ዘመናዊ የታሪክ ምሑራንስ ስለ ንጉሥ አርማሕ "ነጃሺ" ምን ብለዋል..?


ባለፉት ጊዜያት ውስጥ የኢትዮጵያ ታሪክ በተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር የታሪክ ምሑራን በሥፋት ተጽፏል፡፡ በተለይ የውጮቹ  ምሑራን በጦርነትና በተለያየ ምክንያት ከሀገር ቤት ወጥተው የአውሮፓ ሀገራት ሙዚየሞችን ባጣበቡት የብራና መጻሕፍት በመታገዝ፣ ሀገራችንን መላልሶ በመጎብኘት፣ ታሪካዊ ሥፍራዎችን፣ ገዳማቱንና ሐውልቶችን በማጥናት፣ በአርኪኦሎጂ የጥናት መስክ ጥልቅ ምርመራ በማድረግ ትላልቅ መጻሕፍትን አሳትመዋል፡፡ ከእነዚህም ምሑራን መካከል ጀምስ ብሩስ፣ ኤድዋርድ ኡልንዶርፍ፣ ኮንቲ ሮሲኒ፣ ዋሊስ ባጅ፣ ኢኖ ሊትማን፣ ኢግናዝዮ ጉይዲ፣ ስፔንሰር ትሪንግሐም፣ ... ይገኙበታል፡፡ ከሀገራችን ጸሐፊዎችም ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወ/ሥላሴ፣ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ፣ ፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ፣ ፕሮፌሰር ታደሠ ታምራት ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ... ከብዙዎቹ ጥቂቶቹ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
 
እነዚህ የታሪክ አጥኚዎች የሀገራችንን ታሪክ ከተለያየ ማዕዘን አጥንተው በተለያየ ርዕስ ሲፅፉ አንዳንዶቹም ጥቅላዊ ዳሰሳ ሲያደርጉ የአክሱም ነገሥታት ታሪክንና የሰባተኛው ክፍለ ዘመን ሁኔታን ማንሳታቸው አልቀረም፡፡ የአረብ ሙስሊም ታሪክ ጸሐፊያን በተለይም የኢብን-ኢስሐቅ መጽሐፍን በራሳቸው ሥራ ውስጥ ያስተዋወቁት ኢብን-ሂሻምና አት-ጦበሪ እንደሰለመ ስለተናገሩት ክርስቲያን ንጉሥ የየራሳቸውን ምልከታ አኑረዋል። 

በተለይም “History of Ethiopia” በሚል ርዕስ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የፃፈው ታዋቂው ታሪክ ጸሐፊ Sir E.A Wallis Budge እና “Islam in Ethiopia” በሚል ርዕስ ስለ እስልምና ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የፃፈው ሌላው የታሪክ አዋቂ Spencer Tramingham በ615 ዓ.ም የመሐመድ ተከታዮች በእንግድነት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ጽፈዋል፡፡ በተለይ ስፔንሰር ትራሚንግሃም የተባለው ጸሐፊ ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት የእስልምና እምነት ተከታዮች መካከል የተወሰኑት ወደ ክርስትና እምነት እንደተቀየሩ ሲዘግብ “ንጉሡ ሰልሟል” የሚለውን ወሬ ግን “የሙስሊሞች አፈ ታሪክ” ሲል አጣጥሎታል፡፡ ¹ 

ዋሊስ ባጅ ደግሞ ኢትዮጵያ ከሌሎች የክርስትና ሀገሮች ሁሉ የክርስትናን እምነት ስታስፋፋና ስታጠናክር እንደኖረች ገልፆ ነገሥታቱ ሁሉ የክርስትና እምነት ተከታዮች እንደሆኑ አስረግጦ ፅፏል፡፡ በመገረም ስሜትም “የአቢሲኒያ ክርስትናን ታታሪና አክራሪ ባህሪ ስናስታውስ አርማህ እና ጳጳሳቶቻቸው እስልምናን መቀበላቸው ሊያስደንቀን ይገባል” ብሏል፡፡ ²  

እነዚህ የታሪክ ምሑራን የሙስሊሞችን ወደ ኢትዮጵያ መምጣት ፅፈው ስለ ንጉሱ መስለም ትንፍሽ አለማለታቸው የአረብ ጸሐፊያን ትርክት ባዶ ቅዠት መሆኑን አመላካች ነው፡፡ ሪቨረንድ ጎድፍሬይ የተባለው ሌላ ታሪክ ጸሐፊም “እስልምናና አፍሪካ” በሚል ርዕስ በፃፈው መጽሐፍ በተጠቀሰው ዓመት የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውን ሲጠቅስ ንጉሱ የእስልምናን እምነት መቀበሉን የሚጠቅስ ታሪክ አልዘገበም፡፡ ይልቁንም የተወሰኑት 
ስደተኞች ወደ ክርስትና እምነት መቀየራቸውን በደማቁ ጽፎታል፡፡ በትለር የተባለ ጸሐፊም “to-day remains the one power which has never bowed the knee to Islam.” “ኢትዮጵያ እስከዛሬ ለእስልምና ጉልበቷን ያላንበረከከች ብቸኛ ኃይል እንደሆነች ነው” ብሏል፡፡ ³ 

በዚሁ ጉዳይ ላይ Ancient & Medieval Ethiopian History በሚል መጽሐፋቸው ጥናታዊ ዳሠሣ የሠሩት ፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለ ሥላሴ “በዚያን ወቅት ማለትም የመሐመድ ተከታዮች ተሰደው ወደ አክሱም በመጡበት ጊዜ እስልምና ገና በማቆጥቆጥ ላይ ያለ አዲስ ሃይማኖት ስለሆነ ንጉሥን ያህል አስፈላጊ ስብዕና ለመሳብ ያልዳበረ” መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የሙስሊሞቹ ወኪል ጃዕፈር በንጉሡ ፊት ያነበበው ንባብም ሆነ መሐመድ ልኮታል በተባለው ደብዳቤ ውስጥ የሚገኘው “ሰማይንና ምድርን የሚገዛውን አንድ አምላክ እንድታመልክ አሁን እጠራሃለሁ” የሚለው አንኳር ቃል ፈፅሞ አዲስነት የሌለውና የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርትን የሚደግም በመሆኑ ንጉሡ በዚህ ቃል የክርስትና ሃይማኖቱን ተወ ማለት እንደማይቻል ጽፈዋል፡፡ ⁴  

እንዲያውም የዚህ ታሪክ ምንጭ የሆነውን አት-ጦበሪን የንጉሡን መስለም አስመልክቶ የፃፈውን ሲተቹ “ይህ የጦበሪ አገላለጥ ግልጽ ምኞት ነው ተብሎ ሊወሰድ የሚችል ከሃይማኖታዊ ስሜት የመነጨ መግለጫ ነው” ብለዋል፡፡ ⁵ 

ተክለ ጻድቅ መኩሪያም የአበሻው ንጉሥ ወደ እስላምነት ለመዞሩ ብቻ ሳይሆን ልጁን ከ60 ሰዎች ጋር ወደ መሐመድ ለመላኩም ደንበኛ ማስረጃ የለም ብለዋል፡፡ ጨምረውም ስደተኞቹ ስለተደረገላቸው እንክብካቤ ለመሐመድ በመናገራቸው ምክንያት በአክሱም ንጉሥና በመሐመድ መካከል መልካም ወዳጅነት ነበረ፡፡ ይህን የወዳጅነት ግንኙነት፣ የተደረገውን የሰላምታና የደብዳቤ ልውውጥ የሚያውቁ የአረብ ጸሐፊዎች የአክሱሙ ንጉሥ የሰለመ መስሏቸው ፅፈው እንደሆነ አይታወቅም የሚል አስተያየት አክለዋል፡፡ ⁶ 

ሙስሊም ጸሐፊያን የእነዚህ የታሪክ ሊቃውንትን አስተያየት በከፍተኛ ቅሬታ ሲያብጠለጥሉ ይታያሉ፡፡ እስላማዊ የታሪክ ጸሐፊዎች የፃፉትን በሙሉ ያለ አንዳች ጥያቄ ማንም ሰው እንዲቀበልላቸው መመኘት ራሱን የቻለ ነገር ነው፡፡ የንጉሡን መስለም ስለምን አልተቀበላችሁም ብሎ እስልምና ላይ ጥቃት እንደተሰነዘረ መቁጠር ግን ተገቢ አይደለም። እነዚህ የታሪክ ምሑራን ኢትዮጵያዊ ዕደ ክታባት (manuscripts) ላይ የሚሰነዝሩትን ትችት በደስታ ተቀብለውና ይህንንም እንደ መረጃ ተጠቅመው ሲያበቁ እስላማዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ሥራ ላይ ያቀረቡትን ትችት ማውገዝ ግን በትንሹ ሚዛናዊ ያለመሆንን የሚያሳይ ነው፡፡ 

ስለዚሁ ጉዳይ የሚያትተው “የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ታሪክ” የሚለው መጽሐፍ የሚከተለውን ይላል፡፡ “ፕሮፌሰር ስርግው እንደሚሉት ጦበሪ ስለ ነጃሺ መስለም የፃፈው ከሃይማኖታዊ ስሜት የመነጨ አጉል ምኞት ተጭኖት መሆኑን የሚያስረዳ፣ ትሪሚንግሃምም በነጃሺ መስለም ጉዳይ ላይ ጦበሪ ያሰፈረውን ዘገባ ‘አፈ-ታሪክ’ ብለው ለመፈረጃቸው የሚያቀርቡት አሳማኝ ማስረጃ ቢኖር ኖሮ የዘገባውን እውነትነት ማጠራጠሩ ወይም የአድሏዊነት ጥያቄ መነሳቱ አያስገርመንም ነበር”፡፡ ⁷ 

የፕሮፌሰር ሥርግውን መጽሐፍ ያነበበ ሁሉ በግልፅ እንደሚረዳው ክርስቲያኑ ንጉሥ ሊሰልም የማይችልበትን ምክንያት ዘርዝረው አስቀምጠዋል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው የጃዕፈር ገለፃ ለክርስቲያኑ ንጉሥ ምንም አዲስ ነገር የሌለው መሆኑን፣ በወቅቱ እስልምና ገና ያልዳበረ እንቅስቃሴ ስለሆነ በፖለቲካ ጉዳዮችም ማንም ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደማይችልና በንጉሡ ስም ተዘጋጅተው የተሠራጩት ሳንቲሞች ክርስቲያንነቱን የሚያስረዱ የመስቀል ምልክት ያሉባቸው እንደሆነ ጽፈዋል፡፡ ከዚህ የበለጠ ምን ዓይነት ማስረጃ እንዲያቀርቡ ተፈልጎ እንደሆነ ግልፅ አይደለም፡፡ ነው ወይንስ አረብ ጸሐፊያን የጻፉት ነገር ሁሉ ሊተች የማይችል የመረጃ አልፋና ኦሜጋ ተደርጎ እንዲቆጠር ታስቦ ይሆን..? 

የዚህ ነገር መነሻ ፦የሆነው አት-ጦበሪና ኢብን-ሂሻም የፃፉት ታሪክም ቢሆን ዝቅ ብለን በዝርዝር እንደምናየው ምንጩ ከሰዎች አፍ የተለቀመ አረባዊ ትውፊት ነው፡፡ በኋላም በብዙ ውጣ ውረዶችና ማስተካከያ ያለፈ ነው፡፡ ስለሆነም ትሪሚንግሃም የንጉሡን መስለም “የሙስሊሞች አፈታሪክ” እንደሆነ መግለፁ የአዋቂ ሰው አስተያየት እንጂ ከፍረጃ የሚቆጠር አይደለም፡፡ የንጉሡን መስለም ለመቀበል የተቸገሩትን የታሪክ ምሑራን የሚወቅሰው እስላማዊ መጽሐፍ ስሞታውን በመቀጠል እንዲህ ይላል። 

“ሌላው የኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ምሑር "በጅ" የአክሱም ነገሥታት እጅግ አጥባቂ ክርስቲያን ከመሆናቸው አኳያ ‘እስልምናን ተቀብለዋል’ ብሎ ለማሰብ እንደሚያዳግታቸው ገልፀዋል፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ በቅንነት ለሚተነትን ሰው ፕሮፌሰር በጅ ‘አንድ አጥባቂ ክርስቲያን ንጉሥ እስልምናን ተቀበለ’ ብሎ ማሰብ የሚከብዳቸው ከሆነ በዚሁ የእርሳቸው አመክንዮ (ሎጂክ) መሠረት በመቶ ከሚቆጠሩ ባልደረቦቹ ጋር በእምነቱ ምክንያትና ለእምነቱም ሲል ከትውልድ ቀዬው የተሰደደ አንድ ሙስሊም ‘ያንን የተሰደደበትን እምነት ይቀይራል’ ብሎ ማሰብ ለምን አልከበዳቸውም?’ ⁸ 

የወቀሳው መነሻ የታሪክ ምሑሩ ዋሊስ ባጅም ሆኑ ሌሎቹ በስደት ከመጡት የመሐመድ ተከታዮች የተወሰኑት እምነታቸውን ወደ  ክርስትና የቀየሩ እንዳሉ መፃፋቸው ነው፡፡ ወደ ክርስትና እምነት የተቀየረው አንድ ሰው ብቻ እንደሆነ የሚከራከረው ይህ መጽሐፍ ምሑሩን ንጉሡ አጥባቂ ክርስቲያን ስለሆነ ሊሰልም አይችልም ባለበት ሎጂክ በእምነቱ ምክንያት የተሰደደው ይህ ግለሰብ ስለ እምነቱ የከፈለውን መሥዋዕትነት ግምት ውስጥ በማስገባት ክርስቲያን ሊሆን አይችልም ስለምን አላለም ? በማለት ነው የሚወቅሰው፡፡ ለወቀሳው ምላሽ የመስጠት ተገቢው መብት የተወቃሹ ግለሰብ ቢሆንም ጉዳዩ ከተነሳ አይቀር እዚህ ነጥብ ላይ አስተያየት ሰጥቶ ማለፍ ጠቃሚ ይሆናል፡፡ 

ራሳቸው የእስላም ጽሑፎች እንደሚጠቁሙት መሐመድ በተነሳበት ዘመን "ሐኒፎች" በመባል የሚታወቁ ጥቂት ሰዎች ነበሩ፡፡ እነዚህም ወገኖች ጣኦት አምላኪዎች ከሆኑት አብዛኞቹ አረቦች ተለይተው የአብርሃምን እምነት የሚከተሉ የሚባሉና አንዱን አምላክ ብቻ በማምለክ የፀኑ ናቸው፡፡ ⁹ እነዚህም ሰዎች “ዋረቃ ኢብን ናውፋል፣ ኡቤይዱላህ ኢብን ጃሽ፣ ኡሥማን ኢብን አል-ሑዋሪሥ እና ዘይድ ኢብን ዐምር መሆናቸውን ኢብን ኢስሐቅ ዘግቧል። ¹⁰  

እነዚህ ሐኒፎች ዋንኛ ተግባራቸው ራሳቸውን ከጣኦት አምልኮ፣ ለጣኦት ከተሰዋና ከተመሳሳይ ልምምድ ጠብቀው ወደ እውነት የሚያደርሰውን ትክክለኛ መንገድ በመፈለግ የተጠመዱ ነበሩ፡፡ በስደት አቢሲኒያ መጥቶ እምነቱን ወደ ክርስትና የቀየረው ግለሰብ ከአራቱ ሐኒፎች ውስጥ አንዱ የሆነው ኡቤይዱላህ ኢብን-ጃሽ የተባለው ነው፡፡ ይህ ሰው በሐኒፍነት ፀንቶ ከጣኦት አምልኮም ራሱን አቅቦ እውነተኛውን መንገድ በሚፈልግበት ጊዜ ነበር መሐመድ እስልምናን የመሠረተው፡፡ በኋላም እስልምና ወደ ሕይወት የሚወስደው ትክክለኛው መንገድ ነው ብሎ ሰልሞ ነበር፡፡ 

በስደት ከወገኖቹ ጋር አክሱም ከመጣ በኋላ ግን ከክርስትና ጋር ተዋወቀ፡፡ ወትሮም ልቡ እውነት ፈላጊ ነበርና ክርስትና የተሻለው ብርሃንና የዘላለም ሕይወት የሚያስገኝ ትክክለኛው ፍኖት መሆኑን በመገንዘቡ ወደ ክርስትና ሃይማኖት ተቀየረ፡፡ የዚህ ሰው እርምጃ እውነትን በገለልተኝነት ለሚፈልጉ ልባሞች አርአያ የሚሆን ድንቅ ተግባር ነው፡፡ የመሐመድ የአንድ አምላክ አስተምሕሮ ቀድሞውኑ የሚያውቀው በመሆኑ ለእርሱ እንግዳ አልነበረም፡፡ በክርስትና እምነት ውስጥም በአንዱ እግዚአብሔር ማመንን ሲመለከት በተጨማሪ መሥፈርቶች ሁለቱን እምነቶች ሳያመዛዝን አልቀረም፡፡

የሚበልጠውንና እውነተኛ የሆነውን ጎዳና በመምረጡም ክርስቲያን ለመሆን በቅቷል፡፡ ለዚህ ነው እንደ ኢብን-ኢስሐቅ ዘገባ አብረውት በተሰደዱት ወገኖቹ አጠገብ ሲያልፍ “እኛ በግልፅ እናያለን፣ የእናንተ ዓይኖች ግን በከፊል ነው የተከፈቱት፤ ማለትም እኛ በግልፅ ስናይ፣ እናንተ ግን ገና ለማየት እየሞከራችሁ ነው ሆኖም ገና ማየት አልቻላችሁም” ይላቸው የነበረው፡፡ ¹¹ 

አስደናቂው ነገር እውነተኛውን መንገድ ሲፈልጉ ከነበሩትና በስም ከተጠቀሱት አራቱ ሐኒፎች ውስጥ ሦሥቱ ክርስቲያን ሆነው ነው የሞቱት፡፡ ዋራቃ ኢብን-ናውፋል የተባለው ሐኒፍ የመሐመድ የመጀመሪያ ሚስት የከድጃ አጎት ልጅ ሲሆን መሐመድ የመጀመሪያው ራዕይ ተገለጠልኝ ባለ ጊዜ ያረጋጋውና ለሙሴ የተገለጠው የእግዚአብሔር መልአክ ተገልጦልህ ይሆናል የሚል አስተያየት የሠጠው ሰው ነው፡፡ ይህ ሰው ብዙም ሳይቆይ የሞተ ሲሆን እስከሚሞትበት ቀን ድረስ ክርስቲያን የነበረ ነው፡፡ አይሻ በተረከችው ሀዲሳት ላይ ዋራቃ ክርስቲያን የነበረና ከመጽሐፍ ቅዱስ የወንጌል ክፍሎችን በዕብራይስጥ ቋንቋ ይፅፍ እንደነበር ገልፃለች ¹²  

ሌላኛው ሐኒፍ ዑስማን ኢብኑ-ሁዋሪስ የተባለ ሲሆን ወደ ሮም ከተጓዘ በኋላ በዚያ አስተርጓሚ ሆኗል፡፡ በኋላም ክርስትናን ተቀብሎና በማሕበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ የያዘ ግለሰብ ለመሆን መብቃቱ ተዘግቧል፡፡¹³  ሦሥተኛው ደግሞ ከላይ የጠቀስነውሀገራችን በስደት መጥቶ ክርስቲያን የሆነው ኡቤይዱላህ ኢብን-ጃሽ ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በቅንነት ሆኖ ከልብ ለሚፈልገው ሁሉ ክርስትና እውነተኛው የሕይወት መንገድ ለመሆኑ ማረጋገጫ ይሆናል፡፡ 

ማጣቀሻዎች 

¹ Spencer Trimingham, Islam in Ethiopia ገጽ 46 ኅዳግ ማስታወሻ

² W. Budge, op. cit., p. 273

³ A. Butler, The Arab Conquest of Egypt [1902] p. 141

⁴ Sirgiw Hablesilassie; Ancient & Medieval Ethiopian History pp.190

⁵ Sirgiw Hablesilassie; Ancient & Medieval Ethiopian History pp. 185

⁶ ተክለ ጻድቅ መኩሪያ 1951ዓ.ም የኢትዮጵያ ታሪክ ኑብያ፣ አክሱም፣ ዛጉዌ, ገጽ፡376

⁷ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ታሪክ ከ615 - 1700 ገጽ 70

⁸ የኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ታሪክ ከ615 - 1700 ገጽ 72

⁹ አር-ረሒቁ-ል መኽቱም ገጽ 75

¹⁰ Guillaume. The Life of Muhammad; p. 99

¹¹ Guillaume. The Life of Muhammad; p. 146

¹² Bukhari 1:1:3., Bukhari 4:55:605

¹³ Francis E. Peters (1994). Muhammad and the Origins of Islam. pp. 122-123

(የሳንኮፋ ሰንኮፍና ሌሎች ከገጽ 89-95)
Share on Google Plus

ስለ የተለጠፈበት ቀን

    Blogger Comment
    Facebook Comment