የታቦተ ጽዮን ዘመናዊ አሰሳ


✍ ታደሰ ሞጎስ | ኢትዮጵያ አውታር | ሰላቢ እጆች

የአሥርቱ ትዕዛዛት መገኛ የሆነው ያ ቅዱስ ታቦት ለዘመናት የት እንዳለ ሳይታወቅ ሚስጥር ሆኖ ቢቆይም፣ አሁን ግን አርኪዮሎጂስቶች ከምንጊዜውም በላይ ወደ መገኛ ስፍራው እየተቃረብን ነው በማለት እየገለጹ ይገኛሉ።
​መጽሐፍ ቅዱሳዊ ታሪኮችን መነሻ በማድረግ፣ ይህ ክቡር ንዋየ ቅዱሳት እስራኤላውያን ከግብፅ በወጡ ማግስት በ13ኛው ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ አካባቢ የተሰራ መሆኑንና ሙሴም ጽላቶቹን በውስጡ እንዳስቀመጠ ይታመናል። የታሪክ ተመራማሪዎች ታቦቱ በኢየሩሳሌም ጥንታዊ ቤተ መቅደስ ውስጥ በ"ቅድስተ ቅዱሳን" ክፍል ይቀመጥ እንደነበርና በ586 ዓ.ዓ ባቢሎናውያን ከተማዋን ሲያወድሙ እንደተሰወረ ይገልጻሉ።

ከዛሬ 19 ቀን በፊቴት​ በሚያዝያ 21/2026 ዓ.ም (እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር)፣ በዓለም አቀፍ የዜና አውታሮች ላይ የወጣውና በሳይንስና ቴክኖሎጂ አምደኛዋ ስቴሲ ሊበራቶር (Stacy Liberatore) የተሰናዳው ዘገባ፣ የሰው ልጅ ለሺህ ዓመታት ሲያሳድደው የኖረውን ትልቅ ጥያቄ በድጋሚ ተቀስቅሷል። 

ይህ በዴይሊ ሜይል (Daily Mail) እና በኒው ዮርክ ፖስት (New York Post) ላይ ትኩረት ያገኘው ጽሑፍ፣ ታዋቂው አርኪዮሎጂስት ዶ/ር ክሪስ ማክኒ (Dr. Chris McKinny) በዘመናዊው “ሙኦን ቶሞግራፊ” (Muon Tomography) ቴክኖሎጂ ታግዘው የጀመሩትን አዲስ የምርምር ምዕራፍ ያበስራል። 

አርኪዮሎጂስቱ ዶ/ር ክሪስ ማክኒ (Dr. Chris McKinny) ባቀረቡት አዲስ ጥናታዊ መላምት፣ ይህ ቴክኖሎጂ ከመሬት በታች ያሉ ስውር ክፍሎችንና እንደ ወርቅ ያሉ ማዕድናትን ያለምንም ቁፋሮ መለየት የሚችል ሲሆን፣ ታቦቱ ከኢየሩሳሌም የቤተ መቅደስ ተራራ በስተደቡብ በሚገኘው "በዳዊት ከተማ" (City of David) ስር ባሉ የምድር ውስጥ ስርጥና ዋሻዎች ውስጥ ተደብቆ ሊሆን እንደሚችል አመልክተዋል።

ተመራማሪዎቹ በምድር ጥልቀት ውስጥ ያሉ ክፍተቶችንና ማዕድናትን መለየት የሚችል እጅግ የረቀቀ ቴክኖሎጂን ለመጠቀም አቅደዋል። ይህ ዘዴ "Muon detectors" የተባለውን መሣሪያ የሚጠቀም ሲሆን፣ ይህም ከጠፈር የሚመጡ ጨረሮች (Cosmic rays) ከምድር ከባቢ አየር ጋር ሲጋጩ የሚፈጠሩ ጥቃቅን ቅንጣቶችን በመከታተል፣ መሬቱን ሳይቆፍሩ በውስጡ ያሉ ስውር ክፍሎችን ለማየት ያስችላል።

​በአሁኑ ወቅት በተደረጉ የመጀመሪያ ደረጃ ቅኝቶች፣ ከጥንታዊው መልክአ ምድር ስር ከዚህ ቀደም ያልታወቁ ክፍተቶችና መዋቅሮች መኖራቸው ተረጋግጧል። ይህም "ታቦቱ በድብቅ ዋሻዎች ውስጥ ይገኛል" ለሚለው መላምት ተስፋ ሰጪ ፍንጭ ሆኗል።

ዶ/ር ማክኒ ባዘጋጁት "የጠፋው ታቦት አፈ ታሪኮች" (Legends of the Lost Ark) በተሰኘው ዘጋቢ ፊልም፣ ታቦቱ ከባቢሎን ወረራ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል የሚጠቁሙ ሦስት ዋና ዋና ትውፊቶችን ዳስሰዋል፦

1. ​የተራራው ትውፊት (The Mount Legend)፦ ታቦቱ በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ተራራ ስር ባሉ ስውር ክፍሎች ውስጥ በካህናቱ ተደብቋል የሚል ሲሆን፣ ይህም ለዘመናት በሰፊው የሚነገር መላምት ነው።

2. ​የአለቱ ትውፊት (The Rock Legend)፦ ነቢዩ ኤርምያስ ታቦቱን በሁለት ተራራዎች መካከል በሚገኝ ሚስጥራዊ አለታማ ስፍራ እንደደበቀው ይተርካል።

3. ​የኔቦ ተራራ ትውፊት (Mount Nebo Legend)፦ በቀድሞው አይሁዳዊ ጽሑፍ (2nd Maccabees) ላይ እንደሚሰፍረው፣ ኤርምያስ ታቦቱንና ሌሎች ቅዱሳን ንዋያትን ሙሴ እንደሞተበት በሚታመነው በኔቦ ተራራ ላይ ባለ ዋሻ ውስጥ አኑሯቸዋል።

ዶ/ር ማክኒ ታቦቱን አግኝቻለሁ የሚል ድምዳሜ ላይ ባይደርሱም፣ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ወደፊት ቅዱስ ስፍራዎችን ሳይረብሹ የምድር ውስጥ ምስጢራትን ለማውጣት እንደሚረዱ ትልቅ ተስፋ አላቸው። ሆኖም ግን፣ እንዲህ ያሉ ምርምሮችን ለማድረግ ሃይማኖታዊ፣ ፖለቲካዊና ሌሎች ውስብስብ መሰናክሎች አሁንም ከፊታቸው እንደሚጠብቁ አልሸሸጉም።

ይህ የአሁኑ ፍለጋ ግን በድንገት የተከሰተ ሳይሆን፣ ላለፉት ምዕተ ዓመታት ሲካሄዱ የነበሩ የፍለጋ ሙከራዎች ቀጣይ ነው። በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ቻርለስ ዋረን (Charles Warren) የተባሉ እንግሊዛዊ መኮንን በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ግርጌ ያደረጉት ቁፋሮ የታቦቱን መገኛ ፍንጭ ለማግኘት የተደረገ የመጀመሪያው ሳይንሳዊ ሙከራ ነበር። ከዚያም በ1980ዎቹ አጋማሽ ሮን ዋይት (Ron Wyatt) የተባሉ አሰሳዊ ታቦቱን በጎልጎታ ስር አግኝቻለሁ በማለት ዓለምን ቢያነጋግሩም፣ በቂ ሳይንሳዊ ማስረጃ ባለመቅረቡ ጉዳዩ እንደ ተረት ተቆጥሮ ቀርቷል።

የዶ/ር ማክኒ የአሁኑ ጥረት ግን በሃይማኖታዊ ትውፊት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ “ሌጀንድስ ኦፍ ዘ ሎስት አርክ” (Legends of the Lost Ark) በተሰኘው ዘጋቢ ፊልማቸው እንደገለጹት፣ ታሪክን ከቴክኖሎጂ ጋር በማስተሳሰር የታቦቱን ስውር ጉዞ ለመከተል ያለመ ነው።

​ታቦቱ ከባቢሎን ወረራ በፊት በካህናቱ ተደብቋል የሚለው መላምት በብዙዎች ዘንድ ቢታመንም፣ ከኢየሩሳሌም ቅጥሮች ውጭ ያለው ታሪካዊ ሐቅ ግን ወደ ደቡብ፣ ወደ ሀገረ ቀደምት ጥንታዊቷ ኢትዮጵያ ያመላክታል። ታቦቱ በእየሩሳሌም የለም የሚሉ ወገኖች ዋቢ የሚያደርጉት በ1950ዎቹ እና 60ዎቹ አካባቢ ኤድዋርድ ኡለንዶርፍ (Edward Ullendorff) የተባሉ የታሪክ ምሁር ያደረጉትን ጥናት ነው። ምንም እንኳ እርሳቸው ታቦቱ በአክሱም መኖሩን እርግጠኛ ለመሆን ቢቸገሩም፣ ሌሎች እንደ ግርሃም ሐንኮክ (Graham Hancock) ያሉ የታሪክ ተመራማሪዎች ግን በ1992 ባሳተሙት “ዘ ሳይን ኤንድ ዘ ሲል” (The Sign and the Seal) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ታቦቱ ከእየሩሳሌም ተነስቶ በግብፅ በኩል አድርጎ ጣና ቂርቆስ ላይ ለ800 ዓመታት ከቆየ በኋላ ወደ አክሱም እንደገባ በማስረጃ አስደግፈው አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መረጃዎችና እንደ “ክብረ ነገሥት” ያሉ ጥንታውያን ድርሳናት ደግሞ ጉዳዩን ከመላምት በላይ ያደርጉታል። በሀገር ውስጥ ያሉ ሊቃውንት ታቦቱ በቀዳማዊ ምኒልክ አማካኝነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣቱንና አሁንም በአክሱም ጽዮን ማርያም ቅጽር ግቢ ውስጥ በክብር ተቀምጦ እንደሚገኝ በጽኑ ይናገራሉ። ይህንኑ ሃሳብ የሚያጠናክሩት የውጭ ሀገር ተመራማሪው ፖል ራፋኤል (Paul Raffaele) እ.ኤ.አ በ2007 ለ“ስሚዝሶኒያን” (Smithsonian) መጽሔት ባደረጉት ጥናት፣ ታቦቱን የሚጠብቀው መነኩሴ በሕይወት እያለ ማንም ሰው ወደ ስፍራው ሊገባ እንደማይችልና የአክሱሙ ታቦት የዓለምን ትኩረት መሳብ የቀጠለ ምስጢር መሆኑን መስክረዋል።

​በአጠቃላይ፣ በ2026 የወጣው የዶ/ር ማክኒ ጥናት በቴክኖሎጂ የታገዘ አዲስ የፍለጋ አቅጣጫ ቢከፍትም፣ የታቦቱ መንፈሳዊና ታሪካዊ ግርማ ግን አሁንም በኢትዮጵያ አድባራት ውስጥ በምስጢር እንደተሸፈነ በግርማው እንደ ረበበ ይኖራል። ዓለም አቀፍ አርኪዮሎጂስቶች በኢየሩሳሌም አፈር ስር በሚያደርጉት ፍለጋ እና በኢትዮጵያ ሊቃውንት ትውፊታዊ እውነት መካከል ያለው ትንቅንቅ፣ ታቦተ ጽዮን ተራ ቁስ ሳይሆን የሰማይና የምድር ግንኙነት መገለጫ መሆኑን በድጋሚ የሚያረጋግጥ ነው። ቴክኖሎጂው የምድርን ስንጥቅ ቢመረምርም፣ የሺህ ዓመታቱ የታማኝነት ምስክር የሆነችው ኢትዮጵያ ግን የታቦቱ እውነተኛ ባለቤት ሆና መቆየቷ በታሪክ ድርሳናት ውስጥ በደመቀ ቀለም ተጽፎ ይገኛል።

Graham Hancock ታቦቱን ለሚጠብቀው መነኩሴ ስለ ታቦቱ ላቀረበው ጥያቄ መለኩሴው ሲመልሱለት "የራሳችሁ ያልሆነ ነገር ስለምን ትፈልጋላችሁ" በማለት ፍለጋቸውን እንዲያቆሙ በገደምዳሜ ነግረውታል። ግን አሁንም እየተፈለገ ነው........
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment