የአገዛዙ የጥላቻ ትርክትን በሐውልት!

✍ ሚካኤል ዘኢትዮጵ

ከሃጫሉ ዘፈኖች መካከል 'ማላን ጅራ' በሚለው የመጀመሪያ ዘፈኑ ላይ ጉለሌ የከንቱፋ ነው የሚል ነገር አለው። ሽመልስም ሥልጣን በያዘ ማግስት መሐል መስቀል ዐደባባይ ላይ "እነቱፋ ሙና የተሰበሩበት ቦታ ላይ መልሰን ሰብረን ተቆጣጥረነዋል" ሲል የጥላቻ ንግግሩን ያስወነጨፈው ይሄን አጣቅሶ ነበር። የኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚያስጮሑት ሌላኛው የሐሰት ትርክት "ምኒልክ መሐል አራዳ ላይ በቆመለት ሐውልት የጋለበው ፈረስ የሲዳ ደበሌ ፈርዳ ነው። ወይም ሲዳ ደበሌ ከሚባል ኦሮሞ የቀማው ፈረስ ነው" ብለው ያምናሉ። ሃጫሉም በዘፈኑ አካቶበታል። የሐውልቱ ይዘት ይሄው ነው። 

ሥርዓቱ ለሃጫሉ ሁንዴሳ የቆመውን ሃውልት እንደ አንድ ጥበባዊ መታሰቢያ ሳይሆን፣ የቆየውን የማኅበራዊ ክፍፍልና የቂም በቀል ትርክት ማደሻ አድርጎታል። የኦሮሞ የጥላቻ ፖለቲካ አራማጆች እንደሚሉት፤ "ጉለሌ የከንቱፋ ነው" የሚሉ ትርክቶችንና የአድዋ ድል ምልክት በሆነው በፈረሰኛው ምኒልክ ሃውልት ላይ የሚሰነዘሩ "የፈረስ ቅሚያ" ትችቶችን በሃውልት ይዘት ውስጥ ለማካተት መሞከሩ፣ ሥርዓቱ የጋራ አገራዊ ዕሴቶችን ከመገንባት ይልቅ ሕዝብን በታሪክ የሚያጋጩ ትርክቶችን የመንግሥት መመሪያ ማድረጉን ያሳያል። ይህ ደግሞ ለአንድ አገር መሪነት የሚጠበቀውን አስተዋይነት የጎደለውና ይልቁንም በቁስል ላይ እንጨት የመስደድ ያህል የሚቆጠር ኃላፊነት የጎደለው አካሄድ ነው።

የሥርዓቱ ባለሥልጣናት የሚሰነዝሯቸው ንግግሮች በተለይም "መልሰን ሰብረን ተቆጣጥረነዋል" የሚለው የሽመልስ አብዲሳ የጥላቻ ንግግር በውስጣቸው ያለውን ጥልቅ የሆነ የዝቅተኝነት ስሜትና በድል የመኩራራት አባዜን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ሥልጣን በያዙ ማግስት የጥንት ስብራቶችን እንደ ድል ማጣቀሻ መጠቀም፣ ሥርዓቱ ካለፈው የታሪክ ጠባሳ መውጣት ያልቻለና የወደፊት ራዕይ የሌለው መሆኑን ያረጋግጣል። የሃውልቱ ግዝፈትና ይዘትም (ፈረስና ጦር)፣ ይህንን ሥነ-ልቦናዊ ክፍተት በቁሳዊ ግርማ ሞገስ ለመተካት የተደረገ ጥረት ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ይህም ለሕዝቡ ሰላምና ልማትን ከመስጠት ይልቅ፣ በምልክቶችና በምስሎች የበላይነትን ለማሳየት የሚደረግ "የትርክት ጦርነት" ላይ መጠመዱን ያሳያል።

አገዛዙ የድምፃዊውን ሥራና ዝና ለራሱ የፖለቲካ ትርክት ማገዶነት መጠቀሙ፣ ለጥበብና ለጥበበኛው ካለው ክብር ይልቅ ለራሱ ሥልጣን ያለው ስግብግብነት የላቀ መሆኑን ያሳያል። የሃጫሉን ማንነትና የታሪክ ትርክቱን ከፈረሱ ጋር አላብሰውት የቀረቡበት መንገድ፣ የድምፃዊውን እውነተኛ የኪነ-ጥበብ አበርክቶ ከማክበር ይልቅ ለፖለቲካዊ ፍጆታና ለተቃራኒ ጎራዎች የማስፈራሪያ ምልክት እንዲሆን ታስቦ የተሠራ ነው። ይህ ዓይነቱ አካሄድ ጥበብን ነፃነቷን ነጥቆ የገዥው ፓርቲ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጫ ማሽን ማድረጉን የሚያሳይ ሲሆን፣ ይህም በረጅም ጊዜ ሂደት በሕዝብ መካከል ያለውን አብሮ የመኖር ስሜት የሚሸረሽር አደገኛ አካሄድ ነው።


Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment