ኢብን-ኢስሐቅ የተባለው የመሐመድ የሕይወት ታሪክ ጸሐፊ “ሲራ ረሱለላህ” በተባለው መጽሐፉ በርካታ ነገሮች አካቷል፡፡ ይህ መጽሐፍ በራሱ የተዘጋጀው “አል-ሙብታዳ ዋ አል-ባዝ ዋ አል-ማጋዚ” የተሰኘ ሰፊ መጽሐፍ አካል ነበር፡፡ መጽሐፉ ከአዳም መፈጠር ጀምሮ ያሉ ዋና ዋና ክስተቶችን ጨምሮ የመሐመድን የሕይወት ታሪክና ያደረጋቸውን ዘመቻዎች የሚያካትት ሲሆን እንግሊዝኛ ስያሜው (In the Beginning, the mission [of Muhammad], and the expeditions) በመባል ይታወቃል፡፡
ኢብን-ኢስሐቅ የመሐመድን የሕይወት ታሪክ ያዘጋጀው ስለ እርሱ የተነገሩ የቃል ወጎችን በማሰባሰብ ነበር፡፡ ይህም መሐመድ ከሞተ ከመቶ ዓመት በላይ በሆነ ጊዜ ውስጥ የተከወነ ሥራ በመሆኑ የመረጃ ምንጮቹ አፈ ታሪኮች መሆናቸውን ያሳያል፡፡
🔹 የጸሐፊውና የመጽሐፉ ተአማኒነት
“ሲራ” የተባለው የመሐመድን የሕይወት ታሪክ የሚያትተው የዚህ መጽሐፍ አካል በተደጋጋሚ የመጥፋት ችግር ደርሶበታል፡፡ የኢብን ኢስሐቅ ኦርጂናል ሥራ በመጥፋቱ በተማሪው በአል-ባኪይ የታረመና የተስተካከለ ቅጂ ሆኖ ወጥቶ ነበር፡፡ ሆኖም ይህ ቅጂም በመጥፋቱ ምክንያት ወደዚህ ዘመን ሳይተላለፍ ቀረ፡፡ የአል-ባኪይ ተማሪ የነበረው ኢብን-ሂሻም የተባለው ሰው ግን የራሱን ቅጂ በማዘጋጀቱ ወደ ዘመናችን ሊተላለፍ ችሏል፡፡ በሌላ መስመር ደግሞ ሰልማህ ኢብን ፋዲ አል-አንሳሪ የተባለ የኢብን-ኢስሐቅ ሌላ ተማሪ የመምህሩን ሥራ የተሻሻለ ቅጂ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ ይህም ሥራ በመጥፋቱ ቅጂው የተገኘው በተማሪው ሙሐመድ ኢብን ጃሪር አል-ታባሪ “የነቢያትና የነገሥታት ታሪክ” በተሰኘው መጽሐፍ ውስጥ ነው፡፡ በአጭር
ቃል አሁን የኢብን-ኢስሐቅ “ሲራት ረሱላህ” እየተባለ የሚጠራው የመሐመድ የሕይወት ታሪክ መጽሐፍ የተዘጋጀው ኢብን-ኢስሐቅን በአካል ባላገኙትና በማያውቁት የተማሪዎቹ ተማሪዎች የቅጂ ቅጂ ሆኖ ነው ማለት ነው፡፡
መጻሕፍት በዘመናት መካከል በቅጂ መተላለፋቸው የታሪካቸው ገጽታ በመሆኑ ብዙም የሚነቀፍ አይደለም፡፡ ምንጫቸውና የቅጂ ሂደታቸው በጥርጣሬ የሚታይ ከሆነ ግን ተአማኒነታቸው ላይ ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም፡፡ የሲራው ዋነኛ ጸሐፊ ኢብን-ኢስሐቅ መጽሐፉን በአፈ ታሪክ ላይ ተመስርቶ ከመፃፉም በላይ ቀጥለን እንደምንመለከተው ከፍተኛ የተአማኒነት ችግር ያለበት ሰው ነው፡፡ የእርሱን ሥራ ቅጂውን ያስተላለፉ ሰዎችም የሚጣልባቸው እምነት የሚወሰነው በራሳቸው ግንዛቤ አስተካክለው ባዘጋጁት በዚህ መጽሐፍና ጸሐፊ የታማኝነት ደረጃ ላይ ነው፡፡ እነርሱም በቅጂያቸው ላይ ያሳዩት ልዩነት ከራሳቸው ግንዛቤ በመነሳት ይቆርጡና ይቀጥሉ እንደነበር ያመላክታል፡፡
የኢብን-ሂሻምና የአል-ታባሪ ሥራዎች በአብዛኛው ተመሳሳይ ቢሆኑም በርካታ ልዩነቶችም አሏቸው፡፡ በአል-ታባሪ የተጠቀሱ አንዳንድ ታሪኮች በኢብን-ሂሻም ውስጥ አይገኙም፡፡ የጠፋው የኢብን- ኢስሐቅ ኦርጂናል ጽሑፍ ሕልውናው የቀጠለው በኢብን ሂሻም የራሱ ሥራ ውስጥ በአብዛኛው በመገልበጡ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ ሆኖም ኢብን ሂሻም በዚህ ግልበጣው በአጭሩ የተቀመጡ የኢብን-ኢስሐቅ አገላለጦችን ለማብራራት በመሞከሩ አልፎ አልፎ ዓረፍተ ነገሩን እንደቀየረው መጽሐፉን ወደ እንግሊዝኛ የተረጎመው አልፍሬድ ጉይላውም በትርጉም ሥራው (ገጽ xvii) ላይ አመልክቷል።
በተጨማሪም ጉይላውም እንደጠቀሰው ኢብን ሂሻም በአል-ታባሪ መጽሐፍ ውስጥ የተነገሩ ብዙ ትረካዎችን በእርሱ ጽሑፍ ውስጥ አላካተተም፡፡ አል-ታባሪ ግን ለእነዚህ ትረካዎች ኢብን-ኢስሐቅን በምንጭነት መጥቀሱ ተዘግቧል፡፡ ¹ ራሱ ኢብን-ሂሻምም ከራሱ ግንዛቤና ከመምሕሩ አስተያየት በመነሳት አንዳንድ ነገሮችን ይቀንስ እንደነበር እንዲህ ሲል ተናግሯል “ለመነጋገር አሳፋሪ የሆኑ ነገሮች፣ አንዳንድ ሰዎችን ሊያስጨንቁ የሚችሉ ጉዳዮችና በአል-ባካኢ [የኢብን ሒሻም መምህር] ተዓማኒ ተደርገው እንደማይቆጠሩ የተነገሩኝን ጉዳዮች እንዲወገዱ አድርጌያለሁ” ²
የዚህ መጽሐፍ ቅጂ አዘጋጆች ከዋናው ሥራ ላይ ማጉደላቸውና መጨመራቸው ራሱን የቻለ ግዙፍ የተአማኒነት ጥያቄ የሚያስነሳ ቢሆንም ትልቁ ችግር ግን በርካታ ምሑራን በራሱ በኢብን-ኢስሐቅ ላይ አመኔታ ማጣታቸው ነው፡፡ እምነት ያጡበት ደግሞ ራሳቸው ሙስሊም ምሑራን ናቸው፡፡ ለዚህ አስተሳሰባቸው የሚጠቅሱት ብዙ ማሳያዎች ቢኖራቸውም ጥቂቶቹን ብቻ እንመልከት፡፡ በቅድሚያ እንደ ትልቅ መሥፈርት የሚታየው የሙስሊሞች ነቢይ መሐመድ የቁርአን አንቀጽ በመጥቀስ የዘር ሀረግ ቆጣሪዎችን የገሰፀበት ንግግር ነው፡፡ እንዲህ ይላል
“ነቢዩ የዘር ሐረጋቸውን ሲናገሩ ከመአድ ኢብን አድነን ኢብን ኡደድ በኋላ ያለውን ጠቅሰው አያውቁም፡፡ ከዚህ በኋላ ዝም አሉና እንዲህ አሉ፡- የዘር ሐረግ ቆጣሪዎች ውሸታሞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም አላህ እንዲህ ብሏል፦ ‘… የእነዚያም ከእነሱ በኋላ የነበሩት ከአላህ በስተቀር ሌላ የማያውቃቸው (ሕዝቦች)… አሉ' ³ ኢብን አባስ እንዲህ አለ፦ ነቢዩ ከአድናን በፊት ያለውን የዘር ሐረጋቸውን ከአላህ መስማት ቢፈልጉ ይችሉ ነበር”፡፡⁴ ኢብን-ኢስሐቅ ግን የመሐመድን የዘር ሐረግ እስከ አዳም ድረስ በመቁጠር በመጽሐፉ አስፍሮታል፡፡ ኢብን-ሂሻምና አል-ታባሪም ያለ አንዳች ማስተካከያ ይህንኑ የዘር ሐረግ ዝርዝር በመጽሐፋቸው አካተውታል፡፡
እንግዲህ አላህ በቁርአኑ ማንም እንደማያውቅ የገለፀውን ያለፈውን ትውልድ ሐረግ የፃፉ ሰዎችን ማመን ይሻላል ወይንስ የቁርአኑን ተናጋሪ ማመን..? ጥያቄውን ለሙስሊም ወገኖች እንተወዋለን፡፡ “የዘር ሐረግ ቆጣሪዎች ውሸተኞች ናቸው” የሚለውን የመሐመድ ተግሳፅ ወደ ጎን ብሎ “ከባለቤቱ ያወቀ..” እንደሚባለው “የትውልድ ቁጥርህ እንዲህ ነው” ያለውን ኢብን-ኢስሐቅ ሀሰተኛነት መግለጥ ተገቢ ነው፡፡ ይህንንም በግልፅ የተናገሩ እስላማዊ መምሕራን አሉ፡፡
ከእነዚህም አንዱ የኢማሙ ማሊክ የፊቅህ ትምህርት ቤት ባልደረባ የነበረው ማሊክ ኢብኑ-አነስ ይገኝበታል፡፡ ማሊክ ኢብኑ-አነስ በዚያው በኢብን-ኢስሐቅ ዘመን የነበረ ሰው ሲሆን ከእርሱ ጋርም በመዲና ተገናኝቶ ተከራክሯል፡፡ ከዚያ በኋላ ኢብን-ኢስሐቅ ከትውልድ ከተማው ለመሰደድ ግድ ሆኖበታል፡፡ ይህንንም አስመልክቶ ማሊክ “ኢብን ኢስሐቅ እጅግ ከማይታመኑ አጭበርባሪዎች አንዱ ነው፤ ስለዚህ ከራሱ ከተማ ከመዲና አባረነዋል” ሲል መናገሩ ተዘግቧል፡፡⁵ እስከ አዳም ድረስ የዘር ሐረግ ስለሚቆጥር ሰው ተጠይቆም ተቃውሞውን በገለጸበት ወቅት እንዲህ በማለት ነበር ትችቱን ያቀረበው “ይህንን የመሰለ እውቀት ከየት አገኘ?” እስከ እስማኤል ድረስ ስላለው በተጠየቀ ጊዜም በተመሳሳይ ተቃውሞውን ሲገልጽ፦ “ይህንን መረጃ ማን ማቅረብ ይችላል?” ብሎ ጠይቋል፡፡ ⁶
በተጨማሪም ማሊክ ኢብኑ-አነስ በመዲና ከሚኖሩ አይሁዶችና ወደ እስልምና ከመቀየራቸው ዜና ጋር ተያይዞ ያለውን የመሐመድ ታሪክ ፈፅሞ አልተቀበለውም፡፡ እንዲህ ያለው አቋም ግን የእርሱ ብቻ አልነበረም። ታዋቂው እስላማዊው ሊቅ ኢብን ሃጃር አል-አስቃላኒም እነዚህኑ ታሪኮች “ያልተለመዱ ተረቶች” ሲል አጣጥሏቸዋል፡፡⁷ ኢብን-ኢስሐቅ የተዘበራረቁ ግጥሞችን በሥራው ውስጥ እንዳካተተ የተናገሩ የተለያዩ ሃያሲያንም አሉ፡፡ የ14ኛው ክፍለ ዘመን የታሪክ ምሑር የነበረው አል-ዳሐቢ የሀዲስ የቃላት አሰያየምን በመጠቀም ባቀረበው ትችት ኢብን-ኢስሐቅ በስራው ውስጥ በርካታ የትረካ ሰንሰለታቸው የተሰበረ ትረካዎችንና ከአጠራጣሪ ተራኪዎች የመነጨ ዘገባን ማካተቱን ተናግሯል፡፡ ⁸
ኢብን ኢስሐቅ የተለያዩ ሀዲሳትንም ሰብስቦ እንደነበር ይታወቃል፡፡ ከታወቁት የሀዲስ ዘጋቢዎች በዘመን የቀደመ ቢሆንም እንኳ ሀዲሳቱ ግን ተቀባይነት አላገኙለትም፡፡ በርካታ እስላማዊ ሊቃውንት ሙሐመድ አል-ቡኻሪን ጨምሮ የእርሱን ትረካዎች በሳኂህ መጻሕፍቶቻቸው ውስጥ አልተጠቀሙባቸውም፡፡ ታዋቂው የፊቅህ ሊቅ አሕመድ ኢብን-ሀንበልም ከፊቅህ ጋር የሚገናኙ የእርሱን ትረካዎች አልተቀበላቸውም።
በእርግጥም በሀዲስ ጥናትና የመረጃ አጠቃቀስ ሂደቶች ውስጥ ኢብን-ኢስሐቅ አይታወቅም ማለት ይቻላል፡፡ እነዚህና ሌሎች በርካታ እስላማዊ ሊቃውንት እንደ ውሸታም እንደሚያዩት የእስልምና መዝገበ ዕውቀት ያትታል፡፡⁹ እንግዲህ በእስልምናው ዓለም ከቁርአን ቀጥሎ እንደ ሁለተኛ የመረጃ ምንጭነት በሚያገለግሉት ሀዲሳት ትረካዎች እምነት ያልተጣለበት ግለሰብ የቃል ወጎችን ሰብስቦ ባዘጋጀው የተጋነነ ታሪክ እንዴት ሊታመን ይችላል..?
ሌሎች የቅርብ ጊዜ ጸሐፊያንም በኢብን-ኢስሐቅ መጽሐፍና መሰል ድርሰቶች ስለ መሐመድ የተነገረው ሊታመን የማይችል ግነት እስልምናን እያስተቸ መሆኑን ጽፈዋል፡፡ ይሄ ሁሉ ነገር የሚያሳየን የቃል ወጎችን ሰብስቦ፣ በርካታ የፈጠራ ትርክቶችንም ጨምሮ ከፃፉት በኋላ እርሱኑ እንደ ኦርጂናል መረጃ ለማሳየት መሞከር “ተጨፈኑ ላሞኛችሁ” ከማለት ተለይቶ አይታይም፡፡ በዚያው ዘመን የነበሩ ኢብን-ኢስሐቅና ሥራውን የሚተቹ ሙስሊም ምሑራንን ችላ ብለው የእርሱን የሀሰት ትርክት አበጃጅተው ያስተላለፉት ኢብን ሂሻምና አል-ታባሪም ከዚህ ወቀሳ አያመልጡም፡፡ ከ”ነቢዩ” መሐመድ የተገለጠ ተግሳፅና ቁርአኑ ካስቀመጠው ገደብ በድፍረት ያለፈን ሰውና መጽሐፍ እንደ ሁነኛ የታሪክ ምንጭ መቁጠር ከፍተኛ የመርኅ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው፡፡
የሚደንቀው በመዲና የነበሩትና "በኒ ቁራይዛ" የተሠኙትን የአይሁድ ጎሣዎች የጅምላ ግድያ ይኸው ኢብን ኢስሐቅ በመጽሐፉ ዘግቦታል። በዚህ ጭፍጨፋ ከስድስት መቶ እስከ ዘጠኝ መቶ የሚደርሱ የተማረኩ ወንዶች በመሐመድ ሠራዊት ተገድለዋል። ይህንን ታሪክ ለማስተባበል የሚሞክር አንድ ጥናት ዋሊድ አራፋት በሚባል ሰው በ1976 ዓ.ም ወጥቷል።¹⁰ ይህ ሰው ኢብን ኢስሐቅ የዘገበውን ይህን ታሪክ ሐሰት ለማድረግ ብዙ ጥረት አድርጓል።
ዋንኛ መከራከሪያውም ኢብን ኢስሐቅ ታሪኩን የሰበሰበው ከመቶ ዓመት በኋላ መሆኑንና ዘገባው የተወሰደው "ሰለባ ከነበሩት ወገኖች" በመሆኑ እንደ ጠላት የሚቆጠሩት አይሁድ የታሪኩን መጠን ሊያጋንኑት ይችላሉ የሚል ነው። በተጨማሪም ይህ ታሪክ በአይሁዶች ዘንድ ቀደም ብሎ ከነበረው የማሳዳ (Masada) የጅምላ ጭፍጨፋ ታሪክ ጋር እንደሚመሳሰልና፣ ዘጋቢዎቹ የድሮውን መከራቸውን ከዚህ አዲስ ክስተት ጋር ቀላቅለውት ሊሆን እንደሚችል ያትታል።
በርካታ እስላማዊ ምሑራን ይህንን አዲስ ጥናት የነቢያቸውን ነቀፌታ ለመሸፈን ሲጠቀሙበት ይስተዋላል። እንዲህ የሚያደርጉ ሁሉ አንድን ነገር በተመሳሳይ መመዘኛ የመለካት ግዴታ ውስጥ ይገባሉ። አሊያ ነገራቸው ሁሉ የአባይ ሚዛን ልኬት (double standard) ተጠቃሚ መሆናቸውን ያሳይባቸዋል።
ኢብን ኢስሐቅ ከመቶ ዓመት በኋላ አፈ ታሪኮችን ወደ ጽሑፍ የመቀየር ሥራው ለዘገባው እምነት የማያስጥልበት ከሆነ ስለ ሐበሻው ንጉሥ ያወራውም የማይታመን ተደርጎ መወሰድ ይኖርበታል። የባኑ ቁራይዛ ጭፍጨፋ የመረጃ ምንጮች እንደ ጠላት መቆጠራቸው መረጃውን የሚያዛባው ከሆነ ስለ ንጉሱ ያወሩት ደግሞ የመሐመድ ወዳጆች በመሆናቸው ተወዳጅነት ለማግኘት የፈጠሩት የማይሆንበት ምክንያት አይኖርም። አይሁዶቹ አስቀድሞ የደረሰባቸውን የሌላ ሥፍራ ጭፍጨፋ ከባኑ ቁራይዛ ጋር ደባልቀው አውርተውት ይሆናል ተብሎ ከተገመተ በዚሁ ስሌት የንጉሱ መስለም ወሬ ከአንድ ግለሰብ ወይም አካባቢያዊ ተጠሪ መስለም ጋር ተምታቶ ተጽዕኖን ለማስፋትና ተቀባይነትን ለመጨመር የተፈበረከ ሊሆን ይችላል ብሎ ማሰብስ ምክንያታዊ አይሆንምን..? በእርግጥም ይህንኑ የሚያሳዩ በርካታ መረጃዎችም አሉ።
በጥቅሉ እስላማዊው ትውፊቶች እምነት የሚጣልባቸው ስላልሆኑ እንኳን ባልነበሩበት ሥፍራ ይቅርና በዚያው ክበብ ስለሆነው ነገርም የሚሰጡት መረጃ ተቀባይነት ያለው ሚዛንም የሚደፋ አይደለም። ኢትዮጵያዊው ክርስቲያን ንጉሥ ሰልሞ ነበር የሚለው ትርክትም ከበርካታዎቹ ፈጠራዎች እንደ አንዱ የሚቆጠር ብቻ ነው፡፡ ይህንኑ የሚገልፁ ተጨማሪ ማስረጃዎችና ትንታኔዎችንም በሥፋት ማቅረብ ይቻላል፡፡
ማጣቀሻዎች 👇
¹ E.g., al-Tabari, The History of al-Tabari, volume VI. Muhammad at Mecca (SUNY 1988) at p. 56)
² Alfred Guillaume. The Life of Muhammad, A Translation of Ibn Ishaq’s Sirat Rasul Allah; 1955, p. 691
³ ሱረቱ-ኢብራሒም፡14÷9
⁴ ሲራ ኢብን ሳድ ቅጽ 1, ክፍል 1.11.3
⁵ Halabieh, I, page 93
(Siyar Alam al-Nubala Vol. 7 P. 37)
⁶ ሲራ አል - ናባውያህ ቅጽ 1፣ ገጽ 51
⁷ Tahdhib al-Tahdhib
⁸ Al-Dhahabī , Mī zā n al-iʿ tidā l fī naqd al-rijā l, at “Muhammad ibn Ishaq”
⁹ Encyclopidia of Islam vol 3, page 810-811
¹⁰ Arafat, W. N. (1976-01-01). “New Light on the Story of Banū Qurayẓ a and the Jews of Medina”. Journal of the Royal Asiatic Society of Great Britain and Ireland (2): 100–107]
(የሳንኮፋ ሰንኮፍ እና ሌሎች ከገጽ 102-107 ከውስን ተጨማሪ ሃሳቦች ጋር)
Blogger Comment
Facebook Comment