ብዙዎቹ እንዲህ ናቸው።

አቋም ያላቸው ቢኾኑ ግን፥ እውነት ለአምላካቸው ፍቅር ቢኖራቸው ኖሮ፡ ከማን ጋር መቆም እንዳለባቸው ተረድተው፥ በአንድነት ቆመው፡ መኾን ያለበትን አስፈጽመው፥ መኾን የሌለበትን አስቁመው፡ ቤተክርስቲያን፡ ከእለት ጭቅጭቅ ወጥታ፡ በትውልዱ ላይ ያላትን ተልዕኮ መፈጸም እንድትችል ጉልበት ይኾኗት ነበር።

የሐዋርያት ትምህርት ያ ነበረ!

Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment