የህልውና አደጋና አሳሳቢው የውሉደ ክህነቱ ዝምታ

  
✍ መንግሥቱ ጎበዜ  

በአሁኑ ወቅት የሀገራችን፣ የቤተክርስቲያናችንና የሕዝበ ክርስቲያኑ የህልውና ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ ለሆነ አደጋ መጋለጡ ግልጽ የሆነ እውነታ ነው። በአሩሲና በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች በኦርቶዶክሳውያን ክርስቲያኖች ላይ የሚፈጸመው ሰቅጣጭ እልቂትና የአብያተ ክርስቲያናት ውድመት፣ ተደራራቢና የተለመደ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል። ይሁንና በዚህ አስቸጋሪ ታሪካዊ ወቅት የሚታየው የውሉደ ክህነቱ (የጳጳሳት፣ ቀሳውስትና ዲያቆናት) ሚና ግን ከሚጠበቀው በታች ሆኖ ይገኛል። ቅዱስ መጽሐፍ “መልካም እረኛ ራሱን ለበጎቹ አሳልፎ ይሰጣል” (ዮሐ. 10፡11) የሚል ቢሆንም፤ ራስን አሳልፎ መስጠት ይቅርና፣ ድምፅን እንኳ አውጥቶ ፍትሕን ለመጠየቅ የሚታየው ፍርሃትና መሽኮርመም እጅግ የሚያስገርም ነው።

ሀገራዊ ቀውስና  የካህናት አኩሪ ሚና በቀደመው ዘመነ ታሪክ

በቀደመው የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጉዞ ውስጥ ሀገርንና ቤተክርስቲያንን የህልውና አደጋ ላይ የሚጥል ፈተና ሲያጋጥም የካህናት፣ የጳጳሳት፣ የቀሳውስትና የዲያቆናት ሚና የጎላ እንደነበር ይታወቃል። የሀገር ሉዓላዊነት ሲደፈርና የክተት አዋጅ ሲታወጅ፣ ካህናት ታቦታትን በክብር ተሸክመው ወደ ጦር ግንባር መዝመታቸው የታሪክ እውነት ነው። ለአብነት ያህል፣ በዓድዋ ጦርነት ወቅት የቅዱስ ጊዮርጊስና የሌሎችም ቅዱሳን ታቦታት ተይዘው አብረው ዘምተዋል፤ ይህም ለታላቁ ድል ከፍተኛ የስነ-ልቦና ስንቅ መሆኑ ይታወቃል።

ምንም እንኳን በፍትሐ ነገሥቱ እና በቀኖና ቤተክርስቲያን መሠረት ካህናት በቀጥታ መሣሪያ አንስተው መዋጋት እንደሌለባቸው የተደነገገ ቢሆንም፣ በህልውና ትግል ውስጥ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ግን ከጦር መሣሪያ በላይ ዋጋ ያለው ነው። ካህናት ሕልውናን አደጋ ውስጥ በሚጥል የፈተና ወቅት ሕዝበ ክርስቲያኑ ተስፋ እንዳይቆርጥና በፈጣሪ እርዳታ ድል እንደሚገኝ በማስተማር የሞራል ግንባታ እና የስነ-ልቦና ጥንካሬ ይፈጥራሉ። በረሃብና በድካም የተሰበሩትን ያበረታታሉ፣ የቆሰሉትን ያጽናናሉ፣ እንዲሁም በጦር ሜዳ የወደቁትን ጀግኖች በክብር ሥርዓተ ቀብር በመፈጸም የሰራዊቱን ሞራል ይጠብቃሉ።

በተጨማሪም ጠላት ሕዝብን በዘርና በሃይማኖት በመከፋፈል የውስጥ ኃይልን ለማዳከም ሲሞክር፣ ካህናት የሰላምና የአንድነት ድልድይ በመሆን ሕዝቡ በአንድነት ቆሞ ራሱን፣ እምነቱንና ሀገሩን እንዲከላከል ይቀሰቅሳሉ። በማንነታቸውም ይሁን በሌላ ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች እርዳታ ያስተባብራሉ፤ ማኅበረሰባዊ ትሥሥሩ እንዳይፈርስ ያደርጋሉ። የሀገር ህልውና መሬቱ ብቻ ሳይሆን ታሪኩና ቅርሱም ጭምር በመሆኑ፣ ካህናት ጥንታዊ መጻሕፍትን፣ ንዋየ ቅድሳትንና የታሪክ ሰነዶችን ከጠላት ወረራና ዘረፋ በመደበቅ የሀገርን ማንነት ለቀጣዩ ትውልድ ያቆያሉ። ጦርነት በሰላም ድርድር እንዲደመደም ሲፈለግም፣ ካህናት መስቀል ይዘው በመሃል በመግባት "ደም አይፍሰስ" በማለት የማስታረቅ ታላቅ የዲፕሎማሲ ሥራ ይሠራሉ።

መጽሐፍ ቅዱሳዊና ታሪካዊ ማሳያዎች 

በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በጦርነት ወቅት የካሕናት ተሳትፎ በልዩ ልዩ መልክ ተገልጾ ይገኛል። በብሉይ ኪዳን ሕግ መሠረት እስራኤላውያን ለጦርነት ሲሰለፉ መጀመሪያ ንግግር የሚያደርገው ጦር መሪው ሳይሆን ካህኑ ነበር (ዘዳግም 20፡2-4)። በጦርነት ጊዜ መለከት የመንፋትና ጩኸትን ወደ እግዚአብሔር የማቅረብ ሥልጣን የካህናት ሲሆን (ዘኍልቁ 10፡8-9)፣ ታዋቂው የኢያሪኮ ግንብ የወደቀውም በኃይለኛ ተኳሾች ሳይሆን ታቦቱን በተሸከሙ ካህናት ዝማሬና ጸሎት ነው (ኢያሱ 6፡4-5)።

በአንዳንድ ልዩ አጋጣሚዎች ካሕናቱ ራሳቸው በቀጥታ በጦርነት ውስጥ የተሳተፉባቸው ታሪኮች አሉ። ሳሙኤል ካህንና ነቢይ ቢሆንም፣ የእግዚአብሔርን ሕግ የጣሰውን የአማሌቅን ንጉሥ አጋግን በገዛ እጁ እንደገደለ ተጽፏል (1ኛ ሳሙ 15፡33)። በምድያማውያን ጦርነት ወቅትም ካህኑ ፊንሐስ የመቅደሱን ዕቃዎችና የምስጋና መለከቶችን ይዞ ግንባር ተገኝቷል (ዘኍልቁ 31፡6)።

ይህ ዓይነቱ ልዩ የታሪክ አጋጣሚ በኢትዮጵያም ተከስቷል። ለምሳሌ፣ ካህኑ ንጉሥ ቅዱስ ነአኩቶለአብ በተደጋጋሚ ዓመፅ ያስነሳ የነበረውን “ፀረ ቅምጽ” የተባለውን ሽፍታ ድል በማድረግ ግዛቱን ማረጋጋቱ በገድሉ ላይ ተመዝግቧል። በተመሳሳይ ሁኔታ በ16ኛው ክፍለ ዘመን በክርስቲያኖች ላይ አስከፊ ጥቃት ያደርስ የነበረው የአዳል መሪ ማህፉዝ፣ በገብረ እንድርያስ በተባለ ቆራጥ መነኩሴ እጅ ተገድሏል።

ከበርካታ የመጽሐፍ ቅዱስና የሀገራችን ታሪኮች መረዳት እንደሚቻለው ካህናት በሦስት ልዩ ምክንያቶች በቀጥታ  በጦርነት ውስጥ ይሳተፋሉ፤ ይኽውም የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ሲደፈር፣ የሕዝብ ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ፣ እና ኢፍትሐዊነትና የግፍ አገዛዝ በአማኞች ወይም በሕዝብ ላይ ሲጫን ነው።

መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ሥልጣንን በአንድ ላይ በመያዝ የሀገርን ደኅንነት የመጠበቅ ጥንታዊ የኢትዮጵያ እውነት በዓለም አቀፍ ደረጃም ይታወቅ ነበር። በመስቀል ጦርነት ጊዜ ምዕራባውያን ክርስቲያኖች ወታደራዊ እገዛ ያደርግልናል ብለው ተስፋ ያደርጉት የነበረውና “ፕሬስተር ጆን” (Prester John) በመባል የሚታወቀው መሪ፣ መንፈሳዊና ፖለቲካዊ ሥልጣንን ወይም ንግሥናን ከክህነት ጋር በአንድ ላይ የያዘ የኢትዮጵያ መሪ እንደሆነ በጽኑ ያስቡት ነበር።
 
የካህናቱ ገዥዎችን የመገሠጽ ኃይልና ድፍረት በቅዱሳት መጻሕፍትና በታሪክ

ካህናትና ነቢያት ለሰው ፊት ሳያደሉ ለእግዚአብሔር ሕግና ለሕዝብ ፍትሕ ሲሉ ነገሥታትን የመገሠጽ ታላቅ ታሪክ አላቸው። ነቢዩ ናታን ንጉሥ ዳዊትን ፊት ለፊት በድፍረት ገሥጾ ለንስሐ አብቅቶታል (2ኛ ሳሙኤል 12: 1-14)። መጥምቁ ዮሐንስም ንጉሥ ሄሮድስን በመገሠጹ አንገቱን እስከ መስጠት ድርሷል (ማቴ 14: 3-12)። ነቢዩ ኤልያስም የናቡቴን የወይን ተክል ቦታ በግፍ ለቀማው ለንጉሥ አክዓብ “ሰው ገድለሃል ደግሞም ርስት ወርሰሃልን?” (1ኛ ነገሥት 21) በማለት ፊት ለፊት ተጋፍጦታል።

በኢትዮጵያ ታሪክም ይህ መርህ በተግባር ታይቷል። በ14ኛው ክፍለ ዘመን ዐፄ አምደ ጽዮን ከሃይማኖት ሥርዓት ውጭ የሆነ ጋብቻ በመፈጸማቸው፣ እንደ አባ ፊልጶስ፣ አባ አኖሬዎስ፣ አባ በጸሎተ ሚካኤል እና አባ ፊልሞና ያሉ አበው መነኮሳት ንጉሡን ፊት ለፊት በመቃወማቸው ምክንያት ግርፋት፣ እሥራትና ስደት ገጥሟቸዋል። በአፄ ቴዎድሮስ ዘመንም አቡነ ሰላማ የንጉሡን አንዳንድ እርምጃዎች “ከሕግ ውጭ ነው” በማለት ይቃወሙና ይገሥጹ ነበር። በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ወቅት ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ ለወራሪው እንዳይገዙ ሕዝቡን አውግዘው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፤ በዚህም መሣሪያ ሳይተኩሱ በቃላቸው ብቻ የጠላትን የፕሮፓጋንዳ ምሽግ አፍርሰዋል። አቡነ ሚካኤልም በባሌ አርበኞችን በረሃ ለበረሃ እየተዘዋወሩ ሲያጠናክሩ ቆይተው፣ ሀገራቸውንና ሃይማኖታቸውን አሳልፈው ባለመስጠታቸው በሰማዕትነት አልፈዋል።

ከመከላከልና ከተግሳጽ በተጨማሪ፣ የአባቶች ታላቅ ሚና ሊከሰት የሚችለውን ደም መፋሰስ በማስቆም የሀገርን መረጋጋት ማምጣት ነው። ለዚህ ትልቅ ማሳያ የሚሆነው በዘመነ ላስታ (ዛጉዌ) የመጨረሻ ንጉሥ በነበረው ዐፄ ይትባረክ እና በሰሎሞናዊው ዐፄ ይኩኖ አምላክ መካከል ሊፈጠር የነበረውን አስፈሪ ጦርነት፣ የደብረ ሐይቁ አባ ኢየሱስ ሞዓ እና የደብረ ሊባኖሱ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ጣልቃ በመግባት፣ በሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ሊከሰት የነበረውን ከፍተኛ ደም መፋሰስ ማስቆማቸው ታሪካዊ ምስክር ነው። ዐፄ ሱስንዮስ የካቶሊክን እምነት ማወጁን ተከትሎ በተፈጠረው ሀገራዊ ትርምስና ከፍተኛ ደም መፋሰስም፣ ከማኅበረ ሥላሴ ገዳም የመጡ አባቶች ጣልቃ ገብተው መንግሥታዊ ሥልጣን ወደ ልጁ ዐፄ ፋሲለደስ እንዲተላለፍ፣ ሀገር እንድትረጋጋና ሃይማኖት እንዲመለስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል።

ወቅታዊው ቀውስና የቤተክርስቲያን አባቶች ‘ስልታዊ ዝምታ’ 

የኢትዮጵያ ወቅታዊ ቀውስ መባባስ ምክንያት ከሆኑት ዋነኛ ነገሮች አንዱ ሕዝቡ ለሀገሩና ለእምነቱ ታማኝ ቢሆንም፣ እውነትን በድፍረት የሚመሰክር የሃይማኖት መሪ ማጣቱ ነው። ለዚህ ደግሞ መሠረታዊው ምክንያት የቤተ-መንግሥትና የቤተ-ክህነት ያልተቀደሰ ጋብቻ፣ የብሔር ፖለቲካ መቅደሱን መውረሩ፣ እንዲሁም የምድራዊ ምቾትና የጥቅም ፍላጎት የአባቶችን አንደበት ማሰሩ ነው። በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ ባለው ጦርነት፣ የክርስቲያኖች እልቂትና አጠቃላይ የሰላም እጦት ውስጥ የቤተክርስቲያን አባቶች የሚያሳዩት ዝምታ እጅግ አስደንጋጭ ሲሆን፣ ለዚህ 'ስልታዊ ዝምታ' በምክንያትነት የሚጠቀሱ በርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ተግዳሮቶች አሉ።

አንደኛው ተግዳሮት የፖለቲካ ተጽዕኖና ወገንተኝነት ነው፤ የእምነት መሪዎች ከብሔርና ከፖለቲካ በላይ መሆን ሲገባቸው፣ አንዳንዶቹ በዘር ሐረግና በፖለቲካ ዝንባሌ ተጽዕኖ ሥር ወድቀው ለእውነት መቆምን ትተዋል። ይህም መንፈሳዊ ግዴታቸውን እንደ 'ፖለቲካዊ ተቃውሞ' እስከመቁጠር አድርሷቸዋል። ሌላኛው ምክንያት የጥቅም ትስስርና ፍርሃት ነው፤ መንፈሳዊው ሥልጣን ከዓለማዊ ጥቅም ማለትም ከገንዘብ፣ ከቤት፣ ከመኪና እና ከሹመት ጋር ሲቆራኝ መሪዎችን መገሠጽ ዋጋ ያስከፍላል። ያንን ዋጋ ለመቀበል ፈቃደኛ አለመሆንና የሚመጣውን መከራ መፍራት፣ በአሁኑ ወቅት በዝምታ ማለፍን እንደ 'ብልህነት' አስቆጥሮታል። በተጨማሪም በሲኖዶስ ውስጥ የሚታዩ የአስተሳሰብና የቡድን ክፍፍሎች፣ የሲኖዶሳዊ አንድነት መላላትና የቀኖና ጥሰት ቤተክርስቲያኗ በአንድ ሉዓላዊ ድምፅ ለፍትሕና ለተበደሉት እንዳትቆም አግዷታል። የሀገሪቱን ቁስል በጎሳ መነጽር ብቻ መመልከታቸውም የጋራ የሰላም ድምፅ እንዳይኖራት አድርጓታል።

የውሉደ ክህነቱ ዝምታ ሊበቃ ይገባል! 

ታሪክ እንደሚያስተምረን የቤተክርስቲያን መሪዎች ዝምታ በበዛ ቁጥር ግፈኞች ይበረታሉ፣ ገዥዎች መረን ያጣሉ፣ ሕዝብም ተስፋ ይቆርጣል። የቤተክርስቲያን ህልውና የሚጠበቀው ግዑዝ ሕንጻዎችን በመገንባት ብቻ ሳይሆን፤ የአማኞችን ደኅንነት በመጠበቅና የወንጌልን እውነት በድፍረት በመመስከር ነው። በአሁኑ ወቅት የተጋረጠውን አሳሳቢ የህልውና አደጋ ለመቀልበስ የቤተክርስቲያን መሪዎች ከብሔርተኝነት ሰንሰለት፣ ከዓለማዊ ጥቅም ፍላጎትና ከፍርሃት ቀንበር መላቀቅ ይኖርባቸዋል።

እንደ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስና ብፁዕ አቡነ ሚካኤል ያሉ አባቶች ለሐቅና ለሰማያዊ ክብር ሲሉ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡበት የሰማዕታት ታሪክ፤ ታሪክ ብቻ ሁኖ መቅረት የለበትም። የአሁኑ ዘመን አባቶች ዝምታቸውን ሰብረው “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል” (ሐዋ. 5:29) የሚለውን መለኮታዊ መመርያ በተግባር ማሳየት ይኖርባቸዋል።

ዛሬ ኢትዮጵያ የምትፈልገው የቢሮክራሲ ጳጳሳትንና የደብር አለቆችን ሳይሆን፣ እንደ መጥምቁ ዮሐንስ በበረሃ የሚጮህ ድምፅ የሚሆኑ፣ ከጥቅምና ከፖለቲካ ተጽዕኖ ወጥተው “ደም ማፍሰስ ይብቃ!” የሚል የእውነት ሰይፍ የሚመዙ፣ እንዲሁም ለራሳቸው ምቾት ሳይሆን ለበጎቻቸው የሚሳሱ እውነተኛ እረኞችን ነው። ቤተክርስቲያን ድምፅ ለሌላቸው ወገኖች ድምፅ መሆን ሲያቅታት የጨውነት ጣዕሟን ታጣለች። በመሆኑም የሀገሪቱ ትንሣኤ ከመቅደስ ይጀምር ዘንድ፣ ውሉደ ክህነቱ ካለበት የፍርሃት ቆፈን ወጥቶ፣ የተጋረጠውን ጥላቻና በቀል “ንስሐ የሚያስፈልገው ብሔራዊና መንፈሳዊ ቀውስ” መሆኑን ተገንዝቦ በአደባባይ የእውነት መብራት በመሆን እውነተኛ የእረኝነት ሚናውን ሊወጣ ይገባል።
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment