✍ መንግሥቱ ጎበዜ
ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነኝ ሰሞኑን በማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን የከተማ መንኮሳትን በተመለከተ እየተንሸራሸረ ያለው ወሳኝ ጉዳይ ነው። እኔም በበኩሌ በዘመናችን ያለው የምንኩስና ሕይወት—በተለይም የካህናት መነኮሳትን የሚመለከተው ክፍል—ፈር እስካልያዘ ድረስ፣ የቤተ ክርስቲያናችንን መዋቅራዊ ችግሮች መፍታት የሚቻልበት ዕድል ይኖራል ብዬ አላምንም። ከዚሁ አንጻር፣ ምናልባት የችግሩን ዳራ ማወቅ ለመፍትሔው አጋዥ ይሆናል ከሚል እምነት ጋር የበኩሌን ሐሳብ ለማበርከት ስል፣ የምንኩስና ሕይወት አሁን ላለበት ቀውስ ምክንያት የሆኑ ታሪካዊ ዳራዎችን ባጭሩ ማሳየት ወደድኩ።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥ የምንኩስና ሕይወት የቅድስና፣ የመንፈሳዊ ትሩፋት እንዲሁም የሀገር ባሕልና ዕውቀት ጥበቃ ማዕከል ሆኖ የኖረ ታላቅ ተቋም ነው። ይሁን እንጂ በተለያዩ ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ምክንያቶች የተነሳ ይህ መንፈሳዊ ሥርዓት፣ በተለይም ባለፉት አምስት መቶ ዓመታት ውስጥ የጥራትና የሥርዓት መላላት ፈተናዎች ገጥመውታል።
ለዚህ የምንኩስና ሕይወት መዳከም በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀሰው ታሪካዊ ክስተት በ16ኛው ክፍለ ዘመን የተነሳው የአሕመድ ግራኝ ጦርነት ነው። በዚህ አስከፊ ጦርነት ወቅት ለዘመናት ተከብረው የኖሩ በርካታ ታሪካዊ ገዳማት የወደሙ ሲሆን፣ በሺዎች የሚቆጠሩ መነኮሳትና ባሕታውያንም በሰማዕትነት አርፈዋል። ይህም የገዳማትን መንፈሳዊ ሰንሰለት በማቋረጥ ሥርዓተ ገዳሙ እንዲነጥፍና እንዲላላ አድርጓል። ከጦርነቱ ማብቃት በኋላ ገዳማቱን መልሶ ለማደራጀት በተደረገው ጥረት፣ ወደ ገዳማቱ የሚገቡ መናንያንን የመቆጣጠሪያና የመመዝገቢያ ሥርዓቱ ደካማ በመሆኑ በምንኩስና ሕይወት ጥራት ላይ የመጀመሪያው ትልቅ ስንጥቅ መፈጠር ጀመረ።
ልክ እንደ ግራኝ ወረራ ሁሉ የፋሺስት ኢጣሊያ ወረራም በገዳማትና በምንኩስና ሕይወት ላይ የማይሻር ከባድ ጠባሳ ጥሎ አልፏል። ወራሪዎቹ ኃይሎች እንደ ደብረ ሊባኖስ ያሉ ታላላቅ ገዳማትን ያወደሙና በርካታ መነኮሳትን በጅምላ የፈጁ በመሆኑ፣ ከነፃነት መልስ ገዳማቱን በፍጥነት ለማንቀሳቀስ ሲባል በምልመላ ሥርዓቱ ላይ መላላትን ማስከተሉ አልቀረም።
ከነፃነት መልስ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት ድጋፍ በርካታ ገዳማት በከተሞችና በከተሞች አቅራቢያ እንዲመሠረቱ መደረጉ ደግሞ ሌላ መልክ ይዞ ብቅ አለ። ይህ አሠራር ገዳማቱ የልማትና የትምህርት ማዕከል እንዲሆኑ ቢረዳም፣ መነኮሳቱ ከከተማው ማኅበረሰብና ከዘመናዊው አኗኗር ጋር በቅርብ እንዲገናኙ በር ከፍቷል። ይህም የምንኩስና መሠረት ከሆነው "ከዓለም መለየት" ይልቅ መነኮሳቱ የከተማ ሕይወትን እንዲለማመዱና ለዓለማዊ ፈተናዎች እንዲጋለጡ የራሱ የሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።
የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ የደርግ ወታደራዊ መንግሥት ሥልጣን መያዙና የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለምን ማንገቡ ለገዳማቱ ሌላው መቅሠፍት ነበር። መንግሥት የቤተ ክርስቲያንን ይዞታዎችና የገዳማትን መተዳደሪያ መሬቶች በሙሉ በመንጠቁ ምክንያት ገዳማቱ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ወደቁ። በዚህም ሳቢያ በርካታ ታሪካዊ ገዳማት በችግር ምክንያት ለመዘጋት ሲገደዱ፣ መነኮሳቱም መተዳደሪያ በማጣታቸው በስደት በብዛት ወደ ከተሞች እንዲፈልሱ ሆነ። ይህ ፍልሰት የምንኩስናን ክብርና መንፈሳዊ ሥርዓት በእጅጉ ያዳከመ ክስተት ነበር።
ከዚህም በተጨማሪ በደርግና በሕወሐት መካከል በነበረው የረጅም ዓመታት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት በተለይ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የነበሩ ገዳማት የጦርነት ቀጠና ሆኑ። የሕወሐት ታጋዮች ወደ ገዳማት ሰርገው በመግባት መሸሸጊያ ማድረጋቸው ገዳማዊ ሕይወት እንዲረክስና ቦታዎቹ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ውጭ የፖለቲካ ካድሬዎች መፈልፈያ እንዲሆኑ በር ከፈተ።
በሕወሐት የሚመራው የኢሕአዴግ መንግሥት ሥልጣን ከያዘ በኋላ ደግሞ ችግሩ ይበልጥ ተቀጣጠለ። በዚህ ወቅት በሺዎች የሚቆጠሩ የቀድሞ ታጋዮችና የፖለቲካ ታማኞች "በምንኩስና ስም" ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳደራዊ መዋቅርና ከፍተኛ የስልጣን እርከን እንዲሰገሰጉ ተደረገ። ይህ ሴራ ምንኩስናን ከመንፈሳዊ ይዘቱና ፈሩ አውጥቶ የስልጣን፣ የሀብት ማከማቻ፣ የጥቅምና ወደ አማላይ የከተማ ሕይወት መወጣጫ እርከን አድርጎ የመጠቀም አደገኛ መጥፎ ልማድ ወለደ።
ከዚሁ ጎን ለጎን ከ1980ዎቹ ዓ.ም ጀምሮ ማንሰራራት የጀመረው ዘመናዊው የ"ተሐድሶ" እንቅስቃሴ ለምንኩስና ሕይወት ትርጉም ማጣት ሌላው ምክንያት ነበር። የተሐድሶ እንቅስቃሴ አራማጆች ገዳማዊ ሕይወት መጽሐፍ ቅዱሳዊ እንዳልሆነና ምንኩስና ትርጉም አልባ ሥርዓት እንደሆነ በመስበክ የሐሰት ትምህርታቸውን አስፋፉ። በዚህም ምክንያት አንዳንዶች የገዳማዊ ሕይወትን ክብር በመጠራጠር የያዙትን የምንኩስና ሥርዓት ጥለው ወደ ዓለም ሲገቡ፣ ከዚያም አልፎ የቀድሞ የምንኩስና ሕይወታቸውን በይፋ በመንቀፍ የሌሎችን ምእመናን ልብ ማናወጥና ማሳሳት ጀመሩ።
ከእነዚህ ታሪካዊና ውጫዊ ተጽዕኖዎች በተጨማሪ፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጣዊ የአስተዳደር መዋቅር በከፍተኛ የሙስና፣ የንቅዘትና በፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት ምክንያት መምከኑ የችግሩ ዋነኛ ማጠናከሪያ ሆኗል። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የገዳማዊ ሥርዓቱና የምንኩስና ሥርዓቱ አለባበስን ጨምሮ አጠቃላይ እንቅስቃሴ አንጻር ሙሉ በሙሉ ዝብርቅርቁ የወጣ ሆኗል። ወደ ገዳማት የሚደረጉ መንፈሳዊ ጉዞዎች በርካታ በጎ ነገሮችና በረከቶች ቢኖሯቸውም፣ መነኮሳት ከገዳማዊ ሕይወትና ከማኅበራዊ የምንኩስና ሥሪት ያፈነገጡ ልምዶችንና ዓለማዊ ሥራዎችን እንዲለማመዱ በማድረግ በኩል የራሱ የሆነ አሉታዊ ድርሻ አሳድሯል። ከዚህም በላይ መነኮሳት ከአንድ ገዳም ወደ ሌላ ገዳም የሚያደርጉት ፍልሰት ምንም ዓይነት የታወቀ ሕግ ወይም ሥርዓት የሌለው መሆኑ በምንኩስና ሕይወቱ መበላሸት ላይ ከባድ ተጽዕኖ ፈጥሯል።
የውስጥ አስተዳደሩ መላላት በቤተ ክርስቲያኒቱ ማዕረጎችና የአደረጃጀት መዋቅሮች ላይም ከፍተኛ መቃወስ አስከትሏል። መነኩሴ ለሆነ ሰው ሁሉ ያለ በቂ መንፈሳዊ ብቃት የቁምስና ማዕረግ በብዛት መሰጠቱና የደብራት አስተዳዳሪዎችን መነኮሳት ብቻ እንዲሆኑ መደረጉ፣ የምንኩስና ሕይወት ከመንፈሳዊ ተጋድሎ ይልቅ ለሥልጣንና ለከተማ ጥቅማጥቅም መሻኮቻ እንዲሆን በማድረግ ችግሩ እንዲባባስ በር ከፈተ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ካህናት መነኮሳት ጳጳሳትን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች ከክህነት የሚያሽር ከባድ ውድቀት ወይም ድቀት እንደገጠማቸው እየታወቀ፣ ተገቢው የቀኖና ቅጣት ሳይደረግላቸው በክህነት አገልግሎታቸው እንዲቀጥሉ መደረጋቸው የምንኩስና ሕይወት ጥራት እጅግ የላላና የተጎዳ እንዲሆን አድርጎታል።
ይበልጥ አሳሳቢው ነገር ደግሞ፣ ለከፍተኛው መንፈሳዊ ማዕረግ (ለጵጵስና) የሚደረገው ምርጫ በወገንተኝነት፣ በጎሳ፣ በጉቦና መማለጃ፣ እንዲሁም በፖለቲካዊ ድጋፍና ጣልቃ ገብነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ በግልጽ በምንኩስና ሕይወት ጥራትና በመንፈሳዊነቱ ላይ ታላቅ አደጋ በማስከተሉ በኩል የራሱ የሆነ ከፍተኛ ድርሻ አለው።
በአጠቃላይ የምንኩስና ሕይወትን አሁን ካለበት ሥርዓታዊና መንፈሳዊ መናጋት አውጥቶ ወደ ቀደመ ክብሩ ለመመለስ በሀገር አቀፍ ደረጃ ሁሉንም ገዳማት በአንድ ወጥ መመሪያ የሚገዛና የምልመላ ሥርዓቱን የሚያጠብቅ ጠንካራ የገዳማት መተዳደሪያ ሕግ በተግባር ላይ ማዋል አስቸኳይ እርምጃ መሆን ይኖርበታል። ከዚህ ጎን ለጎን፣ መነኮሳት ከአንድ ገዳም ወደ ሌላ ገዳምም ይሁን ወደ ከተሞች የሚያደርጉትን ሕገወጥ ፍልሰትና በገዳማት ከሚታዩ ዓለማዊ ልምዶችን በመግታት፣ የምንኩስናን መሠረት ወደ ሆነው "ከዓለም መለየት" ወደሚለው ጥንታዊ ትውፊት መመለስ ይገባል።
በተጨማሪም፣ ያለ በቂ መንፈሳዊ ልቅና የሚሰጡ የቁምስና ማዕረጎችን መገደብ፣ መነኮሳት በከተማ አድባራት አስተዳደር ላይ ከሚፈጠሩ ጥቅማጥቅሞች ርቀው ወደ ገዳማዊ ተጋድሏቸው እንዲያተኩሩ ማድረግ፣ እና ከክህነት የሚያሽር ውድቀት የገጠማቸውን አካላት በጠንካራ የቀኖና ቁጥጥርና ተጠያቂነት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ከሁሉም በላይ ደግሞ፣ ገዳማዊ ሕይወትን ከፖለቲካዊና ከካድሬዎች ሰርጎ ገብነት ሙሉ በሙሉ ነፃ በማድረግ፣ ከፍተኛው የጵጵስና ሹመት ምርጫ ከወገንተኝነት፣ ከጎሳ፣ ከጉቦና ከፖለቲካ ጣልቃ ገብነት የጸዳ ሆኖ በቅድስና፣ በመንፈሳዊ ብቃትና በዕውቀት ብስለት ላይ ብቻ እንዲመሠረት ግልጽ ሕግ መተግበር የምንኩስናን ሕይወት ጥራትና መንፈሳዊነት ወደ ነበረበት የታሪክ ማማ በመመለስ በኩል ታላቅ አስተዋጽኦ ሊኖረው ይችላል።
Blogger Comment
Facebook Comment