✍ ኑዕማን ኢድሪስ
ጽሁፉን በትዕግስት አንብቡት። ከዚያም የናንተን ሃሳብ በኮሜንት አስፍሩ .. አመሰግናለሁ!
በኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ የማንነት መገለጫዎች ውስጥ የፊደላት ቅርጽ ዝም ብሎ የሚመረጥ ሳይሆን ጥልቅ የሆነ ታሪካዊ፣ ሃይማኖታዊ እና ፍልስፍናዊ ትርጉም ያዘለ ነው።
ድምጻዊ ቴዲ አፍሮ በስራዉ ላይ "ቶ" የተሰኘችውን ፊደል በመስቀል ቅርጽ መጠቀሙ ከግል ምርጫ ባለፈ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትውፊት እና ከጥንታዊው የዓለም ስልጣኔ አፈ ታሪክ ጋር የተቆራኘ ነው። ይቺን ፊደል በደንብ የማስታዉሳት የይስማዕከ ወርቁ 'ዴርቶጋዳ፣ ራማቶሃራ፣ ዣንቶዣራ፣ ዮራቶራና ዮቶር' የተሰኙት መጽሃፎች ላይ ነዉ። በርግጥ ሌሎች መጽሃፎችም ላይ አለች። አስተዉላችሁ ከሆነ ሁሉም መጽሃፍ ርዕሶች ላይ 'ቶ' አለ። ከፊደላቶቹ መካከልም ለየት ብሎ የሚታየዉ እሱ ነዉ። መጸሐፉን ካነበብኩት አስራ አምስት አመት ቢያልፈኝም ሁሉንም በደንብ አስታዉሳለሁ።
'ቶ' እና የቀደምት ስልጣኔ ምልክት
በጥንታዊው የዓለም ታሪክ በተለይም በግብፅ ቤተክርስትያን ስልጣኔ (ይህም ከጥንታዊ ኢትዮጵያ/ኩሽ ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ይታመናል) "አንክ" (Ankh) የሚባል ምልክት አለ። ይህ ምልክት የሕይወት መገለጫ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
የቴዲ አፍሮ የ'ኢትዮሪካ' (Ethiorika) አርማ ላይ እንደምናየው 'ቶ' ፊደልን ከዚህ ከጥንታዊው የሕይወት ምልክት ጋር አዋህዶታል። ይህም 'ኢትዮጵያዊነት (በዚያ ጊዜ በነበር አተረጓጎም) ክርስቲያናዊነት የሕይወት እና የጥንታዊ ስልጣኔ ምንጭ ነው' የሚል ፍልስፍናዊ መልእክት ያስተላልፋል።
የ'ቶ' ምስጢር በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ትውፊት
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ትምህርት ውስጥ ፊደላት የራሳቸው መንፈሳዊ ትርጓሜ አላቸው። 'ቶ' ፊደል በመስቀል ቅርጽ መሳሏ የሚከተሉትን ትርጉሞች ይይዛል ...
1ኛ የመዳን ምልክት .. በመጽሐፈ ሕዝቅኤል (9፡4) ላይ 'በግምባራቸው ላይ ምልክት አድርግ' ተብሎ የተጠቀሰው በጥንታዊው የዕብራይስጥ ፊደል "ታው" (Taw) እንደሆነና ቅርጹም እንደ መስቀል እንደነበር ሊቃውንቶች ያስረዳሉ። በግዕዝ ደግሞ ይህ 'ቶ' ነው። ስለዚህ በነሱ አተረጓጎም 'ቶ' የመዳን እና የጥበቃ ምልክት ተደርጋ ትታያለች።
2ኛ የመጨረሻነት (Omega) .. በግዕዝ ፊደላት ውስጥ 'ቶ' የመጨረሻዋ (ተ ብሎ ለሚጀምረው ፊደል ማሳረጊያ) ሆና ታገለግላለች። ይህም ክርስቶስ 'ፊተኛውና ኋለኛው' (Alpha and Omega) መሆኑን ለማብሰር በመስቀል ቅርጽ ትሳላለች።
ቴዲ አፍሮ አብዛሃኛዉን ጊዜ ሙዚቃዎቹን ከፖለቲካና ከአፈ ታሪክ ጋር ማያያዝ ይወዳል። እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎቹ የሀገራችን ደራሲዎች ድርሰታቸዉን ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያይዙታል። 'ፍቅር እስከ መቃብር' መጽሃፎችን ሁሉ በምን የሚበልጥ መሰላችሁ? ...
ወደ ቴዲ ስንመለስ .. 'ቶ'ን በመስቀል ቅርጽ መጠቀሙ 'ኢትዮጵያዊነት እና ክርስትና የማይነጣጠሉ ናቸው' የሚለውን የቆየ ትውፊት ለማንጸባረቅ ነው።
በአድዋና በተለያዩ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ክስተቶች ውስጥ መስቀል እንደ ሰንደቅ ዓላማ እና እንደ ጽናት ምልክት ሆኖ አገልግሏል። ቴዲ አፍሮም ይህንን ምልክት ሲጠቀም የጥንቱን የፊደል ቅርጽ (አርኪታይፕ) ወደ ዘመናዊው የጥበብ ዓለም በማምጣት ማንነትን የመለየት (Identity branding) ስራ እየሰራ ነው።
ከላይ ከተጠቀሱት ታሪካዊ ትርጉሞች በተጨማሪ 'ቶ' ፊደል በተፈጥሮዋ የመስቀል ቅርጽ ስላላት ለግራፊክስ ዲዛይን እና ለምስላዊ ውበት (Aesthetics) በጣም ምቹ ነች። ቴዲ አፍሮ 'ኢትዮሪካ' በሚለው ጽሁፍ ውስጥ 'ቶ'ን በመስቀል መልክ በማስቀመጥ .. የአፍሪካን አንድነት (በመሃል ባለችው የአፍሪካ ካርታ)፣ የሃይማኖት ጽናትን (በመስቀል ቅርጿ ቶ)፣ የንግስና ግርማን (በአንበሳው ምልክት) በአንድ ላይ አዋህዶ አቅርቧል። እኔ እንደተረዳሁት!
በአጠቃላይ ቴዲ አፍሮ 'ቶ'ን በመስቀል ቅርጽ የተጠቀመው ኢትዮጵያ የፊደል የጥበብና የክርስትና ምድር መሆኗን ለመግለጽ ነው (እርግጠኛ ስለሆንኩ ይመስለኛል አልልም)። ይህ ምልክት ለሱና ለመሰሎቹ የጥንታዊ ስልጣኔ ትንሳኤ (Renaissance) እና የኢትዮጵያዊነት ኩራት መግለጫ ድልድይ ነው። (እንደዛ ያስባሉ 😁)
ሌላዉ ደግሞ ...
ኢትዮጵያዊው የዜማ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ በደረሳቸው ዜማዎች ውስጥ ፊደላትና ምልክቶች የራሳቸው የሆነ መንፈሳዊ ምሥጢር አላቸው። ቴዲ አፍሮ በዜማዎቹ ውስጥ የጥንታዊውን 'በዝ' እና 'ግዕዝ' ስልቶችን ከዘመናዊው ሬጌ እና ፖፕ ሙዚቃ ጋር ያዋህደዋል። 'ቶ'ን በመስቀል ቅርጽ መጠቀሙ የሙዚቃው መሰረት ከያሬዳዊ ዜማና ከቤተክርስቲያን ቅኔያዊ ስርአት የተቀዳ መሆኑን በምስል ለመግለጽ (Visual metaphor) የተጠቀምበት ስልት ነው።
እሱም ሆነ ሌላ አርቲስት ደጋግሞ የሚጠቀመው ምልክት ብራንድ (Brand) ብቻ ሳይሆን የተመልካቹን ስነ ልቦና ለመቅረጽ የሚያገለግል መሳሪያ ነው።
ቴዲ .. ከክርስቲያኖች በተጨማሪ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሙስሊሞች ሙዚቃዉን እንደሚያዳምጡት ጠንቅቆ ያዉቃል። ታዲያ አዕምሯችን ላይ የሆነ መልዕክት እያስተላለፈ እንደሆነ ግልጽ አይደለም? 🤔
መስቀል ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኞች የመሸሸጊያ፣ የመጽናኛ እና የድል ምልክት ነው። 'ቶ'ን በመስቀል ቅርጽ በማቅረብ አድማጩ ከሙዚቃው ባለፈ መንፈሳዊ ትስስር እንዲሰማው ያደርጋል።
በምስሉ ላይ እንደምናየው "ቶ" ፊደል በ 'ኢቶሪካ' ቃል ውስጥ በደማቅ ቀለምና በመስቀል ቅርጽ ተቀምጣለች። ይህ ዲዛይን በምዕራባውያን ዘንድ ከሚታወቁ የ'T' ቅርጽ ምልክቶች ጋር ተቀራራቢነት ስላለው የኢትዮጵያን ፊደል ለዓለም አቀፍ ማህበረሰብ በቀላሉ "Iconic" በሆነ መንገድ እንዲታወቅ ያደርገዋል። የፊደሉ የላይኛው ክብ ክፍል የዓለምን አንድነት ወይም የፀሐይን ብርሃን እንደሚወክል ተደርጎም ሊተረጎም ይችላል።
በመጨረሻም .. ቴዲ አፍሮ እና መሰል አርቲስቶች፣ ደራሲዎች 'ቶ'ን በመስቀል ቅርጽ መጠቀማቸው የአጋጣሚ ጉዳይ አይደለም። ይልቁንም የታሪክ ትውስታን (ከጥንታዊው አንክ እስከ አሁኑ ግዕዝ) ለማደስ፤ መንፈሳዊ ማንነትን ከሀገራዊ ፍቅር ጋር ለማጣመር፤ የጥበብ ፍጽምናን (የመጨረሻዋ ፊደል በመሆኗ) ለመግለጽ የተጠቀሙበት ጥልቅ ምስጢር ነው።
ታዲያ እኛ ምን ቤት ነን? .. እኛ ያልኩት ሙስሊሞችን ነዉ። አዎ ኢትዮጵያዊ ነን ግን ደግሞ ኢትዮጵያዊ ነን ብለን የአዝማሪዎችን ተረትና አፈ ታሪክ አዕምሯችን ላይ ማተም አለብንዴ? ..እንኳን ሙዚቃ አዳማጭ ያልሆናችሁ ሙስሊሞች ሙዚቃ አዳማጭ እንኳ ብትሆኑ በእንደዚህ አይነት ተራ ተንኮሎች ልትታለሉ አይገባም። ንቁ ... ንገረኝ ካላችሁኝ 'ሃይማኖታችሁ ከሀገራችሁም በላይ ነዉ!'
Blogger Comment
Facebook Comment